(ሙሉቀን ተስፋው)

በጥላሁን ጉግሳ መልቲ ሚዲያ እየተዘጋጀ በየሳምንቱ የሚቀርበው ‹‹ቤቶች›› ድራማ ብዙ ተመልካችም እንዳለው ይታወቃል፡፡ ብዙዎቻችን ከሚያስተላልፈው መልእክት ይልቅ ስለሚያስቀን ነው የምናየው፡፡

ማዝናናቱን ባንጠላውም በድብቅ እያስተላለፈ ያለው መልእክት ግን ዝም ብዬ እንዳላልፈው አስገድዶኛል፡፡ እስካሁን ድረስ በሁለት መልኩ ዝም ብዬ ቆይቼ ነበር፡፡ አንደኛው በቶሎ ይቋጫል በሚል ስሜት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‹በጎሰኝነት!› ስሜት የጥበብን ነጻነት መጋፋት ይሆናል ብዬ በማሰብ፡፡ መቼም በዘመኑ ‹ፈሊጥ› ስለ አማራ ማውራት ‹ዘረኛ› የሚያስብል ቢሆንም እንዲህ አይነቱን በህዝብ ላይ ማላገጥ ከዚህ በላይ መታገስ አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም፡፡

ቀጥታ ወደ ጉዳዩ ስንገባ ‹የዘሩ›› (ጥላሁን) እና ‹አዛሉ› ሰራተኞች (የቤት ሰራተኞቹም ጥበቃውም ማለት ነው) ሁሉም ከአማራ ሀገር የመጡ ናቸው፡፡ ጥላሁን ሶስቱንም ሰራተኞች ተመልካቹ በአማራ ላይ እንዲይዝለት የፈለገው ምስል (Ethno symbolism) እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ተልኮ የግሉ አሊያም የሌላ ቡድን ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ በምንም ይሁን በምን በአማራ ህዝብ ላይ ግን መጥፎ እውቅናን እየፈጠረ ነው፡፡

ጥላሁን ጉግሳ

መጀመሪያ የዘሩ ጥበቃ እንቅልፍ ወስዶት ሳለ ሌባ ሰርቆ አዲስ አበባ አመጣው፡፡ ይህ ግለሰብ /እከደከ/ አሁንም በጥበቃ ከተቀጠረበት ቤት በእንቅልፉ ይታወቃል፡፡ የትም ቦታ ላይ በየትኛውም ሰዓት ‹ለሽ› ይላል፡፡ ጥላሁን የተደበቀ አላማ ከሌለው በስተቀር እንደዚህ እንቅልፋም የሆነ አማራ እንደሌለ ማንም ሰው ያውቃል፡፡ አማራ እንኳንስ ተኝቶ ሌባ ራሱን ሊሰርቀው ቀርቶ ሀገሩን በንቃትም ሲጠብቅ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ በእኔ እምነት የትኛውም ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን የአለምም ህዝብ ውስጥ እንደ እከደከ አይነት እንቅልፋም አይኖርም- ምናልባትም በቆላ ዝንብ የሚተላለፈው ‹የእንቅልፍ በሽታ› ካልተጠቃ በስተቀር፡፡ በዚያ ላይ የእከደከን የማሰብ (ማንሰላሰል) አቅም እጅግ አናሳ (Low IQ) አድርጎ ቀርጾታል፡፡

ሁለቱን የቤት ሰራተኞችን ስናይ ደግሞ አንዷን ‹ሆዳም› ሌላኛዋን ደግሞ ‹አዋቂ መሳይ ግን መሀይም› አድርጎ ቀረጻቸው፡፡ ትርፌ ያለ ሆዷ የምታወቀው ነገር የለም፡፡ ረዳቷ ደግሞ ሁልጊዜ ‹እኔ ስድስተኛም አይደለሁ ከእውቀቴ አንጻር ስመረምረው…› እያለች የማታውቀውን የምትዘባርቅ ሴት ነች፡፡

ከዚህ ላይ የምንገነዘበው አንደኛ የቤት ሰራተኛ ከአማራ ሀገር ብቻ እንደሚመጣ ነው፡፡ ምንም እንኳ የአዲስ አበባ የቤት ሰራተኞች የሚመጡት ከደሀ የአማራ ቤተሰቦች እንደሆነ ቢታወቅም በህዝቡ ድህነት በጅምላ ማላገጥ ከሰው ቁስል ላይ እንጨት መስደድ ነው፡፡ በሁለቱ ሰራተኞች የአማራን ህዝብ ‹ሆዳም እና አውቃለሁ ባይ መሀይም› የሚል መልእክት ለተመልካቹ ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ አንደኛዋን ሰራተኛ ከምእራብ፣ ከደቡብ፣ ከሰሜን አሊያም ከምስራቅ ኢትዮጵያ ሊያስመጣት ይችል ነበር፡፡

የጥላሁን ጉግሳን ብዙዎቹን ትዕይንቶች (Episodes) ካየንም በአማራ ባህልና እምነት አላግጧል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከባህር ዳር አንድ መስማት የተሳነው ሰው (ጆሮውን የሚያከራክረው) ማሳቂያ (ማሳቀቂያ) አድርጎታል፡፡ አንዳንዴ ሰውየው መካር የለውም እንዴ እላለሁ! የዚህ መስማት የተሳነውን ግለሰብ ተመልካችን ያስገለፍጥልኛል ብሎ ያስብ ካልሆነ በስተቀር ምንም የሚያስተምረው ነገር አላየሁም፡፡ በአማራነት ስም የሚከሰው ሰው ቢያጣ ቢያንስ የአካል ጉዳተኛዎች ማህበር ግን እንዴት ዝም ብሎ እንዳለፈው አላውቅም፡፡

በቤቶች ድራማ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በጠቅላላው ግን ጥላሁን ጉግሳ አማራን ደንቆሮ፣ እንቅልፋም፣ ሆዳም፣ መሀይም… እያለ እየተሳደበ ነው፡፡ አማራ ምንም መልካም የሆነ ምግባር የሌለው ሰው አስመስሎታል፡፡ ይህን የጥላሁንን እኩይ ምግባር ማስቆም ያለብን ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ አንድን ሰው መሳደብ ምንም ላይሆን ይችላል፤ ሁለትም ሶስትም እንዲሁ፡፡ ግን በጅምላ ሚሊዮኖችን መሳደብ ‹ዘር› ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ነው፡፡ አቶ ጥላሁን ወይ የድራማውን ይዘት ማስተካከል አሊያም ማቆም አለበት፡፡