Corruption by TPLF secu

ከባርናባስ ገብረማሪያም
bega2260@comcast.net

ከሁሉም አሰቀድሜ መብታችን ይከበር ብለው ስለጮኹ ብቻ የጥይት ሰለባ በመሆን የነፃነት ዋጋ እየከፈሉ ላሉት ሰማእታት ወገኖቼን
ሁሉ የሚሰማኝን ጥልቅ ሃዘን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ:: ለወላጅ ዘመዶቻቸው፣ ለወዳጆቻቸውና ለትግል ጓዶቻቸው በመሉ
መፅናናትን እመኛለሁ:: ከዚህ በተረፈ በውጭ ዓለም ለምትገኙ ኢትዮያውያን ወገኖቼ ሁሉ መልካም የ2018 ዓ.ም የፈረንጆች አዲስ
ዓመት:: አዲስ ዓመቱም የትግል ወኔያችንን የምናድስበት፣ አሮጌውን አስተሳሰብና አሰራር ጥለን ለሁላችንም የሚበጅ አዲስ የትግል ጎዳና
ይዘን አንድ እርምጃ ወደፊት በመራመድ ወደ አዲስ ብሩህ ተሰፋ የምንሸጋገርበት ዘመን እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ::

“ የዝንጀሮ መንገድ ቢከተሉት መጨረሻው ገደል ነው ” እንደተባለው ሁሉ ላለፉት በርካታ ዓመታት ህዝቡን በማሸበርና በማፈን ሲገዛ የቆየው የህወሓት ቡድን እኖሆ ዛሬ በህዝብ ዓመፅ ወላፈን እየተለበለበ እሱም በተራው የደርግ ስርዓት የገባበትን ከርሰ መቃብር አፋፍ ላይ ቆሞ የግብኣተ መሬቱን ዋዜማ ላይ መሆኑን በሀገራችን ያለው እውነታ ራሱ እየተናገረ ይገኛል:: የህዝብ ቁጣ በተነሳ ቁጥር እንደ እሳት አደጋ መኪና መጮኽ የለመዱ የህወሐት መሪዎች ዛሬም የነብስ አድን ስብሰባና የቀቢፀ ተስፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ተጠመደው በመቆየት ዛሬም አስቂኝ መግለጫ ይዘው ቀርቧል:: ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ላለፉት ዓሰርቱ ዓመታት
መፍትሄ ያላገኙ፣ የሀገራችንን አንድነትና የህዝቧን ህልውናም ጭምር አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ጥልቅና ስር የሰደዱ ስለሆኑ በጥቂት ሰዎች ስብሰባና መግለጫ፣ በግለ ሰቦች ሹም ሽርና ግድያ ሊፈቱ የማይችሉ ከስርዓቱ እይታና ዓቅም በላይ መሆናቸውን ካለፈው ልምዳቸው አይተናል:: ሌላውን ትተን ከመለስ ዜናዊ ህልፈት በሗላ እንኳን ስንመለከት ስንት ጉባኤዎችና ስብሰባዎች ተደርጓል:: የተለያዩ የአዋጆች ክምር ወጥቷል::

በትራንስፎረመሽን ስም ስንቱ የግለ ሰቦችን ሹም ሽር ተካሄዷል:: ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ጋጋታ ቅንጣትን
ታህል ለውጥ ለማምጣት አልቻለም:: እንዲያውም ይባስ ብሎ በፊት ከነበረበት ሁኔታ በከፋ መልኩ ዓፈናው፣ ግድያውና ቅራኔው ተባብሶ የስንቱን ህይወት ጠፍቷል:: የስንቱን ቤት ፈርሷል:: ስንቱን በእስር ቤት ታጉሯል:: ስንቱን ዜጋ ሀገሩን ጥሎ ተሰዷል:: ስርዓቱም እንደ መንግስት ሀገሪቱን ማስተዳደርም ሆነ ቀውሱን ማረጋጋትና የህዝቡን ጥያቄ መልስ መስጠት ቀርቶ የራሱን ህልውና እንኳን መጠበቅ አልቻለም::

የችግሮቹን መንሲኤ ስርዓቱ የሚከተላቸው ፓለሲንና የሚመራበትን ርእዮተ ዓለምም ከሀገሪትዋ ተጨባጭ እውነታና ከህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄ ጋር ሲነፃፀር ፈፅመው አይገናኙም:: ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የሚጠይቀው ሌላ ህወሓቶች ደግሞ የሚያራምዱትን ፓሊሲና የሚሰሩት ስራ የድሮ የደደቢት አስተሳሰብ ነው:: “ ብርሌ ከነቃ አይሆንም ዕቃ ” ነውና እነ አቦይ ስብሓት ከወጣትነታቸው ጀምሮው ለአርባ ዓመታት ስልጣን ላይ ተቀምጠው ለውጥ ያላመጡ ሰዎች ዛሬ በ80 ዓመት ዕድሜያቸው ከተጣለቡት ጎዳና ተሰባስበው ባለቀ ሰዓት ላይ ለውጥ ያመጣሉ ብሎ ማሰብ የሞተ ሰውን እንደመቀስቀስ ያህል ይቆጠራል:: ለህወሓት መሪዎች የፓሊሲ ለውጥ
ማድረግ ማለት ራስህን በራስህ እንደ መግደል (ሱሳይዳል) እርምጃ አድርገው ነው የሚያዩት:: የፓለሲ ለውጥ ለማድረግ የሚሰጉበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ዓቅማቸውንና ባህሪያቸውን ስለማይፈቅድላቸው ብቻ አይደለም:: አንደኛ ነፃ የውድድር መድረክ ከከፈቱ ህዝባዊ አሜኔታ ስለሌላቸው በህዝብ ፊት ተወዳድረው በስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችሉ በ97ቱ ምርጫ በተግባር አይተውታል:: ሁለተኛ በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት ከተከበረ፣ ህዝቡ መብቱን የሚያስከብርበትና መሪዎቹን የሚቆጣጠርበት ነፃ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከተረጋገጠ
ደግሞ ከሕግ በላይ ሆነው እንደፈለጉ መዝረፍ እንደማይችሉና የዘረፉትንም ሃብት በሕግ ሊጠየቁበት እንደሚችሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ::
ሶስተኛውና ዋናው የሚያሰጋቸው ምክንያት ደግሞ እጃቸውን በንፁሃን ደም የተነከረ በመሆኑንና ነገ እንደሚፋረዳባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ:: ከዚህ ሁሉ ስጋት በመነሳት ከህዝቡ ጋር ወግነው የለውጥ አጋር ሆነው ከመገኘት ይልቅ የመረጡት መንገድ ስልጣን እስከ መቃብራቸው ድረስ የሙጡኝ ብለው በመያዝ እንደለመዱት እየገደሉና እየተሟሟቱ መኖር ነው:: ከመለስ ዜናዊ የወረሱት አደራም ይህንን ነው::

በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የህዝብ ዓመፅና ብሎም በኢሕአዴግ አካባቢ እየታየ ያለው ውስጠ ቅራኔም መነሻው የነ ለማ መገርሳና የነ ገዱ ጉዳይ ሳይሆን በአንድ በኩል ሾላ በድፍ ሆኖ ታምቆ የቆየ የችግሩን ጥልቀትና ውስብስነት ምን ያህል ስር እንደሰደደ የሚያሳይ ነው::
በሌላ በኩል ደግሞ ከመለስ ዜናዊ ህልፈት በሗላ የህወሓት የበላይነትና የስልጣን ሄጀሞኒ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረና እየተናደ መጥቶ አሁን የሀይል ሚዛኑንና የፓለቲካ ጨዋታውን እንደ ተቀየረ በግልፅ ያሳየናል:: አጠቃልለን ስናየው አሁን ህወሓት የመደራደሪያና የማስፈራሪያ ካርዱን አልቆበት ከኔ በላይ ጀግና የለም እያለ በህዝብ ላይ የውሸት ድራማ እየሰራ እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬ ሀገርን ማስተዳደር ቀርቶ ራሱን ማዳንና መከላከል የማይችልና የፓለቲካ ካፒታሉን በልቶ የጨረሰ ጥርስ የሌለው አሮጌ አንበሳ ሆኖ ቀርቷል::

ለተከሰተው የፓለቲካ ቀውስ መፍትሄው ምንድን ነው?

በሀገራችን የተፈጠረው ቀውስ ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ መጀመሪያ የችግሮቻችንን መሰረታዊ መንሲኤ ማወቅ አስፈላጊ ነው:: ብዙውን ጊዜ ተቃዋሚ የፓለቲካ ሀይሎችን አስመልክቶ የሚቀርበው የህዝቡን አስተያየትና ቅሬታ ህወሓትን በአግባቡ አያውቁትም የሚል ነው::
የህወሓትን መሰሪ ባህርይ፣ ማንነት፣ አረማመድና ተንኰል እንዲሁም ህዝቡን ለማጭበርበር ሲባል በየጊዜው ስልቱንና ቀለሙን እየቀያየረ የሚጠቀምባቸውን የማታሊያ ካርዶችንና ስትራተጂዎችን በቅጡ ማወቅና አለማወቅ ማለት ለመሰረታዊ ችግሮቻችን መፍትሄ መፈለግና አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላ ትግላችንም ወሳኝ ነው:: ቀንደኛ ጠላታችንን ጠንቅቀን ባለማወቃችን የተነሳም አብዛኞቻችን ሁሉ ጊዜ የምናየው እሳቱን ሲቃጠል እንጂ ከእሳቱ በስተጀርባ ሆኖ ክብሪት የሚጭር ፣ የግጭቱንና የቅራኔውን ቀያሽና መሃንዲስ ማን እንደሆነ
በአግባቡ አናየውም:: በዚህ ምክንያት እሳት ሲፈጠር ጊዚዊያዊ የሆነ እሳቱን የመከላከል ስራ መስራት እንጂ ጠላታችንና ወዳጃችን ማን መሆኑን ለይተን በማወቅ ለሱ የሚመጥን አጀንዳ ይዘን ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ ጥረት አናደርግም:: የኛን ደካማነት በውል የተገነዘቡ የህወሓት መሪዎችም የህዝቡን ዓመፅ በተነሳ ቁጥር ወላፈኑን ወደነሱ እንዳይጠጋ አቅጣጫውን በመቀየር መልሰው ወደ ህዝቡ በሚወረውሩት አጅንዳና የቤት ስራ ተቀብለን በመተግበር ዋናውን ጨቋኝ ስርዓት ወደ ጎን ትተን እርስ በራሳችን እየተባላን የገዛ ቤታችንን ራሳችን በራሳችን እንድናፈርስ ሲያደረጉን ቆይቷል:: ውጤቱም ትግላችን አድሮ ቃሪያ ሆኖ አንድ ስንዝር ወደፊት ሳንራመድ በአዙሪት ፓለቲካ ተጠምደን ሁሉ ጊዜ ተከላካይ ሆነን እንድንኖር አድርጎናል::

በመሆኑም አሁን የምንቀይሰው የመፍትሄ አቅጣጫና አካሄድም በቅድሚያ እነዚህን ደካማ ጎኖቻችንን በመሰረቱ የሚቀይርና የሚፈታ መሆን አለበት:: ለለውጥ መታገል መጀመሪያ ራስህን የለውጥ ሀይል በመሆን በልጦ መገኘት የግድ ይላል:: ታግሎ ለማሸነፍ መጀመሪያ ጠላትህንና ወዳጅህን ለይቶ ማወቅና እሱ የሚሸርባቸውን ወጥመዶች ሰብሮ ለመውጣት የሚያስችል ዓቅም መገንባት የግድ ይላል::
የህዝቡን የትግል አጋር ሆኖ ዓመፁን በግንባር ቀደምትነት በመምራት ለዘላቂ ድል ማብቃት የሚቻለውም መጀመሪያ ህዝቡ የኔ ነው የሚለው ፣ ሚናውንና አቋሙን የለየ፣ በሀገራችን ያለውን እውነታ ያገናዘበ ፣ የህዝቡንና የአዲሱን ትውልድ ልብ ትርታ ያዳመጠ፣ አሁን ላለንበት ጊዜ የሚመጥን ጥራት ያለው ራእይና ስትራተጂ መኖርና አለመኖር ወሳኝ ነው:: ካልሆነ ግን “ በረጅም ገመድ የታሰረች ዶሮ ብትሮጥም አታመልጥም ” እንደሚባለው ሁሉ ስርዓቱ የሚሰጠንን አጀንዳና የቤት ስራ ፈፃሚዎች በመሆን የህወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎችን ዕድሜ ማራዘሚያ መሳሪያ ከመሆን አልፎ ለህዝቡ ትክክለኛ አማራጭ መሆን አይቻልም:: ላለፉት በርካታ ዓመታት
በተጨባጭ ያየነው ልምድም ይህንን ነው::

ስለዚህ ህዝቡ ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ እያለ በተደጋጋሚ እንደሚጠይቀን ሁሉ ዛሬ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሞን ስናየው ያለን አማራጭ ከሁለቱ አንዱ ነው:: “ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ አሊያም ድንጋይ ነው ብለው ይጡልሃል” እንዲሉ አሁን ያለን አማራጭ ተስተካክሎ ራሰህንና ሀገርን ማዳን አሊያም ለትግሉ ጋሬጣ ከመሆን ይልቅ ቦታውን ለባለቤቱ ለአዲሱ ትውልድ መልቀቅ ነው:: ዛሬ የህዝቡን ዓመፅና ንቃተ ህሊና ቀድሞን በሄደበት ሁኔታ ላይ ሆነን ራስን በራስ እያሞኙ ለይስሙላ ድርጅት ነኝ እያሉ ሾላ በድፍን ሆኖ  መኖር ወሓት/ኢሕአዴግም አልበጀም:: ጊዜው አብቅቷል:: ሰለሆነም ካለፈው ስህተታችን ተምረን መሰረታዊ ችግሮቻችንን ተባብሮ
ለመፍታትና ወደፊት ለመራመድ መጀመሪያ ራሳችን ቁርጠኛ የሆነ ውስጠ ትግል በማካሄድ ከተከላይነት ወደ አጥቂነት፣ ከመበታተን ወደ አንድነት፣ ከዝገት ወደ ጥራት፣ ከዳበሳ ጉዞና መደናበር ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ፣ ከጭራነት ወደ ግንባር ቀደምትነት ፣ ከግለኝነት ወደ ህዝባዊ ወገንተኝነት፣ ከድብብቆሽ ጨዋታ ወደ ግልፅነት፣ ከፍርሃት ወደ ፅናት ለመሸጋጋር የሚያስችለንን ዕቅድ ይዘን የህዝባችን አለኝታና መከታ ሆነን መገኘት የወቅቱ ጥያቄ ነው:: የድሮ የዘመነ መሳፍንት አስተሳሰብና አስራር ይዞ የዛሬውን የሃያ አንደኛውን ክፍለ ዘመን ትውልድ መምራት አይቻልም::

ዛሬ ህዝቡ በተለይም ለጋ ወጣቱ ከህወሓት ሰው በላ ቡድን ጋር ጎሮ ለጎሮሮ በመተናነቅ እየከፈለ ያለው የህይወት መስዋእትነት ትርጉሙ የነፃነት፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ዋጋ መሆኑን ተገቢውን ክብርና ግምት ልንሰጠው ይገባናል:: ይህ አኩሪ መስዋእትነት ደመ ከልብ ሆኖ ውጤት ሳያስገኝ እንዳይቀር ደግሞ በመካከላችን የነበረንን መለስተኛ ቁርሾ ወደ ጎን ለታሪክ ትተን ትልቁን የሀገርና የህዝብ ጉዳይ በማስቀደም ይቅር ይቅር ተባብለንና እጅ ለእጅ ተያይዘን ለጋራ ሀገር በጋራ የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው:: ይችን ጊዜ በዋዛ ፈዛዛ ካለፈች ደግሞ “ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ“ ስለሚሆን ቀባሪ ያጣውን የህወሓት ስርዓት እንደገና በማንሰራራት በየተራ እየቀጠቀጠን
እንዲኖር ዳግም ዕድል ማግኘት የለበትም:: ስለዚህ የመፍትሄዎቻችን አቅጣጫ መሆን ያለበት ለትብብራችንና ለአንድነታችን እንቅፋት የሚሆንብንን ሗላቀር አመለካከቶችንና ደካማ አሰራሮችን አራግፈን በምትኩ የለውጥ ተሃድሶ ተቀዳጅተን የምንወጣበት ጊዜ እንዲሆን ይጠበቅብናል::

አሁን ምን ይደረግ

በሀገራችን ላይ ያንጃበቡትን ችግሮች አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ ለማሰገኘት ዋል እደር ሳይባል በአንድ የሀገር አንድን ዙሪያ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ መሰባሰብ አስፈላጊ ነው:: ተሰባስቦ በግልፅ ተወያይቶ አንድ ቁምነገር ቋጥሮ ለመውጣት የሚቻለው ደግሞ ከያንዳንዳችን የሚፈለገው ነገር ቅንነትን፣ ቁርጠኝነትንና ፅኑ እምነትን ይዞ መምጣት ብቻ ነው:: እነዚህ ከተሟሉ ከብረት የጠነከረ የትግል አንድነት መፍጠር ይቻላል:: ከዚህ በጎ መንሰስ በመነሳት በቅድሚያ በሀገር ውስጥም ሆነ በዲያስፓራ ስለሀገራችን ጉዳይ ያገባናሉ የሚሉትን ተቃዋሚ የፓለቲካ ሀይሎች፣ አክቲቪስቶች፣ ሲቢክ ማሕበረ ሰቦች፣ የሀይማኖት ተቋቋማት መሪዎችንና ሌሎች ሀገር ወዳድ ወገኖችን
በማሰባሰብና በመመካከር የሚከተሉትን ስራዎች ማከናወን ይቻላል::

1. ከሁሉም የተውጣጣ የሀገር አድንና የምክክር ኮሚቴ እንዲቋቋም ጥሪ ማድረግ::

2. ዞሮ ዞሮ ወሳኙ በሀገር ውስጥ የሚካሄድ ትግል ስለሆነ ከዲያስፓራው እንቅስቃሴ ጋር ማለትም ከሚቋቋመው ኮሚቴ ጋር የተቀናጀ እንዲሆን ማድረግ:: ይህም በተናጠል ሳይሆን መሪነቱን የሚወስድ አንድ በሀገር ደረጃ ከሚቴ እንዲኖር ማድረግ::

3. ሶስተኛ በሚፈጠሩት ኮሚቴዎች አማካይነት በሁሉም አህጉራት አንድ ወጥ የሆነ ሀገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር የዲፕሎማሲ ስራ ዘመቻ እንዲካሄድ ማድረግ:: ለምሳሌ ከሰላማዊ ሰልፍ ጀምሮ መንግስታዊንና መንግስታዊ ያልሆኑትን ተቋማት በአካል እያገኙ ማነጋገርና ሁኔታውን ማሰረዳት ያካትታል::

4. አራተኛ አሁን እየተካሄደ ካለው እንቃስቃሴ ፈልቆ የሚወጣ በተለይም ከወጣቱ ትውልድና ከነባሩ የተቃውሞ ጎራ የተውጣጣ ትግሉን በቀጣይነት መምራት የሚችል ጠንካራ ሀገራዊ የፓለቲካ ሀይል የሚፈጠርበት መድረክ ማመቻቸት የሚሉት ናቸው::

5. በመካከላችን የትግል መንፈስ፣ የአላማ አንድነትና ሀገራዊ ንቃተ ህሊና እየጎለበትና እየጠነከረ እንዲሄድ ለማድረግ በተለያዩ ቦታዎች በየጊዜው ጥናታዊ ፅሑፎችን የሚያቀርቡ ሰዎችን እየጋበዙና የቤት ሰራም እየሰጡ የምክክር መድረክ ፈጥሮ ማወያየት የበለጠ መቀራረብንና መተዋወቅን ይፈጥራል::

ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመሸጋገር እንዴት ይጀመር? ተነሳሽነቱስ ማን ይውሰድ? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ ለፓቢሊክ ግንኙነትም ሆነ ለዲፕሎማሲያዊ ስራዎቻችን እንዲመችና ህዝቡም ሳይሸማቀቅ ነፃ ሆኖ እንዲሳተፍበት ለማድረግ በሀገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት የፓለቲካ ሀይሎች በመተባበር ተነሳሽነቱንና መሪነቱን በመውሰድ ቢጀምሩት የበለጠ ውጤታማና ከሁሉም አቅጣጫ ድጋፍ ሊኖረው ይችላል የሚል እምነት አለኝ:: ይህ ማለት በውጭ ዓለም ያሉትም ቁጭ ብለው እጃቸውን አጣጥፈው ይጠብቁ ማለቴ አይደለም:: ያም ሆነ ይህ ሳይደፈርስ አይጠራምና ሁለቱንም በተጓዳኝ ማካሄድ ይቻላል::
ከዚህ በተረፈ ሌሎቻችሁም በተለያዩ ሚዲያዎች የሰጣችሗቸው አስተያየቶችንና ገንቢ የመፍትሄ ሃሳቦችንም ተደምረው በሂደት የሚጎለብቱ ናቸው:: ዋናው ቁም ነገሩ ፍላጎቱ መኖሩና በትንሽም ቢሆን መጀመሩን ነው:: ከተጀመረ ደግሞ እርግጠኛ ነኝ ወደ አንድ ጥሩ ነገር እንደሚያመራ:: ይቻላል ብለን በቁርጠኝነት ከተነሳን ደግሞ እንኳን ለበሰበሰው የህወሓት ስርዓት ቀርቶ ለሌላም እንተርፋለን:: እነሱ ይህን ያህል ዓመታት በስልጣን ላይ ለመቆየት ያቻሉ እኮ የተቀደሰ አላማ ስላላቸው ወይም እነሱ እንደሚሉት በተፈጥሯቸው ከሌላው ኢትዮያዊ የበለጠ እውቀትና ጀግንነት ስላላቸው አይደለም:: ነገር ግን ባለቤት የሌላት ባዶ ሀገር ስላገኙና ለእኩይ አላማቸው ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው ተባብረው ስለሚሰሩ ብቻ ነው::

ጀግንነት ማለት በዘር ወይም በደም ሐረግ የሚተላለፍ ሳይሆን ዋናው ምንጩና ሚስጢሩ ከአላማ ፅናትና ቁጠኝነት የሚወለድ የተባበረ ክንድና ጥበብ ነው:: አባቶቻችን እኮ በዘመናዊ ጦር መሳሪያ የተካነ የባዕድ ጠላትን በዱላና በጎራዴ መክተው ድል ያደረጉበት ዋናው ሚስጢር አንደኛ የሀገርንና የወገንን ፍቅር በደማቸው ውስጥ ሰርፆ በመግባት የአላማ ፅናትንና የጋለ ወኔን ስለፈጠረላቸው ነው::
ሁለተኛው ሚስጢር ደግሞ በሀይማኖት በዘር በቦታ ሳይለያዩ በአንዲት የእናት ሀገር ጉዳይ ዙሪያ ክንዳቸውን አስተባብረው በአንድነት ስለተሰለፉ ብቻ ነው:: ይህ ዓይነቱ ጥበብና ወኔ ደግሞ በኛ በአዲሱ ትውልድም የማይደገምበት ምንም ምክንያት የለውም::
ሰለዚህ ይቻላል ብለን በቁርጠኝነት በመነሳት ስራችንን እንጀምር:: ደግሞ ይቻላል:: በልቡ የሸፈተና ለለውጥ ቆርጦ የተነሳ ጀግና ህዝብ ከሆናችን አለን:: የህወሓትን የጥይት እሩምታና የሰራዊት ጋጋታ የማይበግረው በቃኝ ብሎ የፍርሃትን አጥር ሰብሮ የተነሳ ወጣቱ ትውልድ አለን:: ስርዓቱም በኛ ድክመትና መበታተን ነው እየኖረ ያለው እንጂ አንድ ሐሙሰ ከቀረው ውሎ አድሯል:: የዓለም ማሕበረሰብም በመክሰም ላይ ካለው ስርዓት ጋር ይወግናሉ ብለን አናምንም:: እነዚህ ሁሉ ደምረን ስናያቸው መጪውን ዘመን የአሮጌውን ስርዓት ሳይሆን የአዲሱን ታጋይ ትውልድ ዘመን መሆኑን ቅንጣት ታህል የሚያጠራጥር አይሆንም::

የህወሓት ጨቋኝና ከፋፋይ ስርዓት ያብቃ

ኢትዮያ ሀገራችን በልጆችዋ መስዋእትነት ዘላለም ተከብራ ትኖራለች