አቶ ገዱ ሕዝብን የሚያክብሩ ናቸው፤ የሕወሃት አገልጋይ አይደሉም #ግርማ_ካሳ
January 25, 2018

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
“ገዱ መሪ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ቆቦ ህይወት አይጠፋም ነበር” በሚል ጽሑፍ ወዳጄ ግዛው ለገሰ ስሜን ጠቅሶ ትንሽ አስተያየት ጽፉአል። “ ወዳጄ (በትጋቱ የማደንቀው፣ ግብረገብነትንና ፖለቲካን የሚያምታታው) ግርማ ካሳ ደግሞ “ገዱ ትልቅ መሪ” ነው ብሎ መለሰልኝ። የግርማ ፅሁፍ ብዙ ምኞትና ያካተት ሆኖ ገዱ ጥሩ መሪ እንደሆን የሚያሳዩ ውሳኔውች፣ ራዕዮች፣ ፅናቶች (courage)፣ ሃቀኝነት (integrity) አላሳየም” ያለው ግዛው፣ “ ገዱ መሪ አየደለም፣ አማራን የሚያክል ህዝብ በህወሃት ድኩማን ሊመራ አይገባም። ብአዴን የህወሃት አገልጋይ ነው፣ ገዱም የህወሃት አገለጋይ ነው።” ሲል ጽሁፉን ያጠቃልላል።
“ግብረገብነትንና ፖለቲካን የሚያምታታው” ሲል የጻፈው ምን ለማለት እንደሆነ ባይገባኝም፣ የአገራችን ፖለቲካ አሁን ያለበት አስቀያሚና አስዛኝ ደረጃ የደረሰበት አንዱ ምክንያቱ ጥሩ ግብረገብነት ( moral value) ካለመኖሩ የተነሳ መሆኑ መቼም ወዳጄ ግዛው ያጠዋል ብዬ አላስብም። በጃንሆይ ጊዜ ( እኔ አላስታውሰዉም ፣ጃንሆይ ሲሞቱ አምስት አመቴ ነበርና) የግብረገብነት ወይም ሞራል ትምህርት በመንግስት ትምህርት ቤቶች ይሰጥ እንደነበረ የሰማሁ መሰለኝ። ደርግ ሲመጣ ያው የወቅቱ ምህራንና ወጣቶች፣ የስድሳዎቹ ማለት ነው፣ ማርክሲዝምን አመጡብን። የሞራል ትምህርት በማሌ ትምህርት ተተካ። አብዮት ርዮታለም ከሰው ልጅ ሕይወት በለጠ።
አሁንም የአገራችን ችግር የሚፈታው ዜጎች ለሠው ልጅ ፣ ሰው ስለሆነ ብቻ ክብር ሲሰጡ ነው። ይሄ የሞራል ጉዳይ ነው። ጥሩ ግብረገብነት የሌለበት ፖለቲካ የጥፋት፣ የዉድመት ፖለቲካ ነው። ለዚህም ነው ግብረገብነትንና ፖለቲካን አገናኝተን የምንጽፍፈው።
ወደ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስመለስ፣ አሁንም ግዛው ላይ አንድ ትልቅ ችግር አያለው። ለውጥ እንዲመጣ መመኘትና ለዉጥ ማምጣት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። የግዛው ስሜትና frustration ይገባኛል። በቆቦ በመቂ ብዙ ወገኖቻችን ዛሬ በግፍ ተገድለዋል፤ በወልዲያ የፈሰሰ ደም ሳይደርቅ። ከዚያ በፊት ላለፉት 6 ወራት ብቻ ከኢሊባቡር፣ ጨለንቆ፣ አዲግራት፣ አወዳይ፣ አምቦ፣ ነቀምቴ፣ ሻምቦ፣ በቤኔሻንጉል፣ አርሲ ነገሌ..የብዙ ዜጎች ደም ፈሷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ምንም የሚሻሻል ነገር የለም። በእያንዳንዱ አሳዛኝ ክስተት ሀዘናችንን፣ ቁጭታችንና ስሜታችንን ገልጽናል። የተለወጠ ነገር የለም። ህወሃቶች አሁንም በስልጣን ማማ ላይ ቁጭ ብላ እንደፈለጉገች እይአደረገች ነው።
ሕወሃትን ስለረገምናት አትዳከምም። ስላወገዝናት ፣ ስለጮህን አምስት ሳንቲም የሚደርስባት ነገር የለም። ሕወሃት መወገድ አለባት ብለን ስለፎከርን ሕወሃት አትወገድም። የሕወሃትን አቅም የሚሸረሽር፣ ህወሃትን የሚያዳክም፣ የሕወሃትን የሃይልና የጥንካሬ ምንጭ የሆኑትን የሚዘጋ በእውቀትና በስትራቴጂ የተመሰረተ ስራ እስክልተሰራ ድረስ በወገዛ የሚፈታ ነገር የለም። እንግዲህ የኔና የነግዛው ለገሰ መንገድ የሚለያየው እዚህ ላይ ነው።
ሕወሃትን ለማስወገድ በዋናነት የሕወሃትን የሃይል መሰረቶች፣ ጠንካራ ጎኖችን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል። አንዱ የሕወሃት ጥንካሬ በአገር ውስጥ አማራጭ የተቃዋሚ ስብስብ እንዲኖር አለማድረጉ ነው። የተቃዋሚ መሪዎች በገንዘብ እየገዛ.፣ እየከፋፌልለ፣ እንዳይስማሙ እያደረገ፣ ከአቅሙ በላይ ከሆኑ ድግሞ መሪዎቻቸዉን እያሰረ፣ ድርጅቶችን እያገደ ህዝቡ ብቃት ያለው መሪ ድርጅት እንዳይኖረው አድርጓል።
በዉጭ ያሉ ተቃዋሚዎችን በተመለከተ ህወሃት እድለኛ ሆኗል። ለምን ቢባል በዉጭ ያሉ ድርጅቶች የሕወሃት አምስት ሳንቲም ጫና ሳይኖርባችው መስማማትና አብረው መስራት አልቻሉም።
ሕዝቡን ሊመራ የሚችል ጠንካራ መሪ ድርጅት ወይንም የድርጅት ስብስብ እስከሌለ ድረስ ህወሃቶች ቢሄዱ በአገሪትቷ አናርኪ ነው የሚፈጠረው ከሚል ስጋት፣ ባይፈለግም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ቦታዎች፣ ሰው በሙሉ ሃይሉ አገዛዙ ላይ እንዳይነሳ የፈራበት ሁኔታ ሊኖር ፈጥሯል። ያ ብቻ አይደለም መሪ ድርጅት ለሌለም በየቦታው የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ግብታዊና በተቀናጀ መልኩ ባለመሆናቸው አገዝዙ በቀላሉ ሊቆጣጠራቸው ችሏል። መሪ ድርጅት ቢኖር ኖሮ ግብታዊ በሆነ መልኩ ሳይሆን በተደራጀና በተጠና፣ ውጤት በሚያመጣ መልኩ ህዝቡን በማንቀሳቀስ ለዉጡን ማፋጠን ይቻል ነበር። እስቲ አስቡት በአንድ ቀን ጎንደር፣ አምቦ፣ ወልዲያ፣ ደብረ ታቦር፣ ነቀምቴ፣ አዳማ፣ ደባርቅ፣ ደሴ፣ አርባ ምንጭ፣ ሸገር … ህዝቡ ሆ ብሎ ቢነሳ ሕውሃት አለቀላት አልነበረም ወይ ?
ሌላው ሕወሃት ለ27 አመታት በአገሪቱ በሙሉ ያለ ምንም ችግር ለመግዛት የረዳው ትልቁ መሣሪያው ብአዴንና ኦህዴድ የሚባሉ ቅልብ አሃያዎችን፣ በቅሎዎችና ፈረሶችን መጋለብ በመቻሉ ነው።
ላለፉት 2 አመታት በብአዴንና በኦህዴድ ውስጥ የለዉጥ ሃይሎች ደፍረው ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። ሕወሃትን ከማገልገል ይልቅ የሕዝብን ጥያቄ ለማስተናገድ ፍላጎት እያሳዩ ነው። በተለይም አቶ ለማና አቶ ገዱ ስር የሰደደ የሕወሃትን hegemony ን ለመስበር የተቻላቸዉን ውስጥ ውሱጡን ደፋ ቀና እያሉ ነው። በፊት 100% የሕወሃት አሽከሮች ስብስብ የነበሩ ድርጅቶች አሁን 30%፣ 50% ፣ 60% ….. የለዉጥ ጥያቄ ማሰማት ከቻሉ ፣ እነርሱን አጠናክሮ የበለጠ አይለው እንዲወጡ ማድረግ ነው የሚሻለው ወይንስ ከወዲሁ እነርሱን እየኮረኮረሙ ብአዴንና ኦህዴድን ጥቅም የለሽ በማድረግ ለህወሃት ፌሽታን ማወጅ?
ከላይ እንደገለጽኩት አማራጭ መሪ ድርጅት ቢኖር፣ ሌላ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን አሁን አንደኛ በመሬት ላይ ህዝቡን ሊያደራጁ የሚችሉት፣ ሁለተኛ ህወሃት ቢወገድ አማራጭ ተተኪ ሊሆኑ የሚችሉት እነርሱ ናቸው።
ስለዚህ “ብአዴን የሕወሃት አገልጋይ ነው፣ ገዱ የሕወሃት አገልጋይ ነው” ማስት በብአዴን ውስጥ ከሕወሃት ጋር ትንቅንቅ የያዙትን የለዉጥ ሃይሎች ማዳከም ነው። ጊዚያዊና ስሜታዊ አስተያየት እንጅ ስትራቴጂክ በሜዳ ላይ ያለዉን ሁኔታ ያንጸባረቀ አስተያየት አይደለም። ብአዴን የበለጠ ጠንካራ ሆኖ እንዲወጣና በአናቱ ላይ የተጫነበነን የሕወሃት ቀንበር አሽቀንጥሮ እንዲጥል ማገዝ ነው እንጅ የሚያስፈለገው፣ ምን ሌላ አማራጭ ሳይኖር፣ ለውጥ ሊገኝበት የሚችልን ትንሿን እድል ለመዝጋት መሞከር ትልቅ ስህተት ነው።
ወዳጄ ግዛው “ገዱ ለምን በአደባባይ የወልዲያንና የቆቦን እልቂት አላወገዘም፣ ለምን በአደባባይ ወያኔ አልሰደበም” ነው እያለን ያለው። እሺ ገዱ ግዛው እንደፈለገው በአደባባይ አወገዘ። ከዚያስ ? ወያኔዎች ለምን እንዲህ አልክ ብለው ቢነሱበት እነርሱን የመቋቋም አቅም አለው ወይ ? ይሄን አጋጣሚ ተጠቅመው ወያኔዎች ገዱንና የገዱ አይነት አስተሳሰብ ያላቸውን መንጥረው ቢያወጡ ማን ነው የሚጠቀመው ? ፈንጂ በሞላበት ቦታ ተጠንቅቆ መሄዱ ነው የሚሻለው ወይስ ደረት እየነፉ መጓዝ በፈንጂ መበጣጠስ ?
በኔ እይታ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቅንነት የሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ የሚሰራ ሰው ነው። በብአዴን ውስጥ የብአዴንን ታርጋ የለጠፉ እንደ በረከት ስሞኦን፣ አማራ ጎሹ ያሉ ሕወሃቶችና በገንዘብ የተገዙ እንደነ አለምነህ መኮንን ያሉ ብአዴኖች የተሰገሰጉበት እንደመሆኑ ለለዉጥ ሃይሎች ለነገዱ በጣም አስቸጋሪ ነው። ቀስ ብለው በርጋታ መንቀሳቀሳቸው ሊያስወግዛቸው አይገባም።
ወያኔዎች አንድ ሌላ የተካኑበት ነገር ኢኖር በተቃዋሚ ጎራ ያሉትን በተለያዩ መልኩ ወደ እነርሱ ለማቀፍ የማይተኙ መሆናቸው ነው። እኛ ግን ትግሉ ስኬታማ እንዲሆን አጋሮችን፣ ወዳጆችን ከማብዛት ይልቅ ስሜታዊ ሆነን ጠላት ነው የምናበዛው። ከሕወሃት ወገን ሕወሃትን ሲያገለግሉ የነበሩትን ወደኛ ለመሳብ፣ እነርሱን ከሕወሃት ለመነጠል አንሞክርም። ህወሃትን የሚደገፉ የነበሩ ለሕወሃት ድጋፋቸው እንዳይሰጡ ማድረግ የፖለቲካ ብስለት ሆኖ ሳለ ይህ ብስለት በእጁጉ ይጎድልለናል። እንኳን ሌሎችን አሳምነን ወደኛ ልንስብ፣ በሕወሃት ተማረው ወደኛ የመጡትን እናርቃለን። እነ ገዱ፣ እነ ለማ ከሕወሃት ጋር ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። አሁን ግን የሕዝብ ወገንተኝንነትን እያሳዩ ነው። የበለጠ ወደ ህዝብ እንዲቀርቡ፣ ሌሎችም እንዲከተሏቸው ማበረታታት እንጂ እነርሱ በመግፋት ትላንት ወደ ነበሩበት ወደ ወያኔ እቅፍ እንዲወሸቁ ባንግፋቸው ጥሩ ነው።
ከዚህ በታች ያለው ዓቶ ገዱ በወልዲያና በቅኦብኦ ዙሪያ የሰጡት መግለጫ ነው። የተፈጠረው ችግር የተጠራቀመ የሕዥብ ብሶት የወለደው እንደሆነ የገለጹት አቶ ገዱ ፣ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ብአዴን ነው ነው ያሉት። በሌላ መልኩ ብ አዴን የሕዝብን ጥያቄ ማክበር አለበት ነው እያሉ ያሉት። ክከዚህ የበለጠ መቺም ጦርና ጎራዴ እንዲያነሱ መጠበቅ የሚቻል አይመስለኝም)