January 30, 2018
ሚዲያ ላይ አስተያየት ሰጥተው ያውቁ ይሆናል! ጋዜጣ በተናገሩ በሳምንት፣ በሁለተኛው ቀን፣ ወይም ከሰዓታት በኋላ ሊያወጣው ይችላል። ቆርጦት፣ አዛብቶት፣ ለሌላ ጊዜ አስተላልፎት ይሆናል። ማህበራዊ ሚዲያ ማተሚያ ቤት ሳያስፈልግ፣ አዟሪ፣ አከፋፋይ ሳያስፈልግ ሀሳብዎትን በፈለጉት መንገድ ለማድረስ ፅፈው “post” እንዲያደርጉ እድል አመቻችቷል። ሬዲዮና ቴሌቪዥን ላይ ተመሳሳይ ነው። ጊዜ ይጠብቃሉ፣ ተቆርጦ ይሆናል፣ አልተላለፈ ይሆናል፣ ካለፈም አለፈ ነው።
ማህበራዊ ሚዲያ ጠዋት የፃፉትን ለማታ አስጥቶ ያቆይልዎታል፣ ሬድዮ ላይ ካለፈ አለፈ ነው፣ ቴሌቪዥን ላይ ካለፈ አለፈ ነው፣ እንዲያውም አሁን ጋዜጣውም፣ ሬዲዮውም ቴሌቪዥኑም ፌስቡክ ላይ መጥቶ ይጠብቀናል፣ እነሱንም ማቆያ ሆኗል! መልዕክትዎትን እንዲያነብ ለሚፈልግ “tag” ያደርጉታል። ይህ በቴሌቪዥን አይቻልም፣ በሬዲዮ አይቻልም፣ በጋዜጣ አይቻልም። ግን ምን ያህል ተጠቅመንበታል?
በማህበራዊ ሚዲያ የሌሎቹን ግብረ መልስ ወዲያውኑ ያገኛሉ፣ እንደጋዜጣ፣ እንደሬዲዮ፣ እንደ ቴሌቪዥን ሳይቸገሩ ወዲያውኑ ማስተካከል፣ መጨመር፣ መቀነስ……ይችላሉ። ፎቶ፣ ቪዲዮ፣ ሀሳብ፣… …ለመቀነስ፣ ለመጨመር እድል አለዎት! ግን ምን ያህል ተጠቅመንበታል?
ፌስ ቡክ እንደጋዜጣ የገፅ ውስንነት፣ እንደ ራዲዮና ቴሌቪዥን የሰዓት ገደብ የለውም። ያለን መረጃ፣ አቅምና ብርታት እንጅ ፌስ ቡክ ገደብ አልጣለም። ሀሳብን በነፃነት ለመግለፅ የፌስቡክን ያህል እድል የሰጠን መድረክ ያለ አይመስልም! ግን ምን ያህል ለዓላማ ተጠቅመንበታል?
ችግሮቻችን
…………………………
ሌሎች ሚዲያዎች ማህበራዊ ሚዲያ ያጎናፀፈንን እድል ሳይኖራቸው እንኳ ተወዳጅ የሆኑት ሀሳቡን የሚያቀርቡት በዕቅድ፣ ለጉዳዩ የሚመጥን ሰው ተመድቦላቸው፣ የማይደጋገሙ ሀሳቦች ስለሚቀርቡ ነው። ብዙ እድል የሰጠንን ፌስ ቡክ ግን ተነባቢና ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተጠቀምንበት አይደለም። ለዚህም ትልቁ ችግር ፌስቡክ የትርፍ ጊዜ እንጅ ሌሎች ሚዲያዎች ላይ እንደሚደረገው በእቅድ፣ በሙሉ ሰዓት የሚሰሩ ሰዎች ስላልተቀመጡለት ነው። በእርግጥ በስልጣን ላይ ያሉት በርካታ በጀት መድበው ፌስቡክን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ያስተምራሉ፣ ጠቀም ያለ ደመወዝ ከፍለው ያስፅፉበታል፣ በቀን 24 የሚከታተለው አካል አስቀምጠዋል።
በእርግጥም ከገዥዎች ይልቅ ጋዜጣ ከሚዘጋበት፣ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ላይ የተለየ ሀሳብ እንዳያቀርብ ለሚከለከለው ተቃዋሚና ተች በማህበራዊ ሚዲያ ትልቅ መድረክ ነበር። ሆኖም በሚገባ መንገድ ሊጠቀምበት አልቻለም። በስልጣን ላይ ያሉትን ማጋለጥ የሚያስችል ጥሬ መረጃ ያላቸው ለዕለት ጉርሳቸው የሚሰሯትን ስራ ትተው ፌስቡክን ስራዬ ብለው አይዙትም። አንዳንዴ ፌስቡክ የተለየ ትንተና፣ ብቃት የማይጠይቅበት ጊዜ አለ። ብዙ ትንተና ሳያስፈልገው አንድ በፖሊስ የሚደበደብን ዜጋ፣ የተገደለ፣ የተበደለ፣……ሰው ፎቶ ብቻ መለጠፍ በቂ ነው። ይህን የሚተነትን ሌላ አካል ይኖራል! ግን ይህን አንድ ፎቶ ለመለጠፍ ፎቶ የሚያነሳ ሞባይል እንኳ ያስፈልጋል፣ ፎቶው ቢነሳ እንኳ ስራዬ ነው፣ ግዴታዬ ነው ብሎ የሚለጥፍ፣ ወይም ለሌላ የሚልክ ሰው ያስፈልጋል። ይህንም ካደረገ ለዚህ ስራው እውቅና ያስፈልጋል። ይህን ጉዳይ እያየ “ሌላ ስራ አለኝ” ብሎ እንዳያልፍ ዋና ስራው ሊሆን ይገናዋል።
ስልጣን ላይ ያሉት ቢሮ ከፍተው፣ ስልጠና እና ደሞዝ ከፍተው እየሰሩበት ነው። እነሱ ሲሰሩ የሚሰሩት ፌስቡክ ላይ እየቀረበ ያለውን መረጃ ማፈንን ጭምር ነው። ተቃዋሚው ደግሞ በግብታዊነት፣ በነፃና በአጋጣሚ የሚለጠፈውን መረጃ ብቻ እየተጠቀመ ቀጥሏል።
………………………
አፈና በበዛባቸው በተለይም በየ ክፍለ ሀገሩ በትርፍ ጊዜያቸው መረጃ የሚያስተላልፉ፣ ወይንም ሊያስተላልፉ የሚችሉ ግለሰቦች አሉ። ይኖራሉ። እነዚህ ግለሰቦች ለሚያስተላልፉት መረጃ ግዴታ አልተጣለባቸውም። ስራቸው እንዲያደርጉት ኃላፊነት አልተጣለባቸውም። በመምህርነት፣ በአስጎብኝነት፣ በግብርና ሰራተኝነት፣… … የተሰማሩትን በቀደመ ስራቸው የሚከፈላቸውን ደሞዝ በመክፈል መረጃ ማሰራጨትን ስራቸው እንዲያደርጉ አማራጭ የሰጣቸው አካል የለም። መረጃ የማሰራጨት አቅም እያላቸው ስራ አጥተው ተቀምጠው መረጃ እያሰራጩ ኑሯቸውን እንዲገፉ፣ በደልም እንዲያጋልጡ፣ ምን አልባትም ከኢንተርኔትና ትራንስፖርት ላያልፍ በሚችል ክፍያ ህዝብና ሀገርን እንዲያገለግሉ አላደረግናቸውም።
በአንድ በኩል መረጃ እያለው ፌስቡክ ላይ ለጥፎ ለመውጣት፣ ወደተለያየ ቦታ ደውሎ መረጃ ለማግኘት፣ ተንቀሳቅሶ መረጃውን ለማጣራት የገንዘብ አቅም የሌለው አለ። በተጨማሪም ፍላጎቱ እያለው የዕለት ጉርሱን ወደሚያገኝበት ስራ ሲያቀና መረጃውን ወደጎን ይለዋል። ለመረጃው ቅድሚያ ቢሰጥ ስራና ደሞዙን ያጣል።
በሌላ በኩል ግን መረጃውን በቅርብ የማያገኝ ነገር ግን መረጃው ያላቸው እንዲያወጡት መክፈል የሚችል የህብረሰብ ክፍል አለ። በዚህ በኩል ዳያስፖራው፣ ነጋዴው፣ ከኪስ ገንዘብ ያለፈ ያለው ምሁርና ሌላም ኃላፊነት የሚሰማው የህብረተሰብ ክፍል አለ።
ከዚህ የህብረተሰብ ክፍል መካከል ለምሳሌ ዳያስፖራው በየ ክፍለ ሀገሩ የሚመጡት ዜናዎችን ደግሞ ከማጋራት፣ በመረጃዎቹ ከመበሳጨት፣ ከማዘን ያለፈ መሰል መረጃዎች በስፋትና በተጠና መልኩ እንዲወጡ አቅሙን አይጠቀምም። ሀገር ውስጥ የሚኖረው ነጋዴና ሌላ አቅም ያለው አካል የበደሉ ገፈት ቀማሽ ሆኖ መረጃ ማውጣት ሌላ ጦስ ያስከትልብኛል እያለ፣ ነገር ግን የተበጣጠሱት መረጃዎች ሲወጡ በሹክሹክታም ቢሆን ደስታውን ከመግለፅ ባለፈ መሰል መረጃዎች በስፋት እንዲወጡ በተለያየ ስራ የተሰማሩ መረጃ በማስተላለፍ ላይ ኃላፊነት እንዲወስዱ ገንዘብ አያወጣም። ወይንም ስራ የሌላቸው በደሉን፣ የህዝብን በደል እንዲናገሩለት በ30 ደቂቃ ውስጥ እንደዋዛ አልፎ ሂያጁን የሚጋብዝበትን ለአንድ ወር እንኳ ለእነዚህ መረጃ መጋቢዎች አይመድብም።
አቅም እያለው የኢንተርኔት፣ የስልክ፣ የትራንስፖርት፣ ከዛም ሲያልፍ በኃላፊነት ለመስራት የስራ ዋስትና ባለማግኘቱ የህዝብን በደል ማሰማትና ማጋለጥ አልቻለም። የገንዘብ አቅም ኖሮት፣ መረጃ እንዲወጣ፣ በደል እንዲጋለጥ እየፈለገ፣ ይህን ስራ ለመስራት የሚከፍለው ዋጋም በዋዛ የሚያወጣው ሆኖ እያለ ይህን ኃላፊነት ያልተወጣ አካልም አለ። ሁለት አቅም ያላቸው አካላት አልተገባኙም።
ምን ቢደረግ ይሻላል?
……………
የህዝብን ብሶትና በደል የሚያሰሙ ጠንካራ ተቋማት የሉም። እስከዚያው ይህን ማድረግ የሚቻለው በተበታተነ መንገድ፣ በግለብ፣ ወይንም በሚቀራረቡ አካላት ሰብሰብ ብለው በሚያደርጉት አስተዋፅኦ መሰረት ነው። በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ ከተሞች መረጃ ለማሰራጨት አቅምና ድፍረቱ ያላቸው ወጣቶች አሉ። እነዚህን ወጣቶች ሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖር በገንዘብ ማገዝ የሚችል ግለሰብ ያውቃቸዋል። መፍትሄው እነዚህን ማብቃት ነው፣ እነዚህን መደገፍ ነው፣ መረጃ ማሰራጨት የሚችል መምህር አስተማሪነቱም ትቶ መረጃ ማሰራጨት እንዲችል የሚያኖረውን ወጭውን መሸፈን ነው። አንድ ነጋዴ፣ አንድ ዲያስፖራ ወይንም ሌላ አካል የሚያውቀው (ጎረቤት፣ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያውቀው ግለሰብ…) በማገዝ በሚታወቁት የክፍለ ሀገር ከተሞች አንድ አንድ ሰው ማብቃት ቢቻል የህዝብን በደል እጅግ በከፍተኛ ድምፅ ማሰማት ይቻላል።
ለምሳሌ ያህል ቆቦ፣ ወልዲያና ደሴ መሰል ስራ የሚሰሩ ግለሰቦች ቢኖሩ ኑሮ በተበጣጠሰ መንገድ ከምንሰማቸው በላይ በቪዲዮ፣ በፎቶና በሌላ መረጃዎችን ማግኘት በቻልን ነበር። እነዚህ ቦታዎች ላይ ኢንተርኔት ባይኖርም ኃላፊነቱን ያደረገ ግለሰብ አዲስ አበባ ድረስ እንኳ መጥቶ መረጃዎችን መስጠት ይችላል። አሁን እየተሰራ ያለው በበጎ ፈቃደኝነት ብቻ ነው። እነዚህ በጎ ፈቃደኞች ለኢንተርኔት፣ ለትራንስፖርት ሲያጡ፣ የራሳቸው ስራ ሲበዛ፣ ወይም ከመንግስት ስራቸው እባረራለሁ የሚል ስጋት ሲገባቸው መረጃዎቹ ይቆማሉ። በኦሮሚያና በአማራ ክልል ኢንተርኔት በመዘጋቱ በበጎ ፈቃደኝነት መረጃ የሚሰጥ ሰው ግዴታዬ ነው ብሎ፣ ዋና ስራውን ትቶ ኢንተርኔት ያለበት አዲስ አበባ መጥቶ መረጃውን ሊያጋራ አይችልም። ወልዲያ፣ አምቦ፣ ጎንደር፣ ነቀምት፣ ባህርዳር፣ አዳማ፣ ቡታ ጅራ፣ ድሬዳዋ፣ አሶሳ……በየ ክልሉ ከተሞች በትርፍ ጊዜያቸው መረጃ የሚያቀብሉ ስንት አቅምና ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ይኖራሉ? 20? 10? 5? እነዚህ ግለሰቦች በትርፍ ጊዜ፣ በበጎ ፈቃደኝነት የሚለጥፉትና የሚልኩት ለእኛ ዋነኛ መረጃ ነው! ስራዬ ብለው ቢይዙት ምን ያህል አስተዋፅኦ ያደርጉ ነበር?
መረጃዎቹ እንዳይቆሙ፣ ማህበራዊ ሚዲያ የሰጠንን ነፃነት ለመጠቀም ኃላፊነታቸውን ልንጋራቸው፣ ግዴታ ልንጥልባቸው ይገባል። ይህ ስናደርግ በራሳችን ተነሽነት፣ በጓደኛ፣ በዘመድ ብርታትና ታማኝነቱን የምናውቀውን፣ ይጠቅማል፣ መረጃ ይሰጣል ብለን የምናምነውንና የምናምንነትን በማብቃትና በመደገፍ በግል ወይንም የምንግባባ ሰብሰብ ብለን የምናደርገው እንጅ የተለየ ተቋማዊ አሰራር አያስፈልግም!