ለ14 ወራት በእስር ከቆዩ በኋላ ሐሙስ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል ደረጃ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ ከእስር ከተፈቱ 115 ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በኢትዮጵያ አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍ መጀመር አለበት አሉ፡፡
ዶ/ር መረራ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ሪፖርተር አነጋግሯቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ጃንሆይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመርና ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቆ ሲወጣ ለሚመሩት ሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ‹አዲስ ዘመን ጀምረናል ብለው ነበር፡፡ አሁንም የኢሕአዴግ አራቱ ድርጀቶች ሊቃነ መናብርት በነካ እጃቸው ሌሎቹንም እስረኞች ፈትተው አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍ መጀመር አለባቸው፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ነች፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ‹‹አራቱ ሊቃነ መናብርት የጀመሩትን ‹ለውጥ እናምጣ› ጥሪ ቀጥለውበት ሁላችንም አዲስ ዘመን ብለን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገንባ፤›› ብለዋል፡፡
ከእስር ሲፈቱ የተደረገላቸውን አቀባበል በተመለከተ የተናገሩት ዶ/ር መረራ፣ ‹‹የሕዝቡ አቀባበልና እንቅስቃሴ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሳይሆን፣ ጡረታ መውጫ ጊዜህ ገና ነውና ቀጥል የሚል ነው፡፡ በመሆኑም በፖለቲካው ትግል ተሳትፎዬን እቀጥላለሁ፤›› ብለዋል፡፡
መንግሥት ግማሽ መንገድ መጥቶ ከሕዝቡ ጋር አገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ መነጋገርና መመካከር እንዳለበትም ዶ/ር መረራ አሳስበዋል፡፡ መሪዎች አገራቸውንና ሕዝባቸውን በብቃት፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና በቁርጠኝነት እንዲመሩም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ለእስር የተዳረጉት በ2009 ዓ.ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ በብራሰልስ የአውሮፓ ኅብረት ስብሰባን ተሳትፈው ሲመለሱ እንደነበር፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ በነበረችበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የተቀመጡ አስገዳጅ ድንጋጌዎችን ተላልፈው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የሚሉት ነገር ካለ ተጠይቀው፣ ‹‹ስለእሱ ነገር ምንም መናገርም ሆነ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፤›› ብለዋል፡፡
መንግሥት ክሳቸው እንዲቋረጥ ያደረገላቸው ተጠርጣሪዎች የተፈቱት ለሁለት ቀናት የተሃድሶ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ቢሆንም፣ ዶ/ር መረራ ግን ሥልጠናውን አለመውሰዳቸው ታውቋል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ በደርግ ዘመን በዩኒቨርሲቲ ተማሪነታቸው ጊዜ የመኢሶን አባል በመሆናቸው ምክንያት ለሰባት ዓመታት ታስረው ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን፣ ካይሮ ከሚገኘው አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን፣ ከኔዘርላንድስ ሶሻል ስተዲስ ኢንስቲትዩት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስ አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለረዥም ዓመታት ከማስተማራቸውም በላይ፣ በፖለቲካ ተሳትፎአቸው በስፋት ይታወቃሉ፡፡ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃም በበርካታ ፖለቲካዊ የውይይት መድረኮችም ተሳትፈዋል፡፡
የ61 ዓመቱ ዶ/ር መረራ ከእስር በተለቀቁበት ወቅት በሰጡት አጭር መግለጫ መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እውነተኛ ድርድር ቢያደርግ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ሁሉንም ወገን በእኩልነት የምታሳትፍ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል፡፡ እሳቸው በመፈታታቸው ደስተኛ መሆናቸውንና መንግሥት ሌሎች ታሳሪዎችንም እንዲለቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሪፖርተር