ዛሬ "/ር ዐቢይ አሕመድ የኦሕዴድ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ!" ተብሎ ተነገረ፡፡ ይሄም እርምጃ ዶ/ር ዐቢይን የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና 
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ለመሾም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል የተደረገ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ 

እኔ በግሌ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ለቀኩ!” ሲሉ ወያኔ የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫ ወንበር ባይኖራቸውምና በዚህ የተነሣ ሕጉ ባይፈቅድም ዶ/ር ደብረጽዮንን ትግራይ ላይ በሾመበት መንገድ በማንአለብኝነት አቶ ለማ መገርሳን አንሥቶ የግንባሩና የሕዝብ ፍላጎት በመሆኑ!” የሚል ምክንያት ጠቅሶ ጠቅላይ ሚንስትር አድርጎ በመሾም የኦሮሞን ሕዝብ ለመደለል፣ ከሕዝባዊ ትግሉ እንዲያፈገፍግ ለማድረግ ይሞክራል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡

አሁን ላይ ግልጽ እንደሆነው ወያኔ ይሄንን አንገራጋጭ መንገድ በመጠቀም አቶ ለማን መሾም አልፈለገም፡፡ ነገር ግን እዛው ኦሕዴድ ውስጥ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን በመሾም የኦሮሞን ሕዝብ ለመደለል ሁኔታዎችን አመቻቸ፡፡ ዋናው የወያኔ ፍላጎት የነበረው ግን ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ለመሾም ነበረ፡፡ ዶ/ር ወርቅነህ አሜሪካ ተልከው አሜሪካኖችን እነ አቶ ለማ ሲያስመስሉ ነው እንጅ ጽንፈኛ ናቸው፡፡ ከብአዴን ቢመረጥም ለናንተ ጥሩ አይመጣም እኔ እንድመረጥ ድጋፍ ብትሰጡኝ ጥቅማችሁን ያለገደብ አስከብራለሁ!” ብለው ላቀረቡት ተማጽኖ አዲሱ የትራምፕ አሥተዳደር እንደቀድሞዎቹ ባለመሆኑ ይህ ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ በሰው ሀገር ጉዳይ ጣልቃ ገብተን እርስዎ እንዲመረጡም እንዳይመረጡም የማድረግ ፍላጎት የለንም!” የሚል መልስ ሰጥተው አሳፍረው ስለመለሷቸው ነው ዕድሉ ወደ ዶ/ር ዐቢይ የዞረው፡፡

የሚገርመው ነገር በሕጉ መሠረት ሹመቱ ከማንም በላይ ይገባው የነበረው ለምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ነበረ፡፡ እንደምታስታውሱት አቶ ኃይለማርያም ጠ/ሚ ለመሆን የበቁት ምክትል ጠ/ሚ ስለነበሩና አቶ መለስ ዜናዊ በሞት ሲለዩ የጠ/ሚንስትርነቱን ሥልጣን የሚወርሰው ምክትላቸው እንደሆነ ሕጉ ስለሚደነግግ ነበር፡፡ ጠ/ሚ በሞትም ሆነ በሌላ በማንኛውም ምክንያት ሥልጣን በሚለቅበት ወቅት ከማንኛውም ባለሥልጣን አስቀድሞ ለጠ/ሚንስትርነቱ ሥልጣን ተገቢ የሚሆነው ወይም ዕድሉ ያለው ምክትሉ ሆኖ ሳለ አቶ ኃይለማርያም እለቃለሁ ካሉበት ጊዜ ጀምሮ ግን በሕጉ መሠረት አቶ ደመቀ መኮንንን የመተካቱ ነገር ለአንድም ጊዜ እንኳ ሲነሣ ሲወራ አልተሰማም፡፡

ኦሕዴድም ሆነ ብአዴን አድርጉ!” የተባሉትን ብቻ የሚያደርጉ የወያኔ አሻንጉሊቶች በመሆናቸው ብአዴንም ሆነ ኦሕዴድ በሕጉ መሠረት ሥልጣኑ ወደ ምክትል ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን ይተላለፍ!” ሲሉ አልተደመጡም፡፡ ከዚህ ይልቅ ያደረጉት ነገር ምንድን ነው ከወያኔ የተተላለፈላቸውን ትዕዛዝ መፈጸም ነው፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ደመቀም ሆኑ ብአዴን በሕጉ መሠረት የሥልጣን ሽግሽጉ ይፈጸም!” እንዳይሉ ተደረገ ኦሕዴድም በተመሳሳይ ለመርሕና ለሕግ ታማኝ በመሆን ሌላ ጠ/ሚ መምረጥ ሳያስፈልገን በሕጉ መሠረት የሥልጣን ርክክቡ ይፈጸም!” ሳይል ዶ/ር ዐቢይን ለሥልጣን እንዲያመቻች ተደረገ፡፡ እናም ያለው ነገር ይሄው ነው፡፡ ኦሕዴድም ሆነ ብአዴን ወያኔ የፖለቲካ ጨዋታ ሚዛን መጠበቂያ አክተሮች (ተዋንያን) ናቸው እንጅ ወያኔን ከድተው እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ ተቆርቋሪ ወደመሆን የተመለሱ አይደሉም፡፡

እናም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለማሳሰብ እንደሞከርኩት ይህ ጉዳይ የወያኔ/ኢሕአዴግ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑና የሰዎቹ መቀያየር ለእኛ አንዳችም የሚፈይደው ነገር ባለመኖሩ ትኩረታችንን ከዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ አንሥተን ሙሉ ትኩረታችንን ስር ነቀል ለውጥ ልናመጣ በምንችልበት ሕዝባዊ ትግል ላይ በማድረግ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥል!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com