January 29, 2018
በአብዛኛው የአፍሪቃ ሀገራት፤ የቅኝ ግዛት ቅሪት ከአንድ ፓርቲ አገዛዝ ጋር ተዳምሮ የጋዜጠኝነት ሙያን የጠቅልለህ ግዛ ውጤት እንዲሆን አስችሎታል፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ቀደም ሲል በቅኝ ግዛት ወቅት በወረሱት የፕሬስ ነጻነት እና አንዱ አንዱን ደፍጥጦ ወደ ሥልጣን ስለመጣ መገናኛ ብዙኀን የልባቸው መሣሪያ አድርገው “ህዝቡን ጀሮ ዳባ ልበስ” በማለታቸው በአፍሪቃ አህጉር ብዙ የሕዝብ እሮሮ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ በልማት ሥም፣ በአገር ደኅንነት ሥም፣ እና በሌሎች መሠል ምክንያቶች በየሀገራቱ የፖለቲካ መሪዎች ስም የሚሠሩ ከባባድ የጥፋትና የውንጀላ ሥራዎች ላይ በሚደረግ ዘገባ ጋዜጠኞችና አታሚ ድርጅቶች ብዙ ጥቃቶች ሲደርሱባቸው ቆይቷል፡፡ አሁንም ቢሆን አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች የህዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ከመገናኛ ብዙኀን ጋር መወነጃጀል ይቀላቸዋል፡፡ በፕሬስ ነፃነት ይዞታዋ በዘርፉ ተቆርቋሪዎች የምትተቸዉ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በሚፈለገው መልኩ ማሳየት አለመቻላቸው የመገናኛ ብዙኀኑ አቅም መዳከሙን ያመላክታል፡፡ ይህም ሕዝቡ ሀገራዊ ክንውኖችን ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንዲጠብቅ አድርጎታል፡፡ በዚህ ምክንያት ሕዝቡ ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሚያገኘው ያልተጣራ መረጃ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚከሰቱትን ኹነቶች መቆጣጠር እንዳይችል አድርጎታል፡፡
በኢትዮጵያም መገናኛ ብዙኀን በመንግሥት ቁጥጥር ስለመሆናቸውና የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች የሙያ ነጻነት እንደሌላቸው ባለፉት ዐሥር ዓመታት በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ የሚዲያ ተቋማትን በአንድም በሌላም መንገድ ከገቢያ እንዲወጡ በማድረግ፣ ጋዜጠኞችን በማስፈራራት፣ በማሠር፣ በማሳደድ መንግሥት ትልቁን ድርሻ ተወጧል፡፡ ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያ ታሪክ ከገዥው መንግሥት ሥፍር ውጭ የሚተረክ ቅብብሎች መቼም ቢሆን አይመቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ሁል ጊዜ ኢህዴግና ኢትዮጵያ ብቻ እንዲነገር የሚፈልገው ገዝው ፓርቲ አሁንም ከጥልቅ ተሀድሶው የተማረ አይመስልም፡፡ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 እሑድ እሑድ የሚተላለፈውን ዓይነት “የሸገር ካፌ” የአብዱ እና የመዓዛ ውይይት ብቻ በሁሉም መገናኛ ብዙኀን ቢቀጣጠል ኖሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማትም ጋዜጠኞቸም ጥርስ እያወጡ ይሄዱ ነበር፡፡ ሆኖም ሸገር ኤፍ ኤም የበጎ ምሳሌ ሳይሆን “ያሁኗ ኢትዮጵያ እንዳልጣመችው በግልፅ ነው የሚታየው…” የሚል ተቀጽላ እንዲለጠፍበት ሆኗል፡፡ በዚህች ሀገር ኢህአዴግን ከሚያስተቹት ነገሮች መገናኛ ብዙኀንን በተመለከተ ብቻ ሳይሆን ከገዥው ፖርቲ ውጭ ስላለችው ኢትዮጵያ የሚነገር ነገር አይጥመውም፡፡
ይሄ ማለት መገናኛ ብዙኀን ህዝብ የፈለገውን ሳይሆን መንግሥት የፈለገውን ብቻ እንዲያግቱ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ግልጽ አቋሙን አንጸባርቋል፡፡ በተለይ መንግሥት አሁንም ቢያንስ የተለየ አሳብ የሚያስተናግዱ እንደ ሸገር ዓይነት ኤፍ ኤሞችን በተለመደው አካሄድ ጠልፎ ለመጣል ካሰበ አሁን በሀገሪቱ የሚታየውን የህዝብ ችግር ከመፍታት ይልቅ ፖለቲካዊ ትርፍ ማግኘትን ወይም የአገዛዝ ሥርዓቱን ለማዳን ከመሮጥ የዘለለ ትርጉም አይኖረውም፡፡
መገናኛ ብዙኀን ገለልተኛ ባይሆኑ ነጻ መሆን አለባቸው፡፡ ነጻ መገናኛ ብዙኀን ቢያንስ ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃዎችን ለህዝቡ ቶሎ ያደርሳሉ፡፡ ነጻ መገናኛ ብዙኀን በግልጽ የሚታዩ ችግሮችን ያለፍርሃት መተቸት ይችላሉ፡፡ ነጻ መገናኛ ብዙኀን በሀገሪቱ እየታየ ስላለው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ብልሹ አሠራር፣ እንዲሁም ሀገሪቱን በሙስና ስላነቀዟት ፖለቲከኞችና ግለሰቦች ቀደም ብሎ ፈልፍሎ በማውጣት ያጋልጣሉ፡፡ ሆኖም እንዲህ ዓይነት መገናኛ ብዙኀን ሀገሪቱ ውስጥ እንዲኖር መመኘት ብቻ ነው ትርፉ፡፡ በመገናኛ ብዙኀን በኩል ቢሠራ ኖሮ መንግሥት አሁን ከገባበት ፈተና ለጊዜውም ቢሆን ማገገም ይችል ነበር፡፡
ስለሆነም አሣሪ የሆኑት የመገናኛ ብዙኀን ሕጎች፣ በእጅ አዙር የሚደረጉት ቅድመ ምርመራዎች፣ የመንግሥት የትችት ጥላቻ፣ እስከነ ክፍተታቸውም ቢሆን በተለይ በኅትመት ሚዲያው በኩል ይታዩ የነበሩ አንዳንድ ወጣ ያሉ አካሄዶችን መንግሥት ስላልፈለገ ብቻ ከገቢያ እንዲወጠቱ ማድረጉ (critical comment and fair opinion) መንግሥትን በአንድም በሌላም በኩል ጉድተውታል፡፡ ስለሆነም የህዝቡን ችግር በፖለቲካዊ መደርክ እና በፖለቲካዊ መዋቅር ብቻ እፈታለሁ ብሎ የተጓዘበት መንገድ ሚዲያው አቅሙን እዳያሳድግና ፖለቲካውም ጤነኛ እንዳይሆን ክፉኛ አጎሳቁሎታል፡፡ ጠንካራ የዲሞክራሲ ሥርዓት የሚገነባው በፖለቲካዊ መዋቅር ብቻ አይደለም፡፡ መተኪያ በሌላቸው መገናኛ ብዙኀን በኩል በቂ በሆነ መረጃና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ትምህርትና ውይይት ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ ያለ መገናኛ ብዙኀን የሚደረግ የዲሞክራሲ ግንባታ ጉዞው ጨለማ እንጅ ብርሃን አይሆንም፡፡ በአፍሪካ ግን መገናኛ ብዙኀን የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ ብቻ አድርገው መውሰዳቸው ከመገናኛ ብዙኀን እና ከህዝቡ ጋር እንደተጣሉ ይኖራሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በያዝነውም ዓመት ኅዳር ወር ከመገናኛ ብዙኀን ጋር በተገናኛ የፓርላማ አባላት ላነሡላቸው ጥያቄዎች “የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙኀን ችግሩ ሚዲያው ውስጥ ያለው የሰው ኃይል በአቅምና በአፈጻጸም ደካማ መሆን ነው” ብለዋል፡፡ ስለዚህ የመገናኛ ብዙኀን የሪፎርም ሥራ “በአመለካከት፣ በክህሎት፣ በአደረጃት፣ በአሠራር …የማስፈጸም አቅማቸውን” መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡ መገናኛ ብዙኀን በልዩ ልዩ አዋጆች ማለትም የመጀመሪያውና ሁለተኛው የፕሬስ አዋጅ (በአተገባበር ችግር፣ ሚዲያዎችን በእጅ አዙር በማዳከም)፣ የብሮድካስት አዋጅ፣ የማስታወቂያ አዋጅ (ካልተሳሳትኹ የማስታወቂያ አዋጁም ተሻሽሎ ለሁለተኛ ጊዜ የወጣ ይመስለኛል) እንዲሁም በጸረ-ሽብር አዋጅ (በትርጉም አሻሚነትና ሚዲያውንም ጋዜጠኛውንም ጠልፎ በመጣል) የሚዲያዎችን እድገት እንደ ካሮት ወደ ታች ካከሰማቸው በኋላ መገናኛ ብዙኀን የሪፎርም ሥራ አካሄዱ ጠልፎ ለመጣል እንጅ ለማሻሻል አይመሥልም፡፡
ስለዚህ ሪፎርሙ የማይመልሳቸው ነገር ግን በመገናኛ ብዙኀን ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮችን አሁንም መንግሥት ሊያያቸው ወይም ሊወያይባቸው አልፈለገም ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያ ሪፎርም ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው ብለን ስናይ መገናኛ ብዙኀኑ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን ወደ ህዝቡ እንዲያደርሱ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡ መልካም እንደተባለው ይሁንና መንግሥት በመገናኛ ብዙኀኑ ላይ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ያሳየው ጭፍን ጥላቻና ቁጥጥር ሚዲያዎችን የት አደረሳቸው ብለን ስንጠይቅ ግን፤ አንደኛ መገናኛ ብዙኀኑ እለት እለት የመንግሥትን ፕሮፖጋንዳ ብቻ በመለፈፍ አፈ-መንግሥት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፣ ሁለተኛ ህዝቡ መገናኛ ብዙኀኑ ላይ የነበረውን እምነት እንዲሸረሸር ብቻ ሳይሆን እንዲጠፋ አድርጎታል፣ ሦስተኛ በሀገሪቱ ውስጥ ስንት ብልሹ አሠራር፣ ሙስና እና የአስተዳደር ችግሮች እየታዩ መንግሥትን የጠቀሙ መስሏቸው በዝምታ በማለፋቸው ሀገሪቱ ወደ ማትወጣው የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፣ ዐራተኛ መገናኛ ብዙኀኑ እና ጋዜጠኞች ፈሪና አቋም የሌላቸው ሙያተኞች አድርጓቸዋል፡፡
ስለሆነም መንግሥት እንደ ችግር ያስቀመጠውና “በአመለካከት፣ በክህሎት፣ በአደረጃት፣ በአሠራር …የማስፈጸም አቅማቸውን” ለማሻሻል በመገናኛ ብዙኀን ላይ የሪፎርም ሥራ መሥራት አለበት ብሎ ሲነሣ የችግሩ ሥር የሆኑት እነዚህ ውጤቶች ዋና ተዋናኙ መንግሥት መሆኑ ተዘነጋ እንዴ? በአመለካካት፣ በክህሎትና በአደረጃጀት ሚዲያዎቹ ለሁለት ተከፍለው መንግሥትንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እያሉ ህዝቡን ወደ ጎን በመተው ሙያዊ ሓላፊነታቸውን የዘነጉ መገናኛ ብዙኀን የማን ውጤቶች ናቸው?
በአመለካካት ኢህአዴጋዊ ያልሆነ ሚዲያና ጋዜጠኛ የት አለ?፣ በአሠራርና በክህሎት ሙስናውን፤ ብልሹ አሠራሩን፤ የህዝቡን ድምፅ “ጀሮ ዳባ ልበስ” ብለው ልማታዊ ኹነቶችን እንከን የሌላቸው አስመስሎ የማያቀነቅን ሚዲያና ጋዜጠኛ የት አለ?፣ በአደረጃጀት ከላይ ከአመራሩ ጀምሮ እስከ አርታኢያን ድረስ በማን አቋም ነው የሚሾሙት?፣ በየሚዲያ ተቋሙ (በተለይ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን) ጋዜጠኛው በብሄር ተከፍሎ የሚዲያው አደረጃጀት ሲቪል ሰርቪስ እንዲሆን ያደረገው ማን ነው?
ሌላው ቢቀር እንኳን በጆርናሊዝም ወይም በኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ዘርፍ በድግሪ የተመረቁ ወጣት ኢትዮጵያውያንን አንዳንድ ተቋማት በሥራ ቅጥር ጊዜ መንግሥት የሠጠውን የኮሙዩኒኬሽን ሥልጠና የወሰደ እያለ ችግር የሚፈጥረው ማን ነው? በአንድ ወቅት የተሠጠ ሥልጠና እስከ አምስት ዓመት ድረስ እንደ ቅድመ ኹኔታ በማስቀመጥ ችግር እየፈጠረ ያለው ማን ነው? ለምሩቃኑ ከታሰበ ከቅጥር በኋላ ማሰልጠን ይቻል ነበር፡፡
መንግሥት በመገናኛ ብዙኀን በኩል ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ከፈለገ በዋናነት መገናኛ ብዙኀኑን ነጻ ማድረግ አለበት፡፡ ጋዜጠኛ ከተቋም በላይ ማሰብ ካልቻለ መቼም ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ የትኛውም የሚዲያ ተቋም ዓላማው ህዝብና እውነት ነው፡፡ የሚያገለግለውም ለሀገርና ለህዝብ ነው፡፡ ስለሆነም በአንድ የመንግሥት ሹመኛና በአንድ ኤዲተር ጉዳዮቹ ወድቅ በሚያደርግበት ኹኔታ ጋዜጠኛው ከተቋም በላይ የሚያገለግለው ህዝብንና እውነትን መሆኑን ካልተረዳ ለእውነት የሚቆምና ከአንድ ተራ የሚዲያ ተቋም ግላዊና ፖለቲከዊ አላማዎችን ብቻ ከሚያስፈጽም ኤዲቶሪያል ፖሊሲ መላቀቅና ሙያውን ነጻ ሆኖ መሥራት አይችልም፡፡ አንዱ ችግር ያለው ይሄው ስለሆነ፡፡
ለዚህም የሚከተሉትን …አንድኛ መገናኛ ብዙኀኑ በህዝቡ ዘንድ ታማኝ መሆን መቻል አለባቸው፡፡ ይሄውም መገናኛ ብዙኀን ከመንግሥት አሽቃባጭነት ተላቀው ለማንም ሳይወግኑ ነጻና ሚዛናዊ መረጃ እንዲናገሩ መንግሥት ከጫንቃቸው ላይ መውረደ አለበት፡፡ ከቦርድ አባልነት ጀምሮ እስከ አመራርነት ድረስ ያለውን ቦታ መልቀቅ አለበት፡፡ ሚዛናዊና ቆምጣጭ ትችቶችን መገናኛ ብዙኀን በነጻነት እንዲሠሩ መንግሥት አኩራፊነቱን ትቶ ከሚዲያዎች ጋር ፊት ለፊት መነጋገር አለበት፡፡
በእርግጥ ስሜት እንጅ አሳብ የሌላቸው አንዳንድ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን መንግሥት የያዘውን ጥብቅ ቁጥጥር ወደ አልሆነ አካሄድ እንዲሄድና የግልና የፓርቲ ደጋፊዎች በመሆናቸው ዘርፉን እንዲጉዳ አድርጎታል፡፡ መረጃ ለመንግሥት ብቻ አይደልም ውሳኔ ለመወሰን የሚያስፈልገው ህዝቡም ነው፡፡ ሄዶ ሄዶ አጠፋቸው፡፡ እናም የብሮድካስት ባለሥልጣን አካሄድ መንግሥትንም መገናኛ ብዙኀኑን ጠልፎ ከመጣል ውጭ መንግሥት አሁን ከገጠመው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ መውጣት አይችልም፡፡
በእርግጥ ስሜት እንጅ አሳብ የሌላቸው አንዳንድ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን መንግሥት የያዘውን ጥብቅ ቁጥጥር ወደ አልሆነ አካሄድ እንዲሄድና የግልና የፓርቲ ደጋፊዎች በመሆናቸው ዘርፉን እንዲጉዳ አድርጎታል፡፡ መረጃ ለመንግሥት ብቻ አይደልም ውሳኔ ለመወሰን የሚያስፈልገው ህዝቡም ነው፡፡ ሄዶ ሄዶ አጠፋቸው፡፡ እናም የብሮድካስት ባለሥልጣን አካሄድ መንግሥትንም መገናኛ ብዙኀኑን ጠልፎ ከመጣል ውጭ መንግሥት አሁን ከገጠመው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ መውጣት አይችልም፡፡
በእርግጥ ስሜት እንጅ አሳብ የሌላቸው አንዳንድ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን መንግሥት የያዘውን ጥብቅ ቁጥጥር ወደ አልሆነ አካሄድ እንዲሄድና የግልና የፓርቲ ደጋፊዎች በመሆናቸው ዘርፉን እንዲጉዳ አድርጎታል፡፡ መረጃ ለመንግሥት ብቻ አይደልም ውሳኔ ለመወሰን የሚያስፈልገው ህዝቡም ነው፡፡ ሄዶ ሄዶ አጠፋቸው፡፡ እናም የብሮድካስት ባለሥልጣን አካሄድ መንግሥትንም መገናኛ ብዙኀኑን ጠልፎ ከመጣል ውጭ መንግሥት አሁን ከገጠመው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ መውጣት አይችልም፡፡