ወርቅነህ ገበየሁ ወዴት ወዴት?

ኦሕዴድ አራት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን አገደ

ከግራ ወደ ቀኝ የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የኦሕዴድ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ እንዲሁም የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን “ነገዎ” አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን ፍላጎት መኖሩን፣ እሱም ቦታውን እንደሚፈልገው የጎልጉል የመረጃ አቀባዮች ጠቆሙ። ወርቅነህ ቀደም ሲል ከነበረው ሃላፊነት፣ ኦሮሞ አይደለም በሚል የሚቀርብበት ክስ፣ በ1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለተካሄደው ግድያ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው በሚል ስለሚወነጀል ኢህአዴግ ራሱ የበጠሰውን የሕዝብ እምነት ሊቀጥል አይችልም የሚል ስጋት መኖሩንም አመላክተዋል።

ቀደም ሲል በጄኔራል ማዕረግ የፌደራል ፖሊስ አዛዥ የነበረው፣ ከዚያም በጁነዲን ሳዶ እግር ተተክቶ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር የሆነው በኦሮሚያ ማሊያ ለትግራይ የሚጫወተው ወርቅነህ፣ ለውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነትም የታጨው የኦሮሞን ሕዝብ ለማባባበል ነበር። እንደታሰበው ሳይሆን ግን በተሾመ ማግስት የኦሮሞን ሕዝብ ሊወክል እንደማይችልሉ ማስረጃ እየቀረበበት ሲተች ነበር። በወቅቱ አንዱ መስካሪ በዩኒቨርስቲ ፊደል ያስቆጠረው ዶ/ር መረራ ጉዲና ነበሩ። አንዳንዶች የመረራን እስርም ከዚሁ ጋር ያያይዙታል።

ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኦሮሞ ብሄር መሆን እንዳለበት በአብዛኛው እምነት ቢኖረም ህወሃትን የጨነቀውና ያሳሰበው የእነ ለማ መገርሳና አቢይ አህመድ አቋም ነው። ሁለቱም በህወሓት ደህንነት ተቋም ጥርሳቸውን ነቅለው፣አፈር ፈጭተው ያደጉትና ኢህአዴግ የፈጠራቸው የበረሃ ልጆቹ የኦህዴድ መሪዎች ቢሆኑም በሕዝብና በፓርቲያቸው ዘንድ ተቀባይ መሆናቸውም ሌላው በሽታ ነው። በተለይ ስለ ኢትዮጵያዊነት እና ለውጥ የሚሰጡት ዲስኩር የአገሪቱን የፖለቲካ መልከዓምድር እየቀየረው መጥቷል።

በዚህ መመዘኛ፣ በዳግም ውልደት በያዙት አቋም በህወሃት ደጋፊዎች ዘንድ ክፉኛ የሚጠላውን ለማ መገርሣን ወደ ጠቅላዩ ሃላፊነት ማምጣት ዘርፈ ብዙ ችግር ስለሚያስከትል ሌላ የኦሮሞ አማራጭ ሲፈለግ የተገኘው ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን “ነገዎ” ነው።

ሻሸመኔ ያደገው የዛሬው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ይህንኑ በመረዳት ይመስላል አጋጣሚውን በመጠቀም ኦህዴድን በድርጅት፣ ህወሃትን በደም ወክለው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ለመያዝ ዘመቻ የጀመረው። የጎልጉል የመረጃ ሰዎች እንደሚሉት ወርቅነህ ራሱን በማጨት “ረጅም መንገድ” መጓዙን ለቅርብ ወዳጆቹ በሚገባቸው መልኩ አመልክቷል። ዝርዝሩን ወደፊት እንደሚያቀርብላቸው መረጃውን ያቀበሉዋቸው ቃል እንደገቡላቸው ለጎልጉል ተናግረዋል። የዕለት ጉርሱን ለማግኘት በሚሊዮን የሚቆጠር በሚሰቃይባት ኢትዮጵያ፤ ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን “ነገዎ” ከ300 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚሸጠውን ሮሌክስ ሰዓት እያብለጨለጨና አለባበሱን በማሳመር የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ከሆነ ወዲህ ለከፍተኛ ሥልጣን ራሱን እያዘጋጀ እንደሆነ ከመ/ቤቱ አካባቢ የሚያፈተልኩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በለስ ከቀናውም አሁን በሚያደርገው የአሜሪካ ጉብኝት የጌቶቹን ይሁንታ ለማግኘትና “አዲሱ መለስ እኔ ነኝ” በማለት ቡራኬ ለማግኘት
( ) ( )
ደፋ ቀና እንደሚል ከኤምባሲ አካባቢ የመጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በቅርቡ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ከመለስ ሞት በኋላ በዓለምአቀፍ ግንኙነት ላይ የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ቀንሷል” ማለቱንም እርሱ “አዲሱ መለስ” መሆኑን ለመናገር የተጠቀመበት ነው በማለት እንደ አስረጅ የሚጠቅሱ አሉ። ይህ የወርቅነህ እንቅስቃሴ እና የወቅቱ የአገሪቱ ሁኔታ በተለይም “በኦሮሞነት” ካርድ ለመጫወት የሚያካሂደው እንቅስቃሴ ህወሓት ካለው ፍላጎት በላይ ወርቅነህ ለቦታው ራሱን በማጨት ብቸኛ ተወዳዳሪ በማድረግ ራሱን እያነገሠ ነው።

ጎልጉል ባገኘው መረጃ መሠረት ህወሓት አሁን ተገዶም ቢሆን ከፈለፈላቸው ድርጅቶች መካከል ቢያንስ ሕዝብ ሊሰማው የሚችል መሪ መሰየም እንዳለበት በመታመኑ ወርቅነህ ምኞት ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችላል የሚል ግምት አለ። “በአቻ ፓርቲዎች”፣ በራሱ በኦህዴድም በኩል ወርቅነህ ላይታጭ እንደሚችል መረጃ አለ። ይህ ከሆነ ደግሞ ለማ መገርሣ ወደ ፊት ይመጣል።

ለማ መገርሣ እንደ አዲስ የኢትዮጵያዊነት አስተማሪ ሆነው ከመጣ በኋላ ህዝብ ቀና ምላሽ ሰጥቶታል። በዚህ አቋሙ ከቀጠለና ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆነ አስቀድሞ የኢህአዴግም ሊቀመንበር ስለሚሆን ጡንቻው ከህዝብ ድጋፍ ጋር እንዳይፈረጥም በህወሓት በኩል ስጋት አለ። ይሁን እንጂ አሁን ካሉት ውስጥ ከለማ በቀር የተሻለ ሰው ወደፊት ሊመጣ እንደማይችል የሚናገሩ የድርጅት ሰዎች መኖራቸውን የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ በላከው መረጃ ላይ አመልክቷል።

ይህ ካልሆነ ደግሞ አናሳ ቢሆንም አብይ አህመድ ሌላው አማራጭ እንደሚሆኑ መጠነኛ ግምት አለ።

ምንጭ – ጎልጉል