January 30, 2018
በአማራ ክልል 598 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለፀ። ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፀው፥ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው በቅርቡ ከእስር ይፈታሉ።
ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች 224 ከሰሜን ጎንደር ዞን፣ 176 ከአዊ ዞን፣ 107 ከምዕራብ ጎጃም ዞን፣ 41 ከምስራቅ ጎጃም ዞን፣ 17 ከደቡብ ወሎ ዞን፣ 14 ከኦሮሞ ልዩ ዞን፣ 13 ከደቡብ ጎንደር ዞን፣ 2 ከዋግ ኽምራ ዞን እና 1 ከሰሜን ሸዋ ዞን መሆናቸውን ነው ያስታወቀው።
በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ አራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ ላይ “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል።” መባሉ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ 528 ተጠርጣሪዎች ክስ በመጀመሪያ ዙር መቋረጡን መግለፁ ይታወቃል። ከተጠርጣሪዎቹ መካከልም 115ቱ በፌደራል ደረጃ ሲሆኑ፥ ሌሎቹ 413 ደግሞ ከደቡብ ክልል የቀረቡ ናቸው። በተመሳሳይ ኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባለፈው ሳምንት ለ2 ሺህ 345 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል።
ኢዜአ