January 3, 2018
ማክሰኞ፣ ታህሣሥ ፳ ፬ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት ( 1/2/2018 )
በዩናትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ፤ ባሁኑ ጊዜ፤ በአስተዳደሩ ዋና ማዕከላዊ ቦታዎች፤ በሥራ አስፈጻሚው ማዕከል (ዋይት ሀውስ)፣ በሕግ አርቃቂው አካል ማዕከል (ኮንግሬስ)፣ እና በፍርድ ማዕከላዊ ቁንጮው (ሱፕሪም ኮርቱ) ዙሪያ ያለውን ሽርጉድና መደናበር፤ የዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም ሕዝብ በሙሉ ጀሮውን አቅንቶ የሚከታተለው ጉዳይ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ፤ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ ባላት ክብደትና፤ በአሁኑ የዓለም ኢኮኖሚ የምትጫወተው ከፍተኛ ሚና፤ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሂደት፤ የዓለምን ሕዝብ ትኩረት መሳቡ የሚያስገርም አይደለም። እኔ በአሜሪካ ኗሪ ስለሆንኩ፤ ቴሊቪዥኑን ስከፍተው፣ ድረገጾችን ሳሸት፣ ሬዲዮኑን ሳዳምጥ፤ በዚህ ወግ ተከብቤ ነው ያለሁትና፤ አቅሌን ሳይስበው አልቀረም። ደግሞ ስደተኛ የትም ይገኝ የትም፤ ያለበት ሀገር ፖለቲካና የራሱ ሀገር ፖለቲካ እየተዛመዱ እንቅልፍ እንደሚያሳጡት ሁሉ፤ እኔንም እንቅልፍ ነስቶኛል። እናም ይሄን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ማዛመዴ አይቀሬነቱ ግልጥ ነው። የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛው ይሄው ጉዳይ ነው።
በዚሁ አሁን ጣራ ነክቶ ብዙዎቹን እያተራመሰ ባለው ሂደት፤ የቅርብ ተመሳሳይነት አለው የሚባለው የኒክሰን አወዳደቅ፤ ከመነጋገሪያ ጉዳዮች አንዱ ነው። ዋተርጌት፤ የፕሬዘዳንት ሪቻርድ ኒክሰን የሥልጣን መባለግና ቅሌት፤ የመጨረሻ ውድቀት ክንውን ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ የፖለቲካ ታሪክ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ በሥልጣን የባለገ የሀገር መሪ፤ ከሀገር መሪነቱ ተገዶ የወረደበትና በቦታው በሕጋዊ መንገድ ምክትሉ ሥልጣኑን የተረከበበት ክስተት ነበር። ይህ መሪ፤ በተወዳዳሪዎቹ ላይ ያለው ጥላቻ፤ ሀሞቱን መርዞ፤ አቅነዝንዞት፣ ጥላቻው ራሱ፤ ራሱኑ ለክፎ፣ ራሱኑ መርዞ አጠፋው። ምንም እንኳን የፖለቲካ ቅኝታቸው ከኒክሰን ጋር አንድ የሆኑ ጥቂት ሰዎች አሁንም ኒክሰንን ንጹህና ጥሩ ሰው አድርገው ቢመለከቱም፤ አብዛኛው የወቅቱን ሁኔታ የተከታታለው የሀገሩ ሰው፤ ኒክሰን በጣም ዘረኛ፣ ትምክህተኛ፣ መናጢና የተለከፈ ሰው መሆኑን አጥብቆ ያምናል።
ሥልጣንና ተወዳዳሪን መጥላት፤ በጣም በቅርብ ተያይዘው ሊሄዱ የሚችሉ ባህሪያት ናቸው። ይህ ነው በመሠልጣን ላይ ባሉ ሀገራት፤ አምባገነኖች፤ በሥልጣን ላይ ሙጭጭ ብለው ለመቆየት የሚጠቀሙበትን ከሕግ በወጣ መንገድ የሚያስኬዳቸው አባዜ። ሊተኳቸው የምችሉና የሚገቡ ግለሰቦችን በመጥላት፣ እኒህ ሰዎች በሕዝቡ ባላቸው ተቀባይነት በመቅናት፤ በብቃታቸው በመመቅኘት፣ ጉልበትን መሳሪያ አድርገው ሕዝቡን ረግጠው ይገዛሉ። አድርባዮችን በዙሪያቸው ይሰበስባሉ። ሆድ አደሮችን በከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ያስቀምጣሉ። “ሥልጣን ያባልጋል። ከፍ ያለ ሥልጣን ደግሞ፣ ከፍ አድርጎ ያባልጋል!” የሚል አባባል አለ። ለዚህ መባለጊያ ሆኖ የሚያገለግላቸው፤ የሚቆጣጠሩት የሀገሪቱ የሕግ ክፍል፣ የጸጥታ ክፍሉንና፣ ወታደራዊ መዋቅሩን በመጠቀም፣ ሕግና ደንብን ለመጠበቅ፣ ስነ ሥርዓት ለማስከበር፣ የሀገርን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚሉት ናቸው።
ይህ እንግዲህ በመሠልጠን ላይ ባሉ ሀገሮች የዕለት ተዕለት ሙያ ሆኖ ሲሠራ፤ የሠለጠኑ ሀገሮች ላይ እንዳይሠራ፤ ሕግና ደንቡ፣ ከዚያም አልፎ ይህ እንዳይከሰት በቦታቸው የተቀመጡ ተቋሞች፤ ከሕዝቡ የፖለቲካ ግንዛቤና ንቃተ ሕሊና ጋር በመዳመር፤ እንቅፋት ሆነው ባለበት ያቆሙታል። ፕሬዘዳንት ሪቻርድ ኒክሰን፤ እንደ በመሠልጠን ላይ ያሉ ሀገሮች አምባገነን መሪዎች፤ ያደረገው ይሄንኑ ሕገ ወጥ ተግባር ነበር። ኒክሰንን ከሥልጣን እንዲወርድ ያደረጉት ደግሞ፤ በኃላፊነት የተመደቡት፤ ለግል ፍላጎትህ ልታዘኝ አትችልም ያሉት የራሱ ምሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች፣ አእምሯቸው ለመጥፎ ተግባር አልገዛ ያላቸው የአስተዳደሩ የውስጥ አባሎች፣ የተለያዩ የመንግሥት አካሎች ያላቸውን ኃላፊነት በመወጣትና ከሁሉም በላይ፤ ያገሩ ሕዝብ በገፍ የሂደቱ አካል ሆኖ፤ ወጥቶ መቆጠሩ ናቸው። ይህ ዴሞክራሲያዊ አሰራርን በተግባር ማዋል ማለት ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ሕገ መንግሥት፤ በተግባር ላይ ዋለ። ኒክሰን ለተግባሩ ተገቢ ዋጋውን አገኘ። በዙሪያው የነበሩና በመጥፎው ተግባር የተሳተፉት በሙሉ ፍርዳቸውን ተቀበሉ። ኒክሰንም ስህተቱን ሳያምንና ሳይጸጸት ወደ መቃብሩ ወረደ።
ዶናልድ ትራምፕ ከኒክሰን የከፋ በደል በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ፈጽሟል። እንደ ሪቻርድ ኒክሰን ከሥልጣኑ እንዲወርድ ይገደዳል ወይንም አይገደድም? የሚለው፤ ለአሁኑ በንጥልጥል ላይ ነው። ሪቻርድ ኒክሰንን ከሥልጣን ያወረደው፤ የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ በብዛት በያለበት በመውጣትና ተወካዮቹን በማካለብ ነበር። ይሄ አሁን ይከተል ይሆን? ጥያቄው ይቀጥላል። ትራምፕ ለራሱ ጥቅም ብቻ ሳይሆን፤ በማይችልበትና ብቃቱ በሌለው የሥልጣን ቦታ ለመቀመጥ፤ ሩፓብሊኮች ፍጹም በሕልማቸው እንኳን የማያስቡትን፤ በፖለቲካ ግንዛቤዋቸው ለዩናይትድ ስቴትስ ዋና ጠላት ከተባለችው ከሩስያ ጋር በውስጥ በመመሳጠር፤ ሀገሪቱን አጋልጦ፤ የዴሞክራሲያዊ አሰራሩን ባህል ጥሶ፣ ሕግ በማፍረስ ውድድሩን አጣሞ፤ዉጤቱን ለውጧል። ያ ቅዠት አሁንም እያባነነው፤ በየሄደበት ያንኑ ውድድሩን እንደገና እያነሳ ይጥለዋል።
የትራምፕ የሩስያ ቅሌት የፖለቲካ ሂደት አዲስ ስለሆነና ሁላችንም እየተከታተልነው የምንሄድ ስለሆነ፤ የንጥልጥሉን መደምደሚያ ከወዲሁ መጻፍ አልችልም። ነገር ግን፤ ይህ ክስተት በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ፤ ከኒክሰኑ ያላነሰ የጥላሸት ቦታ እንደሚኖረው ጥርጥር የለኝም። ታዲያ፤ ይህ በሠለጠነው አሜሪካ፣ ብዙ የዴሞክራሲ ጠበቆች የሆኑ ተቋሞች ባሉበት ሀገር፣ በዓለም ዙሪያ ዴሞክራሲን አስፋፋለሁ እየለች በምትጠራወዝ ሀገር፤ ይሄን የመሰለ ወለሉ በጣም የዘቀጠ ተግባር ከተፈጸመ፤ ይህ የመሠልጠን ወይንም ያለ መሠለጠን ሳይሆን፤ የሰው ልጅ ባህሪ ሙሉ ሊሆን አይችልም ወይ? ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል። የኒክሰን፣ የትራምፕና የትግሬዎቹ ገዥዎቻችን ባህሪ፤ ሰው ቅዱስ ለመሆን፣ ለሙሉ ጻዲቅነት፣ ለብፅዕና፣ ለቅዱስነት፣ ለመልዐክነት፣ አይበቃምን? ያስብላል። እውነት ግን ያን ማድረግ አይቻልም? ወይንስ በፖለቲካው ዓለም የሚዘፈቁ ሰዎች፤ ከዚህ የፖለቲካ ሥልጣን ጥማታቸው ጋር የተያያዘ የባህሪ ጉድለት ከመሠረቱ አላቸው? በሶስተኛ ዓለም ብቻ የሚተገበር እንዳይባል፤ ኒክሰንና ትራምፕ አለመሆኑን አረጋግጠውልናል። ይህ በሁሉም ሀገሮች ከተከሰተና ከታዬ፤ የሰውን ባህሪ ማመልከቻ እንደሆነ፤ እስኪ ተነጋገሩበት። እኔ ወደ ሀገራችን ፖለቲካ ልመለስ።
ስለ ትግሬዎቹ መንግሥት ምንነትና ተግባር ለአንባቢው መግለጽ፤ ቀባሪውን ማርዳት ይሆንብኛልና። ነገር ግን አሁን በሀገራችን ያለው ሂደት፤ ከኒክሰንና ከትራምፕ ጋር ምን አዛመደው? የሚል ጥያቄ ስለሚነሳ፤ አዛማጁ እኔ ነኝና፤ መልሱን አቀርባለሁ። የትግሬዎቹ መንግሥት፤ እንደ ኒክሰን ቂመኛና መሰሪ፣ መሪዎቹ እንደ ትራምፕ ራሳቸውን ለማበልጸግ ሀገሪቱን የሚቸርችሩና እየቸረቸሩ ያሉ ናቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ኒክሰንና ትራምፕ፤ በወቅታቸው፤ ፕሬዘዳንት ይሆናሉ ብሎ የሚያምን ማግኘት ከባድ ነበር። የኒክሰንን በማንበብ፣ የትራምፕን ደግሞ በማየት ያወቅሁት ነው። የትግሬዎቹ መንግሥትም እንዲሁ ነው። ተከዜን ተሻግረው መጥተው፤ አዲስ አበባ ገብተው መንግሥት ይሆናሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ራሳቸውም ቢሆን፤ ትግራይን ነፃ ከማውጣት አልፈው፤ አዲስ አበባ ገብተን ኢትዮጵያን ረግጠን እንገዛለን የሚል እምነት አልነበራቸውም። የዚህ ዋናው ማመልከቻው፤ አሁንም በትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ስም መግዛታቸው ነው። ዛሬም በቋፍ ተንጠልጥለው ወደ ትግራይ ለመብረር ተዘጋጅተው እንዳሉ ሁሉ፤ አዲስ አበባ ከገቡ ጊዜ ጀምረውም ቢሆን፤ ተማምነውና ተረጋግተው አልተቀመጡም።
የስግብግብነታቸው ብዛት፤ የሀገሪቱን ሀብት ሟጥጠው ወደ ትግራይ ማሻገር ብቻ ሳይሆን፤ የማይነቃነቀውን ሀብት፤ ባለበት ባለቤት ሆነውበታል። ራስ ደጀንንም ባለበት የትግራይ ኩል ለቅልቀውታል። አሁንም ብርጉጎች ናቸው። መስሪዎች ናቸው። ለዐማራው ያላቸው ጥላቻ ወሰን የለውም። የመረረ፣ የጠለሸ፣ የከፋ ጥላቻ በደማቸው ይንቆረቆራል። ይህን የትግሬዎቹን መንግሥት የሚከተለው ፍርድ፤ ከኒክሰንና ከትራምፕ የከፋ እንደሚሆን ጥርጣሬ የለኝም። ከመሪዎቹና ከፓርቲው አባላት፣ ከተራ ተጠቃሚውና ከዘመዶቻቸው፣ በመላ ኢትዮጵያ ከተበታተነው የትግራይ ተወላጅ በላይ አደጋው ፈጦ ይታየኛል። የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመቱ ይዘገንነኛል። እዚህ ላይ፤ እኔ፤ ይሄ እንዲፈጸም የመፈለጌ ወይንም ያለመፈለጌ ጉዳይ አይደለም። በዐማራው ላይ በዐማራነቱ ያተኮረ በደልን የምቃወም ግለሰብ፤ በትግሬው ላይ በትግሬነቱ ያተኮረን በደል ባልቃወም፤ የመጀመሪያው ተቃውሞዬ፤ መሠረታዊና በደልን መቃወም ሳይሆን፤ ለምን በኔ ደረሰ! የሚል የግል ተከላካይነት ብቻ ይሆናል። ለኔ በዐማራው ላይ የደረሰውን የዘር ማጽዳት የምቃወመው፤ መሠረታዊና ፍትኀና በደልና ያገናዘበ በመሆኑ ነው። ይህ በትግሬዎች ላይ የተንጠለጠለው የነገ ሀቃችን፤ ማናችንንም ብንሆን፤ ከራሳችን አብልጠን፤ የትክክለኛ ፍርድና ፍትኅ መከተል አሳሳቢ ሆኖብን፤ አብረን ልንታገል የምንችልበትን መንገድ ባስቸኳይ እንድንፈልግ ግድ ይለናል።
የኒክሰን፣ የትራምፕና የትግሬዎቹ ገዥዎቻችን ባህሪ፤ ሰው ቅዱስ ለመሆን፣ ለሙሉ ጻዲቅነት፣ ለመልዐክነት፣ አይበቃም ያስብላል። እውነት ግን ያን ማድረግ አይቻልም? ወይንስ በፖለቲካው ዓለም የሚዘፈቁ ሰዎች፤ ከዚህ የፖለቲካ ሥልጣን ጥማታቸው ጋር የተያያዘ የባህሪ ጉድለት ከመሠረቱ አላቸው? በሶስተኛ ዓለም ብቻ የሚተገበር እንዳይባል፤ ኒክሰንና ትራምፕ አለመሆኑን አረጋግጠውልናል።
