Thursday, January 18, 2018
- የሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን በእዚህ ደረጃ ለማስከበር መነሳት በሌሎች አጥብያዎች ያለውን ተመሳሳይ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ዘረፋ እና ብክነት ጉዳይ ይቀሰቅሳል የሚል ሽብር በአባካኞቹ መንደር ሁሉ ፈጥሯል።
- ካለ አንዳች ጥፋት ታቦት አጅበው ይዘምሩ የነበሩ መዘምራን በፖሊስ ታፍሰው ነበር።
- ውጥረቱ ተባብሷል።ምእመን አብዛኞቹ የታሰሩትን አስፈትቷል።
በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የዛሬ አስራ አምስት ቀን ምእመኑ በሙስና እና በቤተ ክርስቲያን ንብረት ዘረፋ የከሰሳቸውን የቤተ ክርስቲያኑን አለቃ የሂሳብ ሹም እና የሰበካ ጉባኤ ታህሳስ 10/2010 ዓም በድንገት በቤተ ክርስቲያን በመድረስ የሂሳብ ሹሙ እና የሰበካ አባላት እንዳይወጡ ካደረገ በኃላ ለፓትርያሪኩ ፅህፈት ቤት፣ለአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት እና ለቅዱስ ሲኖዶስ ባለ 26 ነጥብ የያዘ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።በወቅቱ የቀረበው ጥያቄ ዋና ጭብጥ ሐራ ዘተዋህዶበድረ ገፁ እንደዘገበው የሚከተሉትን ነጥቦች የያዘ ነበር። እነርሱም : –
- ዋና አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣ ዋና ጸሐፊው ዕፁብ የማነ ብርሃን፣ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር ካሳሁን ገብረ ሕይወት እና ሒሳብ ሹሙ ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ፤
- በሕገ ወጥ መንገድ ያለምእመን ተሳትፎ በዝግ አዳራሽ የተመረጠውና በቀሲስ ካሳሁን ገብረ ሕይወት የሚመራው ሰበካ ጉባኤ ፈርሶ በቃለ ዐዋዲው መሠረት ምእመኑንና የካቴድራሉን አገልጋዮች የሚወክል ሰበካ ጉባኤ እንዲመረጥ፤
- በቀጣይም በካቴድራሉ አስተዳደር ላይ የቀረቡትን አቤቱታዎች አጣርቶ ለሕግ የሚያቀርብ ኮሚቴ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከሀገረ ስብከት፣ ከወረዳ ቤተ ክህነትና ከአጥቢያው ምእመናን እንዲዋቀር፤
- የውጭ ኦዲተር ተመድቦ የካቴድራሉ ገቢና ወጪ ኦዲት እንዲደረግ የሚሉ ነበሩ፡፡
በእዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ ኀሙስ፣ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ችግሩ በግልጽ ተጣርቶ የመጨረሻ እልባት እስኪሰጠው ድረስ፡-የሚከተሉት አገልጋዮች እንዲታገዱ ወሰነ።
- አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣
- ዋና ጸሐፊው ሊቀ አእላፍ ዕፁብ የማነ ብርሃን፣
- ሒሳብ ሹሙ ሊቀ ትጉሃን ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃ፣
- ተቆጣጣሪው ቀሲስ ሳሙኤል ደሳለኝ፣
ሆኖም እግዱ ከተፈፀመ በኃላ ቀን ከሌሊት ምዕመናን ቢሮው ውስጥ ያለው ሰነድ እንዳይሰረቅ እየጠበቁ ከአንድ ሳምንት በላይ ቀን ፀሐይ ሌሊት ብርድ እየተፈራረቀባቸው ዘልቀዋል።ቢሮው በክፍለ ከተማ፣በፖሊስ፣ከምዕመናን የተውጣጣ ኮሚቴ እና በሀገረ ስብከት እማኝነት ብቻ እንዲከፈት አፅንኦ ምዕመኑ ሰጥቶ ቀንና ሌሊት እየተፈራረቀ መጠበቅ ጀመረ።ሆኖም በተደጋጋሚ ጉዳዩን ለመሸፋፈን የሞከሩ የሀገረ ስብከት ሰዎች ለብቻቸው በመምጣት ለመክፈት እንደሞከሩ እና ምዕመኑ በተቃውሞ እንዳገዳቸው ተሰምቷል። ከአስተዳዳሪው ጋር የጠበቀ የጥቅም ግንኙነት እንዳላቸው የተወሳው ፓትርያርኩ ለአቤቱታ የሄዱ ምዕመናንን በአግባቡ ከማስተናገድ ይልቅ አግባብነት የሌለው ንግግር ብዙዎችን አሳዝኗል።
ምእመኑ በድንገት የአለቃውንም ሆነ የስራ ባልደረቦቻቸውን ቢሮ ማሸጉ በፖሊስ ኃይል ለአባካኝ ክፍሉ አለቃውን ጨምሮ ሽፋን ለመስጠት እየሞከረ ያለው የመንግስት ኃይልም ሆነ በጥቅም ትስስር የሚታሙት የቤተ ክህነት ሰዎች ትልቅ ዱብ ዕዳ ሆኖባቸዋል።በተለይ የተቃውሞው እለት ምእመኑን ሽጉጥ ቤተ ክርስቲያን ቅፅር ግቢ አውጥቶ ሊያስፈራራ የሞከረው የሂሳብ ሹም ”ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች ” የሚለውን ተረት ተደጋግሞ በብዙ ምእመናን በዕለቱ ከመሰማቱም በላይ ምዕመኑ በከፍተኛ ቁጣ ከአሁን በኃላ ማንንም ኃይል አንፈራም በሚል እንደቆረጠ ተስተውሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ የጥምቀት ከተራ በዓል ምሽት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ፖሊስ መዘምራንን ማፈስ ጀምሮ ነበር።በመቀጠል ህዝቡ ሲቃወም ፖሊስ በተኩስ አካባቢውን አውኮ አምሽቷል።ሁኔታውን መምህር ዘመድኩን በቀለ እንደሚከተለው የነበረውን ሁኔታ ገልጦታል።
ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com