Skip to content
በኢትዮጵያ ታስረው ከሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መካከል እነማን ይፈቱ በሚለው ጉዳይ ምክክር እየተደረገ እንደሚገኝ ምንጮች ለቢቢኤን ጠቆሙ፡፡ ገዥው ፓርቲ በትላንትናው ዕለት በሰጠው መግለጫ፤ ‹‹ለብሔራዊ መግባባት ሲባል›› የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ሆኖም የትኞቹ ፖለቲከኞች መፈታት እንዳለባቸው እስካሁን በእርግጠኝነት ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሲሆን፤ የገዥው ፓርቲ ባለስልጣናትም በዚህ ጉዳይ ላይ እየመከሩበት እንደሚገኙ ነው ምንጮቹ ያረጋገጡት፡፡
በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የትኞቹን እንፍታ፣ የትኞቹን እናስቀር፣ ወይስ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እንፍታ በሚለው ጉዳይ ላይ ገና መግባባት ላይ እንዳልተደረሰ የጠቆሙት ምንጮች፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ባለስልጣናቱ ምክክር እያደረጉ እንደሚገኙ ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ እና የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በተገኙበት ትላንት የተሰጠው መግለጫ፤ ፓርቲው በህዝባዊ ተቃውሞ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን የሚያመላክት እንደነበር ሲነገር ቆይቷል፡፡በመግለጫው መሰረት፤ የተፈረደባቸውም ሆነ ጉዳያቸው በዓቃቤ ህግ ተይዞ በቀጠሮ ላይ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ ቢገለጽም፤ እነማን እንደሚፈቱ ግን እስካሁን ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ ሌላው ሰው ቆርቶ ራሳቸው መግለጫውን የሰጡት ባለስልጣናት እንኳን የትኞቹ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ በቅጡ አለማወቃቸውን ከመረጃ ምንጮች ገለጻ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በኢትዮጵያ ከግንቦት ሰባት፣ ከኦነግ እና ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ፈጥራችኋል፣ አመጽ ቀስቅሳችኋል በሚሉ ውንጀላዎች እጅግ በርካታ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ፍቺው ዋና ዋና የሚባሉትን ወይም በስም የሚታወቁትን የፖለቲካ እስረኞች ብቻ ሊያካትት እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢወጡም፤ ማረጋገጫ ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በስም የሚታወቁ የፖለቲካ እስረኞችን ፈትቶ የህዝብን ጥያቄ መለስን ማለት እንደማይቻል የሚያስገነዝቡ ታዛቢዎች፤ ከተፈቱ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች መፈታት እንዳለባቸው ያስረግጣሉ፡፡
(BBN News January 4, 2018)