January 7, 2018 13:00

ኢሕአዴግ ስልጣን በጨበጠ ጊዜ የአገሪቷን አስተዳደራዊ መዋቅር ቀይሮታል። በአገራችን ፌዴራሊዝም ነው አለ የሚባለው።

ፌዴራሊዝሙ በዋናነት ዘዉግንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነው። የሶማሌ ክልል ባለቤት የሶማሌ ብሄረሰብ ነው። የኦሮሚያ ባለቤት የኦሮሞ ብሄረሰብ ነው። የትግራይ ክልል ባለቤት የትግራይ ብሄረሰብ ነው። ይህ አንድ አካባቢ ለአንድ ብሄረሰብ ብቻ ለይቶ መሸንሸን፣ ክልሉ ከተሸነሸነለት ብሄረሰብ ዉጭ ያሉ ሌሎች ኢትዮያዉያንን ፣ በአገራቸው በክልሉ እንደ መጤ እንዲቆጠሩ ያደረገ ከመሆኑም ባሻገር በአገራችን ለተፈጠሩና ለብዙ ወገኖቻችን ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ የዘር ግጭቶች ምክንያት ሆኗል።
በመሆኑም አንድን ክልል ለአንድ ብሄረሰብ ብቻ የመስጠት አሰራር መቀየር ይኖርበታል። ኢትዮጵያዉያን ዘራቸውን ሃይማኖታቸው የፈለገ ይሁን ፣ በሁሉም የአገሪቷ ግዛቶች በነጻነት የመኖር፣ የመስራት፣ የመነገድ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው መረጋገጥ አለበት። በሁሉም ቦታ ሲሄዱ ባእድ አገር የሄዱ ይመስል መፍራት የለባቸው። በዚሁ ዙሪያ አሁን ያለው ጎጂ አሰራር እንዲቀየር ይረዱ ዘንድ መሰረታዊ ነጥቦችን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡
1) የክልሎች ባለቤት የአንድ ወይንም የሁለት ብሄረሰብ አባላት ብቻ ሳይሆን በክልሉ የሚኖረው ሕዝብ በሙሉ መሆን አለበት። በአንድ ክልል ከየትም ብሄረሰብ ይምጡ ዜጎች እኩል መሆን አለባቸው።
2) በክልሉ አብዛኛው ህዝብ እንደ አንደኛ ቋንቋ የሚናገረው ቋንቋ የሥራ ቋንቋ መሆኑ አስፈላጊ እንደመሆኑ፣ በክልሉ ያሉ ሌሎች መብታቸው እንዲከበርና በቂ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ አማርኛ በሁሉም ክልሎች የሥራ ቋንቋ ይሆናል።
3) ክልሎች ሰፊ መሆን የለባቸው። ስፋት ካለ ለአስተዳደር አመች አይሆንም። ሕዝብን ማጉላላት ነው። በመሆኑም የአማራው ክልል ፣ ኦሮሚያና የደቡብ ክልል አነስ ወዳሉ ክልሎች ተሸንሽነዋል።
4) አዲስ አበባ ሸዋ ውስጥ ተጠቃላለች። አዲስ አበባዉያን ከሸገር ዙሪያ ነዋሪዎች ጋር ተሳስረው ይቀጥላሉ። የሸዋ የስራ ቋንቋ አማርኛና አሮምኛ ይሆናል። ያ ማለት በአዲስ አበባም አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ ይሆናል።
5) ድረዳዋ፣ ሃረርና ፣ በድረዳዋና በሃረር መካከል ያሉ አካባቢዎችና ሽንሌ የሃረርጌ ክልል ውስጥ ተጠቃሏል። በሃረርጌ ሶምሌኛ፣ ኦሮሞኛ፣ አደሪኛና አማርኛ የሥራ ቋንቋዎች ይሆናሉ።
6) ወልቃይት ጠገዴ ወደ በጌምድር፣ አላማጣ ወደ ወሎ ሲጠቃለል፣ የቤኔሻንጉል ክልል ወደ ጎጃም ተጠቃሏል።
7) የጋምቤላና የአፋር ክልሎች እንዳሉ ሲቀጥሉ፣ የሶማሌ ክልል፣ ሽንሌን ሳያካትት የኦጋዴን ክልል ይባላል።