January 29, 2018

ያልተፈቱት እስረኞች እንዲፈቱ ተጠይቋል

አቶ አለምነው መኮንን ወጣቶቹን ወንጅሏል

የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ሊታሰሩ እንደሚችሉ ተግልፆአል

በወልዲያና ቆቦ ንፁሃንን የገደሉት ለፍርድ እንዲቀርቡ እና የታሰሩትም እንዲፈቱ በሰልፍ ሲጠይቅ የነበረው የቆቦ ህዝብ ተወካዮች ጋር የተሰበሰቡት የብአዴን አመራሮች ዛሬ ጥር 21/2010 .. ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

የኃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በቆቦ ከተማ የታሰሩት እንዲፈቱ በጠየቁት መሰረት በትናንትናው ዕለት 40 እስረኞች መፈታታቸው ታውቋል። ይሁንና የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው ሲሳይ አውራሪስ እና ሞላ ትኩዬ ያልተፈቱ ሲሆን የቆቦ ህዝብ ተወካዮች ያልተፈቱት ሁለት ወጣቶች እንዲፈቱ ጥያቄ አቅርበዋል። ሆኖም ስብሰባውን ሲመራ የነበረው አቶ አለምነው መኮንን “በሌላ ጉዳይ ይፈለጋሉ። እነሱ ላይ ምርመራ ይደረጋል” በሚል እንደማይፈቱ ገልፆአል።

በስብሰባው ላይ የተገኙ የህዝብ ተወካዮች “ወጣቶቹ የታሰሩት በወቅታዊ ጉዳይ ነው። ሌላ የሚመረመር ጉዳይ ካለ ሌላ ጊዜ መርምሩ እንጅ አሁን የታሩት የተፈቱት በታሰሩበት ጉዳይ ነው። ከቤታቸው ታፍነው መታሰራቸውን እናውቃለን” በማለት እንዲፈቱ የብአዴን አመራሮችን ለማሳመን ቢጥሩም እነ አለምነው መኮንንም ወጣቶቹ አይፈቱም በሚለው አቋማቸው በመፅናታቸው ተወካዮቹ ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል።

የህዝብ ተወካዮች “አንተን አልፈልግም፣ ገዱ አንዳርጋቸው ያነጋግረን፣ እየተገደልን ያለነው ባልመረጥናቸው ሰዎች ነው” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የብአዴን አመራሮች የህዝብ ተወካዮችን በመጠቀም ህዝብን ካረጋጉ በኋላ በቆቦ፣ ወልዲያና በአካባቢው የሚኖሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ለማሰር እንዳቀዱ መስማታቸውን የቆቦ ነዋሪዎች ገልፀዋል። አቶ አለምነው መኮንን ያልተፈቱት ወጣቶችን “ችግሩን ሲያባብሱ የነበሩ እነሱ ናቸው” በሚል እንደወነጀሏቸው፣ ጉዳያቸውም ይመረመራል የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆናቸው እንደሆነ እና ችግሩን “የእኔ ችግር ነው” ሲል ከነበረው ብአዴን ወደ ተቃዋሚዎች ለማዞር ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ ገልፀዋል