ከሲሳይ መንግስቴ
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላለፉት 17 ቀናት በግምገማ መልክ ለሶስት ሰባት ሩብ የጎደለው ሱባኤ በአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ውስጥ ገብቶ ከቆየ በኋላ ሰፋ ያለ መግለጫ አውጥቷል፣ በዚህም ባለፉት ጥቂት አመታት በሀገሪቱ እየተስተዋለ የሚገኘውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለይቼ በማውጣት መፍትሄውንም ይዠ መጥታቸለሁ ሲል ገልጧል፡፡
በእኔ ግምት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሁንም መሰረታዊ የሆኑትን የአገሪቱን ችግሮች በትክክል የለየና መፍትሄውንም በተሟላ መልኩ ያገኘ አይመስልም፡፡ ለምሳሌ በእኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ላይ አሁንም ድረስ እዚህም እዛም ጠንከር ያሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ፣ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ መሬት ላይ ያሉትን ችግሮች በምሳሌ አስደግፎ በመገምገምና ክብደታቸውንም በአግባቡ በመመዘን ከልብ ተቀብሎ ለማረም ዝግጁ የሆነ አይመስልም፡፡
እንዲሁም ከተለመደው አቀራረብ ውጭ የወጣቱን የስራ አጥነትም ሆነ የእኩል ተሳታፊነት ሁኔታ በአግባቡ የለየ ግምገማ ሆኖም አላገኘሁትም፡፡ የብሔር-ብሔረሰብ ህዝቦች የማንነት ጥያቄ ተገቢ እውቅና ባለማግኘቱ ምክንያት ሀገሪቱ በእጅጉ ስትታመስ መቆየቷን ታሳቢ ያደረገና አሁንም ጭምር እዚህም እዛም የሚነሱትን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ እያስተናገደ መሆኑን የሚያሳይ ግምገማ ባለማካሄዱ ምክንያት ሊያሰራ የሚችል የመፍትሄ አቅጣጫ አለማስቀመጡን መታዘብ ችለናል፡፡
ነገር ግን ላፉት ሁለትና ሶስት አመታት ሀገሪቱ የስጋት ቀጠና እንድትሆንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከመደንገግ ያደረሱ ችግሮች የተስተዋሉት አንድም በሀገሪቱ ውስጥ በሚታየው እድገት ላይ የእኩል ተጠቃሚነት ሁኔታ ባለመኖሩና ለወጣቱ ተገቢ የሆነ የስራ እድል ማመቻቸት ባለመቻሉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዛም አልፎ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያቀርቡት የማንነት ጥያቄ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖ እንኳ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አለመስተናገዱ አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡
ሌላው አስገራሚ ነገር የጨነቀው እርጉዝ ያገባል፣ የባሰበት ደግሞ እመጫት እንደሚባለው የአቶ አባዱላ ገመዳና የአቶ በረከት ስምዖን ወደ ቀድሞ ቦታቸው የመመለስ ሁኔታ ይበልጥ ከግራ መጋባት የመጣ የልጆች ጫወታ አይነት ሊሆን ካልሆነ በስተቀር አሁን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ችግር በማባባስ የነበራቸው ሚና አነሶ አሁን በሚካሄደው ትግል ላይ ምን ሊፈይዱ ይችላሉ ተብሎ ታስቦ ይሆን?
እናም ኢህአዴግ ሆይ ግመል ሰርቆ ጉንብስ ጉንብስ የትም አያደርስምና አሁንም የሀገሪቱንና የህዝቦቿን መሰረታዊ ችግሮች በትክክል ተረድተህና ህዝብንም በሚገባ ማሳተፍ የሚችል አቅጣጫ ቀይሰህ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ አለፍ ያለ ዘላቂ መፍትሄ ይዘህ ብትመጣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ሌላ ምርጫ ስለሌለው ከጎንህ ሊቆም ይችላልና አሁንም ራስህን በደንብ ፈትሽና አባል ድርጅቶችህም ራሳቸውን በሚገባ እንዲፈትሹ አድርግ እላለሁ፡፡
