January 6, 2018 10:44

ብዙ ጊዜ ባል እየመጣላት ባልታወቀ ምክንያት ግን አንዳቸውም ሊያገቧት ቃል ሊገቡላት ባለመቻላቸው ተስፋ የቆረጠች ወይዘሪት ትምቧለል፣ በመጨረሻ ላይ አንድ ደመላሽ የሚባል ጎበዝ “ላገባሽ በግዜር ፊት ቃል ገባሁልሽ” ብሎ ቀለበት ሲያስርላት ነው፣ የብዙ ጎረምሶች በህይወቷ ውስጥ ብቅ ጥልቅ እያሉ መጥፋት በወንዶች ላይ እምነት ስላሳጣት “ካልታዘልኩ አላምንም“ ያለችው።
ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ፣ የአስራ ሰባት ቀኑን የኢህአዴግ ምሥጢራዊ ስብሰባ መጠናቀቅ አስመልክቶ፣ ዉድ ጠቅላይ ሚንስትራችን፣ ከስብሰባው ድምዳሜዎች አንዱ ነው በማለት፣ “ባገሪቷ ያሉት የፖሊቲካ እስረኞች በሙሉ እንደሚፈቱና በመጥፎነቱ በዓለም ዙርያ “ማዕከላዊ” በመባል የሚታወቀውን የሰው ልጆች ማሰቃያ “ምድራዊ ሲዖል” ዘግተን ወመዘክር እናደርገዋለን ብለው በአደባባይ “ለሚወክሉት ህዝብ” የሰጡት ኦፊሴላዊ መግለጫ ነው። ምሥጢራዊው ስብሰባው ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ በያለንበት የስብሰባውን ውጤት ለመስማት የተገኘውን ቀዳዳ ተጠቅመንና የየራሳችንን ግምት አክለንበት፣ ክፉም ደግም ስናስብ ቆይተን፣ መጨረሻ ላይ “ገዢው ፓርቲ” አገሪቱ ያለችበትን ቀውስ ለማርገብ ሲባል የፖሊቲካ እሥረኞችን “እንፈታለን” ብሎ በፓርቲው አውራ በአቶ ኃይለማሪያም በኩል የምሥራቹን ሲነግረን፣ ለብዙዎቻችን ህልም እንጂ ዕውነት አልመሰለንም። እኔም ነገሩ ሕልም ከመሰላቸው አንዱ ነበርኩ። ከጥቂት ወራት በፊት አቶ በቀለ ገርባ በዋስ እንዲፈቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ አንድ ተራ የእስር ቤቱ ኃላፊ፣ የሆነ ያልሆነ ምክንያት ፈጥሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዳይፈታ “ተጻራሪ ውሳኔ” በማስተለለፉና፣ ይህ ተራ የእሥር ቤት ኃላፊ “በሆነ ነገር ተማምኖ” የፌዴራሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ውሳኔ ሲሽር ስላየሁ ነው፣ ወይዘሪት ትምቧለል፣ ካልታዘልኩ አላምንም እንዳለችው ሁሉ እኔም የአቶ ኃይለማርያም ንግግር በተግባር ካልተተረጎመ አላምንም ያልኩት ለማለት ነው።
አቶ ኃይለማርያም የሰጡትን መግለጫ ጠለቅ ብለን ከዳሰስን ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች አሉበት። እንደው ሳስበው፣ ከድርጅቱ ምሥጢራዊ ስብሰባ አንዳች በጎ ነገር ይወጣዋል ብሎ በጉጉት የሚጠብቀውን መላ ያገሪቱን ሕዝብ ጥም ለማርካት ጊዜያዊ ማስታገሻ ብሎ ያመጣው ነው እንጂ ከልብ፣ ላለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ድርጅቱ እያወቀ ይፈጽማቸው የነበረው መጥፎ ድርጊቶች ዛሬ በድንገት ታይቷቸው ከልብ ይቅርታ ለመጠየቅ አይመስለኝም። ምክንያቶቼን ላቅርብ።
የፖሊቲካ እስረኞችን በተመለከተ፣
ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተለያዩ፣ ባገር ቤትና በውጪ የሚገኙ የሰው ልጅ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያለመታከት ያቀርቡት ለነበረው የፖሊቲካ እስረኞች መፈታት፣ ኢህአዴግ ይሰጥ የነበረው አንድ መልስ “በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የፖሊቲካ እስረኛ የለም” የሚል ነበር። የተባበሩት መንግሥት ድርጅት የሰው ልጆች መብት ኮሚሽን ኤክስፔርቶች፣ በሌሎች አገራትም እንደሚያደርጉት በኢትዮጵያም ያለውን ሁኔታ በቦታው ተገኝተው ለመገምገም ቪዛ ጠይቀው እስከዛሬ ድረስ ሳይሳካላቸው በመቅረቱ፣ የኤክስፔርቶች ሪፖርት እየተባለ በየጊዜው የሚወጣው ዘገባ፣ እንደ ሌሎች አገሮች ከምንጩ ሳይሆን በጎረቤት አገር ካሉት ስደተኞች ወይም አክቲቪስቶች የተወሰደ ምሥክርነት ነው። በቅርብ ጊዜም ባገሪቷ የሰፈነውን የሰው ልጆች መብት ጥሰትና ብሎም ከአፍሪቃ በአንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጣትን የፖሊቲካ እስረኞችን ብዛትና በየቀኑ የሚፈጸምባቸውን አሰቃቂ ድርጊት እንዲያቆም ለኢህአዴግ በተደጋጋሚ ለላካቸው ደብዳቤዎች አዎንታዊ መልስ ሲያጣ፣ ራሱ የሰው ልጆች መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በነበረ ጊዜ ለደረጃው ተመጣጣኝ አቀባበል ሊደረግለት ቀርቶ በአግባቡ ያነጋገረውም ባለሥልጣን አልነበረም። ማዕከላዊን ለመጎብኘትና ከፖሊቲካ እስረኞችም ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ላቀረበውም ጥያቄ፣ ያነጋገራቸውም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ባለሥልጣናት ሲመልሱለት፣ “በኢትዮጵያ ምድር እኮ አንድም የፖሊቲካ እስረኛ የለም፣ ይህንንም በጽሁፍ በተደጋጋሚ አሳውቀንዎት ነበር፣ እዚህ ድረስ መልፋት አልነበረብዎትም“ ብለው ባዶ እጁን ነበር የሸኙት።
ታድያ ዛሬ እንፈታዋቸዋለን የሚሉን የፖሊቲካ እስረኞች የትኞቹ ናቸው? ኢህአዴግ ምናልባት የተለየ ትርጓሜ ሰጥቶት ይሆናል እንጂ ለእኛማ ማንም ኢትዮጵያዊ የኢህአዴግን መመርያ ባለመቀበሉና፣ በተለይም ደግሞ በጸረ ሽብሩ ዓዋጅ ሰበብ የታሰረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የፖሊቲካ እስረኛ ነው። ለሩብ ምዕት ዓመት አንድም የፖሊቲካ እስረኛ የለም ሲል ኖሮ ታድያ ዛሬ “በሙሉ እፈታለሁ” ብሎ የሚያውጀው እነማንን ሊፈታ ነው? ለራሱ ግራ ገብቶት ግራ ሊያጋባ የሚሞክር ግራ መንግሥት!
ማዕከላዊን ለመዝጋት መወሰናቸው፣
ይህ ማዕከላዊ የሚባለው፣ ስለ ሕንጻው የምናወራ ከሆነ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በመባል የሚታወቀው የወንጀል ምርመራ ማዕከል ነበር። ደርግ ደግሞ ከቀይ ሽብር ጊዜ ጀምሮ ተቋሙን አስፋፍቶት የተቃዋሚ ድርጅቶችን አባላትና ሌሎችንም በግል የሚቃወሙትን ኢትዮጵያውያንን አስሮ ለአሥራ ሰባት ዓመት ሲሰቃይበት የነበር ማዕከል ነው። ላለፈው ሃያ
ስድስት ዓመት ግን በተቋሙ ካለፉት መንግሥታት ሁሉ በበለጠ መልኩ በደንብ የተጠቀመበትና እየተጠቀመበትም ያለው የኢህአዴግ መንግሥት ነው። ስለዚህ የሰው ልጆች ማሰቃያና ምድራዊ ሲዖል በመባል ስለሚታወቀው “ማዕከላዊ” አብዛኛው የዓለም መንግሥታት አባላት የሚያውቁትና እንዲፈርስም ደጋግመው የጠየቁት በመሆኑ፣ አሁን ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትን ኢትዮጵያውያንን አስቃይቶና ግማሹን ለዘላለም እንዳያገግሙ አድርጎ ከለቀቃቸው በኋላ፣ የዚህን ማዕከል መዝጋት ትርጉሙ ምንድነው ብሎ መጠየቅ አግባብ ያለው ይመስለኛል።
በኔ ግምት፣ ትልቁ ችግር ከህንጻው ሳይሆን በውስጡ ከሚካሄደው ኢሰብአዊ ድርጊት ነው። ህንጻው ሮቦት አይደለም፣ ተንቀሳቅሶም የፖሊቲካ እሥረኞችን አልገረፈም አላሰቃየም። ወገኖቻችን ያሰቃዩና ለሰቆቃ የዳረጉት በወያኔ የሰራተኛ መዝገብ ላይ ያሉና ከኢትዮጵያ ህዝብ ከሚሰበሰበው ግብር በየወሩ ደሞዝ የሚከፈላቸው “መርማሪ” የሚባል የሽፋን ስም ያላቸው በተግባር ግን የሰውን ልጅ ለማሰቃየት ብቻ በወያኔ ልዩ ትምህርት የተሰጣቸው “አሰቃዮች” ናቸው። እንግዲህ አሁን ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላና የብዙ ሺዎችን ወገኖቻችንን ህይወት ካጠፉና ቤተሰብ ካፈረሱ በኋላ፣ በህዝብ ግፊት ምክንያት “ማዕከላዊን ዘግተን ወመዘክር እናደርጋለን” ማለት ከገደሉ በኋላ ለማዳን የመሞከር ያህል ይመስለኛል።
ሌላው ትንሽ ቅንነት የጎደለው ውሳኔ ነው ለማለት የደፈርኩበት ምክንያት “ማዕከላዊን አፍርሰን ሌላ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ እሥር ቤት እንገነባለን” የሚለውን ከሰማሁ ባኋላ ነው። በመጀመርያ ደረጃ የማዕከላዊ መጥፎነት እንዴት ሃያ ስድስት ዓመት ሙሉ ተደብቆባቸው ዛሬ ታያቸው? ለምን ዛሬ ታያቸው ማለቴ አይደለም፥ የሰው ልጅ የንቃት ደረጃ ሁሉም አንድ ዓይነት አይደለምና! ማን ያውቃል፣ ምናልባት ከዚህ ሁሉ ዓመት ባኋላ ዛሬ ከመካከላቸው አንድ የኢህአዴግ አባል ማዕከሉን ጎብኝቶ ኖሮ ስለታዘባቸው ነገሮች ዘገባ አቅርቦ ይሆናል እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት። በጀ! እሱስ ይሁን፣ ግን ዘመናዊ እሥር ቤት ሲሉ የትኛውን መስፈርት ሊጠቀሙ ነው? ምናልባት የኤውሮፓ ህብረት ላገሪቷ ባጀት ከሚደጉመው 33% ለዘመናዊ እሥር ቤት መስርያ አውሉ ብሎአቸው ከሆነ፣ የሚሰራው ዘመናዊው እሥር ቤት መስፈርት የኤውሮፓው ይሆናልና፣ ቤት መጻህፍት፣ መዋኛ ቦታ፣ የተሟላ የየግል መኝታ ቤት፣ በየኮሪደሩ ቴሌቪዥን፣ የሚመገቡት ምግብና የከፌቴርያው ንጽህና በየቀኑ የሚገመገም ወዘተ ስለሚሆን፣ ዘመናዊ እሥር ቤት የመሥራት ሃሳቡ የሚደገፍ ነው። ትልቁ ፍራቻዬ ግን፣ በተለይ የማዕከላዊው አሰቃዮች ወደ ዘመናዊው እሥር ቤት አብረው የማይዛወሩ ከሆነ፣ ዘመናዊው እሥር ቤት፣ ዜጎች የሚሰቃዩበት ሳይሆን መዝናኛ ማዕከል መስሎአቸው ንጹሃን ዜጎች “ፈቃደኛ” ታሳሪዎች እንዳይበዙ ነው።
ስለዚህ፣ ውሳኔው በቅንነት የተሞላና የሰውን ልጅ ከሥቃይ ለማዳን ታስቦ ከሆነ ኢህአዴግ የሚከተሉትን ማድረግ አለበት፣
ሀ) ችግሩ ከህንጻው ሳይሆን ውስጡ የወያኔ ልዩ “አሰቃዮች” በወገኖቻችን ላይ የሚያደርሱት አሰቃቂ ድርጊት ስለሆነ፣ በመጀመርያ ደረጃ መንግሥት መውሰድ ያለበት እርምጃ፣ ማንኛውንም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋለን ኢትዮጵያዊን፣ በህገ መንግሥቱ በአንቀጽ 20 እና 21 በተደነገገው መሠረት ከሥቃይ ነጻ የመሆን መብቱ እንዲጠበቅለት ማድረግ፣
ለ)ይህን ህግ ተላልፈው ቁጥጥር ሥር በዋሉት ዜጎች ላይ የማሰቃየት ተግባር በሚፈጽሙት “መርማሪዎች” ላይ ደግሞ የሰው ልጆች መብት የመጣስ ክስ ተመሥርቶባቸው እንዲቀጡ ማድረግ፣
ሐ) ለብዙ የፖሊቲካ እሥረኞች መወንጀል መሰረት የሆነውና፣ በእውነት የአሸባሪዎችን ዕንቅስቃሴ ለመግታት ሳይሆን የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችን ለማሰርና ድርጅቶቹን ለማዳከም የታወጀውን የጸረ ሽብር ዓዋጅ ባስቸኳይ መሰረዝ ለኢህአዴግ ቀናነት አንድ ማስተማመኛ ይሆናል።
ለመደምደም ያህል፣
ኢህአዴግ ባገሪቷ ውስጥ የፖሊቲካ እሥረኞች መኖራቸውን ማመኑ ለህዝባችን ትልቅ ድል ነው። ለፈለገው ዓላማ ይጠቀምበት፣ የዜጎቻችን ከዚያ ምድራዊ ሲዖል መውጣት እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው። ያሁኑ እስረኞቹን የመፍታታ ውሳኔው ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ስለመጣ፣ የየእሥር ቤቶቹ ኃላፊዎች እንደለመዱት እሥረኞቹን ላለመፍታታ የማንገራገር ኃይል ያላቸው አይመስለኝም። ውሳኔው በተግባር ተተርጉሞ እነ አንዱዓለም አራጌና በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋና መራራ ጉዲና እና ሌሎችም በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ነጻ ወጥተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲቀላቀሉ ባይኔ እስከማይ ድረስ ግን፣ እኔም እንደ ትምቧለል “ካልታዘልኩ አላምንም” ብዬ የመቀመጥ መብቴ ይጠበቅልኝ።
*****
ጄኔቫ፣ ጥር 6 ቀን 2018 ዓ/ም wakwoya2016@gmail.com
