[በወንድወሰን ተክሉ-ጋዜጠኛ]

-መንደርደሪያ ጭብጥ-

ሐሙስ እለት በተሰራጨው ሁለተኛ ዙር ዜና መንግስት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን የተሰጠውን የአጠቃላይ ፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ዜና በሚደንቅ ሁኔታ ያስተባበለ ሆኖ ተገኝታል።

እንደ የእለተ ሐሙሱ መንግስታዊ ዜና ስርዓቱ ጉዳያቸው በአቃቤ ህግ ደረጃ ያለና ያልተፈረደባቸውን የፖለቲካ እስረኞችን ክስ እንዲቃረጥ በማድረግ በይቅርታ ለመፍታት መወሰኑን ለማሳመን የሚጥር ዜና ሲሆን ስለ አጠቃላይ የፖለቲካ እስረኞችን ጉዳይ በተመለከተ ግን ያንን የተለመደእን “የፖለቲካ እስረኞች የሉኝምን” የተማዘዘ እጅ እጅ የሚል ዲስኩሩን ሲያሰማ ተስተውላል።

ይህ ማለት በተሰጠው የፖለቲካ እስረኞችን እንፈታለን መግለጫ ፈጥነው አድናቆታቸውን እንዲገልጹ ያደረጋቸውን የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ታዛቢዎችን ግምት አፈርድሜ ከማስበላቱም ባሻገር በኢትዮጵያ ህዝብ ስሜት ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል የክህደት ጨዋታ መጫወቱን እንረዳለን።

ከዚህ ከእለተ ሐሙሱ መንግስታዊ መግለጫ በመነሳት መንግስት እጅግ መሰሪ በሆነ ስሌት በጣት የሚቆጠሩና ታዋቂ የሆኑትን የቅርብ ግዜ እስረኞችን በመልቀቅ የህዝቡን ህዝባዊ ትግል ላይ ውሃ ለመቸለስ መዘጋጀቱን ከግምት በላይ መግለጽ የሚቻል ሲሆን ዓላማውን ለማሳካት ግን ላይታለል ዓምርሮ የተነሳውን የኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነት ማግኘት ስለመቻሉ ከተለመደው የብልጠት ስሌቱ ውስጥ በማስገባት ይሁንታን የጠበቀ ቢሆንም መልሱ ግን በየእለቱ በገሀድ እየታየ ያለው የተገላቢጦሽ እንደሆነ የህዝቡ እለታዊ ተግባር ይመስከራል።

**ህወሃትና የፖለቲካ እስረኞች በኢትዮጵያ-

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አካል ሊ/ር እና የሀገሪቷ ጠ/ሚ ነኝ የሚሉን አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ድርጅታቸው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በእስር ላይ ያሉ የፖለቲካ እስረኞችን በይቅርታ ለመፍታት ወስኗል ሲሉ ገልጸዋል።

በማያያዝም የብዙዎች መሰቃያ ማእከል የሆነውን የማእከላዊ ተቋምን በመዝጋት ወደ ሙዚየምነት እንቀይረዋለን ሲሉ የተደመጡ ሲሆን ብዙዎችም “ጅምሩ መልካም ነው”ሲሉ ከእነጥራጣሬና ግራ መጋባታቸው ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውሏል።

በእኔ በኩል በውሳኔው ውስጥ ጊዜያዊም እንኳን ቢሆን የሚያስደስት ጉዳይ የሆነ አንዳችም ነገር አላየሁበትምና ለመደሰቱ መቸኮል አልቻልኩም።

በእስረኞች ይፈታሉ ዜና እወጃ ልደሰት ያልቻልኩበት ዋና ምክንያት እንደ የህወሃታዊያኑ መንደር አባላት “በለምን ይፈታሉ -ጠላቶቻችን አይደሉምን”በሚል ስሜት ወይም “እስረኞችን መፍታት የህወሃት ተሸናፊነትን የሚገልጽ ሆኖ ሳለ ለምን ይፈታሉ”በሚል ለህወት ተቆርቋሪነት
በመነጨ ሳይሆን በህወሃት ስነባህሪይ አንጻር ለቃላት መግለጫዎች ስፍራ ባለመስጠትና ብሎም በዚሁ የ”ተስፋ” ቃል መሳይ መግለጫ ውስጥ አስደሳች ይዘት ስላጣሁበት ብቻ ነው የደስታ ስሜት ላፈልቅ ያልቻልኩት።

በተጻራሪ መልኩ ከመግለጫው ውስጥ ያየሁት ፍሬ ነገር የሰፊው ህዝብ ትግልና ግብግብ የቱን ያህል ለድል እየተቃረበ የመምጣቱን እውነታ ያየሁበት ከመሆኑ አንጻር ግን የተሰማኝን የብርታት፣የተስፋና የእርካታ ስሜት ልደብቅ አይቻለኝም። የተስፋዬም ሆነ የእርካታዬ ምንጭ መግለጫውን ካወጣው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ተግባርና ዓላማ ላይ ሳይሆን መግለጫውን አስወጪ በሆነው አስጨናቂው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለንተናዊ ትግል፣ብርታትና ጥናካሬ ላይ ነው።

አስጨናቂው [ህወሃት መራሹ ገዢ] በተራው በተጨናቂው [ተጨቋኙ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ]ተነቅንቆ ሲጨነቅ ቀስፎና ወጥሮ ካስጨነቀው አስጨናቂው ህዝባዊው ትግል ለማምለጥ እርር ድብን፣ቅጥል ንድድ እያለ በአፍ ደረጃም ቢሆን አስጨናቂውና ጨቋኙ ህወሃት መራሹ ስርዓት “አንዳንድ የፖለቲካ እስረኞችን በይቅርታ እንፈታለን” ለማለት መገደዱ በመጀመሪያ ደረጃ የድርጅቱ በጎፈቃድ ተግባር ባለመሆኑ የምደሰትበት አንዳች ነገር የለም።

እኔ በዜና እወጃው ደስተኞች ከሆኑት ውስጥ እራሴን ማግኘት የምችለው “የፖለቲካ እስረኞችን የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በፖለቲካ ክስ የተፈረደባቸውም ሆነ ገና በክርክር ላይ ያሉ እስረኞችን በሙሉ በምህረት ለቀናል” የሚል ቢሆን ኖሮ ከተደሳቾች ውስጥ ልደመር እንደምችል ይሰማኛል።

ይህንን የኢህአዴግን መግለጫ ተከትሎ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ስብሳቢውና የካሊፎርኒያው ኮንግረስማን ኤድ ሮይስ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካን አጋር ለመሆን ከፈለገች መንግስት አሁን የገለጸውን አቋም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ መፍታት ይገባታል”ካሉ በሃላ ሲያክሉም “መንግስት የሰብዓዊ መብትን ማክበር አለበት” በማለት ያወጡትን መግለጫ በጣም እጋራለሁ።

ለመሆኑ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ በምህረት እንዲፈቱ ተወስናል በሚል ዜና እስረኞቹ ሲፈቱ ከመስማት ይልቅ “ህጉ በሚፈቅደው መሰረት እየተጣራ በይቅርታ እንዲፈቱ ወስነናል” የሚል ዜና ለምን ሊነገረን ተፈለገ? እንዴትስ ነው በዚህ ድፍንፍን ባለመግለጫ ብቻ ለመደሰት የሚቻለው?

ህወሃት ለ26ዓመታት ካስተማረን ትምህርት በመነሳት እኔን የሚያሳምነኝ ከአንድ ሺህ የቃላት ጋጋታና የፕሮፖጋንዳ ጩህት ይልቅ አንዲት አነስተኛ የድርጊት ተግባር በመሆኑ የቃል መግለጫውን ከዚህ በፊት ከሰማናቸውና አንዳቸውም ካልተተገበሩት ወርቃማ ቃሎቶች ውስጥ እንደ አንዱ የወቅቱ ማታለያ አሊያም ተቆራርጦና ተበልቶ ቅንጥብጣቢው የሚተገበር ይሆናል ብዬ እንዳየው አድርጎኛል።

ጎበዝ-ተደጋግሞ መታለል እጅግ ያናድዳል። የሚያናድደውም ደጋግሞ በሚሸነግለንና በሚያታልለን ሰውም ሆነ ድርጅታዊ አካል ተደጋጋሚ ማታለያዎቹ ላይ ሳይሆን እንዴት ሁልግዜ እያመንኩ ግን እያወኩት ልታለልለት[ልሸወድለት] ቻልኩ በማለት በራስ ላይ የሚደረግ ግሳጼ ተክትሎ የሚነሳ በራስ ላይ መነዳድ ነው የምናየው።

እናም ቢያንስ ከራሴ በሚመነጭ የዋሃዊ እምነትና ስህተት መልሼ እራሴን እንድከስ፣እንድወቅስና ብሎም በራሴ-ከራሴ እንዳልናደድ የሚያግዘኝን ተግባር በቃላት ጋጋታና በፕሮፖጋንዳ ጩህት ልቤን ከፍቼና በተፈጻሚነቱ አምኜ የምቀበል ባለመሆን የተግባራዊ ድርጊትን ብቻ ተቀባይ ሆኛለሁ።

ለመሆኑ የሚፈቱት “አንዳንድ” የተባሉት የፖለቲካ እስረኞች እነማን ናቸው? “በይቅርታ ይፈታሉ” ሲል ይቅርታ አድራጊውና ጠያቂው ማነው? እስረኞቹ ናቸው ይቅርታ እየለመኑ የሚፈቱት ወይስ በግፍ ያሰራቸው ገዢው ሃይል ነው “በግፍና ያለአግባብ ስላሰርካችሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ” እያለ የሚፈታው? አረ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ አለን? የፖለቲካ እስረኞች አሉን ከተባለ ስንት ናቸው? አምስት? ሃምሳ? አንድ ሺህ? አስርና ከአስር ሺህ በላይ ናቸው?

እነዚህ የፖለቲካ እስረኞች የሚባሉት መስፈርቱ ምንድነው?

ብዙም እሩቅ ሳንጋዝና የማቹን ጠቅላይ ምኒስትር “ዝነኛ” ክህደቶችን መጥቀስ ሳያስፈልገን አቶ ሺፈራው ሺጉጤ የህወሃት መራሹ ገዢ ሃይል አፈቀላጤ “በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ ምክንያት የታሰረ አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለንም። ያሉት እስረኞች ሁሉ ህግ በመተላለፍ ተከሰውና ተፈርዶባቸው ያሉ የህግ እስረኞች ናቸው” ያሉን መቼና የትነው?ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ “አንዳንድ የፖለቲካ እስረኞችን በይቅርታ ለመፍታት ኢህአዴግ ወስናል” የሚለውን መግለጫ አይደለም በደስታ በጥርጣሬ አግራሞት እንድንቀበል ያስገድደናል።

ባለፈው 2016ዓመት[2009]ላይ ህዝባዊውና ሀገር አቀፉ ትግል ተቀጣጥሎ የስርዓቱን ተቃማዊ ስር እየፈነቃቀለና እየመነቃቀረ ለመፈንቀል በተቃረበበት ወቅት ኢህአዴግ ሶስት መሰረታዊ የሆኑ ለውጥ አምጪ እርምጃዎችን በመውሰድ ከተነሳበት ህዝባዊ ማእበል ግዜያዊ እፎይታ እንዳገኘ እናስታውሳለን።

በወቅቱ በአስጨናቂ ማእበል ቀዘፋ ላይ የነበረው ህወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት የወሰዳቸው ነፍስ አድን ውሳኔዎች ውስጥ ሶስቱ-

1ኛ-የስድስት ወር አስቸካይ ግዜ አዋጅ[6ቱ ወር ከተጠናቀቀ በሃላ ሌላ 4ወር ተጨምሮለት በ10ወር የተጠናቀቀው]

2ኛ-መንግስት ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር እስከ ሕግ-መንግስት ማሻሻል ድረስ መደራደርና

3ኛው-ደግሞ በኢህአዴግ ውስጥ ጥልቅ ግምገማና ተሀድሶ በማድረግ በሙስና ላይ የማያወላዳ ዘመቻ መክፈት – የሚሉት ዋንኛ እርምጃዎች አድርጌ ውስጃቸዋለሁ።

በአስቸካይ ግዜ አወጁ ስልጣን በመጠቀም በጄ/ሳሞራ የኑስ የሚመራው መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቷን አገዛዝ ስልጣን ተቆጣጥሮ በጠምንጃና በብርት ሲቆጣጠር የታሰበው ከተቃዋሚዎች ጋር የመደራደር ድራማና ትርኢት በአፍሪካ አዳራሽ መጀመሩ ይታወሳል።

ለድርድሩ የተጋበዙት ተቃዋሚዎችና ለመደራደሪያነት የተመረጣው አጀንዳ የኢህአዴግን “ከተቃዋሚ ጋር እደራደራለሁ” አቋም ከፖለቲካዊ ፍጆታነት ያላለፈ ቧልት መሆኑን የሚገልጹ ተግባሮች ሲሆኑ ከሁሉ በላይ ግን በዚያው ቧልት በሆነው ድርድር ላይ የአቶ ሺፈራው ሽጉጤ “በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም በፖለቲካ ምክንያት የታሰረ የፖለቲካ እስረኛ የለንም። ኢህአዴግ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ አይፈቱ በማለት የሚያደርገው ድርድር የለም” በማለት አስረግጠው መናገራቸውና ብሎም ድርድር በተባለው የቧልት ድራማ ላይ እንዳይነሳ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ድርጅቱ ይህንን አቋሙን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ሀገሪቷን ለጎበኙት የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር በማያሻማ ሁኔታ አስርግጦ ገልጻል።

ታዲያ ዛሬ የፖለቲካ እስረኞች ያለው የትኞቹንና ከየትያመጣቸውን ይሆን ብለን ስንጠይቅ እኛም የስርዓቱን ክህደትና ፕሮፖጋንዳ አምነን የፖለቲካ እስረኞች የሉንም ከሚል እሳቤ ሳይሆን በስርዓቱ መስፈርት የፖለቲካ እስረኞች ተብለው ሊፈቱ የሚችሉትን የህሊና እስረኞችን ብዛትና አይነት ለማወቅ ከመሻት አንጻር እንደሆነ ሊጤን ይገባል።

መግለጫውን የሰማ አንድ ወዳጄ በአንድ ሌላ ፎረም ላይ “የፖለቲካ እስረኛ ኢትዮጵያ ዉስጥ የለም ብሎ አልነበርም ወይ ወያኔ። ታዲያ በኢንኩቤተር ነው በአንድ ምሽት የፈለፈላቸዉና የፖለቲካ እሰረኞችን የሚለን።የሚገርም ነው” በማለት አግራሞቱን አስፍራል።

***ከፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ዓላማ ጀርባ ያደፈጠውን የህወሃትን ሴራ ማወቅም ያስፈልጋል-

በመጀመሪያ ደረጃ ላለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ፣በአማራ፣በአዲስ አበባ ሕዝባዊ የሆነውን ፍትሃዊ ጥያቄ አንግበው ከፍተኛውን መስዋእትነትን በየእለቱ እየከፈሉ አስጨናቂውንና ጨቋኙን የህወሃት ስርዓት ያለማሳለስ ሌት ተቀን እየተጋለ ላለው ሰፊው ህዝብና ትግሉ ያለኝን አድናቆትና አክብሮት መግለጽ እንዳለብኝ ይሰማኛል።

ለዓመታት ያህል በግትር አቋሙ አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለኝም እያለ ሲመጻደቅብን የነበረውን ህወሃት መራሹ ስርዓት ዛሬ እያነቀው በመጣው ህዝባዊው ትግልና ዓመጽ ማንቁርቱን ተይዞ ሳይወድ በግድ የካደውን እውነታ መቀበለኑ እና ብሎም ቆንጥሮም ይሁን ዘግኖ ሊፈታ መገደዱን እየገለጸልን ይገኛል።

ይህ የኢህአዴግ እርምጃና ውሳኔ እንዲሁ በቀላሉና በድርጅቱ በጎፈቃድና ይሁንታ የተገኘ ነጻ ችሮታ ሳይሆን በሺህ የሚቆጠሩ ውድ ዜጎች መተኪያ የሌላትን ድንቅ ህይወታቸውን መስዋእት ያደረጉበት፣በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ድንቅ የሀገር ልጆች ነጻነታቸውን ተገፈው የታሰሩበት፣ የተሰደዱበት፣ቤት ንብረታቸው ፈርሶ የተፈናቀሉበት ትግል ውጤት በመሆኑ የሰፊው ህዝብ እምቢተኝነትና ቆራጥ ትግል ሊመሰገንም ሆነ ሊዘከርበት የሚገባ እንደሆነ ማንኛችንም ብንሆን ልናጤነው ይገባል።

ሆኖም ግን የተጨናቂውን ህወሃት መራሹን መንግስት የአፍ መግለጫ ሳያዘናጋን በመላ ሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ እስር ቤቶች፣የጦር ካምፕና ጣቢያዎች ውስጥ እየማቀቁ ያሉትን በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የህሊና እስረኞች በአጠቃላይ ይፈቱ ዘንድና የፖለቲካ እስረኞቹ የታሰሩበት ዋና ዓላማና ጥያቄም መሳ ለመሳ የሚመለስበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሰፊው ህዝብ እያካሄደ ባለው ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ ትግል ከመቼውም ግዜ ይበልጥ በዚህ አሁን ባገኘው ድል ተበራትቶ መታገልና ህወሃትን ማስጨነቁን ማጧጧፍ ያለበት ወቅት መሆኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ።

እንደከዚህ ቀደምቶቹ የሽንግላ መግለጫዎቹ ህወሃት ዛሬ ተገዶና ታንቆ ያመነውን የፖለቲካ እስረኞችን መኖር እምነቱን በፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያነትና ህዝቡን መሸንገሊያነት ለማዋል ለይስሙላ ያህል እጅግ ጥቂት የሆኑ እስረኞችን የመልቀቅና ብሎም በማእከላዊ የሚፈጽማቸውን አሰቃቂ ማሰቃያ ምርመራዎችን በሌላ አዲስ ስፍራና ተቃም ውስጥ ለመቀጠል እንዳለመ ይነገራል።

“ጉዳያቸው እየታየና እየተጣራ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት በፍርድ ላይ ያሉትም ሆነ በክስ ላይ ያሉት የፖለቲካ እስረኞች በይቅርታ እንዲፈቱ ይደረጋል” የሚለው ጥሬ ቃል ሲተርጎም የሚፈቱና የማይፈቱ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ የሚገልጽ ከመሆኑም ባሻገር ለመፈታት የታጩት እስረኞችም ቢሆኑ በ2008[1999]በቅንጅት አመራሮች ላይ የፈጸመውን ደባ በይቅርታ ስም እያስፈረመ ለመልቀቅ መዝጋጀቱን መረዳት ይቻላል።

የሰፊው ህዝብ ህዝባዊ ዓመጽና ትግል አሁን ከመቼውም ግዜ በላይ ተጠናክሮና ሃይሎ መካሄድ ያስፈለገበት ዋና ምክንያትም መሪዎቹ የሆኑት የፖለቲካ እስረኞች እንደነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣አቶ በቀለ ገርባ፣ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ፣አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣አቶ አንዱዓለም አራጌ…ወዘተ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና መሰል ጸሃፊያንን የሰብዓዊ መብት ተማጋች አክቲቪስቶችን –

1ኛ- ባጠፋሁት ጥፋት ተጸጽቼ መንግስትን ይቅርታን ይቅርታ ስጠይቅ ዳግሞ በፖለቲካ ውስጥ ላልሳተፍ ቃል እየገባሁ ነው የሚል ቅጽ ፎርም እንዳይቀርብላቸው ለመከላከል።

2ኛ- “ጉዳያቸው እየተጣራ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት”በማለት የሚፈቱና የማይፈቱ እስረኞች እንዳይኖሩ ተከላክሎ በአጠቃላይ በመፈንቅለ መንግስት ክስ፣በአሸባሪነት ክስና በተራ ወንጀል ክስ ተከሰው የተፈረደባቸውም ሆኑ ገና ያልተፈረደባቸው በመላ ኢትዮጵያ እስር ቤቶች እየመቃቁ ያሉ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች፣የፖለቲካ መሪዎች፣ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች፣አርሶ አደሩ እና የመከላከያ አባላትና የንግዱ ማህበረሰብ አባላትና የሃይማኖት አባቶች ሁሉ ይፈቱ ዘንድ እጅግ ወሳኝ የሆነ ህዝባዊ ትግል ማስፈለጉ አጠያያቂ አይደለም።

ህወሃት መራሹ ስርዓት ለህዝብ ይፋ ባደረገው የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ውሳኔ ከፖለቲካዊ ጠቀሜታ አንጻር ውስን እና የተመረጡ [Selected ]በጣት የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ከተፈቱ በሃላ ሊያንቀሳቅስ በማይችል ፊርማ በመልቀቅ የትግሉን ጎራ ከፋፍሎ የማዳከም እቅድ እንደያዘ ለስርዓቱ ቅርበት ካላቸው ምንጮች መረዳት ተችላል።

እንደምንጮቹ መረጃ መሰረት በስርዓቱ የተዘጋጀውን የይቅርታ ፎርም ፈርመው እንዲወጡ የታጩት የፖለቲካ እስረኞች ከአማራና ኦሮሞ ክልል ተመጣጣኝ እንዳይሆን በማድረግና በተለይም ከአንደኛው ክልል [ኦሮሚያ] በህዝብ ዘንድ ታዋቂ የሆኑትን ውስን በመፍታት በህዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን ህብረት ለመከፈል የታለመ እንደሆነ ይገልጻል።

ይህ ማለት የታሰሩ ወገኖቹ የተፈቱለትና ያልተፈቱለት ክልል በመፍጠር የጋሪዮሽ ትግሉን እና ትብብሩን እናቀዘቅዘዋለን በሚል ስሌት የተነገረ እንደሆነ መገመት የተቻለ ሲሆን ለተግባራዊነቱ ወሳኙ ግን አሁንም ህወሃትን አስገድዶ የለኝም ሲላቸው የነበሩትን የፖለቲካ እስረኞች መኖርን ያናገረው የህዝቡ ትግል ብቻ እንደሆነ ከግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል።

ህወሃት መራሹ ስርዓት የፖለቲካ እስረኞችን ቆንጥሮም ይሁን ዘግኖ በይቅርታ አስፈርሞም ይሁን በምህረት አላክኮ ለግል ፖለቲካዊ ጥቅሙ ስሌት ለመፍታት ቢንቀሳቀስ የሰፊው ህዝብ ትግል ይህን ያህል አስጨንቆና አስገድዶ የካደውን እስካሳመነ ዘንዳ ዛሬም እስረኞቹን በማስፈታት ሂደት ውስጥ እንደ ስርዓቱ ፍላጎትና ሴራ ሳይሆን ያለምንም አስገዳጅ ፊርማና መለያየት በአጠቃላይ የታሰረ የፖለቲካ እስረኛ ሁሉ በአንድነትና በነጻ እንዲፈቱ ሰፊው ህዝብ ማድረግ ይቻለዋል ብዬ አምናለሁ።

ለ26ዓመታት በተደጋጋሚ ግዜ በህወሃት መራሹ ሃይል የተታለለውና የተደለለው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ዳግም በዚህ ሰዓት ይታለላል ብሎ ማሰቡ እጅግ አዳጋች እንደሆነ የማምን ሲሆን ይህ ህዝብ ይህን ያህል መስዋእትነት የከፈለበትን ትግሉ በህወሃት ቅንጥብጣቢ በመርካት ይታለላል ማለት አይቸለኝም።

ሕዝባችን የቅንጥብጣቢ ርሃብተኛም እንዳልሆነ ማንም ይረዳል-ከህወሃት በስተቀር። እናም ይህን የቅንጥብጣቢ ሴራን ያነገበውን የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ሂደት በንቃት፣በብልሃትና በተጠናከረ ህዝባዊ ዓመጽና ትግል ሰፊው ህዝብ የሚፈልገውን ልጆች ሁሉ ከእስር የሚያስፈታበት ሂደት ማድረግ ይቻለዋል ስል ጽሁፌን እደመድማለሁ። ቸር እንስንብት!!