ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቅ ጥያቄያቸውን ካቀረቡበት ማግሥት ጀምሮ እሳቸውን የሚተካቸው ማነው ለሚለው ጥያቄ ብዙዎች ግምቶቻቸውን እየሰነዘሩ ነው። አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በተለያዪ ምክንያቶች ከስልጣን በሚወርድበት ወቅት ስለ ተተኪው ግለሰብ ሕገ መንግሥቱ ምን ይላል በሚል የህግ ምሁሩን አቶ ውብሸት ሙላትን ቢቢሲ ጠይቆት ነበር። ሕገ መንግሥቱንም ጠቅሶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን እንዳለባቸው ውብሸት ይናገራል። የፓርላማ ስርዓትን በሚከተሉ ኃገራት መካከል አሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ መንግሥት የሚመሰርት ሲሆን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማፅደቁን ተግባር ያከናውናል። በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ የግድ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ሊሆኑ እንደሚገባም አቶ ውብሸት አፅንኦት በመስጠት ይናገራል።
ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ በተደጋጋሚ ስማቸው እየተጠቀሰ ከሚገኙት ግለሰቦች መካከል አንዳንዶቹ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሌላ አማራጭ አለ ወይ ለሚለው ጥያቄ የህግ ባለሙያው ሲመልስ “መንግሥት ካልፈረሰ፤ ተጠባባቂ ወይም የሽግግር መንግሥት እስካልተመሰረተ ድረስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ያልሆነ ግለሰብ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሊቀርብ አይችልም ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሆነ ነው።” ይላል። ሌላው የህግ ባለሙያው አማራጭ ብሎ የሚያስቀምጠው የማሟያ ምርጫ ማድረግ ነው።
ድርጅቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ያልሆነ ግለሰብ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን ከተፈለገ ተቃዋሚዎችም ሆነ ሌሎች ግለሰቦች ተወዳድረው ምርጫውን ማሸነፍ የቻለ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን እንደሚችል ውብሸት ይገልፃል። ነገር ግን ይሄ ረዥም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልም ይናገራል። ይህም ሆኖ ሕገ መንግሥቱ ክፍተት እንዳለው የሚናገረው አቶ ውብሸት ይህንን ክፍተቱን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ትምህርት መውሰድ ይገባ እንደነበር ይገልፃል። “እሳቸውም ሲሞቱ ተተኪያቸውን ሕገ መንግሥቱ በግልፅ አላስቀመጠውም” ይላል። ሕገ መንግሥቱ እንደሚያትተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖሩበት ጊዜ ተክተው ይሰራሉ እንዲሁም ተጠሪነታቸውም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። “በማይኖሩበት” ማለት በጊዜያዊነት፣ ለስራ ጉብኝት በሚሄዱበት ወቅት፣ ቢታመሙ፣ እረፍት ላይ ቢሆኑ ማለት እንደሆነና ከስልጣን ቢለቁ፣ ቢባረሩ ወይም ቢሞቱ ማን ሊተካቸው ይችላል ለሚለው ህገ–መንግስቱ በግልፅ ባለመስቀመጡ ችግር እንደፈጠረም ጨምረው ይናገራል።
“በየትኛውም አገር ጠቅላይ ሚኒስትር በሚለቅበት ጊዜ በጣም በአፋጣኝ መተካት አለባቸው፤ በአፋጣኝ ካልተተኩ ስልጣን ይገባናል የሚሉ በርካታ ተቀናቃኝ ሊፈጠር ስለሚችል አገሪቱን አደጋ ላይ ሊጥላት ይችላል ተብሎ ይታሰባል።” ይላል በቀድሞው የነገስታት ስርዓቶች ወራሾችንም ያዘጋጁ እንደነበር የሚናገረው ውብሸት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በኋላ ይህ ክፍተት መሞላት እንደነበረበትም ይናገራል። በቅርብ ጊዜ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አባይ ወልዱ በለቀቁበት ወቅት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የክልሉ ምክር ቤት አባል ባይሆኑም የሟሟያ ወይም ሌላ ሙሉ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የርዕሰ መስተዳድር ስራ እንዲሰሩ ቢያደርጓቸውም ይህ ሁኔታ በፌዴራል መንግሥቱ መድገም ከባድ እንደሆነም ውብሸት ይገልፃል። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ካልሆኑ ተጠሪነት ሊኖረው አይችልም፤ ምክር ቤቱ ሊቆጣጠራቸው አይችልም” የሚለው ውብሸት “ብዙ ምስቅልቅሎችን ያስከትላል” ይላል። በአሜሪካ ጆርጂያ ጉኔት ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ዮሐንስ ገዳሙ በቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆኑ ይችላሉ ለሚለወም ጥያቄም ሲመልሱ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከብአዴን ወይም ከኦህዴድ ውስጥ በአመራር ላይ ያሉ አቶ ደመቀ መኮንን ወይም ዶክተር አቢይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ።
ዶክተር ዮሀንስ ኢህአዴግ እስካሁን እየሰራበት ያለውን አሰራር በማየትም አራቱ ፓርቲዎችም ሆነ መሪዎቻቸው የተለያዩ ቁልፍ የሚባሉ የስልጣን እርከኖችን ተከፋፍለው እንደሚጨብጡ ይናገራሉ። የፓርላማው አፈ–ጉባኤ ከኦህዴድ፣ ፕሬዚዳንቱ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ናቸው የሚሉት ዶክተር ዮሀንስ ከዛ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከኦህዴድ ያደርጋል የሚል ግምት እንደሌላቸው ይናገራሉ። “ይህ ሁኔታ ከተቀየረና ዶክተር አብይ ልዩ የሆነ ዕድል ሊኖራቸው የሚችል ከሆነ አመራሩ ላይ ያለው የስልጣን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ይቀያየራል። “ይላሉ ያለውን ሁኔታ በማየት ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
BBC
