ለፍትሕና ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል ይቀጥላል!

የኢትዮጵያ ህዝብ የግራ ትግል ሸንጎ በነአቶ በቀለ ገርባ፤ አንዱአለም አራጌ፤ እስክንድር ነጋና በሌሎችም እስረኞች መፈታት የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ ለመግለጽ እንወዳለን። ለቤተሰቦቻቸው፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ ያለን እንላለን።

አሁን የምናየው ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ ለአመታት ያደረገው ትግል ያስገኘው ተጨባጭ ውጤት ነው። ። ይህ ውጤት የተገኘው ከፍተኛ መስዋእትነት የተከፈለበትን ፈታኝ ትግል በጽናት በማካሄድ እንደሆነ ስናወሳ፤ አሁን ከእስር የተለቀቁት ታጋዮች ያሳለፉት ሰቆቃ ለዚሁ ትግል የተከፈለ ዋጋ መሆኑን እንረዳለን። ከዚህም ባሻገር ለዚህ ድል እውን መሆን ህይወታቸውን ለሰጡ፣ ለታሰሩ፣ ለተሰደዱና ለተሰቃዩ ታጋዮችና ቤተሰቦቻቸው ሁሉ የሚሰማንን ዘላላማዊ ክብር መግለጽ እንወዳለን።

እነ አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ሲለቀቁ እንደተናገሩት፤ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች በመላ አገሪቱ በየእስር ቤቱ እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ሌሎች ደግሞ መዳረሻቸው እንኳን ያልታወቀ በርካታ ዜጎች እንዳሉ አገር ያውቃል። የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሐት በሚዘወረው መንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ በይፋ መግለጽ ከጀመረ ውሎ አድሯል። መንግስቱም ይህንኑ አመለካከት የሚያጠናክሩ ተግባራትን በየእለቱ ስለሚፈጽም ግፍና በደል የበዛበት ህዝብ እምቢ አልገዛም ብሎ ተነስቷል።፡ ይህ መንግስት እስረኛ እፈታለሁ ብሎ የተናገረውን አልፈጸመም፤ ሶስትና አራት እስረኛ በየሳምንቱ እየፈታ በንጹሃን ሕይወት የፖለቲካ ቁማር መጫወቱን ቀጥሏል፤ አገራዊ መግባባት ብሎ ሳይጨርስ በማግስቱ በሰላማዊ ህዝብ ላይ ይተኩሳል፤ በመሆኑም ትግላችን ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እስከሚፈቱ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

ከዚህ በተጨማሪም በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ህዝባችን የሚሻው የፖለቲካ ኢስረኞችን መፈታት ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ የሆኑት ዴሞክራሲአዊና ሰብአዊ መብቶች ሳይሸራረፉ መከበርንም ጭምር ነው፤ የህግ የበላይነት ተግባረዊ መሆንን ነው። ህዝብ የሚፈልገው መሪወቹን መርጦ መሾም፤ ሳይፈልጋቸው ደግሞ ማሰወገድን ነው።አምባገነንንት እንያዲያከትም፣ አድልዎ፤ ጎጠኝነት፤ ከፋፋይነትና ሙሰኝነት እንዲያበቃ ነው። በአጠቃላይ ብሄራዊ ኩራቱ እንዲታደስ ነው።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን የምትገኘው መሰረታዊ ችግሮቻችን እየተወሳሰቡና እየቀጠሉ እንዲሄዱ በሚያደርግ የአገዛዝ ስርአት ስር ነው።

የአገራችን ችግሮች እጅግ የተመሰቃቀሉ ናቸው፤ በጊዜ ካልተፈቱም ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉ። እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውንና ሌሎችንም ችግሮች ለመፍታት ደግሞ ህዝብ፤ ተቃዋሚ ድርጅቶችና የአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሁሉ አሳታፊ የሆነ ብሄራዊ መግባባትና ሁሉን አቀፍ ሽግግር መኖር በግድ አስፈላጊ ነው። በህወሃት የሚዘወረው ጨቋኝ መንግስት የህዝብ አመኔታ ከማጣቱም ባሻገር፤ በአሁኑ ሰዓት ብቻውን ለውጥ ለማምጣት አቅምና ፍላጎት እያጠረው ነው። የህዝብን ዋይታ በቅጡ ያደመጡ የስርዓቱ ተባባሪዎች ስራአቱን ከድተው ወደ ህዝብ ጎራ መቀላቀል ስለጀመሩ። የኢሕአዴግ መንግስት ‘’ጥልቅ ተሃድሶ” እያለ በህዝብ ላይ ከማፌዝ ይልቅ ከህዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በትክክል እንዲመልስ ማስገደድ ይኖርብናል።

ይህን እውን ለማድረግ ትግላችን መቀጠል አለበት ፤የህዝባችን መብት የሀገራችን ክብር መከበር መሰረቱና ዋስትናው የህዝባችን ትግል ነው። በስርአቱ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ክፍሎች እያሳዩት የሚገኘው አበረታች የለውጥ ፍላጎትም አንድ እርምጃ ወደፊት ሄዶ አገራችንና ህዝባችንን እንዲታደግ ተጨባጭ አስርምጃዎችን ባስቸኳይ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

አገዛዙም የድፍረት እርምጃ ተራምዶ በአገራችን ውስጥ ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለውን ብሄራዊ መግባባት እና ሰላማዊ ሽግግር እውን ለማድረግ የሚያሰችል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ከወዲሁ እናስገነዝባለን።

ትግሉ ይቀጥላል

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ