ዛሬ ሰኞ ማለዳ መናኸሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በከተማዋ የሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለቀው ይወጣሉ ሲሉ ቃል ቢገቡም ዛሬ ጠዋት ተጨማሪ ኃይል ወደ ከተማዋ በመግባቱ ለሌላ ተቃውሞ መቀስቀስ ምክንያት ሆኗል።
በወልዲያ ከተማ በጥምቀት በዓል ማግስት የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካቶች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል። መንግሥት የሟቾች ቁጥር ሰባት ነው ቢልም የከተማዋ ነዋሪዎች ግን የሟቾችን እና የቁስለኞችን ቁጥር ከፍ ያደርጉታል።
ቅዳሜ የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ እሁድ ዕለት የበርካታ ነጋዴዎች፣ የአካባቢው ባለስልጣናት እና የመንግሥት ደጋፊዎች ናቸው በተባሉ ግለሰቦች የንግድ ተቋማት እና መኖሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ሰኞ ጠዋትም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከከተማዋ እንዲወጡ አልተደረጉም በሚል ምክንያት በመንግሥት ተቋም ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከትናንት ጀምሮ የከተማዋን ነዋሪዎች ሰብስበው እያወያዩ ነው። የውይይቱ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል አንድ ወጣት በስልክ እንደነገረን፤ ትናንት በነበረው ውይይት የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአስቸኳይ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ተሳታፊዎች ጠይቀው ነበር። አቶ ገዱም በበኩላቸው የሠራዊት አባላቱ ከተማዋን ለቀው እንደሚወጡ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ዛሬ ጠዋት 4 ሰዓት ገደማ ተጨማሪ የመከላከያ ኃይል ወደ ከተማዋ ገብቶ በወልዲያ ጎዳናዎች እና አቋራጭ መንገዶች ላይ ተሰማርቷል ሲሉ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። በዚህም የተቆጡ የከተማዋ ወጣቶች የወልዲያ ከተማ ቤቶች ልማት ጽ/ቤት ላይ ዛሬ ከምሳ ሰዓት በኋላ ጥቃት ፈጽመዋል። ወጣቱን በስልክ እያነጋገርን በነበረበት ወቅት የተቃውሞ ድምጽ ይሰማ ነበር። ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ጋር በነበረው ውይይት ተሳታፊ ከነበረ ሌላ ወጣት እንደሰማነው፤ ርዕሰ መስተዳድሩ የሃይማኖት አባቶችን ጨምረው ስብሰባው፤ ተሳታፊዎች የሥርዓት ለውጥ እንፈልጋለን ከሚሉ ጥያቄዎች አንስቶ ፍትህን፣ ሥራ አጥነትን እና ከማንነት ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎችን ለክልሉ መስተዳድር አቅርበዋል።
የጥቃቱ ኢላማ
ግጭቱ ከተከሰተበት ዕለት አንስቶ በሰው ሕይወትና አካል ላይ ከደረሰው ጉዳት ባሻገር በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። የዚህ ጥቃት ኢላማ እነማን እነደሆኑ ለማወቅ ያነጋገርናቸውን የከተማዋን ነዋሪዎች ጠይቀን ነበር። ከአነጋገርናቸው መካከል እንዱ፤ ”በቤት እና ንብረታቸው ላይ ጥቃት የተፈጸመባቸው የአካባቢው ባለስልጣናት እና ወጣቶችን በመጠቆም የሚያሳስሩ የመንግሥት ደጋፊዎች ላይ ነው” ብሏል። ”የከተማዋ ከንቲባ መኖሪያ ቤት ላይ እና ባለቤትነቱ የክልሉ ተወላጅ በሆነው መቻሬ ሆቴል ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። እንዲሁም የመንግሥት ደጋፊ በሆኑ የግለሰብ ንብረቶች ላይ ጥቃት ደረሰ እንጂ የሌላ ክልል ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ ምንም አይነት ጥቃት አልደረሰባቸውም” ሲል ይሞግታል።በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ንብረት ላይ ጨምሮ በአካባቢው ባለስልጣናት እና የመንግሥት ደጋፊዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል ሲሉ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ነግረውናል።በአሁኑ ሰዓት በወልዲያ ከተማ ውስጥ ምንም አይነት እንቅሳቀሴ አይታይም። በርካታ ነዋሪዎችም ለደህንነታቸው በመስጋት ከመኖሪያ ቤታቸው ከመውጣት መቆጠባቸውን ነግረውናል።
BBC