27 December 2017

ታምሩ ጽጌ

አቶ በቀለ ገርባ በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፍርድ ቤት የማይቀርቡ ከሆነ፣ በፖሊስ ተገደው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤትን ጠየቁ፡፡

በእነ አቶ አያና ጉርሜሳ የክስ መዝገብ የተካተቱት (22 ተከሳሾች ናቸው) አቶ ደጀኔ ጣፋና አቶ አዲሱ ቡላ (በተከሰሱበት የሽብር ተግባር ወንጀል ተከላከሉ የተባሉ ናቸው)፣ እንዲሁም አቶ በቀለ ገርባ ለማክሰኞ ታህሳስ 17 ቀን 2010 .. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት፣ በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸውን ከፍተኛ ባለሥልጣናት የምስክርነት ቃል ለማሰማት ነበር፡፡

ችሎቱ እንደተሰየመ የመከላከያ ምስክሮቹ መምጣት አለመምጣታቸውን ሲያረጋግጥ መከላከያ ምስክሮቹ እንዳልመጡ የአራቱ ተከሳሾች ጠበቃ አቶ አመሐ መኮንን አረጋግጠዋል፡፡ በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (/) እና የአቶ በቀለ የግል ምስክር ናቸው የተባሉ ግለሰብ ቢሆኑም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ አቶ አመሐ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 3 ቀን 2009 .. ለምስክሮቹ መጥሪያ እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ ሲሰጥ በእነሱ በኩል (በተከሳሾች) ማቅረብ ስለማይችሉ ለከፍተኛ ባለሥልጣናት በፍርድ ቤቱ በኩል እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን በችሎት የተሰጠው ትዕዛዝ በጽሕፈት ቤት በኩል ተቀይሮ መጥሪያው በጠበቆች በኩል እንዲደርሳቸው ሌላ ትዕዛዝ መሰጠቱን በማወቃቸው፣ መጥሪያውን ወስደው ያደረሱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ መጥሪያው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረሱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማቅረብም የመዝገቡ አካል እንዲደረግላቸው ሲጠይቁ፣ ሰብሳቢ ዳኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥራ ብዛት ምክንያት እንደማይቀርቡ የሚገልጽ ደብዳቤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንደተላከ አስታውቀዋል፡፡ ደብዳቤ የተጻፈውም ጠበቆች ባደረሱት መጥሪያ ሳይሆን በፍርድ ቤቱ በኩል በተላከ መጥሪያ መሆኑንም አክለዋል፡፡ አቶ አመሐ ግን መጥሪያው በእነሱ በኩል መድረሱን የሚያረጋግጠው ማስረጃ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝላቸው በድጋሚ ጠይቀው ሰጥተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያቀረበው ደብዳቤ ግልጽ እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ አመሐ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥራ ብዛት በዕለቱ መቅረብ ባለመቻላቸው ቀጠሮው ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍላቸው ነው? ወይስ አይቀርቡም ነው?›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ‹‹አልቀርብም ከሆነ ትክክል አይደለም፣ ጊዜ ይሰጠኝ ከሆነ ግን እኛም አንቃወምም፤›› በማለት የተላከው ደብዳቤ ግልጽ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

አቶ በቀለ መናገር እንደሚፈልጉ ጠይቀው ሲፈቀድላቸው እንደተናገሩት፣ እነሱ በመከላከያ ምስክርነት የጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን መሆኑን ጠቁመው፣ ጽሕፈት ቤታቸው መልስ የሚሰጥበት አግባብ የለም፡፡ ተላከ የተባለውም ደብዳቤ ግልጽ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመከላከያነት የቆጠሯቸው እንደ ማንኛውም ዜጋ በመሆኑ፣ የማይቀርቡ ከሆነ ሕግ መተላለፍ ስለሆነ በፖሊስ ተገደው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መከላከያ ምስክሮቹን ለመስማት ቀጠሮ የያዘው ታህሳስ 1718 እና 19 ቀን 2010 .. መሆኑን ጠቁሞ፣ ለቅሬታውና ለአቤቱታው ትዕዛዝ የሚሰጠው መጨረሻ ላይ መሆኑን (ታህሳስ 19 ቀን 2010 ..) ገልጿል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቶ በቀለ ገርባ ባቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለታህሳስ 17 ቀን 2010 .. ቀጥሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ በሥራ ጫና ምክንያት ሊደርስለት እንዳልቻለ ገልጾ ለጥር 7 ቀን 2010 .. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡