31 December 2017

ዘመኑ ተናኘ

2010 .. መግቢያ ጀምሮ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ሳቢያ፣ ከኦሮሚያ ክልል በመፈናቀል በባቢሌ መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ የሶማሌ ክልል ተወላጆች የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

በሶማሌ ክልል ባቢሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችን ማክሰኞ ታኅሳስ 17 ቀን 2010 .. በክልሉ የተጋበዙ የጋዜጠኞች ቡድን ተዟዙሮ የተመለከተ ሲሆን፣ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ቡርቃ ትርትሬ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከወራት በፊት ከዘጠኝ ልጆቻቸው ጋር እንደመጡ የተናገሩት ወ/ሮ ሐሊማ መሐመድ፣ ለአንድ ወር 50 ኪሎ ግራም ስንዴና አንድ ሊትር ዘይት ብቻ እንደሚሰጣቸውና ይህም በቂ ባለመሆኑ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ሐሊማ እንደሚሉት፣ የሚሰጣቸው ስንዴ ለአሥር ቀናት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህም ምክንያት የልጆቻቸውን ሕይወት ለማቆየት መቸገራቸውን ጠቁመው፣ የሚሰጠው የምግብ ድጋፍ መጠኑ ከፍ እንዲል ጠይቀዋል፡፡

በነበሩበት አካባቢ ግጭት ሲፈጠር በፍርኃት ልጆቻቸውን ይዘው እንደመጡ የሚናገሩት ወ/ሮ ሐሊማ፣ የክልሉ መንግሥት እያደረገላቸው ያለውን ድጋፍ አድንቀው፣ መላው የአገሪቱ ሕዝብና መንግሥት ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከወራት በፊት ከአወዳይ መጥተው መጠለያ ካምፕ እንደገቡ የሚናገሩት አቶ መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው፣ በወር 50 ኪሎ ግራም ስንዴና አንድ ሊትር ዘይት የሚበቃው ልጅ ለሌላቸው ተፈናቃዮች ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሒርና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደተወለዱና በአወዳይ ለ35 ዓመታት እንደኖሩ የሚናገሩት አቶ መሐመድ፣ አባታቸው የሶማሌ ተወላጅ ስለሆኑ ብቻ መፈናቀላቸውን ያስረዳሉ፡፡

የጋዜጠኞች ቡድኑ የባቢሌን መጠለያ ካምፕ ተዟዙሮ የተመለከተ ሲሆን፣ በመጠለያ ካምፑ ከ70 ዓመት አዛውንት ጀምሮ እርጉዝ እናቶችና ሕፃናት ይኖራሉ፡፡ ከ30 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በመጠለያ ካምፑ እንደሚገኙም የክልሉ አደጋ መከላከልና ሥጋት አመራር ቢሮ ገልጿል፡፡

አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ፊት ላይ ከሚነበበው የሐዘን ድባብ በተጨማሪ፣ አካባቢው የሁለቱ ክልሎች ወሰን በመሆኑ ሌላ ግጭት ይከሰታል በማለት ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጠለያ ካምፑ አካባቢ መሠረተ ልማትና ትምህርት ቤቶች ባለመኖራቸው እንደተቸገሩና የልጆቻቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደሚያሳስባቸው፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ከሃሮ ለቡ ወረዳ እንደመጡ የተናገሩት ወ/ሮ ሐምዚያ አህመድ አስረድተዋል፡፡

ከበደኖ እንደመጡ የተናገሩት ወ/ሮ ዋርዶ አመኑር በበኩላቸው፣ ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው ከመምጣታቸው በላይ የመጀመርያ ልጃቸው በግጭቱ እንደ ሞተና ይዘዋቸው የመጡ ሦስት ልጆቻቸውን በሚሰጣቸው ምግብ እየመገቡ ማኖር እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከኦሮሚያ ክልል በደኖ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው የመጣሁት፡፡ ከትናንት ጀምሮ እኔና ልጆቼ ምግብ አልበላንም፤›› ሲሉ ወ/ሮ ዋርዶ አስረድተዋል፡፡

ስንዴ፣ ስኳር፣ ሩዝና ዘይት በመጠለያ ካምፑ ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች ሲከፋፈል ሪፖርተር የተመለከተ ሲሆን፣ የዕርዳታ እህሉን ለመውሰድ በአራት ሠልፎች የተከፋፈሉና በአንዱ ሠልፍ ብቻ ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ተሠልፈው ይታዩ ነበር፡፡

በመጠለያ ካምፑ ከምግብ እጥረት ባሻገር የውኃና የመድኃኒት እንዲሁም የጤና ችግር መኖሩንም ተፈናቃዮች ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዓለም አቀፍ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በመጠለያ ካምፑ ውስጥ ያለውን የሕፃናት የምግብና የጤና ችግር ለመፍታት የበኩሉን እያደረገ መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፣ ይህ በቂ እንዳልሆነ ተወካዮቹ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ከዚህ የባሰ ችግር እንዳይከሰት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ተፈናቃዮች ዓይንና ልባቸው በሚሰጠው ምግብ ላይ መሆኑን፣ ሕይወታቸውን ከዛሬ ነገ የማቆየት ፈተና ውስጥ መግባታቸውን ያስረዳሉ፡፡ የልጆቻቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንቅልፍ እንደነሳቸውም ገልጸዋል፡፡

ለዘመናት አብረው በልተው፣ ጠጥተውና በደም ተሳስረው ከኖሩበት አካባቢ ዜጎች እንዲጨፈጨፉና ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉን ኮንነዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ግጭቱ ሲከሰት አፋጣኝ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ሳቢያ ዜጎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈናቀሉና ሕይወታቸውን እያጡ መምጣታቸውን ተፈናቃዮች ያስረዳሉ፡፡ በአወዳይ ከተማ በንግድ ሥራ ተሠማርተው እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ አህመድ አብዲ፣ የፌዴራል መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ግጭት ሲከሰት የማስቆም ኃላፊነት እንደነበረበት ጠቁመው፣ ‹‹ይህ ባለመሆኑ ንብረታችንን ጥለን ለመፈናቀል በቃን፤›› ብለዋል፡፡

ከጅግጅጋ በ65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የባቢሌ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ፣ በምዕራብ በኩል በተራራ የተጋረደና ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚያዋስን አካባቢ በመሆኑ፣ አሁንም ግጭት እንዳለና እንዳልበረደ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ዜጎችን አፍኖ የመያዝና አስሮ የማሰቃየት ድርጊቶች በብዛት እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

ከስድስት ወራት በላይ በመጠለያ ካምፑ እንደቆዩ የሚናገሩት ተፈናቃዮች  ለልጆቻቸው በቂ ምግብ፣ ውኃ፣ ሕክምናና ትምህርት የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሪፖርተር ካነጋገራቸው ተፈናቃዮች መካከል አብዛኛዎቹ ቀድሞ ወደነበሩበት አካባቢ መመለስ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡ መሠረታዊ ጉዳዮቻቸው ተሟልተውላቸው በክልላቸው መኖር እንደሚፈልጉ የተናገሩ አሉ፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚቀሰቀሰውን ግጭት ለማብረድና ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ለማድረግ ቢታሰብም፣ ሳይሳካ መቅረቱን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቱ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ የአገር ሽማግሌዎችንና ወጣቶችን መርጠን ስንጠብቅ ተደውሎ ተላልፏል ተባልን፤›› ሲሉ እሑድ ታኅሳስ 15 ቀን 2010 .. በጅግጅጋ ከተማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየው ውይይት ወደፊት ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ክልል መንግሥታት ጋር በመነጋገር ይቀጥላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡ ውይይቱ ቢካሄድ ኖሮ በምዕራብ ሐረርጌ ሃዊና ዳሮ ወረዳዎች የተከሰተው ሞት ላይከሰት ይችል እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

በግጭቱ ብዙ ተዋንያን መሳተፋቸውን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) እና በኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) መካከል ጥላቻ የለም ብለዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች መካከል መወነጃጀል እንዳለ የጠቆሙት አቶ አብዲ፣ ጥፋተኛው አካል ማን እንደሆነ ግን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት በአንድ ካምፕ ብቻ ከ35 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ከስድስት መቶ ሺሕ በላይ መሆናቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በግጭቱ ምክንያት በሁለቱ ክልሎች ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ምን ያህል እንደሆኑ እስካሁን ባይገለጽም፣ የአሟሟታቸው ሁኔታ ዘግናኝ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ጭካኔ በተሞላበትና ኢሰብዓዊ በሆነ አኳኃን ከሁለቱም ወገን የዜጎች ሕይወት ማለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ግጭቱን አስቁሞ የተፈናቀሉ ዜጎች በሚቋቋሙበት ላይ መንግሥት እየሠራ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገር ቢሰማም፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አለመጀመሩ ይታወቃል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በባቢሌ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ዜጎች ካለባቸው የምግብ፣ የጤናና የውኃ ችግር በተጨማሪ በዘላቂነት የሚቋቋሙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡ በመጠለያ ካምፑ ከሚገኙ ተፈናቃዮች አብዛኛዎቹ ከአወዳይ፣ ከበደኖ፣ ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሃዊና ዳሮ ለቡ ወረዳዎች የመጡ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ በጅግጅጋ ከተማ ይኖሩ የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች አብዛኛዎቹ ወደ ክልላቸው መሄዳቸው ታውቋል፡፡ በከተማው ውስጥ ቀበሌ 12 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ብቻ 83 አባወራዎች መፈናቀላቸው ተጠቁሟል፡፡ የሶማሌ ክልል መንግሥት ባደረገው ጥሪ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄደው ከነበሩ 83 አባወራዎች መካከል ሦስቱ ተመልሰው በመምጣት ወደ ቀድሞ ሥራቸው መመለሳቸውን የሶማሌ ክልል ገልጿል፡፡

ንብረትነታቸው የኦሮሞ ተወላጆች የሆኑ ሱቆችና ሌሎች የንግድ ቤቶች አሁንም እንደተዘጉ ይታያሉ፡፡

ሪፖርተር