በወልዲያ አንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች ከሳምንት በኋላም ተቃውሞዎች መቀጠላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ። በተለይ መናኸሪያና ጎንደር በር በሚባሉት አካባቢዎች መንግሥትን የሚቃወሙ መፈክሮችን የሚያሰሙ ሰዎች እንደተመለከቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልፀዋል። በከተማዋ የሚደረጉ የሥራ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መቋረጡንም ጨምረው ተናግረዋል። በሰው ላይ ስለደረሰ ጉዳት እንዳልሰሙ ቢናገሩም ትናንትናና ዛሬ ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። ከወልዲያ ሃያ ሰባት ኪሎሜትር ርቃ ወደምትገኘው በመርሳ ከተማም የነበሩት ግጭቶች ቀዝቀዝ ቢሉም የሥራም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሌለና ከተማዋ ጭር እንዳለች ነዋሪዎች ገልፀዋል። ስሙ እንዲገልፅ ያልፈለገ የከተማዋ ነዋሪ መምህር ለቢቢሲ እንደተናገረው ዛሬ ጠዋት አንዳንድ ሰዎች ለሥራ ወጥተው የነበረ ሲሆን መስሪያ ቤቶች ዝግ ስለሆኑ ወደቤታቸው ተመልሰዋል።

በጥምቀት ማግሥት በወልዲያ ከተማ ግጭት ተነስቶ የሰዎችን ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል። ይህም ተቃውሞ በአቅራቢያዋ ወደሚገኙት የሰሜን ወሎ ዞን ከተሞች የተዛመተ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የተጨማሪ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። ቀደም ባሉት ቀናት ቆቦ ውስጥ ተከስቶ የነበረው ግጭትና ተቃውሞ ቅዳሜ ዕለት በመርሳም የተከሰተ ሲሆን ቢያንስ አስር ሰዎች እንደሞቱ ተነግሯል። ለተቃውሞ የወጡት ሰዎች ፀረ-መንግሥት መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን በወልዲያና በቆቦ የተከሰተውን ግድያና ግጭቶችን ተከትሎ ሰዎች መታሰራቸውን ተቃውመዋል። ተቃውሞው እሁድ ዕለትም በቅርብ በምትገኘው ሲሪንቃ ከተማ ተከስቶ የነበረ ሲሆን በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ግን የወጣ መረጃ የለም። ነገር ግን በተለያዩ ከተሞች በተከሰቱት ተቃውሞዎች በሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል ጉዳቶች መድረሳቸውን ተከትሎ በመንግሥትና በግለሰብ ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን በቆቦና በመርሳ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። በመርሳ ከተማ የተከሰተው ግጭትና በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት የከፋ እንደነበረ የሚናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች በግጭቱ ቆስለው ከነበሩት መካከል ሁለቱ ቀብራቸው እሁድ መፈፀሙን ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ አንድ የከተማው ነዋሪ ተናግረዋል።  በመርሳ እና ሲሪንቃ የፀጥታ ኃይሎች በበርካታ ቁጥር የተሰማሩ ሲሆን በተቃውሞው ተሳትፈዋል የተባሉ ቁጥራቸው ያልታወቀ ወጣቶች መታሰራቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በቆቦ ከተማም መረጋጋት ቢሰፍንም ከተማዋ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ እንዳልተመለሰችም እኚሁ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

ከከተማዋ የሚያስወጡ መንገዶች አሁንም እንደተዘጉ፤ የመጓጓዣ አግልግሎት ይሰጡ የነበሩ ባለሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ አስረድተዋል። የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የብአዴን ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮነን ሕዝቡን ሰብሰብው ለማወያየት ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም፤ ሕዝቡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲያነጋግሩን ነው የምንፈልገው በማለቱ ምክንያት ስብሰባው ሳይከናወን እንደቀረም ነዋሪዎቹ ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት አቶ አለምነው ከወጣት ማኅበር እና የሐገር ሽማግሌ ተወካዮችን ለብቻ ሰብሰብው ለማናገር እንደተገደዱም ጨምረው ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለት በከተማው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች የአስተርዮ ማርያም በዓልን እያከበሩ ሲሆን፤ በዓሉ በሚከበርበት ቤተ ክርስትያን በሰላም እና በፀጥታ ሥርዓቱ እንደተከናወነ የቆቦ ከተማ ኮምኒኬሽን ቢሮ የቡድን መሪ የሆኑት ወይዘሮ ሸዋዬ አሸብር ለቢቢሲ ከእኩለ ቀን በፊት ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሸዋዬ ጨምረውም በቆቦ የተከሰተውን ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ ታስረው ከነበሩት ወጣቶች መካከል የተወሰኑት መለቀቃቸውን ገልፀዋል።

BBC