ሰሞኑን ገና ለሚመረጠው ጠ/ሚኒስቴር ብዙዎች ጠ/ሚኒስቴር እንዲሆን እያሰቡ ያሉት እነሱ የእኛ ከሚሉት ወገን እንዲሆን እንጂ ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ከግንዛቤ የወሰደ አለመሆኑን ሳስተውል አሁንም ገና ብዙ ያለተፈወስን ለመፈወስም ፍቃደኛ ያልሆንን ብዙዎች እንዳለን ሰጋሁ፡፡ በአለፈው እኔ ለማ ጠ/ሚኒስቴር አሁን ባይሆን ምርጫዬ መሆኑን ሀሳቤን ሰጥቻለሁ፡፡ አሁን ዶ/ር አብይ ይሁን በሚለው ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ ግን አሁንም ሌላ ሰው ቢታሰብ ከሚሉት ነኝ፡፡ የእኔ ስጋት ከዘር ማንነት ጋር የተያያዘ አደለም፡፡ ነገሩ ለማም ሆነ አብይ አሁን በአለበት ሁኔታ ጠ/ሚኒስቴር ቢሆኑ ከሚገኘው ትርፍና ኪሳራ አንጻር እንጂ፡፡ መልሼ እዚህ ዝርዝር ውስጥ አልገባም፡፡ ሀሳቤን በሊንኩ ላይ እዩት
ወደተነሳሁበት ልመልሳችሁ፡፡ ብዙ ኦሮሞዎች የአብይና ለማ ደጋፊነታቸው አሁንም በኦሮሞነት ከዚያም ሲያልፍ ኦሮሞ ሥልጣን ቢይዝ ሕወሐት ትግሬዎችን ባለጊዜ እንዳደረገ እኛም በተራችን ባለጊዜ እንሆናለን የሚል ይመስላል፡፡ አዝናለሁ፡፡ እውነታውን አንደብቀው፡፡ ሌሎች ደግሞ ምንም እንኳን ለማም ሆነ አብይ ወይም ሌላ የእነሱ ቡድን ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ፍትሐዊነት በግልጽ የሚናየውን ሥራ እየሰሩ እያዩ ጠ/ሚኒስቴር ለመሆን ግን ኦሮሞ ስለሆኑ ቅር የተሰኙ አሉ፡፡ ሌላ ሌላ ምክነያት ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ይንንም አውነታ አንካደው፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ የተረፉት ናቸው ለማም ይሁን አብይ ጠ/ሚኒስቴር ቢሆኑ በእርግጥም ፍትህን በአገራችን ያሰፍናሉ በሚል በቅን አስተሳሰብ የሚደግፉት፡፡ ከእነዚህ ውጭ የሆኑም ይኖራሉ፡፡ የምርም ከልባቸው በለማም ይሁን በአብይ ድክመት አለ ብለው የሚያምኑ፡፡ እነዚህ ጥሩ ናቸው፡፡ ሲገባቸው ይገባቸዋልና፡፡ ከነዚህ ሌላ ግን በባለፈውም የጠቆምኳቸውን (ሊንኩን እዩ) ለማም ይሁን አብይ አሁን ያተያያዙትን በሕዝብ ዘንድ ያሰወደዳቸውን አካሄድ ለማበላሸት፣ ጠልፎ ለመጣል ብዙ እየሰሩ እንደሆነ የሚታሰቡ፡፡ እነዚህ ደጋፊ መስለውም፣ በግልጽም በማበላሸት ሊሆን ይችላል፡፡ ለዛሬ ግን በዘር (ማንነት) ቀመር የጠ/ሚኒስቴርነቱን ቦታ ወደሚሰፍሩት ጥቂት ልበላችሁ፡፡
ብዙ(አብዛኛው ማለት አደለም) ሊባሉ የሚችሉ ኦሮሞዎች ለማንም ሆነ አብይን በኦሮሞነት ልኬት እንጂ ፍትሀዊነታቸው ብዙም ሳይታሰብ ጠ/ሚኒስቴር ቢሆኑ በሚደግፉት ልጀምር፡፡ አብዛኞቹ እነዚህ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያዊነት አሉታዊ አስተሳሰብ ያለቸው አልፎም ኦሮሚያ የምትባል አገር ለመፍጠር በሚያስቡ ኢትዮጵያዊ አደለንም አስከማለት የደረሱ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ግን ሀሳባቸው ተሸንፎ ይሄው ዛሬ ኦሮሞ ከእኔ በላይ ኢትዮጵያዊ የለም ሲላቸው ዝም ያሉ አሁን ደግሞ በሌላ ስልት የመጡ ናቸው፡፡ ኦሮሞን በሌሎች ዘንድ እንደ ልዩ ጠላት እንዲታይም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ምክነያቱም ከሌላ ኦሮሞ ይልቅ የነሱ ድምጽ ብዙ ቦታ መድረስ ስለቻል ለሌሎች ኦሮሞ ሁሉ የእነሱ አይነት እንዲመስላቸው በማድረጋቸው ነው፡፡ ብዙ ሰምተናል፡፡ ኦሮሚያን ከን ኦሮሞቲ ከሚለው መጤዎች ከአገራችን ውጡ፡፡ የሚኒሊክ ሰፋሪዎች ምናምን ብዙ ብለዋል፡፡ እነዚህና የመሳሰሉ ንግግሮች ሌሎችን በኦሮሞ ላይ ልዩ ሥጋት እንዲኖራቸው አልፎም በጠላትነት እንዲያዩ አድርጓል፡፡ ቀደም በአሉትም በዚሁ ሥርዓት ብዙ ሌሎች በተለይ የአማራ ተወላጆች በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በማንነታቸው የደረሰባቸው ግፍ ተደምሮ ብቻ ነገሩን በሕዝቦች መካከል ይበልጥ ጥላቻ እንዲኖር ብዙ ተሰርቷል፡፡ ይሄ ወያኔና ኦነግ ያሳደጉት አስተሳሰብ ያመጣው ዋነኛ ችግር ነው፡፡ ቆይቶም ይሄንኑ አስተሳሰብ በኦሮሞ በራሱ ላይ ሌሎች ተገበሩት፡፡ ዛሬ ከግማሽ ሚሊየን በላይ በገዛ አገሩ በማንነቱ ምክነያት ከሚኖርበት ተባሮ በስደት የሚኖረው ኦሮሞ ሌላ ምንም ምክነያት ሳይሆን ኦነጋውያንና ወያኔያውያን በቀመሙትና በሚነዙት መርዝ መሆኑ ባንደብቀው ጥሩ ነው፡፡ አሁን ላይ አብዛኛው ኦሮሞ ይሄ ገብቶታል ብቻም ሳይሆን ይሄን የአስተሳሰብ መርዝ ከአገር ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለማና ቡድኑ የአመጡት ለመረዛማው የዘር አስተሳሰብ መድሀኒት የሚሆን ልዩ አስተሳሰብ ፍልስፍና አቅም እያገኘ ብዙዎን ማርኮት ዛሬ እነ ለማም ዘር ሀይማኖት ሳይለይ ትልቅ ድጋፍን ከሁሉም እያገኙ ነው፡፡
የኦሮሞ ፈርስት ቀመር ግን አሁንም ገና ነው፡፡ ዛሬም ሰው አስተያየት ሲሰጣቸው ላለመቀበል አመክንዮያዊ (ሎጂካል) ከመሆን ይልቅ ሁሉንም ከኦሮሞነት ጋር ለማያያዝና እራሳቸውን በኦሮሞነት ለማስጠለል ይሞክራሉ፡፡ ኦሮሞ ፎቢያ (ኦሮሞን መጥላት/መፍራት) የምትል ሀረግ ለሚሰጣቸው አስተያየት ዋና መልስ ነው፡፡ ሲጀምር ኦሮሞ ፎቢያን የፈጠሩት ከላይ እንደጠቆምኩዋችሁ እነሱ ራሳቸው ናቸው፡፡ ሲቀጥል ግን የሚሰጣቸው አስተያየት በአብዛኛው ከልብ በጎ ሕሊና ከአላቸው ሆኖ ሳለ ያንን ስለማይወዱት የበጎ አስተያየት ሰጭዎቹን ሀሳብም ለማጠልሸት ነው፡፡ አሁን በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ያለው አስተሳሰብ ከ4እና 5 ወር በፊት አልነበረም፡፡ ዛሬ ላይ ግን ኢትዮጵያዊነት ጉልበት አግኝቷል፡፡ ጎንደሬዎቹ የአቀጣጠሉት የወንደማማችነት ጥር ዛሬ በዋናነት ኦሮሞ ተቀብሎ እያስተጋባው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሰው ጥበብ አደለም፡፡ የእግዚአብሔር ነው!! ጎንደሬዎች ተጣሩ፣ አዳማዎች መለሱ፣ የኦሮሞንና አማራን ሕዝብ ለ26 ዓመት የጥላቻ ግንብ ሲገነቡለት የነበሩት ደነገጡ፣ በአደባባይ እንዴት 26 ዓመት በጥላቻ ያጠርናቸው ሕዝቦች አንዱ ለአንዱ ጥሪ ሲያደርግ ሌላው ሲመልስ ተሰማ በለው ተናገሩ (ዝምስ ቢሉ እኮ ተንኮላቸው በዚህ ያህል ባልወጣ)፣ ቀጥሎ ይሄኑ የሁለቱን ወገኖች እንደገና አንዳይጠራሩ ብዙ ተሞከረ፣ በዛው ልክ የሴራው ሚስጢር የገባቸው ለካ ይሄ ነው አሉ፡፡ ሕዝቡንም አሁን ለደረሰበት ወንድማማችነት አበቁት፡፡ እነለማና አብይ ዋናው ሥራቸው ይሄ ነበር፡፡ በግልጽ ግን የኦሮሞ ፈርስቶች ይሄን ለማፍረስ ያልማሱት ጉድጓድ አልነበረም፣ ከለንደኑ ኢትዮጵያን አናፈርሳለን፣ አትላንታው ቻርተር፣ ኋላም እንደዘመቻ የቀጠሉት በተለይ አማራን ኢላማ ያደረገ የጥላቻ ዘመቻ ብዙ ነው፡፡ ከወያኔ በአልተናነሰ እንዴት ጎንደሬዎች ለኦሮሞ ሞት ተቆርቋሪ ሆኑ በሚል እጅግ ተበሳጩ፡፡ ይህ በተግባር ያየነው አውነት ነው፡፡ በዛው ልክ ግን ብዙዎች በአለማወቅ የተከተሏቸው ወደ ልባቸው ተመለሱ፡፡ አሁንም ለማም ሆነ አብይ ጠ/ሚኒስቴር ሆነ ሌላ ሥልጣን እንዲኖራቸው ሕዝብ የሚፈልገው በኦሮሞነታቸው አደልም፡፡ በኢትዮጵያዊነታቸውና ለአገርና ሕዝብ በአላቸው በጎ አስተሳሰብ እንጂ፡፡ ስለዚህ በኦሮሞነት ቀመር ይመታስቧቸው እነዚህ ሰዎች እናንተ ለምተስቡ አላማ አይሆኑም፡፡ ግን አሁንም የሌሎችን አስተሳሰብ አትበርዙ፡፡ ከዚህ ድርጊት ተቆጠቡ፡፡
ሌሎች ለማንም ይሁን አብይን ወይም ሌላ ኦሮሞ ይሁን ሌላ እናንተ የእኔ ከምትሉት ውጭ የሆነን ሰው በማንነቱ ብቻ ሥጋት ከምታበዙ አስተሳሰብን ተመልከቱ፡፡ ብዙ ስለእናንተ አልልም፡፡ ግን አሁም አማራ ነን ብለው ደግሞ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ኦነጋውያን የአማራ ብሔረተኝነትን ለማጽነፍ የሚንቀሳቀሱ በብሔር ማንነት ልክ ነው እንዲሆን የሚፈልጉትና ታቀቡልን፡፡ ከበደኖ እስከ ጉራ-ፈርዳ ግፍ ሲደርስበት የነበረው ሕዝብ በአማራነቱ አንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን ከዛ በፊት ሁሉም አንድ በሆኑባት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነት እንዲወድም በመደረጉ መሆኑ ነበር ዋነኛ ምክነያቱ፡፡ በገዛ አገራቸው ኢትዮጵያ መጤ በመባላቸው ነው፡፡ ዛሬ አማራ ነኝ የምትለው ማንነትህ እንኳንስ በሰፊዋ ኢትዮጵያ የእኔ ብለህ እንድታስብ ሴረኞቹ በከለሉልህም ክልል ያለስጋት አትኖርም፡፡ ሕዝቦችም በሩቅ በቋንቋና ሴረኞች በአመሳሰሏቸው መስፈርት ከሚመሳሰሉት ይልቅ አብረው በመኖር የሚመሳሰሉባቸውና የሚጋሯቸው እሴቶች ወዳጅነትና አብሮነታቸውን ያጠነክራል፡፡ ሁላችንም በዛች አገር ለመኖር ከኢትዮጵያዊነት ዝቅ ያለ ማንነት የሴረኞች ስሌት እንጂ እውነትም እንደተባለው የማንነት መብትን ለማስከበር አደለም፡፡ በአይናችን እያየን ያለነው እኮ ወገናችን በአገሪቱ ታሪክ ሆኖ የማያዎቅ በማንነታቸው ሞትና መከራ እየደረሰባቸው ነው፡፡ የአማራው ብሔረተኛ ነኝ የሚለውን ቡድን ከኦነግና ወያኔ አሳንሶ ማየትም ሌላው አደጋ አንዳይሆን፡፡
ይህን ከአልኩ በኋላ ግን ሁሉም በበጎነት በማንነቱ ቢደራጅም ሆነ ሕብረት ቢፈጥር ችግር ላይፈጥር ይችላል፡፡ ለምሳሌ የጉራጌ ሕዝብ ማሕበር መንገድ በመስራት ይታወቃል፡፡ በኃይለስላሴ ጊዜ ብዙዎች በአካባቢ ማንነታቸው እየተደራጁ አንዳንድ የልማት ሥራዎችን ያግዙ ነበር፡፡ የሜጫና ቱለማም የተመሰረተው ጅምሩ በዚህ መንፈስ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን ብዙ አልልም፡፡ በወቅቱ የመንዝ ማሕበር ሌላም ነበር፡፡ ችግሩ የሚመጣው የሕዝብን ማንነት ለራስ ሴራ ለማዋል በሚያስቡ ሴረኞች መጠቀሚያ ሲሆን ነው፡፡ ሴረኞቹ ከሚተቀሙበት ሥልት አንዱ ብሔርን መሠረት ማድረግ ነው፡፡ ይሄውም ብዙ አካባቢን ለመቆጣጠር፡፡ ብሔር ስል ደግሞ አሁን ያለውን የብሔር አስተሳሰብ ማለቴ ነው፡፡ ማንነት ሲመጣ ግን የሸዋ ኦሮሞና የባሌ ኦሮሞ አይገናኝም፡፡ ይበልጠውንም የሸዋ ኦሮሞና የሸዋ አማራ አንድ ነው፡፡ በዘርም በሐይማኖትም፣ በባሕልም፡፡ ከጎንደር አማራ ለመርሀቤቴ አማራ የፊቼ ኦሮሞ በዘርም፣ በእምነትም፣ በባሕልም ይመስለዋል፡፡ ዛሬ በዚህ አስተሳሰብ ስላልሆንን ብዙ እውነታዎችን መቀስቀስ አልፈልግም፡፡ ግን አንድ ሴረኞች የተጠቀሙበትን ስልትና የሄዱባቸውን ሂደቶች ጠቁሜ ላብቃ፡፡
ዛሬ የማንነትን ጉዳይ ትልቅ ቦታ ሆኖ ሊያሳዩን የሚፈልጉት እውን የሕዝቦች ማንነትና ባሕል እንዲከበር ነበር ወይ የታገሉት የሚለውን አስተውሉ፡፡ አሁንም እንደምሳሌ የኦሮሞን ሕዝብ ላንሳ፡፡ በዚህ ሕዝብ ብዙ ቁማሮች ተቆምረዋልና ነው፡፡ ለምሳሌ ቀላሉ የኦሮምኛ ቋንቋን የፌደራል ሥራ ቋንቋ ማድረግ ለምን ይሄን ያህል ከባድ ሆኖ የሄው ጥያቄው 50ዓመት ገደማ ሆነው ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ አስቂኝ ሊሆን ይችላል፡፡ የእስከዛሬው የኦሮሞ ሕዝብን በማሳተፍ እንታገላለን የሚሉት ራሳቸውን ይፈትሹ፡፡ ሕዝብም ከዚህ ወዲያ መሸወዱ ይብቃ፡፡ ኃ/ስላሴ በዘመናቸው መጨረሻ ሊያጸድቁት ከነበረው ሕገ መንግስት ውስጥ ከተካተተው ጉዳይ አንዱ ከአማርኛ በተጨማሪ ቢያንስ አንድ ሌላ ቋንቋ በፌደራል ደረጃ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ነበር ይባላል፡፡ እኔ አላነበብኩትም፣ ስለሰነዱ ሌሎች የጻፉትን እንጂ፡፡ አስቡት ያኔ በሕገ መንግስት ደረጃ የጸደቀን ጉዳይ እስከዛሬ እንዴት መፍትሄ አላገኘም? ይሄ የቁማርተኞቹን አሰላለፍ ለማሳይት እንደምሳሌ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተነሱ አብዛኞቹ የፖለቲካ ቁማርተኞች ለሕዝብና አገር መፍትሄ ላይ አደለም የሚሰሩት እራሳቸውን በሕዝብና አገር ሥም ለማበልጸግ እንጂ፡፡ አሁንም መፍትሄ እናምጣ ከተባለ ነገሮች ሁሉ ቀላል ናቸው፡፡ ግን በአብዛኞቹ እሱ አደለም የሚፈለገው፡፡ የሕዝብና አገር ችግሮች መፍትሄ ከተገኘላቸው አብዛኞቹ አሁን ያሉት ፖለቲካና መሰል ቡድኖች ውስጥ ያሉ ቦታ የላቸውም፡፡ ኦሮምኛን የፌደራል ቋንቋ ማድረግ የኃ/ስላሴ ጊዜ የጸደቀን ሀሳብ ዛሬም ጀግነውበት እናያለን፡፡ አሁንም መፍትሄዎቻችን ፍትሀዊነትን፣ የሕዝብና አገር ደህንነትን፣ ሰላምን ማስፈን ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አደጋ የሆኑባቸው ናቸው ዛሬ ችግር የሆኑብን፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ እንነዚህን አደጋዎች ማጽዳት ነው፡፡ ጠ/ሚኒስቴር በሉት ሌላ ለእኔ ቁም ነገር አደለም፡፡ ግን የኢትዮጵያ ጠላቶች በኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ላይ የዘረጉትን መዋቅራዊ ሴራ መበጣጠስና ግብዓተ መሬቱን መፈጸም ቅድሚያ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለማም ሆነ አብይ ሌሎችም በጀመሩት ለዚህ ሂደት እገዛቸው ከጎናችን ይሁን አኛም ሁላችንም በዘር በሀይማኖት በጎጥ ሳንከፋፈል ከጎናቸው ልንሰለፍ ፍቃደኞች ነን፡፡
አመሰግናለሁ!
ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይታደግ!
አሜን
