
ከመጀመሪያው ልጀምር፤ ቋንቋ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ የመገናኛ ዘዴ ነው። እንደማንኛውም ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። አንድ ሰው የማሰብ ችሎታው የቱን ያህል እንደሆነ የሚመረምሩ ጠበብት፥ “ደንቆሮ ሆኖ የተወለደ ሰው መነጋገር ለምን አይችልም?” የሚል ጥያቄ አላቸው። ሲያድግ የሰማው ቋንቋ ስለሌለው በየትኛው ቋንቋ ይናገር? ቋንቋ አንድ ማኅበረሰብ የፈጠረው መሣሪያ ነው። ያንን ማኅበረሰብ ነገድ ያደርገዋል። ሌላ ቋንቋ ከሚናገር ማኅበረሰብ (ነገድ) ያርቀዋል፤ ባዳ ያደርገዋል። ወገን የመለያ ማስረጃ ያደርገዋል። ተሳስቶ ዘር መለያም ያደርገዋል።
ቋንቋ ያድጋል፤ ይሞታልም። የሚያድገው ብዙ አዳዲስ ነገሮች ሲፈጠሩ ለነሱ ስም በማውጣት መዝገበ ቃላቱ ሲተልቅ ነው። አዳዲስ ነገሮች እቃዎች ብቻ አይደሉም፤ አዳዲስ ሐሳቦችም አሉ። “ይኸንን የእንግሊዝኛ ቃል በአማርኛ ምን እንበለው?” እያልን የምንጠይቀው እቃን ብቻ ሳይሆን ሐሳብንም ነው።
ቋንቋ የሚሞተው ተናጋሪዎቹ እሱን ትተው ሌሎች የሚናገሩትን ቋንቋ ሲናገሩ ነው። የወላጆችን ቋንቋ ትቶ ሌላውን ቋንቋ መናገር በቀላሉ የሚፈጸም ሲሆን ውጤቱ ትልቅ ነገር አለው። ሕዝብን በቋንቋ መከፋፈልን ይንደዋል። ያ ሰው ራሱን ለጊዜው የወላጆቹ ዘር ቢያደርግም ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ራሳቸውን የወላጆቻቸው ዘር ወይም ነገድ አያደርጉም። በማህል ቤት ጋብቻና ፍልሰት አሉ።
ሰዎች የራሳቸውን ቋንቋ ትተው ወደሌላው ቋንቋ የሚሄዱበት ምክንያት አላቸው። ዋናው አካባቢው ነው። በአንድ አካባቢ ያለው አብዛኛው ሕዝብ የሚናገረው ጉራግኛ ከሆነ፥ የአማርኛ ተናጋሪ ቤተ ሰብ ልጆች ቋንቋቸው የአካባቢው ልጆች ቋንቋ ይሆናል። ይህ ሁኔታ ብዙ ቋንቋዎችን ገድሏል። ዛሬ አማርኛ የሚናገሩ ሰዎች ባሉበት አካባቢ ብዙ ቋንቋዎች ይነገሩ ነበር። ዛሬ አማርኛ ተናጋሪዎች ሆነዋል። እንዲሁም ዛሬ ኦሮምኛ የሚናገሩ ሰዎች በሰፈሩበት አካባቢ ብዙ ቋንቋዎች ይነገሩ ነበር። ዛሬ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ሆነዋል። ከዚያም አልፈው እነዚህ አማሮች እነዚያ ኦሮሞዎች ሆነዋል። አብሮ መኖር ይኸንን ለውጥ ተቀባይነት አስገኝቶለታል።
ግን ከዚያው ጋራ ተያይዞ የሚመጣ አደጋ አለ። አንዱን ቋንቋ ክቡር ሌሎቹን ቋንቋዎች ሕሱራን (የተናቁ) የሚያደርግ አደጋ አለው። ከዘመን ብዛት በአካባቢው የጋራ ቋንቋ የሆነውን ኦሮምኛን ወይም አማርኛን የባዳ ቋንቋ ያደርገዋል። በተለየ አማርኛ የመንግሥትና የምሁራኑ ቋንቋ በመሆኑ ብዙዎቻችን የራሳችንን ቋንቋ ትተን አማርኛን ቋንቋችን አድርገነዋል። ሁሉም ወደጥንት ዘመዶቹ ቋንቋ ይመለስ ቢባል ብዙዎቻችን መግቢያ እናጣለን። አለዚያም ቋንቋችንም ነገዳችንም አማርኛ ነው ብለን እንከራከራለን። የሆነውም ይህ ነው።
ብዙ ቋንቋዎች እሚነገሩበት ሀገር አንዱ ቋንቋ የሁሉ መገናኛ የሚሆነው በተለመደ የታሪክ ሂደት ነው። ሂደቱ በፈረንሳይና በጀርመን ሲፈጸም አይተናል። ይህ የነገዶች ተጨማሪ መገናኛ መሆን ለቋንቋው ክብር ስለሚያለብሰው፥ ሌሎችም ምክንያት እየፈለጉ የራሳቸው ቋንቋም ብሔራዊ የመገናኛ ቋንቋ እንዲሆን ይጠይቃሉ። ግን አንድ ቋንቋ በሀገር ደረጃ የመገናኛ ቋንቋ የሚሆንበት የራሱ “የተፈጥሮ” መንገድ ስላለው፥ በዚያ መንገድ ያልመጣ ቋንቋ ተጨማሪነት ዕድል የለውም። እርግጥ፥ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ሕዝቦች ከቅኝ ግዛት ሲላቀቁ፥ “በምን ቋንቋ እንጀምር” ሊሉ ይችላሉ። ያም ቢሆን የታሪክ ሂደት ስላለበት ምርጫው ውሱን ነው። አብዛኛውን ጊዜ በዚያው እስከዚያች ዕለት ይተዳደሩበት በነበረው ቋንቋ ይቀጥላሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፥ ብሔራዊ ቋንቋ መሆኑን አማርኛ ቀደም ብሎ ወስዶታል። ዛሬ ከእንግሊዝኛ በቀር የሚያሰጋው ቋንቋ የለም። ግፋ ቢል፥ “የኛም ቋንቋ በመንግሥት ደረጃ ተጨማሪ መጠቀሚያ ይሁን” የሚሉ ፖለቲከኞች ቢነሡ ነው። ይህን ዓይነት ጥያቄ ማስተናገድ ደግሞ ከታሪካዊ ሂደት ወጥቶ ሕዝብ ላይ ከባድ ጫና በግድ መጫን እንጂ፥ ባይማሩት ቢቀር የማይጐዳ ቋንቋ ለማስተማር በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ቋንቋ የመገናኛ መሣሪያ ከሆነ ሁለተኛ ቋንቋ መማርና ማስተማር ጊዜና ሀብት ማባከን ነው። ቋንቋም እንደ ልብስ የዘወትርና ለበዓል የሚሆን ሌላ የክት ቋንቋ ቢያስፈልግ ተጨማሪ ቋንቋ እንማር ነበር።
የተናጋሪውን ሕዝብ ብዛት ምክንያት የሚያደርጉ አሉ፤ አያስኬድም። አንድ ሰው እንኳን ተናጋሪ የሌለው ግዕዝ የኢትዮጵያ የጽፈት ቋንቋ በመሆን ለዘመናት አገልግሏል። አንድ ሰው እንኳን ተናጋሪ የሌለው እንግሊዝኛ የኢትዮጵያ ተጨማሪ ቋንቋ በመሆን እያገለገለ ነው። ለመገናኛ የማያስፈልግ ቋንቋን “ተናጋሪዎቹን ለማስደሰት እንማረው” አይባልም። ልብስ የምንገዛው ዕርቃናችንን ለመሸፈን፥ ከብርድ ጥቃት ለመዳን እንጂ፥ ሸማኔውን ለማስደሰት ወይም ልብሱ የሚገዛው አጥቶ ስላሳዘነን አይደለም።
በቅርብ ጊዜ ያነበብኩት ሌላ ምክንያት አለ፤ በየክልሉ ትምህርት ቤቶች ሦስት ቋንቋዎች (1. የክልሉ ቋንቋ፥ 2. አማርኛ፥ 3. እንግሊዝኛ) ሲሰጡ በአማራው ክልል የሚሰጡት ቋንቋዎች ሁለት (1. አማርኛና 2. እንግሊዝኛ) ብቻ ስለሆኑ፥ እዚህም የሚሰጡት ቋንቋዎች እንደሌሎቹ ክልሎች ሦስት እንዲሆኑ ኦሮምኛ ይጨመርላቸው የሚል ነው።
ይኸንን ምክንያት የሚያደርጉ ፖለቲከኞች በየክልሉ ሦስት ቋንቋዎች ሲሰጡ በአማራው ክልል ሁለት ቋንቋ ብቻ የሚሰጥበትን ምክንያት ያዩት አይመስለኝም። ክልሎች በራሳቸው ቋንቋ ላይ እንግሊዝኛ የሚማሩት የዓለም-አቀፍ ቋንቋ ስለሆነ፥ አማርኛ የሚማሩት ብሔራዊ ቋንቋ ስለሆነ ነው። “ኦሮምኛን በተጨማሪ በአማራው ክልል እናስተምር” ካልን፥ ተጨማሪ ቋንቋዎች በሌሎቹ ክልሎች ለማስተማር ከተሰጠው ምክንያት ወጥተን ሌላ ምክንያት መፈለግ ሊኖርብን ነው። ያ ሌላ ምክንያት ምንድ ሊሆን ነው? ሦስት እንዲሞላ ከተባለ፥ ቋንቋ ማስተማር ከቁጥር ሦስት፥ ማለት ከሥላሴ፥ ጋር ግንኙነት የለውም። ሦስት የመጣው ሁኔታው አስገድዶ ነው። “አማሮቹ ተጨማሪ ቋንቋ መማር ቀረባቸው” ተብሎ ታዝኖላቸው ከሆነና እነሱም ሐዘኑ ከተሰማቸው የትኛውን ቋንቋ እንደሚማሩ ምርጫው የነሱ ይሁን። አጠገባቸው ሌሎች ቋንቋዎች ስላሉ፥ ምናልባት ከነሱ ውስጥ የሚጠቅማቸውን ቋንቋ ይመርጡ ይሆናል። ኦሮምኛንም ሊመርጡ ይችላሉ። ግን ቋንቋ የመገናኛ ዘዴ ከሆነ፥ ሁላችንም በክልል ታጥረን ሳለ፥ አማሮቹ ኦሮምኛ ቢማሩ፥ አማርኛ ከማያውቁ ኦሮሞዎች ጋር የት ተገናኝተው ነው የሚነጋገሩበት? ቋንቋ እንዲስፋፋ ለማድረግ የሚቻለው መጀመሪያ ክልሎቹን በማፍረስ፥ ከላሊዎቹን በመደምሰስ ነው። ካየሁት ልናገርና፥ የሸዋ ሰዎች ብዙዎቻችን ቋንቋችን አማርኛና ኦሮምኛ ነው። ታዝዘን ሳይሆን አስፈልጎን የምናደርገው ነው።
በዛሬው ፖለቲካ፥ አማሮች ሁለት ቋንቋ ብቻ የሚማሩበትን ታሪካዊ ምክንያት ብዙ ሰው አያውቅም። ታሪኩ እንዲህ ነው፤ የራሳቸውን የጎሳ ቋንቋ (አገውኛን፥ ቅማንትኛን፥ ወዘተ.) ከዘመን ብዛት ትተው አማርኛን የጎሳ ቋንቋቸው ስላደረጉት ነው። የጎሳ ቋንቋቸውን አልተዉት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሦስት ቋንቋዎች ይማሩ ነበር። በየሌሎች ክልሎችም ሁለት ቋንቋ ብቻ ለመማር ከፈለጉ በአማራው ክልል ውስጥ ያሉ ጎሳዎች እንዳደረጉት ሊያደርጉ ይችላሉ። ወያኔዎች መጥተው አደናቀፉት እንጂ፥ ማድረግም ጀምረው ነበር። ቋንቋ በመማር የመንግሥት እጅ ከገባበት እጅ እጅ ይላል። አማርኛ በመንግሥት ቋንቋነት በሰላም በሁሉ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ሳለ፥ ያስፈራራው ያለ ይመስል፥ “የመንግሥቱ ቋንቋ አማርኛ ይሆናል” የሚል ሕግ ተደነገገ፤ ሳይቸግር ጤፍ ብድር። በዚህ ጊዜ ነው፥ ሌሎች “የኛ ቋንቋስ” ማለት የጀመሩት።
ሆኖም፥ ሌሎች ቋንቋዎች በከፍተኛ ደረጃ ለመማር ሦስት ምክንያቶች አሉ፤ አንደኛው የቋንቋው ሥነ ጽሑፍ ነው። ብዙ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ፈረንሳይኛ፥ ጀርመንኛ፥ ረሽኛ፥ ያስተምራሉ። የእነዚህ ቋንቋዎችን ሥነ ጽሑፍ ለማወቅ የሚፈልጉ ብዙ ተማሪዎች አሉ። ግዕዝንም ያካበተውን ዕውቀት ለማግኘት የሚማሩት አሉ። ትርፍ ቋንቋ የመማር አስፈላጊነት አንዱ ምክንያት ይኸ ነው።
ሁለተኛው ምክንያት በየቋንቋው ያሉ ተረቶችና የአፍ ታሪኮች በዚያው ቋንቋ ሊጠኑና ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ሊተረጐሙ የሚገባቸው መሆኑ ነው። በየቋንቋው ያሉ ተረቶችና ምሳሌዎች ፍልስፍና አዝለዋል። መታወቅ አለባቸው።
ሦስተኛው ምክንያት የቋንቋ ተመራማሪዎችን ይመለከታል። እነዚህ ባለሙያዎች እንደሚሉት እያንዳንዱ ቋንቋ ሊታወቅ ሊመረመር የሚገባው አወቃቀር አለው። የሰው አካል አወቃቀር እንደሚመረመር የቋንቋ አወቃቀርም ይመረመራል። ለምሳሌ፥ ዳዊት ውስጥ እንዲህ የሚል አረፍተ ነገር አለ፤
የዐቅብ ሕፃናተ እግዚአብሔር።
ይጠብቃል ሕፃናትን እግዚአብሔር።
ግዕዙ ከግራ ወደቀኝ የሄደውን አማርኛ ከቀኝ ወደግራ ሄደው።
ብዙ ምሳሌዎች ለመስጠት ቦታው አይደለም። ዋናው ቁም ነገር ቋንቋን የሰው አእምሮ እንዴት እንዳነጸው መታወቅ እንዳለበት ይታመናል። ቋንቋዎች አደጋ ላይ እንዳሉ ዘሮች (እንደ endangered species) ልንከባከባቸው ይገባላል።
አንድ ቋንቋ በመጻፍ መጠቀሚያ እንዲሆን ከተወሰነ፥ የሚቀጥለው ጥያቄ “በምን ፊደል ይጻፍ?” የሚለው ይሆናል። እስከዛሬ እንዳየነው፥ የተፈጥሮ ወሳኙ ጉርብትና ወይም ሃይማኖት ነበር። የጐረቤት ወይም የራስ ሃይማኖት የተጻፈበት ቋንቋ ሳይመረጥ ዐውቆ ይመረጣል። “ሳይመረጥ ዐውቆ ይመረጣል” ማለት “የታሪክ፥ የተፈጥሮ ሂደት ነው” ማለት ነው። “በምን ፊደል ይጻፍ” ማለት በውሳኔው የሰው እጅ ማስገባት ስለሆነ፥ መወሰኑ የተጠቃሚዎቹ መብት ይሆናል። ለምሳሌ፥ ኦሮምኛን መላ የኢትዮጵያ ልጆች እንዲማሩት በበቂ ምክንያት ከተወሰነ፥ ልጆቹ በለመዱት፥ በተፈተነው፥ በቆንጆው የኢትዮጵያ ፊደል መጻፍ አለበት። ትምህርቱም ከሰሜን ከትግራይ ጀምሮ እደቡብ ድረስ መሰጠት አለበት። “የሚፈለገው የኦሮሞ ልጆች ብቻ እንዲጽፉት ነው” ከተባለና በሙያዬ ምክንያት እንዳማክር ካልተጠየኩ፥ የኦሮሞ ነገድ በፈለገው ፊደል ቢጽፈው መብቱ ነው። ሆኖም፥ በሀገር በቀሉ በኢትዮጵያ ፊደል መጻፋቸውን ትተው ያለ በቂ ምክንያ በሌላ አገር ፊደል ከጻፉ ግን ሌላ የጥላቻ ሐውልት ማቆማቸው እንዳይሆን እሰጋለሁ።
