29 ዲሴምበር 2017
ኬንያ ሺሻን አገደች

ኬንያ ከታኅሳስ 19/2010 ዓ.ም ጀምሮ ሺሻ ማስመጣት፣ መሸጥም ሆነ መጠቀም የሚከለክል ሕግ አወጣች።

የኬንያ ጤና ሚንስትር ክሌዎፓ ማይሉ በትላንታው ዕለት እንዳስታወቁት ሺሻ ሲጠቀሙም ሆነ አስመጥተው ሲሸጡ የተያዙ ግለሰቦች 50 ሺህ የኬንያ ሽልንግና (500 ዶላር) ከ6 ወር በማያንስ እሥራት ይቀጣሉ።

ኬንያ ሺሻን በማገድ ከታንዛኒያና ከሩዋንዳ ቀጥላ ሦስተኛዋ ሃገር ሆናለች።

“ሸሻን ማገድ ያስፈለገን ከሚያደርሰው የጤና እክል እና ማሕበራዊ ቀውስ አንፃር ነው” ሲል የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ ያትታል።

ሺሻ በኬንያ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን ከውሳኔው በኋላ ኬንያውያን ወደ ትዊተር በማምራት በእገዳው ዙሪያ ሲወያዩ ነበር።

የዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ ሺሻ ማጨስ ጤናን እንደሚጎዳ የሚጠቁም ጥናት ማውጣቱ ይታወሳል።

ፓኪስታን፣ ዮርዳኖስ፣ ሲንጋፖርና ሳዑዲ አረቢያ ሌሎች ሺሻን ያገዱ ሃገራት ናቸው።

ተያያዥ ርዕሶች