ፋሽስቱና ወራሪው ህወሃት መራሹ ስርዓት በኢትዮጵያ ህዝብ መራር ትግል ወደ ታሪክነት የመቀየሩን የቁልቁለት ጉዞ ከተጠበቀው ፍጥነት በላይ እየሸመጠጠው እንደሚገኝ በደስታ እያየን ነው። ይሁን እንጂ በዚህ እልህ አስጨራሽ የህዝብ ትግል ውስጥና የጭቆና ታሪካችን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እየተመዘገቡ ከሚገኙት ደማቅ የህዝብ ድሎች ጋር በተያያዘ ከሚደረጉ ፈንጠዝያዎች ባሻገር በህልቆ መሳፍርት ንጹሃን ወገኖቻችን ክቡር መስዋዕትነትና ተጋድሎ የተጎናጸፍናቸውን ጣፋጭ ድሎች እያስጠበቅንና እያፀናን፣ በጥንቃቄና በማስተዋል ወደፊት መገስገስ ሲኖርብን፤ በተጓዳኝም የአምባገነኖችን ርዝራዦች በማጽዳትና መርዞቻቸውን በማርከስ ሊሆን ይገባል።

ምክንያቱም ከጅምሩ የኢትዮጵያንና ህዝቧን አጥፍቶ ለመጥፋት የቆረጠውና ከባንዳዊ ተፈጥሮውና ተልዕኮው ጋር ወደ ታሪክነት ለመቀየር የተዘጋጀው ህወሃት በተደጋጋሚ ከህዝብ የተሰጠውን የሰላም እድልና የእርቅ መንገድ ሊጠቀምበት ባለመፈለጉ ምክንያት ብቻ ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ መራር ቁጣ እያስተናገደ ይገኛል። በዚህም እንደቀደሙት አምባገነን ስርዓቶች ሁሉ ዳግም ታሪክ ሊሆንና  የዚህን ታላቅ ህዝብና ገናና ሃገር የወደፊት እጣፈንታና ህልውና የመወሰን ስልጣን በህዝብ የተነጠቀበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለንና ነው።

ዛሬ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዷለም አራጌ፣ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ፣…ወዘተ ከአስፈሪዋና ከጠባቧ የህወሃት የማሰቃያ ጉሮኖ ወደ ትልቁና ብዙዎቻችን ወዳለንበት እስርቤት በድል አድራጊነት መንፈስና ወኔ ተቀላቅለዋል። እነዚህን ጀግኖችና የህዝብ ልጆች ለዚህ ለማብቃት የተከፈለው መስዋዕትነት እጅግ ውድ ቢሆንም እንኳ የተገኘው ድል ለቀጣዩ መራራና የመጨረሻ ዙር ትግል ተጨማሪ ሃይል ሊሆኑና ለረዥም ጊዜ ተፈጥሮ የነበረውን የአመራር ክፍተት የሚሸፍኑ መሪ ሃይሎችን ያስገኘ በመሆኑ መስዋዕትነቱ የሚያኮራንና ለበለጠ ትግልና ድል የሚያነሳሳን ሆኖ አግኝተነዋል።

ዛሬም የህዝብ ጀግኖችና ቁርጠኛ ልጆች እነ አቶ አታላይ ዛፌ፣ አባ ወ/ኢየሱስ፣ ወጣት ንግስት ይርጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ሌ/ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ … ወዘተ አሁንም ያሉበት ሁኔታ ያልለየ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ንጽሃን ወገኖቻችን በተለያዩ ድብቅ የማሰቃያ ስፍራዎች በተለይም ትግራይ ውስጥ በሚገኙና “ባዶ ስድስት” እየተባሉ በሚጠሩ የህወሃት ጉድጓዶች ውስጥ እየተሰቃዩ የሚገኙ ሲሆን፣ የእነሱ በይፋ ነጻ አለመውጣት ህወሃት ተጨማሪ የህዝብ ቁጣ ለማስተናገድ እንደወደደና የትግሉም ማጠንጠኛና አቅጣጫ በትግራይ ህዝብና መሬት ዙሪያ ለማድረግ እንደሚጥር እንረዳለን። በሌላ በኩል  ደግሞ “ጉድጓዱ” የተማሰውና “ልጡ” የራሰው ህወሃት ዛሬም እንደልማዱ “አፈር ልሶ” ለመነሳት እለት በእለት እየተላላጠ ይገኛል።

ህወሃት በአንድ እጁ “ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት” የሚል ከበሮ ያስደልቃል፣ በሌላው ደግሞ ፍጹም አፋኝና ጸረ-ህዝብ የሆነ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ያውጃል። ይልቁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስም የተሰየመውና የሃገሪቱን መንግስታዊ ስልጣን እንዲቆጣጠር የሚደረገው “ወታደራዊ አገዛዝ” ብቸኛ ተልዕኮ የተቀጣጠለውን የህዝብ ትግል በሃይልና በፍጹም ጭካኔ መጨፍለቅና ሃገሪቱንም ወደ ለየለት ወታደራዊ አገዛዝ ውስጥ ማስገባት ነው። ይሁን እንጂ በዚህም ሂደት ምንግዜም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሆን፣ ተጎጂውና የከፋውን ዋጋ የሚከፍለው ደግሞ ፋሽስቱ ህወሃትና ህወሃትን ተገን አድርጎ ሃገርና ህዝብን በመጨቆንና በመዝረፍ ላይ የተሰማራው ቡድን ብቻ ናቸው።

ስለሆነም ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን አስቀድሞ አቋሙን በግልጽ እንዳስቀመጠው ሁሉ የትግሉ ዋነኛ ግብና መዳረሻ ህወሃት መራሹን ፋሽስት ስርዓት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ በህዝባዊ ሃይል ማስወገድና በምትኩም ህዝባዊ መንግስት ማቋቋም ብቻ ነው። ስለዚህ ህዝባችን የጀመረውን የነፃነት ትግል አጠናክሮ በመቀጠል የህወሃት የቀብር ስነስርዓት ባልተንዛዛና ወጪ ባልበዛበት ሁኔታ ለማጠናቀቅና ቀጣዩን የሃገራችን እጣ ፈንታ ያማረና የተደላደለ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የሚከተሉትን የትግል ግቦችና አቅጣጫዎች ጥቅም ላይ እንዲያውል ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን አበክሮ ይመክራል። ያሳስባል።

 

 

 

የትግል ግቦቻችን፡

1ኛ.  ከእስር መፈታት ያለባት ሃገራችን ኢትዮጵያና 100 ሚሊዮን የሚጠጋው መላው ህዝባችን ነው!

2ኛ. ህወሃት መራሹ መንግስት በሃይል የያዘውን የህዝብ ስልጣን በአስቸኳይ ለህዝብና በህዝብ ለተቋቋመ የአደራ መንግስት እንዲያስረክብ ማስገደድ!

3ኛ. በህዝብ የሚቋቋመው የአደራ መንግስት በመላው ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የውይይትና የምክክር መድረክ በማዘጋጀት ወደ ብሄራዊ እርቅና ሃገራዊ መግባባት የምንሄድበትን መንገድ መጥረግ!

4ኛ. የአደራው መንግስት በሚያዘጋጀው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያለገደብ በሚሳተፍበት ነፃ ህዝባዊ ምርጫ ህዝባዊ መንግስት መመስረት!

 

የትግል አቅጣጫዎቻችን፡

  1. በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ ማንኛቸውንም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች! በተለይም የኢትዮጵያም ህዝብ በማይጎበኛቸው የህወሃት የማሰቃያ ጉድጓዶች ተጥለው ፍዳቸውን እያዩ የሚገኙ ወገኖቻችን ሁኔታ ህዝባችን በንቃትና በአንክሮ እንዲከታተል እናሳስባለን።
  2. አጥፍቶ ጠፊው የህወሃት ቡድን በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚያደርጋቸውን ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ሴራ በንቃት በመከታተል ማንኛውም ሰላማዊ ህዝብ ጉዳት እንዳይደርስበት መጠበቅና ህዝባችን በየአካባቢው እራሱን በማደራጀት ቀዬውን የማረጋጋትና የማስተዳደር ሚናውን በትጋት እንዲወጣ አደራ እንላለን።
  3. በሁሉም አቅጣጫ የተጀመረውና ፍፃሜው ላይ የደረሰው ህዝባዊ ተጋድሎ እጅግ በላቀና በተናበበ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ትግሉ ለወሳኙ ድል እንዲበቃ ጥሪ እናቀርባለን።
  4. እስከ አሁን በተደረገው የህዝብ ትግል ከእስር የተለቀቁ የፖለቲካ መሪዎችና በቀጣይም የሚለቀቁ የህዝብ ልጆች በፍጥነት ወደ ህዝቡ ውስጥ በመግባትና ትግሉን በመቀላቀል የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት መሸፈንና ትግሉን ወደ ላቀ ድል እንዲያሸጋግሩ አደራ እንላለን።
  5. ማንኛውም በህወሃት ጦር ውስጥ በተለያየ ምክንያት እያገለገለ የሚገኝ የህዝብ ልጅ ወደ ህዝብ ባለመተኮስና ህዝብን ባለማሰቃየት የህዝብ አጋርነቱን በተግባር እንዲያረጋግጥ ጥሪ እናቀርባለን።
  6. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምሁር፣ የሃገር ሽማግሌና፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ዛሬ ነገ ሳይሉ ቀጣዩን ወሳኝ የሽግግር ሂደት እንዲተልሙና የአደራው መንግስት የሚመራበትን ሃገራዊ ፍኖተ ካርታ ከወዲሁ እንዲያዘጋጁ በአክብሮት እንጠይቃለን!

 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ድል የህዝብ ነው!

ልሳነ ግፉዓን ድርጅት

የካቲት 12, 2010 ዓ.ም