ጌታቸው ሽፈራው

~ ፋና በደረሰው አጣዳፊ መረጃ መሰረት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከሳሽ ያሉትን ላይ ፍርድ ቤት ያላስተላለፈው 6 ወር ተጨማሪ ቅጣት ጥሎባቸዋል። ቀሪዎቹን ደግሞ አንድ አመት ከ6ወር ቀጥቷቸዋል! ፋና፣ እያንዳንዳቸው አንድ አመት እና 6ወር ቅጣት ተበይኖባቸዋል ይላል። እኔ የማውቀው ጉርሜሳ አያኖ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላና በቀለ ገርባ የተፈረደባቸው ሁለት ጊዜ6 ወር፣ በአጠቃላይ አንድ አመት መሆኑን ነው። ምን አልባት በቀጣይ ቀጠሮም አይነሱም ነበር ብሎ ካልሆነ!

~ ቀሪዎቹ 8ኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ፣ 11ኛ ተከሳሽ በየነ ሩዳ፣ 12ኛ ተከሳሽ ተስፋየ ሊበንና 14ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ (ይፈታል ተብሎ አልተጠቀሰም) እስካሁን “በችሎት መድፈር”ም አልተፈረደባቸውም።

~በመሆኑም ክሱ ከተነሳ ጉዳያቸው በይቅርታ ቦርድ ይታያል የተባለው የ1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያኖ፣ 2ኛ ተከሳሽ ደጀኔ ጣፋ፣ 3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ቡላላ እና 4ኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ መሆን አለበት።

~ጌቱ ጋሩማ የተባለው ጌቱ ግርማ መሆን አለበት። ፋና ሌላ ጊዜ በዝርዝር ይዘግባል፣ ዛሬ ውሳኔውም በአስቸኳይ ተነግሮ፣ ዜናውም በአስቸኳይ ተሰራ መሰለኝ። ስንትና ስንት የመንግስት ምንጭ ያለው ፋና፣ ዳኞች ከማንበባቸው በፊት ክሱን ዜና የሚሰራው ፋና የ8ቱን ተከሳሾች ስም እንኳ አጠቃልሎ አልዘገበም። ያው አድማው አቅል ነስቷቸው ይሆናል!

 

______

የፋና ዘገባ እንደወረደ ይኸው:-

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት በተከታታይ በሁከትና ብጥብጥ፣ በሽብር እንዲሁም በሀይማኖት አክራሪነት ክስ የተመሰረተባቸው እና ቅጣት የተወሰነባቸው ግለሰቦች ላይ ክስ የማቋረጥ እና ይቅርታ የማድረግ ተግባር ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፀው፥ ይህንን ተከታታይነት በመቀጠል በሀገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ ግለሰቦች ክስ እንዲቋረጥ መንግስት ወስኗል።

በዚህም መሰረት አቶ በቀለ ገርባ፣ ጉርሜሳ አያና፣ አዲሱ ቡላላ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ ጌቱ ጋሩማ፣ ተስፋዬ ሊበን እና በየነ ሩዳ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተወስኗል።

ነገር ግን ተጠርጣሪዎቹ ችሎት ፊት ቀርበው ጉዳያቸውን በሚከታተሉበት ጊዜ ባሳይዋቸው ችሎት የመድፈር እና ህግ የመጣስ ተግባራት ምክንያት ጉዳዩን የሚመለከተው ፍርድ ቤት በእያንዳንዳቸው የአንድ ዓመት እና የስድስት ወር ቅጣት መበየኑ ይታወቃል።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ በዚህ ምክንያት ጉዳያቸው በፌደራል የይቅርታ ቦርድ እንዲታይ የተወሰነ መሆኑን እና ጉዳዩም ለሀገሪቱ ርእሰ ብሄር ቀርቦ ሲፀድቅ ወደ ህብረተሰቡ እንደሚቀላቀሉ ነው ያስታወቀው።