(ዘ-ሐበሻ) በጎንደር የተለያዩ ከተሞች እንዲሁም በባህርዳር በዛሬው ዕለት የሥራ ማቆም አድማ እየተደረገ ነው:: አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመቃወምና በግፍ የታሰሩ ነጻ ሃሳቢ ዜጎች ከ እስር እንዲለቀቁ የሚጠይቀው ይኸው የሥራ ማቆም አድማን ለማስተጓጎል የሕወሓት ተላላኪዎች እየሰሩ መሆኑም ታውቋል::
በጎንደርና ባህርዳር የሥራ ማቆም አድማው በቀጠለበት በዚህ ሰዓት የአማራ ክልል ቴሌቭዥን ጣቢያ የወልቃይት አማራ ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ዛሬ ከእስር ቤት መውጣቱን ዘግቧል:: እንደ ጣቢያው ዘገባ ከ እርሱ ጋር ክስ የተቋረጠላቸው 10 ሰዎችም አብረው ተፈተዋል::
በባህርዳርና ጎንደር የመከላከያ ሠራዊት ዋና ዋና መንገዶችን እንደተቆጣጠረው የሚገልጹት የዘ-ሐበሻ ምንጮች የህወሓት መንግስት ተላላኪ የሆኑና ከሕዝብ ጎን ያልቆሙ የወረዳ አስተዳዳሪዎች በአድማው ተሳትፋችኋል ያሉ የንግድ ድርጅቶች ላይ ቀይ X በማድረግ እንዲሁም ደብዳቤ በመለጠፍ ንግዶቻቸውን እንዲከፍቱ እያስገደዱ ይገኛሉ:: መኪናዎችን እና ባጃጆችንም ታርጋ እየነቀሉ መሆኑን ገልጸዋል::
ለሕወሓት መንግስት አድረው የባህርዳርና የጎንደር ሕዝብ እያደረገ ያለውን አድማ ለማስተጓጎል የሚሰሩት የወረዳው ባለስልጣናት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ከአካባቢው ወጣቶች የወጣው ማስጠንቀቂያ ይገልጻል:: በአሁኑ ወቅትም ወጣቶቹ አድማውን ለማስተጓጎል የሚሰሩትን የወረዳ ባለስልጣናትን መኖሪያ ቤት አድራሻዎችን እየተለዋወጡ መሆኑም የደረሰን መረጃ አስታውቋል::
ይህ በ እንዲህ እንዳለ በጎንደር ትራንስፖርት ባለመኖሩ የተነሳ ወደ ኤርፕርት የሚሄዱ ሰዎች በመስተጓጎላቸው ከጎንደር የሚደረጉ የሃገር ውስጥ የአውሮፕላን በረራዎችን እንዳስተጓጎለና አየር መንገዱም የበረራ ሰዓት ለመቀየር እንዳስገደደው የዘ-ሐበሻ ምንጮች ዘግበዋል::
በሌላ በኩል ደብረታቦር ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት እንዳለና በአካባቢው ምንም ዓይነት መኪና እንደማያልፍ ምንጮቻችን አስታውቀዋል::


