January 3, 2018
በዚህ መግለጫ ያላላገጠ ቢኖር የኢህአዴግ ፅንፈኛ ደጋፊዎች ብቻ ናቸው፡፡ መቼም እነርሱም ደስተኛ አይደሉም፤ ለአቅመ ማፌዝ ባይደርሱም፡፡ ከተመቸኝ እና ለብቻዬ ያሳቀኝ ግን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ መግለጫ ሙሉ ቃል “`ዱDጉGኩKጁJኩጁሹSኩኁHጉGኩዱሹኁኩሉሀጀሀለሀከጀሀከጀሀገቨገኒነከኖከመጀከነነመነመ፣ ነልልመ፣፣ ሞቦ፣ በ፣በ፣በበበመ ነበሀሁፈደጎጀለመ፤ ክጅክ…” በሚል ያቀረቡት፡፡ በቃ ይህ ነው መግለጫው፡፡ ከቀልድ ባለፈ ግን ይህ ግንባር የዳዊት ዓይነት ጅግና ተነስቶ ግንባሩ እስኪለው ድረስ አገር እየመራ ነው ብለን የምር ለምናስብ ሰዎች መግለጫውን በትነን ማየት ያለብን መሰለኝ፡፡ ይህ ጉደኛ መግለጫ፤
“በአገራችን የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከነዝርዘር መገለጫቸው በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሃሳብ አንድነትና መተማመን ፈጥሯል፡፡ ችግሮቹን በመቅረፍ በእስካሁን ትግላችን የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ቁርጠኝነትና ጠንካራ መግባባትን አረጋግጦ ወጥቷል፡፡” በማለት ይጀምራል፡፡
ከዚህ አባባል መረዳት የሚቻለው ይህ ድርጀት አሁን ከሃያ አምሰት ዓመት በፊት የነበሩ የሚባሉ ችግሮችን፣ ዘለግ ሲልም ከሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ አሉ ከሚላቸው ችግሮች ቅርቃር እንዳልወጣ እና አሁንም ችግሩን በሌሎች ለማላከክ ፍላጎት እንዳለው ነው፡፡ በመቀጠልም ፓርቲው በሃሳብ መለያየት እንደ ሀጥያት የሚመለከት፤ ይህንንም እንደ አለመተማመን የሚቆጥረ መሆኑን ነው፡፡ ወይም ደግሞ እርስ በእርስ የማይተማመኑ ስብሰቦች ሆነዋል፤ስብሰባውም እንተማመን ብለው ሲማማሉ መክረማቸውን ነው የሚነግረን፡፡ ይህን ለማለት ይህን ሁሉ ቀን ዘግተው መቀመጣቸው ያስገርማል፡፡
“አገራችን በአንድ በኩል በተከተልነው መሰረታዊና ትክክለኛ አቅጣጫ በተገኙ መልካም ውጤቶች እጅግ የሚያስጎመዥ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፈፀምናቸው ስህተቶችና ከእድገታችን ጋር ተያይዘው በተከሰቱ አዳዲስ ለውጦችና ፍላጎቶች ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን በአሳሳቢ ወቅታዊ ችግሮች ተወጥራ የቆየችበት ሁኔታ መፈጠሩን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በትኩረት ገምግሟል፡፡”
ልብ በሉ አስጎምዥ በዚሁም ላይ ደግሞ በችግር የተወጠረች ይሉናል፡፡ የሚያስጨንቅ ፍቅር የሚሉት ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ በምን መመዘኛ እንደሚያስጎመዥ ለአንባቢ ትዝብት መተው በቂ ሲሆን፣ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው የቃላት ድሪቶ ደግሞ “በተከተልነው መሰረታዊና ትክክለኛ አቅጣጫ …” በሚል የተቀመጠው ሃሳብ ነው፡፡ መሰመራቸው የተሳሳተ መሆኑን በተደጋጋሚ እየተነገራቸው ቢሆንም መስመራቸውን ለማሰተካከል ያልተዘጋጁ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በፌስ ቡክ በሰጠሁት አስተያየት ኢህአዴግ ለመሞት መወሰኑን የተረዳሁበት፤ ነብስ ይማር ለማለት ያብቃን ያስባለኝ የመግለጫው ክፍል ይህ ነው፡፡ አቶ ሸፈራው ሸጉጤ ልዩ ውሳኔ ያሳልፋል ያሉን ምን እንደሆነ ፈልገን ያጣንበት መግለጫ ነው፡፡
መግለጫው ከላይ እንዳስቀመጥኩት በረጅም ዘመን ጨለማ የነበረች አገር በኢህአዴግ ባለፉት 25 ዓመታት ወደ ብርሃን ማቅናቷን በልማታዊ ሰሜት የሚገልፅ ብቻ ሳይሆን የህዝቡም ጥያቄ እባካቸሁ ሰህተት አርማችሁ ለዝንተ ዓለም ግዙን፤ የያዛችሁት መስመርም እንከን የለውም በሚል ጥያቄ የተወጠረ የሚያስመስል ነው፡፡ ህዝቡ ከዳር እስከዳር እየተንቀሳቀሰ የሚያነሳውን የነፃነት፣ የዴሞክራሲ፤ በእኩል የመልማት፤ የእውነተኛ ፌዴራል ስርዓት ግንባታ፣ ወዘተ … ወደ ቁስና የዳቦ ጥያቄ ከፍ ሲል የልማት ማለትም የመንገድና የግድብ ጥያቄ ለማውረድ የፈለገ መግለጫ ነው፡፡ ለነገሩ እኛ እንደ ህዝብ የምንጠይቀው ጥያቄ ለራሳቸው የሌላቸውን መሆኑ አንዱ ችግር ሲሆን፤ ሌላው ችግር ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል የምንረዳበት አረዳድም ከኢህአዴጋዊያን ጋር ልዮነት አለው፡፡
“የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ … በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች በተለይ ደግሞ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ስር እየሰደደ እንደመጣ አረጋግጧል፡፡ ይህም ሐሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርባቸውን የመታገያ መድረኮች የሚገድብና የሚያጠብ ስለዚህም ደግሞ በአመራሩ ውስጥ የአመለካከትና የተግባር አንድነትና ጥራት እንዳይፈጠር መሰናክል ሆኖ እንደቆየ ተመልክቷል፡፡ ይህ ችግር በዋነኛነት በድርጅታችን ከፍተኛ አመራር ደረጃ ከታየው የተዛባ የስልጣን አተያይና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የተከሰተ ሲሆን ችግሩ የድርጅታችን አይነተኛ መለያ የሆነውን ዴሞክራሲያዊነት በማዳከም ሳይወሰን ስልጣን የህዝብ መገልገያ እንዲሆን የጀመርነውን መልካም ጉዞ ለአደጋ ያጋለጠ ሆኖ ቆይቷል፡፡”
ይህ ትክክለኛ ግምገማ ተብሎ ሊወሰድ ቢችል እንኳን፤ መሰረቱ ልክ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ መቼም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሆኖ አያውቅም፡፡ ሲጀምርም ዴሞክራሲ የሚባለውን ቃል ከማንብነብ አልፎ በተግባር አውሎት አያውቅም፡፡ ድርጅታዊ ዲሲፕሊን እና ማዕከላዊነት በሚል መርዕ ሲመራ እና በግለሰቦች ሃሳብ አምንጭነት ሌሎች በፈፃሚነት ብቻ የሚታወቁበት ድርጅት ነው፡፡ አሁን እንዳውም ችግሩ የመጣው የተወሰኑ ግለሰቦችና አባል ድርጅቶች ከዚህ ማዕከላዊነት በማፈንገጥ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ በመንቀሳቀሳቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ግምገማው ሰለዚህ ትክክለኛውን መስመር ለማሳት እና ወደ ቀደሞ አንባገነን ስርዓት ለመመለስ የሚመስል ነው፡፡ ይህ ግን ፍላጎት ካልሆነ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የራሱ ሃሳብ ያለው በሌሎች ላይ ሃሳቡን የሚጭን የኢህአዴግ አመራር የለም፡፡ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በዚህ አይታሙም፡፡ ካላቸው የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ይህን ማድረግ አያቅታቸውም ብለን እድል ይስጣቸው ስንል ለነበርን ሰዎች አንገት አስደፉን እንጂ ምንም ተጨባጭ ነገር አላሳዩንም፡፡ ይህ ከበቂ በላይ የሙከራ ጊዜ ይመስለኛል ለአቶ ሀይለማሪያም፡፡
መግለጫው የብዙዎችን ቀልብ የሳባው ክፍል ደግሞ የሚከተለው ነው፡፡
“ዴሞክራሲ እየጠበበ አድርባይነት በመስፋፋቱ ምክንያት በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመስርቶ ከመተጋገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙነትና አካሄድ ማስፈን የተለመደ ስልት ወደመሆን ተሸጋግሯል፡፡ ይህን የመሰለው በጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ መርህ አልባ ግንኙነት ኢህአዴግና አባል ድርጀቶቹን የማዳከም ውጤት አስከትሏል፡፡”
“ማንኛውም መርህ አልባ ቡድናዊ ትስሽር ከምንም ነገር በፊትና በላይ እያንዳንዱን ብሄራዊ ድርጅትና በእሱም የሚመራውን ህዝብ የሚጎዳ አደገኛ ጉዳይ ነው፡፡ በመቀጠልም በግንባራችን የሚመራውን የጋራ ትግልና አገራዊ የለውጥ ሂደቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በየትኛውም ክልል ሆነ ብሄራዊ ድርጅት የሚከሰቱ መርህ አልባ ጉድኝቶች በጥልቅ እየተፈተሹ ሊወገዱ እንደሚገባ ወስኗል፡፡”
መቼም ይህ ጉዳይ ብዙዎች እንደገመቱት የብአዴን እና ኦህዴድ የጀመሩትን አማራ ጠላትህ የሚለውን የጫካ ፕሮፓጋንዳን ሰብሮ ሁላችን ኢትዮጵያዊ ነን፤ ወደሚል መምጣት ከሆነ በእውነትም ኢህአዴግ መሞቻው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሀወሓት ከአብዲ ጋር የጀመረችውን ግንኙነት ለመግለፅ ከሆነ ለቡድን ፍለጎት ሲባል ከግምሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ የተፈናቀለበትን በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ትክክለኛ ነጥብ ይሆናል፡፡ ይህም ቢሆን የቡድን አባቶቹ እና ፈፃሚዎቹ ለፍርድ የማይቀርቡበት ለሚሊዮኖች ሰቆቆ ምክንያት የሆነን ጉዳይ በመግለጫ ለማለፍ ከሆነ ተቀባይነት የሚኖረው አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ የኦሮሞ ኤሊቶች እንደ ቀድሞ በትንሽ በትልቁ ተጨቆንን ብለው ሲያለቅሱ ለማላቀስ፤ በተረት ተረት ታሪክ ዛቢያ ጠምዶ የኢትዮጵያ ባለቤቶች እንዳይሆኑ ከህዝቡ ጋር ተሰማምተው እንዳይኖሩ የተሸረበ ሴራ በውስጥ መስመር የሚነበብ ነው፡፡
በኢህአዴግ መነፅር የምታስጎመዠው አገራችን ብሎ በገለፀበት መግለጫ ውስጥ ይህም ይገኛል፤
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ባሉ የአገራችን አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እየደፈረሰ ሁከት የለት ተለት ክስተት እየሆነ መጥቷል፡፡ በክልሎችም ሆነ በክልሎች መካከል በልዩ ልዩ ሰበቦች የሚከሰተው የሰላም መደፍረስ ለዜጎቻችን አሳዛኝ ሞት መበራከትና መቁሰል እንዲሁም ከባድ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ የንብረት ውድመትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መገታት አስከትሏል፡፡ ይህ ለረጅም አመታት በሰላም በኖረችው አገር ውስጥ የስጋት መንፈስና ጭንቀት ፈጥሯል፡፡ ከየቦታው እየተነሱ ያሉ ግጭቶች ከሰው ሞትና ከንብረት ውድመት በዘለለ ሃገራዊ ሕልውናችንን ለአደጋና ሕዝባችንን ለጥፋት ቋፍ ያደረሱበት ሁኔታ ከመኖሩ በላይ ለውጭ ጥቃት ተጋላጭነታችንን የመጨመር ውጤት አስከትለዋል፡፡”
እዘህ ጋ የውስጥ ሰላም አለመኖሩ የሁላችን እመም ከሆነ መቆየቱ ሳይሆን ለመፍትሔው በጋራ እንቁም ማለት ከጀመርን የቆየን ቢሆንም፣ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ተገቢ ምላሽ ማግኘት ያለመቻሉ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ደግሞ “`ሉውጭ ጥቃት ተጋላጭነታችንን የመጨመር ውጤት አስከትሏል” በሚል መርዶ ነግሮናል፡፡ የትኛው የውጭ ሀይል እንደሆነ ባይገለፅም የተዳከመች አገር እጣ ፈንታ ይህ ሊሆን እንደሚችል ግን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ምንአልባትም መዳከማችንን አይተው የጎመዡ ሀይሎች ምልከታ ሳይሆን አይቀርም የምታስጎመዥ አገር እያሉ ኢህአዴጎች የሚቀልዱት፡፡
ቀልደኛዎቹ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚዎች ሰለመድበለ ፓርተ ስርዓትም ተነጋግረናል ነው የሚሉት፤ አሁንም በበቂ ሁኔታ ችግሩን ለመፍታት በሚያስችል ደረጃ እንዳልገባቸው የሚያስገነዝበው መግለጫው እንዲህ ይላል፤
“በአገራችን የሚገነባው ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በፍላጎትና ጥቅሞች ብዝሃነት ላይ የተመሰረት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በድርጅታችንና በመንግስት መሪነት ለ25 አመታት የቀጠለ ቢሆንም ከቅርብ አመታት ወዲህ የአስተሳሰብ ብዝሃነት በአግባቡ እንዲገለፅ የሚያደርግ ተጨባጭ ሁኔታ እየተዳከመ መጥቷል፡፡ ይህንን ችግር በጊዜና በአግባቡ ተገንዝቦ ማስተካከል የሚገባው ድርጅታችን ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ያሳየው ዳተኝነት የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ችግር እንዲገጥመዉ አድርጓል፡፡ የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ጉዳይ ምንም እንኳ በአዋጅና በድርጅታችን በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የሚመሰረት ባይሆንም በዚህ ረገድ ልንወስደው ይገባን የነበረውን ርምጃ ከመውሰድ አንፃር ሰፊ ክፍተት እንደነበር ሥራ አስፈፃሚው ይገነዘባል፡፡”
ኢህአዴግ እንደፓርቲም ሆነ መንግሰት ሆን ብሎ አውራ ፓርቲ ለመመስረት በሚል ያጠፋቸውን የመድበለ ፓርቲ ምሶሶወች የሆኑትን አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በእስር የሚያማቅቃቸው የፖለቲካ መሪዎች፣ በደሞዝተኛና ቅጥረኛ የፖለቲካ መሪዎች ተክቶ በፓርቲዎች ምክር ቤት ስም መቀለዱን በደንብ የተገነዘበ መሆኑን መግለጫው አያሳይም፡፡ ለሚዲያም ቢሆን በተመሳሳይ ሁኔታ ሸውራራ እይታ እንዳለው እና ግምገማው ከክልል ሚዲያዎች ፉክክርን ከማንሳት ያልዘለለ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህን መግለጫ ለተመለከተ እነዚህ ሰዎች ምን እየሰሩ ነው? ብሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡
መግለጫው እንዲህም ይላል፤
“የህግ የበላይነት የማስፈን ድክመት በመታየቱ በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱና ህጋዊና አስተማሪ በሆነ መንገድ መጠየቅ ሳይቻል ቆይቷል፡፡ ዜጎች በህገ መንግስቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸውን የሚጥሱ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ መሆን በሚገባው ደረጃ ሳይፈፀም ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም መንግስት የህዝብና የአገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በነደፋቸው ፕሮጄክቶት ዙሪያ የሚታዩ የአፈፃፀምና የስነ ምግባር ችግሮችን አስተማማኝና ውጤታማ በሆነ መንገድ የማረምና የማስተካከል ጉድለት ታይቷል፡፡ በዚህ የተነሳ አገራችንን በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ ሊያደርጉ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ሊያሰፉ የሚችሉ ፕሮጄክቶች፣ የጊዜ የዋጋ ንረትና የሃብት ብክነት የሚታይባቸው ሆነዋል፡፡”
በዚህ ደረጃ የውረደን ደካማ መንግሰት ለተሸከመ ህዝብ ፅናቱን መመኘት ተገቢ ነው፡፡ ሞራል ያለው አመራር ቢኖር ግን ፓርላማውን በትኖ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረብ ብቻ ነበር መፍትሔው፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፈጻሚ እንደመፍትሔ ያቀረበው “ግድ የለም አስተካክላለው ነው፡፡” ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፤ ሚዲያውን፣ ሲቪል ማህበራትን፣ ወዘተ.. በትክክል እንዳይሰሩ ማድረጉን የገመገመ ስራ አስፈፃሚ ውጤቱ የሚሆነው ከላይ እንደተቀመጠው በህግም በአሰራርም የተዝረከረከ መሆኑን ነው፡፡ የህግ የበላይነትን ማስፈን ያልቻለ፣ በህገ መንግሰት እውቅና ያገኙ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያፍን መንግሰት “መንግሰት” ተብሎ ለመጠራት አይመጥንም፡፡ መግለጫው ይህን ችግር የከፍተኛ አመራሩ መሆኑን ይቀባላል፡፡ እንዲህ በማለት፤
“ከላይ የተገለፁት ችግሮችና በተራዘመ ትግል የተገነባችውን አገር ለአደጋ ማጋለጥ የጀመሩት ጉድለቶች በዋነኛነት የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር በተለይም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ድክመቶች ናቸው፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱና የድርጅትና የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች በተናጠልና በጋራ፣ ስትራቴጂያዊና ታክቲካዊ አመራር የመስጠት ሃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ በዚህ ግምገማ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የመንግስት የበላይ አመራሮች ወቅቱ የሚጠይቀውን ስትራቴጂያዊ አመራር የመስጠት ጉድለታቸው ሰፊ እንደሆነ ታይቷል፡፡ ከፍተኛ አመራሩ ችግር አስቀድሞ የመለየት፣ ተንትኖ የማወቅ፣ የመፍቻ መንገዶች የመተለምና በዚሁ መሠረት የመፍታት ብቃቱ ወቅቱና መድረኩ ከሚጠይቀው ደረጃ ጋር አብሮ ባለማደጉ የተወሳሰበውን አገራዊ መድረክ በብቃት የመምራት ጉድለት እንደነበረበት የጋራ አቋም ተይዟል፡፡ በመሆኑም ለተፈፀመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡”
ለዚህ ደግሞ ከሃላፊነት መልቀቅ ትንሹ ጉዳይ መሆን ነበረበት፡፡ ሃላፊነት ይወስዳል፣ ልባዊ ይቅርታም ይጠይቃል በሚል ብቻ ታለፈ፡፡ ከዚህ ሁሉ ረብ የለሸ ሀተታ በኋላ ለመግለጫው መቋጫ የሆኑት ሰምንት ነጥቦች ያስቀመጠ ሲሆን፣ እንደተለመደው ኮንፈረንስና ስብሰባ በመጥራት የህዝብን ሀብትና ንብረት ከማባከን ያለፈ አንድም ፋይዳ ያላቸው ነገሮች የሉትም፡፡ የህዝብ ጥያቄ የስርዓት ለውጥ በስርዓት የሚል መሆኑን መረዳት ያቀተው መንግሰትም እዚህም እዚያም የሚነሱ ምልክቶችን እየተከተለ ለመፍታት ሲባዝን አገር እንዳትበተን ስጋታችን ነው፡፡ ከዚህ ቀደሞ ግን ይህን መረዳት ያቀታቸውን ገዢዎቸ በማንኛውም ሁኔታ መወገድ አለባቸው፡፡ አዲዮስ ….. ሰዮም ተሾመ እንዳለው ከሚያፈርሱን አፍረሰናቸው ንሰሐ መግባት ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፡፡
ግርማ ሰይፉ ማሩ
