January 3, 2018 mail
——
ሸንቁጥ አየለ
—————-
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ይቅርታ መጠየቁ መልካም አድርጓል:: ሆኖም እሱ እራሱ ይቅርታ የጠዬቀዉን ነገር አንዳንድ ደጋፊዎቹ ለምን ተተቸብን እያሉ አካኪ ዘራፍ ማለታቸዉ አልገባኝም::እነሱን የቆረቆራቸዉ የዶ/ር ታደስ ብሩ መተቸት ነዉ::እኛን የቆረቆረን ደግሞ የሚሊዮን ህዝባችን የነገ እጣ ፋንታ ነዉ::

በወያኔ ሀያ ስድስት አመታት ዉስጥ ዜጎች ከዬ አካባቢዉ የሚፈናቀሉት: የሚታረዱት እና የሚሰደዱት አንዱን ህዝብ ለአንዱ አካባቢ መጤ ሌላዉን ደግሞ ባለ ሀገር ነዉ በማለት ወያኔ የሚከተለዉ የጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና ነዉ::
ሁለት ምሳሌ ብቻ እጠቅሳለሁ::ሶማሌ ክልል ላይ ግማሽ ሚሊዮን ኦሮሞዎች ለሶማሌ ክልል መጤ ተብለዉ እንዲፈናቀሉ እና እንዲጨፈጨፉ ተደርጓል::ጉራ ፋርዳ ላይ ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን አማሮች መጤ ተብለዉ እንዲፈናቀሉ እና እንዲጨፈጨፉ ተደርጓል::አሁን ዶክተር ታደሰ ብሩ አማራን የመሃል ሸዋ መጤ ህዝብ ብሎ ተናግሯል::ይሄ የመጤ ፍልስፍና በአዲስ አበባ ሚሊዮን ነዋሪ ላይ ምን ሊያስከትልበት ይችላል ብሎ ማሰብ ህዝባዊነት ነዉ::
የወያኔ የጎሳ ፍልስፍና ሁሉ መደምሰስ አለበት::የወያኔ ህገመንግስትም መሻር እና በሌላ ህገመንግስት መተካት አለበት:: በወያኔ ኢትዮጵያ ወላይታዉ ለአዋሳ ከተማ መጤ ነዉ::በርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያን ለበርካታ የሀገሪቱ ክፍል መጤ ናቸዉ:: ይሄም ሀገሪቱ በርስ በርስ ፍጅት ዉስጥ እንድትመሰግ ዋና የመንደርደሪያ ሀሳብ ነዉ::ይሄን የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ የሚያነሳ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ጠላት ነዉ:: ስለዚህ ይሄን የመጤ ፖለቲካን የሚያነሳን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀላሉ አይለቀዉም::
ዶ/ር ታደስ ብሩም የተናገረዉ ነገር ስህተት መሆኑን አልካደም::እራሱም ይቅርታ ጠይቆበታል::ዝም ብላችሁ የምትደግፉት እና ለምን ተነቀፈ ብላችሁ የምትከራከሩ ሰዎች ግን እራሳችሁን መርምሩ::
የሀገር ህልዉና ከግለሰቦች ማንነት በላይ ነዉ::የህዝብ ጥቅም ከግለሰቦች በላይ ነዉ::
ወያኔ 87 ብሄረሰብ ያለባት ኢትዮጵያን ለሰባት ብሄሮች ብቻ ሸንሽኖ ሰጥቶ ሰማኒያዉ የኢትዮጵያ ብሄረሰብ አገር አልባ እና መጤ እንዲሆን ያደረገው አካሄድ መፍረስ ነዉ ያለበት::ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዉያን ነች::የትኛዉም ክልል የአንድ ብሄር ብቻ አይሆንም::የወያኔ ጠንቀኛ ህገ መንግስት ይፈርሳል:: የሀገሪቱም አስተዳደራዊ ክፍፍል ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ሰፊ እና ጥልቅ ምክክር አድርገዉበት ዘላቂነት እና አስተማማኝ መሰረት ላይ በቆመ ጽንሰ ሀሳብ እየተመራ ይሆናል::
ለአንድ አካባቢ ማንም ኢትዮጵያዊ መጤ ወይም ማንም ኢትዮጵያዊ የጥንት ነዋሪ የሚባል ህሳቤ ሁሉ ይደመሰሳል::
