የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር በዱከም የሚገኘውን የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን እንዲጎበኙ የተያዘላቸው ፕሮግራም፣ ከሰኞ የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያና በሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች እየተካሄደ በሚገኘው ተቃውሞና አድማ ሳቢያ መሰረዙ ታወቀ፡፡
ሚስተር ቶኒ ብሌር እሑድ የካቲት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ በመግባት በማግሥቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ተነጋግረው ረፋዱን ወደ ዱከም በማቅናት፣ በቻይና መንግሥት ኩባንያ አማካይነት የተገነባውን የኢንዱስትሪ ዞን ለመጎብኘት የተያዘላቸው ዕቅድ ተሰርዟል፡፡ ለጉብኝቱ መሰረዝ ምክንያት የሆነው በኦሮሚያ በቀጠለው አድማና ተቃውሞ ሳቢያ መንገዶች በመዘጋታቸው ጭምር እንደሆነ ታውቋል፡፡ ወደ ዱከም ከሚስተር ቶኒ ብሌር ጋር አብረው የሚያቀኑ የጋዜጠኞች ቡድን አባላትም እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣናቸውን ካስረከቡ በኋላ ቶኒ ብሌር ፋውንዴሽን የሚባል ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከመመሥረታቸውም በላይ፣ አፍሪካ ገቨርናንስ ኢኒሺዬቲቭ የሚባልና የአፍሪካ ባለሥልጣናትን በአመራር ረገድ የሚያማክር ተቋም በመመሥረት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ በተጓዳኝ ቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ፎር ግሎባል ቼንጅ በሚል ስያሜ የሚጠራ ኩባንያ በመመሥረት በሰው ኃይል አስተዳደር፣ በኩባንያ አመራርና በሌሎችም መስኮች የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጥ አማካሪ ድርጅት እየመሩ ይገኛሉ፡፡
ይህ ተቋም ላለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና አመራር በኩል እያማከረና ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ወኪል ጽሕፈት ቤቱን በመክፈትም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ከኩባንያው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መተግበር የጀመረውና ዴሊቨሮሎጂ የተሰኘውን የአስተዳደርና የሥራ አመራር ፍልስፍና በማስረፅም፣ የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ሚና እንዳለው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ዴሊቨሪ ክፍል ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ፣ በቶኒ ብሌር ጉብኝት ወቅት በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡
የቶኒ ብሌር ጉብኝት በኢትዮጵያ የተገነቡና ወደፊትም እንደሚገነቡ በሚጠበቁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ መረጃዎች ጠቁመው፣ በዱከም ሊያደርጉት የነበረውን የቻይኖቹ የኢንዱስትሪ ዞን ጉብኝት ግን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ሪፖርተር
