—————————————-
*የአማራ ሕዝብ ኢትዮጲያ-ኢትዮጲያ ማለት
*የአማራ ሕዝብ ባንዲራውን ማፍቀር
*የአማራ ሕዝብ የኢትዮጲያን የድል ታሪክ ጀግኖችን ማክበርና መኩራት
*የአማራ ሕዝብ እንደዜጋ የኢትዮጲያ የኦርቶዶክስ ኀይማኖትን ማክበር፣ተከታይ መሆን…
እነዚህ ባህላዊ እና ማህበረሰባዊ እሴቶቹ ሊከበሩ እና ሊወደሱ ሲገባ የጎረቤት ፣ የወንድም ጠላት አፈሩለት። ህወሓት የአማራን ሕዝብ መጥላት ብቻ ሳይሆን ከጫካ ጀምሮ ቀምሮ የመጣውን የዘረኛነት ጥላቻን የስልጣን መንበር ከተቆጣጠረበት ዕለት አንስቶ ላለፉት 26 ዓመታት በጭካኔ ተግብሯል።

አማራን ያዋረደ መስሎት የኢትዮጲያን ታሪክና ባለታሪኮች ዘቀዘቀ፣ ሰርዞ-ደልዞ የተዛቡ ታሪኮችን መዝራትን መረጠ። አማራን ጎዳሁ ብሎ የኦርቶዶክስ ኀይማኖትን በካድሬ ቀሳውስትና ዲያቆናት ከመሙላት ባለፈ የህወሓት ፖለቲከኞችና ወታደራዊ አዛዦች የሚዘውሩት ሆነ። የአማራ ለም መሬት ከወሎና ከጎንደር እየተመረጡ ወደ ትግራይ ካርታ እንዲካለሉ ተደረገ። አማራው ከትግሬ ባለፈ ለኦሮሞው፣ ለጋምቤላው፣ ለሶማሌው፣ ለደቡቡ…ለሁሉም ጠላት ተደርጎ ተሰበከ፣ “ነፍጠኛ” የሚል የማጥቂያ ቅጥያ ተለጠፈበት።
አማራን ለመጉዳት የኢትዮጲያ መሬት ለሱዳን ገበሬዎች ተሸልሞ ትላንት ቀና ብለው ኢትዮጲያዊን ለማየት የማይደፍሩት ሱዳኖች ወታደሮቻቸውን ልከው እንዳሻቸው እየገቡ የአማራን ገበሬ እንዲገድሉ ፈቃድ ተሰጣቸው። በሑመራ፣ በጠለምት፣ በቃፍቲያ፣በዳንሻ፡በአብደራፊ…በረኻዎች ስንቶች ደማቸው ፈሰሰ። ይኼ ሁሉ ግፍ ወያኔን አላረካም። አማራ የተባለ ሰው ሁሉ ከየክልሉ እየተገደለ፣ ንብረቱ እየተዘረፈና እየተዋረደ እንዲፈናቀል ህወሓት አቀነባበረ፣ ሎሌዎቹ ፓርቲዎችም ትዕዛዙን ፈጸሙት:: አማራን ህወሓቶቹ እነ በረከት እንዲመሩት ተመደበለት።
በዚህ ሁሉ ሲዖል ውስጥ አማራ ከፈር ቀዳጁ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ጀምሮ መብቱን ለማስከበር በሰለማዊም ሆነ ብረት አንስቶ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ እየተጋደለ ነው። አርበኞች ግንባር አማራው በትጥቅ ትግል ለህልውናው እንዲፋለም አንቀሳቅሶ በርካቶች ለመብታቸው ተሰውተዋል። በዚህ ሁሉ የሞት ሽረት ትግል ሂደት እንደ ወልቃይት-ጠገዴ አማራ አሳሩን ያየ የለም ማለት ይቻላል። አማራነቱን ፍቆ ትግሬ ነኝ እንዲል ሚስቶችን እየነጠቁ የግዳጅ ጋብቻ ከማድረግ እስከ መረሸን የደረሰ ግፍ ለውስን ጊዜያት ሳይሆን ለ26 ዓመታት በየዕለቱ ተፈጽሞባቸዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ወደተለያዩ ሀገራት ለመሰደድ ተገደዋል።
ሆኖም በሞት ውስጥ ለማንነታቸው ሲሉ ከዚያም በላይ እንደ ሰው ለመኖር ሲሉ ለህልውናቸው ለመታገል የቆረጡ እሳት ወልዷቸዋል። እነዚህ ሰዎች የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ናቸው። እነ አቶ አታላይ ዛፌ ፣ አቶ ጌታቸው አዳመ፣ አቶ አለነህ ሻማ፣ አቶ መብራቱ ጌታሁን፣ አቶ አደራጀው ዋኘው…ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ::
የኢትዮጲያዊያን ሕዝባዊ እምቢተኝነት በድንገት ከጊንጪ ተነስቶ መላው ኦሮሚያን ሲያቀጣጥል ምነው አማራው ተኛ ሲባል አመድ ለብሶ የነበረው ረመጥ ገሞራ ሆኖ የፈነዳው በነዚሁ የወልቃይት አማሮች ነበር።
መለስ ዜናዊ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ በሰላማዊ መንገድ በተደራጀና በሰለጠነ ሁኔታ የመብት ጥያቄቻቸውን ቢያቀርቡም እብሪት ያደነደነው ንኩ ስርዓት ምላሹ ንቀትና እያሳደዱ መግደልና ማሰር ሆነ።
ይኽ እርምጃ ተጠናክሮ ህወሓት መብት ጠያቂዎቹን በሽብር ተግባር ላይ የተሰማሩ ብሎ እንደሌባ የክረምት ወርን ጨለማ ጠብቆ ሐምሌ 2008 ዓም ጭምብል የለበሱ ወታደሮቹን ወደ እነ ኮሎኔል ደመቀ ቤት አሰታጥቆ ላከ።
አቶ አታላይን በማሰር የጀመረው ዘመቻ ህወሓት አራት ሰዎችን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ኮሎኔል ደመቀ ቤት ሲደርስ ያልተጠበቀ ዱብ-ዕዳ ጠበቀው። በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ሀገራቸውን አገልግለው እስከ ኮሎኔል ማዕረግ የደረሱት ደመቀ በሌሊት የመጡት የሞት መልክተኞች በሕጉ መሠረት በቀን እንዲመጡ በጥሞና በመንገር ሊመልሷቸው ቢሞክሩም ሕግ አለ በሚባልበት ሀገር የሕግ የበላይ እና አድራጊ-ፈጣሪ እንዲሁም እንደመንግሥት ሳይሆን እንደሽፍታ ሀገርን የሚያስተዳድሩት ታጣቂዎች ተደፈርን በሚል ትዕቢት ኮሎኔል ደመቀ ላይ የኃይል እርምጃ ወሰዱ። በዕለቱ ያልታሰሩት የወልቃይት የአማራ ማንነት ጠያቂ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ አደራጀው ዋኘው ለአሜሪካ ድምፅ ቪኦኤ በሰጡት ቃለምልልስ ታጣቂዎቹ ወደ ደመቀ ቤት 3 ቦምብ መወርወራቸውን ገልጸዋል።
ይኽ ያላስደነገጣቸው ኮለኔሉ የግድያ እርምጃውን ለመከላከል የአጸፋ ምላሽ በመስጠት በጠላትነት ከፈረጃቸው ህወሓት ጋ’ ቤታቸውን ምሽግ አድርገው ለሰዓታት ተታኩሰዋል። 3 የፌደራል ፖሊስ ፀረ ሽብር ግብረኃይል ልዩ ቡድን አባልት ሲገደሉ፣ ሌሎች 5 መቆሰላቸውን አፋኙን ቡድን የላከው መንግሥት በወቅቱ አምኖ ተና’ዟል።
ያቺ የኮሎኔል ደመቀ ጥይት የጫረቸው እሳት ውስጡ በቁጭት ለዓመታት ሲብሰለሰል የቆየውን የጎንደር ሕዝብ አቀጣጠለችው። ተጨማሪ የህወሓት ሠራዊት መጥቶ የጀግናው ቤት ቢከበብም ሕዝቡ በሬሳችን ላይ ተረማምዳችሁ ካልሆነ ይኼ ዐይናችን እያየ አይፈጸምም አለ። ህወሓቶች ተደፈረን ብለው ፊት ቢቧጥጡም ሕልማቸው ወደ ቅዠትነት ሲቀየር ስላዩት በብአዴን ሰዎች በኩል ተደራደረው ደመቀን በሰላማዊ ሁኔታ እጅ እንዲሰጡ በማድረግ ወደ እስርቤት ለማስገባት አሴሩ።ይኽም ተሳካ።
ይሁን እንጂ ለሩብ ክፍለ ዘመን የህወሓት ቀንበር የተጫነበት አማራ እባቡ እንዴት ሊነድፍ እንደሆነ ስሌቱ ቀድሞ ገብቶት ኖሯል ኮለኔሉን አፍኖ ወደ ትግራይ ወይም አዲስ አበባ ለመውሰድ የሚደረገው ሸፍጥ እንዳይፈጸም ሌት ተቀን አንገረብ እስርቤትን ከቦ ማደር ጀመረ።
የአፈናው ኦፕሬሽን ከተካሄደበት ሐምሌ 2008ዓ.ም አምስት ወራት አስቀድሞ የካቲት ወር ውስጥ የትግራይ ክልል የፀጥታና የአስተዳደር ኃላፊው አቶ ሃዱሽ ዘነበ “ይህንን ትርምስ የሚመሩት ኃይሎች ኢሕአዴግን በምርጫም በጦር ሜዳም ሊያሸንፉት ያልቻሉ ኃይሎች ናቸው፡፡ የሌለ የማንነት ጥያቄ እያነሱ እርስ በራሱ እንዲጫረስ፣ ከልማት ጎዳና ለማስወጣት እየሠሩ ይገኛሉ፤ ከሻዕቢያና ከሌሎች ኃይሎችም እነማን እንዳሉ መረዳት ይኖርብናል፡፡ መንግሥት ከዛሬ ጀምሮ ትዕግሥቱ ተሟጥጧል” ሲሉ የደነፉትን ሕዝቡ አልረሳም ነበርና ምንሽሩን ይዞ ውሎና አዳሩን አንገረብ እስርቤት ዙሪያ አደረገ።
ውጪ ያለው ብቻ ሳይሆን በወንጀልም ያለወንጀሉም አንገረብ የታሰረ ዜጋ ኮሎኔሉን እኛ መሐል አድርገን እንጠብቃለን ብለው አምጸው ከለላ መከታ ሆኑ። ከውጪ ያለው ወጣትም በእስርቤቱ ዙሪያ ያለ የሳር ክምር አቃጥሎ ደመቀን ነፃ ሊያወጣ ሞከረ፣ ግርግር ተፈጠረ ብዙ እስረኞች በጠባቂዎች ተገደሉ።
ይህ ሁሉ ሲሆን የህወሓት ነጭ-ለበስ ደኅንነቶች ጎንደር ከተማ እንደ እባብ ሲሳቡ እንደሚውሉ ነዋሪው ጠንቅቆ ገብቶታል። ጀግናቸው ክስ ተመስርቶበት ፍርድቤት በተመላለሰ ቁጥር ከ’ስርቤት እስከ ችሎት፣ ከችሎት እስከ እስርቤት እየተመላለሱ ዐይናቸውን ሳይነቅሉ ጠብቀዋል።
አውሬዎቹ ደመቀን ወደ ማዕከላዊ ቢወስዱ ምን ይከሰት ነበር? “አንት ሽንታም አማራ” እየተባሉ እየተሸናባቸው ግድግዳ ይገፉ ነበር፣ ብልታቸው ላይ ኮዳ ተንጠልጥሎ ተዘቅዝቀው ይገረፉ ነበር፣ እንደ አበበ ካሴ የእጅና የእግር ጥፍር በፒንሳ ይነቀል ነበር:: ይኽን ሰቆቃ የታደገው ጥይቱን ለደረቱ የሰጠው የጎንደር ሕዝብ ነው።መቀመቅ እንዲወርድበት ተፈርዶበት የነበረው አማራው ነው::
ይኽ አጀብና መቆርቆር ለኮሎኔል ደመቀ ኩራት ቢሆንም ከምንም በላይ ተዳፍኖ የቆየውን የአማራ ሕዝብ ለዓመታት የታመቀ በደል እየጋመ ከወልቃይት አልፎ እንደሰደድ ጎንደር፣ጎጃም፣ ወሎ እያለ መላውን አማራን ማንቦግቦጉ ለተገፉትና ለተናቁት መላዕክ አድርጓቸዋል።
*ከዚያች ዕለት ጀምሮ አማራው የተጠላበትን ኢትዮጲያ ዳግም አክብሯል
*ከዚያች ዕለት ጀምሮ አማራው የሚያፈቅራትን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ 💚💛❤ባንዲራን የሚነድ እሳት መሐል አውለብልቧል::
*ከዚያች ዕለት ጀምሮ አማራው ብሔራዊ ጀግናው አፄ ቴዎድሮስን አውስቷል::
*ከዚያች ዕለት ጀምሮ አማራው እንደውርደት የተቆጠረበትን ኀይማኖቱን በባንዲራ አንቆጥቁጦ በድምቀት ለማክበር በቅቷል::
በቃ፣ ግቡ ይኸው ነው? በፍጹም:: ኮሎኔል ደመቀ በተያዙና ሌሎች የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት በታፈኑበት ወቅት “ነገ ከነገ ወዲያ ብንከዳችሁ የአማራ አጥንትና ደም ይውጋን” ብሎ ምኅላ የፈጸመውና ጉልበት ስሞ ቃል የገባው የአማራ ወጣት ላለፉት ሁለት ዓመታት የሚያደርገውን ተጋድሎ ሳያቋርጥ አርበኞቹ እነ ደመቀ ወደ ትግራይና ማዕከላዊ ማሰቃያ ተላልፈው እንዳይሰጡ ከመከላከል ባለፈ እነ ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ታጋይ ሞላ አጃውና ታጋይ ጎቤ መልኬ ተሰውተው ነፃ ሊያወጧቸው የተነሱትን ጀብደኛ ኢትዮጲያዊያንን ነፃ አውጥተዋል። በጨለማ ሊታፈኑ የነበረው እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ የታፈኑት እነ አታላይ ዛፌ የሐሰት ድሪቶ የክስ ወረቀት ተጥሎ በቀን-በብርሃን “ምናለ፣ ጀግናው ምናለ? ሀገሬን ለሰው – ሀገሬን ለሰው…አልሰጥም አለ…!” እየተባለ ነፃ እንደነበሩ በጀግና አቀባበል ነፃ ወጥተዋል::
ይኽ ተጋድሎ ለእኩልነትና ፍትሕ የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል የመጨረሻው መጀመሪያ ነው:: ወልቃይት ወይም አማራ ብቻ ሳይሆን ትግራይም ሆነ መላ ኢትዮጲያ ነፃ እስክትወጣ ይቀጥላል:: ምክንያቱም መስዋዕትነቱ ለበላይነት ሳይሆን ለእኩልነት የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ነው::
ተጋድሎው ይቀጥላል!
Qabsoon itti fufa!
The struggle continues!

