ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተናገሩ፡፡ የመልቀቂያ ጥያቄውም በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተቀባይነት እንዳገኘ፣ የፓርቲው ጽ/ቤት ከመሸ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ዛሬ በመንግስት መገናኛ ብዙኃን ቀርበው እንደተናገሩት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸውም ሆነ ከኢህአዴግ ሊቀ-መንበርነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቀርበዋል፤ ወይም የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለፓርላማ ማስገባታውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፓርላማውም መልቀቂያቸውን ተቀብሎ እንደሚያሰናብታቸው ተስፋ እንደሚያደርጉ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከፓርላማው በተጨማሪ ለድርጅታቸው ደኢህዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መልቀቂያ እንዳስገቡ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ መልቀቂያው ለፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀርቦ እንደሚጸድቅም ተናግረዋል፡፡ እንደዚሁም ከኢህአዴግ ሊቀ-መንበርነታቸው ለመነሳት ደግሞ ለፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው፣ ኮሚቴው መልቀቂያቸውን እንደተቀበላቸውም ከመሸ ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት መኖሩን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በዚህም የተነሳ ደም መፋሰስ እየተከሰተ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ እንደዚሁም በግጭቶች የተነሳ ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው እየተፈናቀሉ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ከስልጣን ለመልቀቅ ምክንያት የሆናቸው ጉዳይ ‹‹በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት›› መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ቀናት የኢህአዴግ ምክር ቤት የፓርቲውን ሊቀ መንበር እና የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚመርጥም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

BBN News February 15, 2018

https://youtu.be/kh7_7SgAKCM