የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ)

ጥር ፯ ቀን ፪ሺ፲ ዓ.ም

መግቢያ:-

የኢትዮጵያ የሽግግር ጊዜ መተዳደሪያ ደንብ! – ከትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ውድቀት በኋላ ወዴት?ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሩቅ ታሪክ ከመጡ ጥቂት የዓለማችን ሀገራት አንዷ ናት። በጥንቱ ዘመን የነበረ ተጓዥ፣ አቅጣጫውን እንደሚያመላክትበት የሰሜን ኮከብ ሁሉ፣ ኢትዮጵያም በዚያ ሩቅ ዘመን የሰው ልጅ በተፈጥሮ ተጽዕኖ ከፍተኛ ቁጥጥር ሥር በነበረበት ዘመን ውስጥ፣ ስታበራ  የኖረች ሀገር ናት። ኢትዮጵያን ከሁሉም ሀገራት ልዩ የሚያደርጋት ደግሞ በአንድ ትልቅ፣ደግሞ በተለያዩ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ቁጥጥር ሥር ወድቆ የእርሱነቱ መገለጫ የሆኑ ዕሴቶቹን በተነጠቀ  አህጉር ዉስጥ ብቻዋን የራሷን ታሪክ ስትሠራ የመጣች፣ ከሷ የተጎራበተና ሥልጣኔውን የሚያቋድሳት ሀገር እምብዛም በሆነበት ሁኔታ ውስጥ፣ የራሷ የሆነ ድንቅና ልዩ ሕዝባዊ ትሥሥርን ስትፈጥር የመጣችና የራሷን ነፃነት ጠብቃ ዛሬ ለደረሰችበት የዕድገት ደረጃ የበቃች ሀገር ናት። ዛሬ በዉስጧ የተገነቡ የመንግሥት ተቋማት፣ ከተማዎች፣ የኢንዱስትሪ፣ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የትምህርት ተቋማትና የመገናኛ አውታሮች በሕዝቧ የጋራ ጥረት የተገኙ በመሆናቸው አንድ ኢትዮጵያዊነት ዜጋ ማንነትን ሊፈጥሩ የቻሉ ናቸው። ከዚህ በተቃራኒው በመላው ዓለም ላይ የተገኙ ሥልጣኔዎች፣ ከሞላ ጎደል የተመሠረቱት የሰው ልጅ ዕድገቶች ባስመዘገቡት ውጤት አንዱ ከሌላው ጎረቤቱ ባጋኘው የቴክኖሎጂ ማጋባት ሆኖ እናገኘዋለን።
ኢትዮጵያ ረጅሙን የታሪክ ጉዞዋን አብዛኛውን ያሳለፈችው፣በማኅበረሰብ ዕድገት ታሪክ ውስጥ የፊዉዳል ሥልተ-ምርት በተሰኘው የመሆኑ ምስጢርም፣  ይህ ራሷን ከወረራ የመከላከልና ድንበሯን አጥራ የመቆየቷ የብቸኝነት ታሪኳና ለነፃነቷ ስትል የከፈለችው ተከታታይና ያላቋረጠ ኅልውና እና ማንነትን የማስጠበቅ ተጋድሎ ውጤት ነው። ለኋላ ቀርነቷ መሠረታዊ ምክንያቱም ይህ ነው። በነዚህ ምክንያቶች የማዕከላዊ መንግሥት አመሠራረት ጥረት ረጅምና ደም አፋሳሽ ሆኖ በመዝለቅ፣ እስከ 20ኛው  ክፍለ-ዘመን ድረስ ሊደርስ እንደቻለ በግልጽ ይታያል።
እርግጥ ነዉ፣ ኢትዮጵያ በዚያ ጥንት ዘመን እጅግ በጣም በሚገርም ሁኔታ የራሷ የሆነ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ለመመሥረት የቻለች እንደነበረች፣ በዐፄ ይኩኖአምላክ ሥረወ-መንግሥት በ13ተኛዉ ክፍለ ዘመን ተጀምሮ፣ የመንግሥት አስተዳደር፣ የሃይማኖት፣ አመራርና የሕዝብ ግንኙነት ምን መልክ እንደነበረው «ክብረ መንግሥትና ፍትሓ-ነገሥት» የተሰኙት ሰነዶች ቋሚ ማስረጃዎች ናቸው። በኋላም በዐፄ ሚናስና ዐፄ ሠርጸድንግል ሥረወ-መንግሥት ጊዜ በወቅቱ እጅግ በጣም ዘመናዊ የሚባል የማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታ ቀመሮች ከዘመን ዘመን ተሻጋሪ ጅምሮች ነበሩ:: ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች፣ “የመጀመሪያዉ የኋለኛ ሆነ” እንዲሉ ኢትዮጵያ ሀገራችን በተለያዩ የዉጭ ተስፋፊዎችና ቅኝ ገዥዎች እንዲሁም የእርስ በእርስ የዉስጥ ፍትጊያዎች የተነሳ፣ በታሰበዉ መልካም ጅምር ተረጋግቶ በብልጽግና መዝለቅ እንዳልተቻለ ሀገራችንና ሕዝባችን የሚገኙበት ሁኔታ በግልጽ ያሳያል::
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ከተያያዘችው ከዚያ መልካም የማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታ መልካም ጅምር ጉዞዋ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ግፊቶች ተገቶ፣ በጦር አበጋዞች የሥልጣን ፉክክር ውስጥ ገብታ በታሪካችን «ዘመነ-ፍዳ» ለተሰኘ የእርስ በርስ ተከታታይ ጦርነት ለ70 ዓመታት ማሳለፏ የሚታወስ ነው። ያን አስከፊ የታሪክ ምዕራፍ ለመለወጥና ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ጥንታዊና ታሪካዊ የግዛት ዳር ድንበሯ ለመመለስ፣ አንድነቷን አጽንቶ በዘመናዊ ሥልጣኔ ለመገሥገሥ፣ በዐፄ ቴዎድሮስ  ተጀምሮ፤ በዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ተገፍቶበት የነበረዉ አገርን መልሶ የመገንባት ጅምር በተመሳሳይ ሁኔታ በዉጭ ጣልቃ ገብነት አደጋ ላይ ወደቀ። ይህ አደጋ ኢትዮጵያ ጭራሹን ከዓለም የሥልጣኔ ፈጣን የዕድገት ጉዞ የኋሊት ጎተታት። በዚህ ወቅት የምዕራብ አዉሮፓ አገሮች የሆኑት ጣሊያንና ጀርመን ከእርስ በርስ ጦርነት ወጥተው ተለያይተው የነበሩትን ግዛቶች አንድ አድርገው ሌሎችን በቅኝ ግዛታቸው ሥር ለማዋል ሠፊ ዝግጅት ያደረጉበት ነበር። ይህ ሂደት ኢትዮጵያ ለጣሊያን ወረራ ሰለባ እንድትሆን ምቹ ሁኔታን ፈጠረ። ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያ ኅልውናዋን የማስጠበቅ ተከታታይ ታሪኳ በዚህም ወቅት በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ቆራጥ አመራር ወራሪውን የጣሊያን ጦር ዓድዋ ላይ ድባቅ የመታ ብቻ ሳይሆን፣ በፊት የነበሩ የዉስጥ የእርስ በእርስ ቁርሾዎችን የሻረና አንድነቷና ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለማዘመን ምቹ ሁኔታን ፈጠረ:: ይህም ኢትዮጵያ በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ለዘመናት ተቋርጦ የነበረዉ የሥልጣኔና ዕድገት ጉዞ በር ከፋች ሆነ::
ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን ልዩ የሚያደርጋቸው ይህንን ማዕከላዊ መንግሥትን ለማዋቀር የደረጉት ተጋድሎ ነው።  ኢትዮጵያ እንደ ሉዐላዊ ሀገር በዓለም ተከብራና ታውቃ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለመመሥረት የበቃችውም  በኒሁ  ንጉሠ ነገሥት የታሪክ ዘመን ነው። ለዚህም አብዛኛው ዛሬ፣ በተለምዶ ግን፣ በተሳሳተ መንገድ  “መንግሥት” ተብሎ  የተሰየመው የአስተዳደር መዋቅር  መገንባት ተጀመረ።
በዚህም የመገናኛ፣ የሕክምና፣ የትምህርት፣ የመከላከያ፣ የስልክ፣ የዉኃ፣ የፖስታ  የቴለግራም፣ የኅትመት ወዘተ– ብዛት ያላቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲደረግ ያደረጉት በሳቸው የአስተዳደር ዘመን ነበር። ባጭሩ እምዬ ምኒልክን የዘመናዊት ኢትዮጵያ አባት ከማለት ያለፈ በሌላ ሊገለጡ ከቶም  አይቻልም።
የኒህን ታላቅ መሪ ፈለግ በመከተል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም በዚያው በተጀመረው ጎዳና የኢትዮጵያን የመንግሥት  መዋቅር በመገንባትና በማስፋት ተግባር ብዙ ሄደዋል። ይሁንና ይህ የማዕከላዊው መንግሥት ግንባታ ከፖለቲካ መለወጥና  መሻሻል ጋር ያልተያያዘ ስለነበር የተሟላ የዕድገት ፍሬን ሊያፈራ አልቻለም። እንዲያዉም የመንግሥት ተቋም ግንባታ እየዘመነና ቢሮክራሲው እየሠፋ ቢሄድም፣ በፖለቲካው ፈላጭ ቆራጭ የንጉሡ ሥልጣን ከመሀል፣ የአካባቢ ባላባቶችና የጦር አበጋዞች ከዳር አገር እስከ መሀል የተንሰራፋበት ስለነበር፣ የሀገሪቱን ታዳጊ ኃይል በፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጎት ገድቦ ያዘው። ይህም ለታህሳስ 1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥትና ከ13 ዓመታት በኋላም ለመጣው  ሥር-ነቀል ለውጥ አራማጅ አብዮት መቀጣጠል ምክንያቱ፣ የነዚህ ሁለት የማይጣጣሙ ኃይሎች ዕድገት ሂደቶች  ውጤት ነበር።
ከላይ ባጭሩ የተቀመጠው የኢኮኖሚ ዕድገትን ተንተርሶ የሚመጣ መዘመንና ማኅበረሰቡን አሳታፊ የሆነ ፖለቲካዊና ማኅበረሰባዊ ጥያቄዎች እስካልተጋቡ (እስካልተጣጣሙ) ጊዜ ድረስ፣ የሕዝባዊ ነውጥ ጥያቄ የመነሳቱ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑ የኅብረተሰብ ዕድገት ያሳየው ዕውነታ ነው። እናም የየካቲት አብዮትን የወለደ ነባራዊ ሁኔታ ኋላ-ቀር የፊውዳል ሥልተ-ምርት ባለቤት የሆነው ዘውዳዊ አገዛዝ ጊዜው ላቀረባቸው ሕዝባዊ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አለመቻልና፣ ከኋላው ምንም የተረከበው የፖለቲካና የትግል ቅርስ አልባ በሆነው ወጣቱ ትውልድ የአመለካከት ልዩነት የፈጠረው ቅራኔ ያስከተለው ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደሆነ እንረዳለን። በመሆኑም ሥልጣንን በባለቤትነት የሚረከበው የፖለቲካ አካል ባልነበረበት ሁኔታ የነበረ፣ የዚያ ትውልድ የተማረውና የማኅበረሰቡ መካከለኛው ክፍል የፖለቲካውም ምሕዋር ለመቆጣጠር ሠፊ ዕድል አገኘ። ይህም  ሀግ ባይ ያልነበረበት፣ ሁሉም እኔ ያልኩት ትክክል ነው በሚል መንፈስ የሚመራው የማኅበረሰብ ክፍል፣ በየፊናው  ባደገረው መራወጥ፣ የሀገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ በወሳኝነት የሚያመላክት ኃይል ጎልቶ እንዳይወጣ ያስከተለው ዝብርቅርቅና ውስብስብ ሁኔታ፣ ዛሬ ለምንገኝበት ሁኔታ እንደዳረገን ይታመናል። ከፊሉ  ሊገነጠል ተነሳ። ሌላው ሊያስገነጥል  ጎሰኝነትንና ዘረኝነትን ከታሪካዊ ባዕድ ጠላቶች ጋር በማበር ንድፈ-ሀሳብ ወራሽ ሆነ። ለባዕዳንም ፍላጎት ተገዥ ሆነ። ሌላውም  ሥልጣን  ለብቻዬ   ብሎ ተነሳ። እናም  ይህ አጠቃላይ ሁኔታ፣ እናት ሀገር በወለደቻቸው ልጆቿ ለቅርጫ ሥጋ የተጣለች ላም ሆነች። ሻዕቢያ፣ ኦነግ፣ ሕወሓት (የትግሬ ወያኔ)፣ ኦጋዴን ፣ የአፋር እና ሌሎች ተመሳሳይ የጎሳ ድርጅቶች ነፃ አውጪ ነን ባዮች የተፈለፈሉት  በዚያን ወቅት ሆነ። በመሀል ሀገርም በኅብረ-ብሔር ስም ተደራጀን ያሉት፣ የሌለ ጠላት ዐማራን እንደ  ጠላት  ፈጥረውላቸው ለግንጠላ ለተነሱት የንድፈ ሀስብ መደላድል ፈጠሩላቸው። ይህ ተማርኩ ባይ ወጣት የማኅበረሰቡ መካከለኛ ኃይል፣ ከኢትዮጵያ የታሪክ ጠላቶች ጋር ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በመፍጠሩ ምክንያት፣ የውስጥ   ቅራኔው ዓለም አቀፍ ስፋት እንዲኖረውና ከዓለም ተፎካካሪ ኃያላን ኃይሎች ጥቅም ጋር እንዲያያዝ ለማድረግ   በመቻሉ፣ የሀገራችን ሉዐላዊነት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአደጋላ ወደቀ። በመሆኑም የሀገሪቱ  ግዛት በኤርትራ መሄድ ለሁለት  ተከፈለ። በመሀል ሀገርም ፀረ-ኢትዮጵያ በሆነና በኢትዮጵያ ኪሳራ ትግራይን ገንብቶ የራሱን  ነፃነት ለማወጅ በመንገድ ላይ ለሚገኘው የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ ፋሺስት ቡድን ሁኔታው ተመቻቸለት።
ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ከዚህ የትግሬ-ወያኔ ፋሽስት ድርጅት ዘረኛ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ሕዝባችን ከዳር እስከ ዳር  የተነሳበት አመቺ የታሪክ  ወቅት ዉስጥ እንገኛለን። ይህ ትግል ከዚህ አውሬ ሳንገላገል ወደኋላ ላንል የተነሳንበት ነውና፣ ለዚህ ዓላማ የቆሙ ኃይሎችን ሙሉ ትብብርን ይጠይቃል። ትብብር ምርጫ ሳይሆን፣ ግዴታ የሆነበት ጊዜ ውስጥ ገብተናል። በዚህ ረገድ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት  ድርጅት (ዐኅኢአድ) ትብብርን አስመልክቶ  ምርጫ  ሳይሆን ግዴታው መሆኑን የተቀበለ ድርጅት መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለሕዝባችን ለማረጋገጥ ይወዳል። ትብብርን   በሚመለከት ድርጅታችን (የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት) ግልጽና አጭር የሆነ አቋሙን ይፋ   አድርጓል።
ይህም በኢትዮጵያ ዘርን የማጽዳትና ዘር ማጥፋትን ከሚቃወምና ለዚህም በይፋ ከሚታገል፣ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ከሚቀበል ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት፣ እንቅስቃሴ፣ የብዙኃን ማኅበራትና ስብስቦች ጋር ተወያይቶ በአንድነት የሚያሠራ የጋራ መመሪያ ነድፎ ለመሥራት ዝግጁ ነዉ።
የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) ከዚህ ከ1960ዎቹ የታሪክ ወቅት ላይ ከተነሳው ከፋፋይ፣ ዘረኛ፣ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ዐማራ ከሆነ ትውልድ የከፋፍለህ አባላው ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኅብረተሰባችን ነፃ የመውጫው ጊዜ ዛሬ ነው ይላል።
እናም  በ1983 ዓ.ም. የዐማራውን ነገድ ለማጥፋት በግልጽ ፕሮግራም ነድፈው ከመጡ የኦነግና የትግሬ-ወያኔ ከመሠረቱት የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ሕዝባችን ሊላቀቅ ከሚችልበት የታሪክ ወቅት ላይ ደርሰናል ብለን እናምናለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ አፋኝና ከፋፋይ አገዛዝ መላቀቅ የሚችለው እንዳለፉት ሁሉ፣ ሕዝቡ ባልተሳተፈበት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ከመሠረቱት የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ሂደት የተለየ፣ ሕዝቡ በቀጥታ የሚሳተፍበት፣ በአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎች ተሳታፊ የሚሆኑበት የሽግግር ሥርዓት በወል ሲመሠርቱ ነው። ትናንት፣ ሻዕቢያ፣ ሕወሓት እና ኦነግ ከተስማሙበት የሽግግር መንግሥት ቻርተር ተብየ፣ በተለምዶ የተሰኔ ማንፌስቶ በመባል ከሚታወቀው፣ የተሰነይ ቡድን አምባገነናዊ፣ ፋሽስታዊና ዘረኛ አመለካከት እንደጫኑብን ሁሉ፣ ዛሬም  በድጋሚ ተሰነይ ሁለት ሊባል የሚችል ተመሳሳይ የቡድንተኝነት ቻርተር ሊጭኑብን ማወጃቸውን እየነገሩን ነው።  ከነዚህ ኋላቀር ኃይሎች ጋር ሕዝባችን ዳግም ወደ ባርነት የሚወስደው ጎዳና ውስጥ እንዳይገባ የማመልከትና በጽኑ መታገል፣ በዚህ ትውልድ ትከሻ ላይ የተጣለ አደራ ነው ብለን እናምናለን። በመሆኑም ዳግም የሕዝብ ውክልና የሌለው ማንም ኃይል በሕዝብ ሥልጣን ላይ የመቀመጥ መብት እንዳይኖረው ለማድረግ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) ያምናል። ለዚህም አምርሮ ለመታገል መነሳቱን ለሕዝባችን ለማሳወቅ ይወዳል። ሥልጣን የሕዝብ፣  የሥልጣኑም ምንጭ ሕዝብ ነው፣ የሚለው መርሕ ለድርጅታችን ገዢ መመሪያ ነው። እናም  ከሽግግሩ  ወቅት ጀምሮ እስከ ሕገ-መንግሥታዊ መስተዳድሩ እውን መሆን ድረስ ያለውን ሂደት መምራት ያለበት እራሱ ሕዝቡ   ይሆናል የሚለው እምነታችን የፀና ነው። ይህ የሽግግር ጊዜ መተዳደሪያ ደንብ ሰነድም የተዘጋጀው በዚህ መርሕ ላይ ተመርኩዞ ነው።
አንቀጽ 1 ትርጉም:-
የሽግግር ጊዜ ማለት የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሣ ከፋፍሎ ቀፍድዶ በመያዝ፣ የዘር ፍጅት እያደረገ ያለዉ የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ተወግዶ፣ በምትኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ዘለቄታዊ ዴሞክራሲያዊ ዕኩልነት መገለጫ የሆነ መንግሥታዊ ሥርዓት ምሥረታ ለመሄድ ቅደመ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚዉለዉ ጊዜ ነው:: የዚህ ጊዜ ቆይታ የሽግግር መንግሥቱ እንዲመሠረት ኅብረት በፈጸሙ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና መሰል ድርጅቶች የወል ስምምነት የሚወሰን ይሆናል።

አንቀጽ 2 የሽግግር ጊዜ የጊዜ ገደብ:-
የሽግግር ጊዜዉ የጊዜ ገደብ ምድር ላይ ባሉት ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚወሰን ሆኖ፤ ከፍተኛዉ የሽግግሩ ጊዜ፣ከሦስት ወይም ከአራት ዓመታት የማይበልጥ፣ ከሁለት ዓመታት ያላነሰ ይሆናል።
አንቀፅ 3 የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት!!
ዛሬ ጥያቄው የትግሬ ወያኔ ይወድቃል ወይ? ሳይሆን፣ መቼ ይወድቃል? የሚለው ትኩረት የያዘ እውነት ነው። በትግሬ-ወያኔ ማለፍና ከፋፋይ የአገዛዝ ሥርዓቱ መወገድ ጉዳይ የምዕላተ-ሕዝቡ ጥያቄ ከመሆን አልፎ፣ በሕዝቡ ተከታታይ የለውጥ ጥያቄ አገዛዙ እንደጥንቱ አስገድዶ ለመግዛት ከማይችልበት ደረጃ ላይ እንዳደረሰው በግልጽ እየታየነው። በአሁ ሰዓት ዋናውና መሠረታዊ ጥያቄ ወያኔ ይወድቃል አይወድቅም የሚለው ሳይሆን፣ ከወያኔ ውድቀት በኋላ ተተኪው ማን መሆን አለበት የሚለው ጥያቄ በአግባቡ ሁነኛ መልስ የማግኘት ጉዳይ፣ የእኛንና የሕዝባችን እንቅልፍ የሚነሳ ነው። ማፍረስ ቀላል ባይሆንም፣ መገንባት የበለጠ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ማን ይተካል የሚለው ጥያቄ ትክክለኛና ተገቢ መልስ የሚሻ በመሆኑ እጅግ አስጨናቂና ፈታኝ ነው። የእኛ ሕዝባዊነት የሚመዘነውም ለዚህ ሕዝባዊ ጥያቄ ሕዝባዊ መልስ በመስጠታችን ነው።
ለምንሰጠው መልስ ሕዝባዊነትና ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሊሆነን የሚችለው፣ ሕዝብ አሳታፊ የሆነ የሽግግር ጊዜ ኖሮ፣ በዚያ ጊዜ ሕዝቡ የሚመኘውንና የሚሻውን መሆን የሚያስችል ሕገ-መንግሥት በሕዝቡ ተሳትፎ ዕውን ማድረግ ስንችል እንደሆነ ይታመናል። የሽግግር ጊዜ መንግሥት አስፈላጊነትም፣ ይህንን ሊፈጠር የሚችልን የሥልጣን ተካፈት ለመሙላት ብቻ የታለመ ሳይሆን፣ ሕዝቡ የሚመክርበት ጊዜ ለማመቻቸት ጭምር ነው። ሆኖም ዋና ዓላማው በኅብረተሰቡ መካከል ምንም ዓይነት አደናቃፊና ሥርዓተ አልበኝነት ሳይፈጠር ወደ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ዕኩልነት የሚያመራ የሥርዓት ሽግግር ለማድረግ (ለመፍጠር) የሚያስችል የሽግግር ጊዜና መንግሥት ወቅት ነው። ይህ የሽግግር መንግሥት በሁለት የጊዜ ገደቦች ውስጥ የሚያልፉ አስተዳደሮችን ያካተተ ይሆናል።
3.1 በትግሬ ወያኔ አገዛዝ ውድቀትና በሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ መካከል ከ3-6 ወራት ጊዜ ውስጥ የሚቆይ           የተባበሩና አንድነትን የፈጠሩ የፖለቲካ ኃይሎች በጋራ የሚያስተዳድሩበት አጭር የሽግግር መሰላል ወቅት፤
የነዚህ በድርጅቶቹ የጋራ ኮሚቴ የሚመራው የሽግግር መሰላል(ባላደራ) አስተዳደር የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባሮች የሚከተሉት   ይሆናሉ:-
(ሀ) ጦሩ በሥርዓት ከካምፑ ሳይወጣ፣ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን በተግባር ያሳዩ፣ ወይም በአገር ክህደትና ከተለያዩ ወንጀሎች ነፃ በሆኑ መኮንንኖች አስተባባሪነት በሚሰጣቸዉ መመሪያ መሠረት ፣የሚጠበቅበትን ሀገር የመጠበቅ  ኃላፊነቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩር አድርጎ ማረጋጋትና መምራት፣
(ለ) የፖሊስ ሠራዊትና የአካባቢ ሚሊሻዎች፣ ከልዩ ልዩ ወንጀሎች ነፃ በሆኑና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ባላቸው መኮንንኖች አስተባባሪነት፣ ኃይልን ሳይጠቀሙ ሕዝቡን የማረጋጋት ሥራን እንዲሰሩ መምራት፣
(ሐ) ሕዝባችንን ለከፍተኛ ፍጅትና እንግልት የዳረገዉ የትግሬ ወያኔ የስለላ መዋቅር፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ባላቸው ሙያተኞች እየተመራ፣ የአገሪቱንና የሕዝቡን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነት ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ማድረግ፣

(መ) የቢሮክራሲው እንቅስቃሴ ሳይደናቀፍ የዕለት ተዕለት ተግባሩን እንዲያከናውን ማድረግ፣
(ሠ) የሀገሪቱ የገንዘብ  የአሠራር ሥርዓት ሳይደናቀፍ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ፣
(ረ) በሀገሪቱ ውስጥ ሰላማዊ የሰውና የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ ማድረግ፣
(ሰ) የሽግግር መንግሥቱን የበላይ ሸንጎን ለመመሥረት ከ3 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ በመላ ሀገሪቱ   ከሚገኙ ወረዳዎች እንደ ሕዝባቸው ቁጥር በሚሰጥ ቀመር ላይ ተመሥርቶ፣ በሚሰጥ የውክልና መጠን እያንዳንዱ ወረዳ የሚወክለውን መርጦ  አዲስ አበባ እንዲከት ማድረግ፣
(ሸ) ከየወረዳው ሕዝብ ተመርጠው የሚላኩት የሕዝብ ተወካዮች (ሸንጎ) የሽግግር መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ይሆናል። የሸንጎው አባላት መሟላት እንደተረጋገጠ፣ የሽግግር ጊዜው 3 ዓመት መሆኑንና የዚህ ጊዜ ከፍተኛው የሥልጣን ባለቤት ሸንጎ መሆኑን የሚያረጋግጥ አዋጅ ያውጃል። ሸንጎው ራሱን በሁለት ክፍሎች ያደራጃል፤ የሕግ-መወሰኛ ምክር ቤትና የሕግ መምሪያ። የሕግ መወሰኛው ካሉት ዞኖች እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ሰዎች የሚወከሉበት ይሆናል። ሕግ- መምሪያው እያንዳንዱ ወረዳ ባለው የሕዝብ ብዛት መጠን የሚወከሉ የሕዝብ ተመራጮች የሚገኙበት ይሆናል።
(ቀ) ሸንጎው ተሰብስቦ የራሱን አመራር ከሰየመ በኋላ የሀገሪቱን የሽግግር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትርን   ይሰይማል፣ጠቅላይ ሚኒትስሩ ካቢኔውን ለሸንጎው አቅርቦ ይሁንታን ያገኛል።ያስተዳደር ሥልጣኑንም ከድርጅቶቹ ኮሚቴ  የሽግግር መሰላል (ባላደራ) አካል ይረከባል፣

(በ) ከዚህ የመጀመሪያው የሽግግር ሂደት ማብቃት በኋላ የድርጅቶች ኅብረት ተልዕኮ ያከትማል። ቢወዱ  አብረው ባይወዱ ተለያይተው  ለመሥራት  ወደ  አዲስ ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ፣
(ተ) ከዚህ አጭር የ6 ወራት የድርጅቶች ኅብረት ሽግግር በኋላ የሚመጣው ለ3 ዓመት የሚቆይ  የሽግግር መንግሥት ያስተዳደር ወቅት ይሆናል። በሽግግሩ የ3 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የመንግሥቱ  ሥልጣን ባለቤት ሸንጎው ይሆናል፣
አንቀፅ 3.2 የሸንጎው ሥልጣንና ኃላፊነት፣
ሸንጎው የሚከተሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፤
(ሀ)  የሀገሪቱን ሉዐላዊ ግዛትንና የሕዝቡን አንድነት ይጠብቃል፣
(ለ)  የጠቅላይ ሚኒስትሩን  የሥራ ሪፖርት አዳምጦ ይወስናል፣
(ሐ) በልዩ ልዩ ኮሚቴዎቹ አማካኝነት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የመከላከያ፣ የደYEንነት፣ የማኅበራዊና                 የባህላዊ ጉዳዮችን ይከታተላል፣
(መ) ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ አዋጆችንና ደምቦችን ያወጣል። ለተፈጻሚነታቸው ሕግ ይደነግጋል፣
(ሠ) ገለልተኛና ነፃ ፍርድ ቤት ያቋቁማል፣
(ረ)  አቃቤ-ሕግ ይሾማል፣
(ሰ) በትግሬ ወያኔ የአገዛዝ ዘመን የተፈጸሙ የሀገር ክህደት፣ የዘርማጥፋት እና የዘር ማጽዳት፣ የሀገር ሉዐላዊ ግዛትን መሸጥ መለወጥን፣  ሰቆቃን፣ የግፍ እስራትን፣ በፖለቲካ ላይ የተመሠረተ የግዛት መስፋፋትንና የሀብት  ዘረፋን ወዘተ… ተከታትሎ ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ የሚያቀርብ መርማሪ ኮሚሽንን በአዋጅ    ይሰይማል፣
(ሸ)  የግለሰብን ነፃነት ያውጃል፤ በዚያ ነፃ ሕዝብ ዙሪያ ለመደራጀት ለሚፈቅድ ኢትዮጵያዊ ነፃ የመደራጀት   መብት አዋጅ ያወጣል፣
(ቀ)  በነገድና በሃይማኖት ስም በፖለቲካ መደራጀት ክልክል ይሆናል፤ ወይም ለፖለቲካ ሥልጣን ውድድር ሲባል ሃይማኖትና ጎሳን መሠረት ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች መመሥረት የማይቻል መሆኑን በሕግ ያግዳል።
(በ)  በኢትዮጵያ የመናገር፣ ሀሳብን በማንኛውም ሁኔታ የመግለጽ፣ የፕሬስና የሚዲያ ነፃነት በሕግ እንዲታወቅ  ያደርጋል፣
(ተ)  ሕዝቡ በኢትዮጵያ ውስጥ በፈቀደው ቦታ ያለማንም ፈቃድ ሄዶ የመኖርና የመንቀሳቀስ መብቱን  በሕግ   ይደነግጋል።

(ቸ)  ገለልተኛ የሆነ የአስመራጭ ኮሚሽን በአዋጅ ያቋቁማል። አሠራሩን፣ ደምብና ሕግ ደንግጎ ያወጣል  በሕጋዊነት የተመዘገቡት የፖለቲካ ማኅበሮች አስተያየተቸውን እንዲያክሉበት ያደርጋል፣

(ኀ)  የሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔ ይሰይማል። ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ የውስጥ አስተዳደር ዓይነት  አሀዳዊ ይሁን ፌደራላዊ የሚሉትን አጥንቶ ሁለቱም ለሕዝብ ቀርበው በሕዝብ ወሳኔ እንዲያገኙ  ያደርጋል፣
(ነ) የሕገ መንግሥቱ የመጀመሪያው አንቀጽ የሀገር ባለቤትነት በማወጅ ይጀምራል። እወጃውም  የሰብአዊውን ሰው የግል ነፃነትንና የሀገር ባለቤትነትን ሲገለጥ “ኢትዮጵያ የመላው  ዜጎቿ  ሀገር ናት። የነዚህ ዜጎቿም የግል መገለጫቸው ሰበአዊ ማንነታቸውና ነፃነታቸው ነው” ተብሎ በጥብጣብ እንዲገለጥ   ይሆናል፣
(ኘ) ሕዝቡ በሕገ-መንግሥቱ ተወያይቶና መክሮ ሲጨርስ ነፃና  ግልጽ ምርጫ ተደርጎ አሸናፊው ሲታወቅ                   ብሔራዊ ቀን በሚሆንበት ዕለት ሥልጣን ከሽግግር መስተዳድሩ ወደ አሸናፊው ፓርቲ እጅ ይዞራል፣
(ዐ) ለሽግግር መንግሥቱ ቀዳማይ መሪ ለነበረው ለሸንጎውና ለሽግግሩ ጊዜ የአስተዳደር መሪ ለነበረው ለጠቅላይ ሚንስትሩ ይፋ አሸኛኘት ይደረጋል። በዚሁ ኢትዮጵያም ከገባችበት የጥፋትና የዕልቂት   አዙሪት ውስጥ ወጥታ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ወደምታልፍበት የዕድገት ጎዳናዋ  ትገባለች::

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!
የዐማራው ኅልውና መጠበቅ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!

የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ)