የመጀመሪያው እኔንና ጃዋርን መሰል የማህበራዊ ሚዲያ አሰናሳዮች (ፊታውራሪዎች) የገፋነው በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን የብሄርና ድርጅት ፌዴራሊዝም ተንተርሶ ወያኔ በውስጡ ያለውን እብጠትና ተጠቃሚነት በማሳየት፣ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አባላትና አመራሮቻቸው እንዲቃወሙት ለህሊናቸው ቀጣይና ተስፋ የማይቆርጥ አቤቱታ በማቅረብ ኢህአዴግን ከውስጥ ለለውጥ ማዘጋጀት ወይም ከተቻለ ጦርሰፈሩን ከውስጥ መቆጣጠር ነበር ። በአሁኑ ወቅትም፣ ኢህአዴግ ለሽግግር የሚመች ጠቅላይ ሚኒስትር ሾሞ ራሱን የሽግግሩ አካል እንዲያደርግ እንደ ኦ ኤም ኤን አይነት መድረኮችን ጭምር እየተጠቀመ የሚታገል ነው ።

ሁለተኛው በግንቦት ሰባትና በልሳኑ በእሳት የተራመደው ሁለገብ ትግል ሲሆን፣ ከአመፅ እስከ ፖለቲካል ብለፊንግ ያካተተ የትግል መስመር በማቅረብ ላይ ያለው አማራጭ ደግሞ፣ በአሁን ሰአት ሥርአቱ ሊወድቅ አንድ ሐሙስ ቀርቶታል ስለሆነም የጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስትን አሁኑኑ ማቋቋምን በመፍትሄነት የሚያቀርብ ነው ።

ሶስተኛው አማራጭ ሃሳብ ሆኖ በመቅረብ ላይ ያለው እንደ ፕሮፌሰር አል ማርያም ያሉ ምእራበ ቀመስ ምሁራን በአሜሪካኖች አዋላጅነት ኸርማን ኮኸንንና ያማሞቶን የመሰሉ ዲፕሎማቶች የሸመገሉት የሽግግር መንግስት መመስረት ነው ።

ለእኔ እንደሚገባኝ ፖለቲካ መቼም ሊተገበር የሚቻለው ጥበብ ነው ። እነዚህ ከላይ የቀረቡትን ሦስት አማራጮች በፖለቲካ ዓይን ስንመረምራቸው፣ ወደተግባር ለመለወጥ የትኛው አማራጭ የተሻለ እድል አለው ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው ። ያን ለማድረግም በምድር ላይ ያለውን እውነታ መረዳት የግድ ነው ። በመጨረሻው ብንጀምር፣ አሜሪካኖች ተላላኪ መንግስታቸውን በሌላ የሽግግር መንግስት ለመለወጥ ፈቃዱና አቅሙ አላቸው ወይ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል ። ፈቃዱ ያላቸው መሆኑ አጠራጣሪ ቢሆንም፣ አቅሙ ያላቸው አይመስለኝም። ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነት ቀን እንደሚመጣ በመገመትም ይሁን የርእዮተዓለም ጉዳይ ሆኖበት፣ ማኩረፊያውን ካዘጋጀ ዓመታትን አስቆጥሯል። ቻይና የተባለ ወዳጅ አለው። ተራ ወዳጅ ሳይሆን፣ መሬት ላይ ፈርሾ አብሮት የሚቅም ዓለምአቀፋዊ ወንድም ።ማስገቢያ ገበያ አጥቶ በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር መዋእለ ንዋይ አቅፎ የተቀመጠና፣ ገዢው ፓርቲ እንዳሻው የሚያዝበት ለስላሳ ኮሮጆ (soft money) ያለው ወዳጅ አለው። ኢህአዴግ ማኩረፍ ይችላል፣ ይህንንም ምእራቡ ስለሚያውቅ ብዙ ሊጋፋው አይችልም። በአንፃሩ፣ ቻይና ኢህአዴግን “የአፍሪካ መግቢያ በር” አድርጋ ማየት ከጀመረች ብዙ ክረምቶች አልፈዋል። ስለሆነም የነፕሮፌሰር አልማርያም በምእራቦች አዋላጅነት የሚመሠረት ጊዜያዊ መንግስት ላም አለኝ በሰማይ ነው ።

ሁለተኛው አማራጭ ሆኖ የቀረበው የኢሳቱና ግንቦት ሰባቱ ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት (ጊህመ) ፣ ከ44 ዓመታት በፊት ኢህአፓ ከጠራው ጊህመ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን፣ ይበልጥ የሚያመሳሰለው ግን ተግባራዊ ማድረጊያ ማስፈፀሚያ ዛሬ በእጁ የሌለው መሆኑ ነው ። ከወያኔ አምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የሚያሸጋግር ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት መመስረት ቢቻል እሰየው ነበር ። ግን እንዴት እዚያ ላይ መድረስ ይቻላል? አምስት ሚሊዮን ህዝብ የሚኖሮባት የአዲስአበባ ነዋሪ ለአስር ደቂቃ ሰልፍ እንኳ ፊቱን ፀሐይ ለማስመታት በማይደፍርበት ሃገር ምን ተይዞ ነው ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት የሚጠየቀው። ጊህመ ባይጠላም፣ ገና ጊዜው ያልደረሰ ጥሪ ይመስለኛል። ይህ ጥሪ የሚያስፈልግበት ጊዜ በጣም በቅርቡ ይመጣ ይሆናል ። ምናልባት ኢህአዴግ የለውጡ አካል ለመሆን እምቢተኛ ሆኖና በሽመልና ድለላ ተማምኖ ለመቀጠል ከወሰነ በኋላ፣ የአድአና ጎጃም ጤፍ ወደ አዲስ አበባ መግባት ሲከለከል፣ የማረቆ በርበሬ ላይ የገበያ እቀባ ሲደረግ፣ ያወጀው የአስቸኳይ አዋጁ የሚያሳርፍበት የኢኮኖሚ መዳከም አላላውስ ሲለውና፣ መራብ የሰለቸው የሸገር ሰው “አሁንስ በቃ” ያለ እለት ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት አሁኑኑ ብለን አብረን መዝመት የምንችል ይመስለኛል። ዛሬ እዚያ ቦታ ገና አልደረስንም።

ሁለቱን አማራጮች ውድቅ ካደረግኩ የቀረው የመጀመሪያው ይሆናል። የሶሻል ሚዲያ ፊታውራሪዎች የምንሞግተው አማራጭ ። ኢህአዴግ ውስጥ የገፋነው የውስጥ ተሃድሶ ገፍቶ ሁሉንም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ከማስፈታት አልፎ፣ ኢህአዴግን የለውጡና የሽግግሩ አካል የማድረግ ግፊት። ይህ ምርጫ በተስፋና አደጋ የተመላ ነው። እነ ጄኔራል አሳምነውን እስከማስፈታት የደረሰ ግፊተ ያደረገ ቢሆንም፣ የብአዴን አመራር ከወር በላይ ተሰብስቦ ያወጣውን ሙትና በድን መግለጫ ላየና፣ ኦህዴድ ውስጥ የተካሄደውን “ለስላሳ መፈንቅለ መንግስት” ላስተዋለ፣ ይህ አማራጭ ረጅም መንገድ ሃገራችንን ይዞ የመጣ ቢሆንም አቅሙን እያጣ ሞተሩ መንደፋደፍ የጀመረ መኪና ሆኖ ከሩቅ መሰማት ጀምሯል ። ገና ተንገራግጮ አልቆመም።

ኢህአዴግ አሁንም ለማን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎና፣ ርእዩ በፈቀደለት ጥልቀት እንዲሰራ ተባብሮት ራሱን የሽግግሩ አካል ለማድረግ ሊወስን ይችላል ። ለማም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን ተቀዳሚ ተግባሩ የሚሆነው ሃገሪቱን ወደ እርቅና ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲ የሚያቃርቧትን ተግባራት መፈፀም ይሆናል። ኢህአዴግ “ደቡብ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ጊዜውን አልፈፀመም” በሚል ለሽፈራው ሽጉጤ ለመስጠት፣ ወይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተጠባባቂ በማድረግ ደመቀ መኮንን ይዞ እንዲቀጥልና የነበረውን ህዝብ ያስመረረ አገዛዝ መቀጠል እችላለሁ ብሎ ካሰበ “በጥገና አብዮት” የለውጡ አካል የመሆን እድሉን አጨናግፎ፣ በአመፃዊ አብዮት መደምሰስን ሊያስከትል ይችላል። ኢህአዴግ ይህን ስላልፈለገ ይመስለኛል ብዙ ተጉዞ በአልሞትባይ ተገዳይነት አጋዚ ወታደሮቹን ከገደለበት ሰው፣ እስከ መፈንቅለ መንግስት ጠንስሰውብኛል እስካላቸው የኢህዴን ጄኔራሎች ድረስ የፈታው። አሁን ማመንታት ያለበት አይመስለኝም። ለማን ከፊቱ አድርጎ በውስጡ እጅግ ጥልቅ ለሆነ ተሃድሶና ወደሃገራዊ እርቅ የሚደረገውን ጉዞ ቢያሳልጥ የሚጠቅመው ይመስለኛል። እመው ሲተርቱ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጣ፣ አለበለዚያ ድንጋይ ነህ ብለው ይወረውሩሃል” ያሉትን ምክር ደጋግሞ በእዝነ ህሊናው ማድመጫ ጊዜው አሁን ነው ። ሁሌም እንደምንለው ለመታረም ያልፈቀዱ ለመጥፋት መዘጋጀት አለባቸው። ከኋለኛው ይልቅ ቀዳሚውን እንድትመርጡ ፈጣሪያችሁ ቀናውን ያሣያችሁ።