ወያኔ ሕዝባችንን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው የፈጠራቸውን የጎሣና የቋንቋ ከፋፍለህ ግዛ ቦዮች እንደጎርፍ በመከተል የተደራጁ የፖሊቲካ ድርጅቶች በዓለም ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታና በመሬት ላይ ካለው የሕዝብ ፍላጎት በመራቃቸው ለአገርና ሕዝብ የሚጠቅመውን ዘላቂ ጉዳይ ማየት አልቻሉም፤ በዲሞክራሲ ባህል ሥራ ላይ የሚውለውን የመድበለ ፓርቲ መርህ በወረቀት ላይ ከማስቀመጥ በስተቀር በሥራ ለመተርጎም አልዳዱም፤ በመርህ ደረጃ

እንኳ ከተቃወሚዎቻቸው ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ተደራድረው በጋራ መስኮች አብረው መሥራታቸውን ለሕዝብ አላሳዩም። ስለአገር ጉዳይ ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር በጋራ መታገልን የሚፈሩም ያሉ ይመስላል። ሌሎች ደግሞ በጋራ ለመሥራት መጀመራቸውን አብሥረውን ነበር። እሰየው ቢያሰኝም ዓይን አይቶና ጆሮ ሰምቶ ልብ ይፈርዳል” እንደሚባል የተቃዋሚነት ስም ብቻ በመያዝ በተስፈኛነት መና ከሰማይ እስኪወርድ በምኞት የሚጠባበቁ ሥልጣን ናፋቂዎች ሆነው ከመታየት በስተቀር ሥራቸው በሕዝብ ውስጥ አይታይም።

ሕዝብ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ እያስተዋለና እያመዛዘነ ነው። ነፃነት ያለትግል በቀና መንፈስ ወይም በችሮታ እንደማይገኝ በተደጋጋሚ ታሪክ ያሳየን ሲሆን፤ በአንፃሩ ትግል በባዶ ፉከራና ግብታዊ አሠራር ሳይሆን በዕቅድና በስትራተጂ ካልሆነ፣ ትግልም ድልም የሕዝብ በመሆኑ ሕዝብ በሚገባ ያልተሳተፈበት ትግል ለሕዝባዊ ድል መብቃቱ አጠራጣሪ ነው። የድርጅቶች ሕዝባዊነት በዋና ከተሞች አካባቢ በሕዝብ ስም መንቀሳቀስን ብቻ ሳይሆን፣ በነፃ ገበያ እንዳይወዳደር ከታፈነው ዜጋ አንሥቶ ለከብቱ የግጦሽ ሣር በማጣት፣ በዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት፣ በዝናብ እጥረት ምክንያት ቡቃያው ሜዳ ላይ የሚደርቅበትን፣ ኑሮውን ለማሸነፍ ቆላ ደጋ የሚናውጠውን፣ ቸርችሮ አዳረውን፤ በኑሮ ውድነት በገቢ እጦት ሸምቶ መመገብ የተሳነውን፣ የተሟላ ምግብና የሕክምና አገልግሎት ባለማግኘት በተለያዩ በሽታዎች የሚሰቃየውን፣ ከኑሮው ተፈናቅሎ በገዛ አገሩ ስደተኛ የሆነውንና የወገን ያለህ የሚለውን፣ ተምሮም በሥራ አጥነት የሚታወቀውን ጭምር ነው። ሕዝብ የሚባለው ወንድ፣ ሴት፣ ሕፃን፣ ሽማግሌ ብሎ ዘር፣ ቀለም፣ እምነት፣ ቋንቋ፣ ባላገር፣ ከተሜ፣ ወዘተ… ሳይለይ መሆኑ ቢታወቅም፣ ብዙ የፖሊቲካ ድርጅቶች እነዚህን ድንበሮች ጥሰው ስላልተቀላቀሉት፣ በውስጡ ተንቀሳቅሰው ወይም ለችግሩ መፍትሔ ጠቋሚ ተግባራትን እስካላሳዩ ድረስ በሕዝብና በሕዝብ ስም በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መካከል የላላ ግንኙነት የሚኖር ሲሆን ድርጅቶች ለሕዝብ ፍላጎቶች ተገዥ ካልሆኑ በአግባቡ ሊመሩት ስለማይችሉ የሕዝቡን ትግል በማፋጠን ፋንታ ሊያጓትቱ ይችላሉ። በአንድ ሕዝብ ስምም እርስበርሳቸው የሚቃረኑና እንዲየውም የጨቋኙ ሥርዓት ወኪል ሆነው የሚያገለግሉ ድርጅቶች የሕዝቡን አንድነትና ትግል አሰናክለዋል፤ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የፖሊቲካ ድርጅቶች የሕዝቡን የልብ ትርታ በማዳመጥና አብረው በመንቀሳቀሰ ሕዝቡን በማስተባበር መርዳት ሲገባቸው ከሕዝቡ ተነጥለው ርቀው ይታያሉ፤ በብሔርብሔረሰብ ተደራጅተው ሊሎችን ህዳጣን አድርገው ያንገዋልላሉ። በሕዝብ ስም ተደራጅተው ሳለ እንዲየውም የሕዝቡን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚሞክሩ ያሉም ይመስላል፡

የፖሊቲካ ተንቀሳቃሾች በ1960ዎቹ እንደነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለውጥ እንደሚያስፈልግ እንጂ የለውጡን ሂደትና ውጤት ለመቅረጽ እንደአገር መሪ የኃላፊነት ሚና ሲጫወቱ አይታይም። አገርን ለመምራት የሚያቅዱ ድርጅቶች የጽንፈኛነትና አክራሪ ነገሮችን በማቻቻልና በትላልቅ የጋራ የአገር ጉዳዮች ላይ ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር ተስማምተው ለሰፊው ሕዝብ መሠረታዊ መብቶችና ጥቅሞች መቆም ይጠበቅባቸዋል።

የአውራ ጎዳና መፈክሮችን እያነበነብን 27 ዓመታትን አሳልፈናል። ሆኖም እውነቱን እየተነጋገርን ከድክመቶቻችን በመማር አስተሳሰባችንን ብናርም የተሻለ ውጤት ልናገኝ እንችል ነበር። የፖሊቲካ ድርጅት ዓይነተኛ ሕዝባዊ ሚና የመንግሥት ሥልጣን ለማግኘት መታገል ብቻ ሳይሆን፤ የሥልጣን ባለቤት ሕዝቡ መሆኑን አምኖ ለሕዝቡ ፍላጎት በመገዛት ዓላማው ሕዝብን ማገልገል ብቻ መሆን ይኖርበታል። ከመልካም አመራር እጦት የተነሣ በሚፈጠሩ ግጭቶች እንጂ በመሠረቱ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦች እርስበርሳቸው ጠላቶች ሆነው አያውቁም፤ ፖሊቲከኞች መፍትሔ ከመሆን ይልቅ ባለፉት ጨቋኝ ሥርዓቶች በተፈጠሩ ኢፍትሐዊ እና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ሳቢያ በማኅበርሰቦች መካከል የተከሠቱ ግጭቶችን የዘር፣ ቋንቋና የመሳሰሉትን ቅርጽና ፈርጅ እያወጡ ችግሮችን የሚያባባሱ ተግባራትን ሲፈጽሙ ታይተዋል። የፖሊቲካ ትምክህት የተጠናወታቸው ብሔርተኛ ድርጅቶች ደግሞ የየራሳቸውን ቡድን ከማየት በስተቀር የቀረው ብሔር-ብሔረሰብ ስለማይታያቸው ዲሞክራሲን እያነበነቡ በተግባር ግን አሽመድምደውታል፤ የሚያደርጉት ትግል የተናጥል ስለሆነ የወያኔን ዕድሜ አራዝመውለታል፤ ከወያኔ ጋር ሲሠሩ የቆዩትና አሁንም ስለአገር ደህንነት የሚሰብኩ የድርጅት መሪዎች ችግሩ ሁሉ የተፈጠረው በወያኔ መሠሪነት መሆኑን እያወቁ ያንኑ የወያኔን ሕይወት ለማቆየት ስለሰላምና መረጋጋት በመስበክ የሕዝቡን ትግል ለማኮላሸት ይጥራሉ። ለምሳሌ በአማራው ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የአማራን ካባ ለብሰው የአማራውን መሬት፣ ንብረትና ሀብት እየዘረፉና እያዘረፉ ኢሰብአዊ እርምጃዎችን እየወሰዱ ዘሩን ጭምር እያጠፉ  በሕዝብ ፊት ግን የአዞ እምባ ያነባሉ፤ በነፃነት ስም ይከፋፍሉታል።  ክልሉ ራሱን በራሱ እንዲመራ የአማራን ካባ ለብሰው ክልሉን የሚመሩ የወያኔ ባለሥልጣናት እስካሉ ድረስ ክልሉ ራሱን በራሱ የሚመራ ነው ማለት ስለማይቻልና ከላይ ሆነው የመከፋፈል ሚናቸውን ሌተቀን የሚሠሩ ስለሆነ በእነሱ ፋንታ ሕዝቡ የራሱን ተወካዮች እስካልሾመ ድረስ ሉአላዊ ነው ማለት አይቻልም።

የግንባታ ራዕይ ያላቸው የፖሊቲካ ድርጅቶች ማናቸውም ማኅበረሰቦች ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር በእኩልነት መኖርን እንደሚቀበሉ በመረዳት ከጊዜያዊ ግጭቶች ባሻገር አርቆ በማየት ማኅበራዊና የምጣኔ ሀብት እድገት ፍትሐዊ ሆኖ ፖሊቲካ የሚያራርቃቸው ሳይሆን ሕዝብን በተሻለ መንገድ ለማገልገል የሚወዳደሩበት መንገድ መሆን እንዳለበት የማስተዋል ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል፡፡  ስለሆነም በማናቸውም ማኅበረሰቦች ስም የሚንቀሳቀስ ድርጅት በፍቅር፣ በሰላም እና በደስታ የመኖርን ራዕይ የሚያመለክታቸው መሆኑን ማየት ይፈልጋሉ። በነፃነት ስም ጥላቻንና መከፋፈልን የሚሰብኩ ድርጅቶች ግን የወያኔ ከፋፍለህ ግዛ መሣሪያ ከመሆን በስተቀር አገር መምራት አይችሉም። ስለሆነም ሕዝቦች የወደፊቱን አገር እጣፈንታ ለማየት የሚያስችላቸው ራዕይ ካላዩ በሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን አቅፈው የራሳቸው አካል ለማድረግ ይቸገራሉ። ልዩነቶቻቸውን ይዘው ሰላማዊ ውይይት ለምሳሌ በዲያስፖራ እንኳ ሲያደርጉ አይታዩም፤ ገለልተኛ የሆኑ አካላት መድረክ አመቻችተውላቸው እንኳ ሊጠቀሙበት አልቻሉም፤ የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ ስለዲሞክራሲና ፌዴራሊዝም እያነበነቡ፤ ዛሬ ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር በጋራ የአገር ጉዳዮች  ላይ  አንድነት  ፈጥረው  ለጋራ  እርምጃ  ያልተሰለፉ  ድርጅቶች  እንዴት  አገርን  የሚያኽል  ትልቅ ነገር  የመምራት ብቃት  ይኖራቸዋል ብሎ ሕዝብ  ሊተማመንባቸው  ይችላል?

የድሮዎችንና የቅርብ ፖሊቲካ ፖርቲዎችን አነሳስ፣ አወዳደቅ ወይም ስኬታማነት በማወቅ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። ከሌሎች ስህተቶችና ስኬቶች የማይማር የፖሊቲካ ድርጅት ግን አካሄዱም ግብታዊ ነው የሚሆነው። ለምሳሌ በፈረንሳይ ሮቤስፓየር የመራቸው ጃኮቢኖች ቅጥ ባጣ ሥልጣን አብዮቱን ቀልብሶ ኋላ ያስከተለውን የናፖሊየን ቦናፓርት አምባገነናዊ አገዛዝ፣ በኮንጎ ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ የተመረጠው ፓትሪስ ሉሙምባን ለመጣል ከ80 ዓመት በፊት የተፈጸመውን የኢምፔሪያሊስቶች ሴራ እና የነሙሴ ሾምቤ በውጭ ድጋፍ የመገንጠል ዓላማ ይዞ መነሣትና ከነዚህ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብት ያላት ኮንጎ ተከፋፍላ ወደ ኋላ በመቅረቷ ሕዝቦቿ እስከዛሬ በድህነትና በርስበርስ ግጭት እየተተራመሱ ስደተኛና ለማኝ ሆኖ መቅረት፣ በናይጄሪያ የነያኩቡ ጎዋንን አነሣስ፣ ውድቀትና የነኮሎኒል ኦዱሚኩ ኦጁኩ የመገንጠል ዓላማ ቢከሽፍም ከዚያ በኋላ ተያይዘው የተከሰቱት ተከታታይ አምባገነናዊ መፈንቅለ-መንግሥቶች አገሪቷን ማዳከም፣ ጋናን ከአፍሪቃ አንድነትና ነፃነት /pan-African Movement/ ጋር ለማራመድ ራዕይ የነበረውን የቅዋሚ ንክሩማን በኢምፔሪያሊስቶች ሴራ መገልበጥ እና ሕዝባዊ ሕልሙን ማጨለም፤ በቺሊ  በሕዝብ የተመረጠውን ሳልቫዶር አየንዴን መንግሥት በመገልበጥ በአውግስቶ ፔኖሼ አምባገነናዊ ሥርዓት እንዴትና ለማን ጥቅም እንደተተካ፣ በደቡብ አፍሪካ የነፒተር ቦታን የአፓርታይድ አገዛዝ በመቃወም እሥር ቤት እያለበጥንካሬው የዓለም ኅብረተሰብን ድጋፍ አግኝቶ የአፖርታይድን አገዛዝ ያስወገደው አፍሪካን ናሽናል ኮንግሬስ የተባለውን የፖሊቲካ ድርጅት መሪ መሆኑ የሚታወቀው ጥቁሩ ኔልሰን ማንዴላ በድምፅ ተመርጦ እርቅንና ፍትሐዊነትን በማምጣት ለነጮቹም ትምህርት ሰጥቶ ሰላም መፍጠር፤ እንዲሁም የየመንን፣  የሶማሌን፣ የዩጎዝላቪያን በጎጥ ፖሊቲካ ተከፋፍሎ በድህነት መቅረት፣ የርስበርስ መለያየት በኦፍጋኒስታን፣ በኢራቅ፣ በሲሪያ መከፋፈል ያስከተለው ጥፋት፣ ወዘተ… በተመሣሣይ ሁኔታ  በአገራችን አንድ የተጠናከረ ሕዝባዊ ድርጅት ስላልነበረ  የሕዝቡን አብዮት ወደ ወታደራዊ አምባገነናዊ አመራር የለወጠው ደርግ፤ በተለይም በኃይለሥላሴ አገዛዝ የተፈጠረውን የኤርትራን ችግር ደርግም ሆነ ወያኔ ፍትሐዊ መፍትሔ ሊያስመጡ አለመቻላቸውና እንዲየውም ከጎጥ የተነሣችው ወያኔ የተፈጠረውን ሕዝባዊ የፖሊቲካ ድርጅት አለመኖር ተጠቅማ ሕዝቡን በጎሣና በሃይማኖት ከፋፍላ በዚህ ክፍፍል ላይ ተንሠራፍታ በአምባገነንነት መቆየት፤ ወያኔን ለሥልጣን ያበቃውና አሁንም ማን እና ለምን እንደሚደግፋት የማያውቅ ወይም ማወቅ ያልነበረበት የፖሊቲካ ድርጅት ይኖራል ተብሎ አይታመንም።  ስለ አገር ጉዳይ የተደራጀ አካል የአገራችንን ታሪክ ቢችል ከሞላ ጎደል የጥንቱን ከቅርቡ ጋር አገናዝቦ ለምሳሌ ከ17ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ያሉትን ለአገራችን እድገት እንቅፋት የሆኑትን ተደጋጋሚ የርስበርስ ግጭቶችና ይህን ተጠቅመው የውጭ ኃይሎች ያደረሱብንን ጉዳት፣ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በሰበብአስባቡ ለመጠቀም የእርስበርስ ግጭት በአገራችን እንዲባባስ የሚመኙ አገሮች መኖራቸውን ተገንዝቦ ለአገር ዘላቂ ጥቅም መቆም ይጠበቅበታል። በአንድነታችን አገራችን ህልውናዋ ተጠብቆ ሊቆይ መቻሉን ሕዝባችን ተባብሮ የራሱን መንግሥት ሲያቆም ትክክለኛ የዕድገት መሠረት እንደሚጣል ከዓለም ዕድገቶች ጋር አገናዝቦ ቢያመዛዝን  ለሕዝቦቻችን የሚጠቅመውን መረዳት አይሳነውም።

ታሪክን  ወደኋላ  የምናየው  ካለፈው  ስህተት ለመማር፣ መልካም  መልካሙን  ለመውሰድና  አሻሽሎ  ለማዳበር ነው፣ በማወቅ ወይም ባለማወቅ  የቀድሞ  መረዎች  ባጠፉት ጥፋት ያሁኑን ትውልድ ለመበቀል ሳይሆን  ያለፈው  ስህተት ወይም ጥፋት  እንዳይደገም መሆን ይኖርበታል። እነ ቅዋሚ ንክሩማ፣ ኔልሰን ማንዴላም ሆኑ የነገሥታት እናት ተብለው የሚታወቁት የሐዲያዋ ተወላጅ ንግሥት እለኔ፣ የእነአብቹ ፣ አባዶዮ ዋሚ፣ ጃጋማ ኪሎ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ፣ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ፣ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ መኮንን ሀብተወልድ፣ ደጃዝማች ወልደሐዋርያት፣ ወዘተ… ተዘርዝረው የማያልቁ አያሌ አያቶቻችን አገር ለመገንባት አርቀው ወደፊት ያስተዋሉትን በመገንዘብ አገራችንን ለማሳደግና ሕዝቦቻችንን ለማበልፀግ ምን ማድረግ አለብን ብሎ ማሰብን ይጠይቃል።  በዓለም ላይ ነፃ አገር መሆን እንደብርቅ በሚታይበት ዘመን ሕዝቦቻችን ባደረጉት ትግል የኢትዮጵያን ነፃነት ከተለያዩ ኃያላን ሴራና ወረራዎች አስጠብቀው ስላቆዩዋት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች አገር መሆኗና የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርን ካረቀቁት አገሮች አንዷ መሆኗ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ያላት አገር ዜጋ መሆን  ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ሊያኮራው ሲገባ፤  ዛሬ ግን በወያኔ አመራር ሕዝቦቻችን በጎጥና በጋጥ ደረጃ እንዲያስቡ እየተደረገ፤ የፖሊቲካ ድርጅቶች በወያኔ ወጥመድ ውስጥ ዳኸሩ። የአገርና ሕዝብ ራዕይ ያለው አካል አርቆ በማስተዋል ይህን የከፋፍሎ መግዣ መረብ ለመበጣጠስ ሰፊውን አገራዊ ሚና መጫወት  ይጠበቅበታል።  የኢትዮጵያን ሕዝቦች እንደቤተሰቡ የሚያይ አካል በአገራችን ታሪክ ኮርቶ፤ ተፈጽመው የነበሩ ስህቶትች እንዳይደገሙ ወይም እንዲታረሙ ለተሻሻለ አስተዋፅዖ በሚደረግ ጥረት ቀዳሚ ሚናዎችን ለመጫወት ይሞክራል፤ ለጋራ ጥቅሞቹ  እንዲተባበር ያደርጋል እንጂ ጥቋቁር የታሪክ ጠባሳዎችን እየፈለገ ሕዝቡ እንዲጋጭ አያደርግም። በአገራችን መከፋፍል አያምንም፤ የከፋፋይ ወኪልም አይሆንም፡፡ መከፋፈል ኃይልን ማዳከም መሆኑን ለማረጋገጥ የባለሙያ ትንተና አያስፈልገገውም። የሕዝቦች ኅብረት ወይም አንድነት ደግሞ  የአገር ሉዐላዊነትን ለማስከበር ያስችላል፤  ዳርድንበርን ጠብቆ ብሔራዊ ባንዲራን በማውለብለብ ከማቆየት አልፎ፣ መሬትን፣ ወንዞችን፣ የባህር በሮቹን በሚያካትተው የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ውሳኔ የመስጠትና የመጠቀም የሕዝብ ኃይል ማምጣት ዋናው ነገር ሆኖ፤ የፖሊቲካ ልዩነቶችን በዲሞክራሲ አቻችሎ በማስተሳሰር የተጠናከረ  የሕዝብ ኃይል መፍጠር አምባገነንነትን ብቻ ሳይሆን በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር ሊመጣ የሚችልን የውጭ ተፅዕኖ ለማስቀረት ሲሆን፤ አገር ወዳድ ፖሊቲከኛ የሚቆመውም ለዚህ ዓይነት ረዥምና ሰፊ ሕዝባዊ ዓላማ ነው መሆን ያለበት፡፡

የአገራችን ትልቁ ታሪካዊ ችግር ኋላቀርነት ሲሆን ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉት፣ በሥልጣን ሽኩቻ የአካባቢ የበላይ ለመሆን የተደረጉ የዘመናት የርስበርስ ጦርነቶች፣ ብሎም አምባገነን መሪዎች ሲሆኑ፣ በኋላቀርነታችን በዋናነት የሚጠቀሙት ቅኝ ገዥዎች/ኢምፒሪያሊስቶችና ሥልጣን ናፋቂ ወይም አምባገነኖች  መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። አገር ካላደገ የግል ወይም የቡድን ጥቅሞች ምንጭ ይመክናል፤  በአንድነታችን ግን ሕዝቦቻችን ሁሉ የጥቅም ተካፋይ ሊሆኑ ሲችሉ፤ በልዩነታችን  የሚጠቀሙት ሦስተኛ ወገኖች ናቸው፤ ለምሳሌ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ብትቆይ ኖሮ ሌሎች ነገሮችን ትተን የባህር በሮቹ ለሁለቱም ይጠቅሙ የነበረ ሲሆን፤ ዛሬ ግን ተጠቃሚዎቹ ኢምሬቶች፣ ሳኡዲዎችና ቻይናዎች ሆነዋል፤ ለሕዝቡ የተረፈው ድህነትና ስደት ነው። በተጨማሪ ኮንጎን፣ ኮሪያን፣ የመንን፣ ዩጎዝላቪያን፣ ቺኮዝሎቫኪያን፣ ሶማሌያን ከፋፍሎ በማቆየት ሌተቀን እየሠሩ፤ ሶሪያን፣ ኢራቅንና ኦፍጋኒስታንን ያሽመደመዱ ሲሆን አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ የመከፋፈል መርህን የሕግ ሽፋን ሰጥተው የሕዝቡን ሉዐላዊነት እየገፈፉ ነው። እንዲህ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እንዲያምቻቸው ነው ዛሬ ኢምፒሪያሊስቶች  ያልበለፀጉ አገሮች  ተከፋፍለው እንዲዳከሙ የሚያደርጉት።

አገርን የመበታተን ድርጊቶች የሚፈጸሙት በነፃነት ስም ሲሆን፤  የሕዝቡን ቋንቋ እየተናገሩ በነፃነት ስም የሚከፋፍሉት ቀርቶ የውጭ ወራሪዎች እንኳ ሲወሩ ሕዝቡን “ብርሃንና ብልፅግና ይዘን መጣንላችሁ…” ማለታቸው ይታወቃል። ሕዝብ ግን ለተከታታይ ትውልዶች ጭምር  የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ለይቶ ያውቃል። የቅኝ ገዥዎች ቅኝ ግዛትን የጀመሩት ከአካባቢ የጎሣ መሪዎች ጋር ውለታ በሚፈጸሙ ወኪሎቻቸው አማካይነት እንደነበረ ሁሉ፤  በብሔርተኝነት የሚፈጠሩ  አገሮች መሪዎች ባለማወቅ ወይም አውቀው ለሥልጣን በመጓጓት ለጥቅም ናፋቂ አምባገነኖችና ለኢምፔሪያሊስቶች በወኪልነት የሚያገለግሉ ሲሆን፣ የሚፈጠሩት ትናንሽ አገሮች ራሳቸውን ስለማይችሉ እርዳታ በመሻት የኃያላን አገሮችን ጥቅም ለማስጠበቅ የተመቹ ሆነዋል።  ኢትዮጵያ ሉዐላዊነቷን ጠብቃ ልትቆይ የቻለችው የተለያዩ የጥንት ወራሪዎችን በተለይም  አይሁዶችን፣ ሒምያሮችን፣ ኦቶማኖችን፣ ግብጾችን፣ ደርቡሾችን፣ አውሮፓውያንን፣ ወዘተ፣ በአንድነት የመከላከል የአባቶቻችን ባህል፣ መልካ-ምድራችንና ሕዝባችን እሴቶች ስለሆኑልን ነው። ከወረራ በመከላከል አገራችንን በነፃነት ለማቆየት በተደረገው ጥረት ውስጥ ሕዝቦቻችን የተፈጥሮ  መልከአ-ምድሮችን ማለትም ተራሮችን፣ ባህሮችን እና ወንዞችን እንዲሁም በረሃዎችን ጭምር እንደመከላከያ በመጠቀም በሌላ አንፃር  ሲታይ ከሌላው ዓለም ተለይተው ዓለምም ረስቷቸው ሲኖሩ፤  በእርስበርስ ግጭቶች፣ በወረራ፣ በወረርሽኝ በሽታና የተፈጥሮ መዛባት የተነሣ ብዙዎች በአገር ውስጥ ተዘዋውረዋል፤ ጥቂቶችም ወደውጭ ተሰደዋል።  መቼና እንዴት  እንደሆነ ለጊዜው ባይታወቅም በእንዲህ ያለ ነውጥ ከኢትዮጵያ ፈልሰው ወደአፍሪካ መኸል የተበተኑ የቱትሲ፣ የማሳይ ሕዝቦችን፣ ወደመካከለኛው ምሥራቅ የፈለሱትን የቤጃ/በደዊን ጎሣዎችን በምሳሌነት ማየት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ጥቃቅን የውስጥ ልዩነቶች ይኖራቸው እንጂ  ባሳለፉት ያንድነትና የግጭት አያሌ ዘመናት የእርስበርስ መስተጋብሮቻቸው ስለሚያይሉ ከሌላው ዓለም ሕዝቦች የተለዩ እንዲሆኑ አድርጎቸዋል፦ ዛሬ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ከምባታ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ በማለት በብሔር-ብሔረሰቦች ለይተን የምናያቸው ማኅበረሰቦች በውስጣቸው እስከብዙ መቶዎች ከሚቆጠሩ ቀዳሚ ኅብረተሰቦች የተዋለዱና በዘር የተቀላቀሉ  መሆኑን የባለሙያዎች ጥናት ያመለክታል፡፡

በትለያዩ ሰው-ስስራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች የተነሣ የሕዝቦች ከአንድ አካባቢ ወደሌላ አካባቢ መዘዋወር ወይም መሰደድ ሲፈጸም ኖሯል፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ብሔርብሔረሰቦች የስደት፣ የዝውውርና የመዋለድ ውጤቶች ናቸው፡፡ለምሳሌ አማርኛ ከአረብኛ፣ ከአገውኛ፣ ከግዕዝ፣ እንዲሁም ከሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተካልሶ በራሱ ነባራዊ ሁኔታ ተፈጥሮ ስላደገና የብዙ ሕዝቦች መግባቢያ ሰለሆነ ነው ብሔራዊ ቋንቋ ሊሆን የቻለው፡፡ አማርኛ በ10ኛው ክፍለዘመን የተነሣው የዛጉዌ (ኩሻዊ) ሥርወ-መንግሥት  የዳበረ ቋንቋ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  እንዲሁም ከ16ኛው እስከ 19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ድረስ በተከናወነው የኦሮሞ ሕዝብ ፍልሰት የተነሣ አብዛኛዎቹ ሌሎች ኅብረተሰቦች ቋንቋና ባህላቸው በኦሮሞ ተለውጧል፡፡ ዛሬ አማርኛን  ባዕድ ያደረጉ የኦሮሞ ፖሊቲከኞች ድሮ ለምሳሌ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ ንግሥተ-ነገሥታት ሕንደኬ በሚል ስያሜ ኢትዮጵያን ይገዛ የነበረው ሥርወ-መንግሥት (dynasty) ከኦሮሞ ወገን መሆኑንና ኦሮሞ ኢትዮጵያዊና የግዕዝ ባለቤት መሆኑን፤ የኦሮሞ ነገሥታት ግዕዝ እየተናገሩ ኢትዮጵያን የገዙ መሆናቸውን ቢገነዘቡ፤ በቅርቡ እንኳ የኦሮሞ ሠራዊት በአድዋ፣ በማይጨው፣ በጨለንቆና በሶማሊያ ወረራ ከቀረው  የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ተሰልፎ ከፍተኛ መስዋዕትነትን በመክፈል አገራችንን  ከወራሪዎች ተከላክሎ በማቆየት ከፍተኛ ጀብዱ የፈጸመ መሆኑን፤ ከኢጣሊያ መሸነፍና ከኢትዮጵያ መውጣት  በኋላ እንግሊዝ የቅኝ ግዛት ምኞቷን ለመቀጠል ያደረገቸውን ጥረት ለማምከን እነ ክቡር  አቶ ይልማ ዴሬሳ ያደረጉትን ዲፕሎማሲያዊ ትግልና ድል ወዘተ ቢገነዘቡ ኦሮሞን ወያኔ በከለለው ኦሮሚያ ከመወሰን ይልቅ መላው ኢትዮጵያ አገራቸው መሆኑን ተረድተው አያቶቻቸው የገነቡትትን አገር እንዳይፈርስ ከሚጠብቁት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያደረገው መሬቱ ብቻ ሳይሆን የሕዝቦቿ ብዙ ሺ ዘመናት መዋሐድ ውጤት ነው፤ ኢትዮጵያውያን ተመሣሣይ የቆዳ ቀለም፣ ተመሣሣይ አመጋገብ፣ ተመሣሣይ አለባበስ፣ ተመሣሣይ የፀጉር አበጣጠር፣ ተመሣሣይ የሙዚቃ/ዘፈን/ ቅኝት ፣ በአጠቃላይ ተመሣሣይ ባህል ሊኖራቸው ችሏል፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ወዘተ የሚባሉት መለያዎች በተወሰነ የታሪክ ዘመን የተከሠቱ ነገሮች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ከዚያ የበለጠ የብዙ ሺ ዘመናት  የደምና የማኅበራዊ ኑሮ መስተጋብር ያስተሣሰራቸው ናቸው፡፡  ሦስቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ማለትም የአይሁድ፣ የክርስትናና የእስልምና እምነቶች በብዙ የአውሮፓ፣ የፍሪቃ፣ የአሜሪካና የእስያ ክፍለ-ዓለሞች ሁሉ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የገቡት ወደ ኢትዮጵያ  ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሰዎችን ሰብአዊ መብት በማክበርና በልዩነት ተከባብሮ በመኖር በምሳሌነቷ በቀዳሚነት የምትታወቅ አገር እንደነበረች የኢትዮጵያ ንጉሥ አርማህ በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን  የሙስሊም ስደተኞችን ሰብአዊ መብት አክብሮ ስለተቀበላቸው ንጉሡ እስላም ባይሆንም ስለፍቅራቸው በስሙ መስጊድ ያሠሩለት መሆኑ በቋሚ ምስክርነት ማየት ይቻላል፡፡

የአገራችንና የብዙ ሌሎች አገሮችን ታሪኮች ብናስተያይ በተለይ በ18ኛውና19ኛው እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመናት በአንድ በኩል ትናንሽ የአካባቢ መንግሥታትን በውዴታም ሆነ በግዴታ አንድ አገር እንዲሆኑ በየክፍለ-ዓለማቱ አገር የማቅናት/classical military unification/ ድርጊት  ሲከሠት፣ ይህን ተከትሎ በተለይ አውሮጳውያን አገሮች የምጣኔ ሀብት ምንጭ /resource/ ለማግኛት ባደረጉት ሽምያ ደካማ አገሮችን በቅኝ የመያዝ ሂደት ውስጥ ሲያልፉ የያዙዋቸውን አገሮች ድንበር በመወሰንና በሕዝቦቹ ማንነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ  አድርገውባቸዋል።  የብዙ አፍሪካ አገሮች ካርታ በዚህ መሠረት የተፈጠረ ሲሆን በአፄ ምኒሊክ ዘመን በአንድ በኩል የውጭ ተስፋፊዎችን በመቋቋም በሌላ ብኩል አገርን ከውስጥ የማቅናት ተግባር ባይፈጸም ኖሮ የኢትዮጵያ ካርታ የተለየ ሊሆን ከመቻሉም በላይ ዛሬ የምናውቃቸው የአንዳንድ ብሔር-ብሔረሰቦች ማንነት /identity/ ሊጠፋ ወይም ሊለወጥ ይችል ነበር።

አገር በሚባለው ነገር ውስጥ ብዙ የተለያዩ የአመለካከት/የፍልስፍና፣ የጥቅም፣ ወዘተ ግጭቶች ይኖራሉ፤ እንኳን በአገር ውስጥ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳ ልዩነቶችና ግጭቶችም መኖራቸው የታወቀ ሲሆን፣ አገርን መምራት እነዚህን ልዩነቶችን አቻችሎ  አገራዊ መፍትሔ በመስጠት  ማስተናገድ  ነው። ዛሬ በልፅገው የምናያቸው አገሮች ተመሣሣይ የጎሣና የቁንቋ ልዩነቶች ችግሮች ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን እንዲየውም የቀለም ልዩነትም እያላቸው፣ በአገሮቻቸው ውስጥ የተለያዩ ሕዝቦች ተከባብረው በዲሞክራሲ ታቅፈው በመኖራቸው ነው ሊበለጽጉ የቻሉት። ሕዝብ በቀናነት የሚጠብቀው አገር ወዳድ ፖሊቲከኞች ልዩነቶችን ተከትለው እንዲከፋፍሉት፣ እንዲበታትኑት ሳይሆን ልዩነቶቻችን በፍትሐዊ ዲሞክራሲ ተጠግነው  ጠንካራ የጋራ አገር ማድረግን ነው። ሆኖም አንዳንድ የግልና የቡድን ሥልጣን ናፋቂ  ጠባብ ፖሊተከኞች ሕዝብን  እንደ መንጋ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ለመንዳት መሞከራቸው ለአገር እድገት ሳይሆን ለሁሉም ድክመት ነው አስተዋፅዖ ያደረገውና የሚያደርገው። ስለሆነም ማንኛውም ሕዝብ ደጉንና ክፉዉን፤ ልማትና ሰላም የሚያመጣውን እና በአንፃሩ የተስፋ ዳቦ ብቻ የሚመግበውን ለይቶ የሚሰማበትና የሚያይበት ብዙ ጆሮዎችና ብዙ ዓይኖች ስለአሉት በሕዝባዊ መሠረታዊ ፍላጎቶችና ጥቅሞች ላይ ያልተማከለ የፖሊቲካ ድርጅት የሕዝቦችን ድጋፍ አግኝቶ ለአስተማማኝ ሕዝባዊ ድል መብቃት አይችልም። በአጠቃላይ ማንኛውም ሕዝብ ለማፍረስ ከመሰለፉ በፊት በሚፈርሰው ፋንታ ግንባታ ስለመኖሩ ምልክቶችን ማየት ይፈልጋል።  ሁሉንም ሕዝብና  አገርን የሚያማክል የጋራ ራእይ ያለው የፖሊቲካ ተቋማት ጥምረት ወይም ኅብረት ከሌለ ሕዝባዊ የጋራ ትግል ሊኖር አይችልም፤ ስለዚህ  እስከአሁን ሕዝቡ ለጋራ ዓላማ ተሰልፎ ወደድል ያልተመራ መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም፤ በአንድነት እጦት እጅግ ብዙ ጉዳት ደርሷል፤ ያልዘሩትን መሰብሰብ ስለማይቻል። ስለዚህ ድርጅቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚፈጸም የአፍራሺነት ሚና ከመጫወት መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ማፍረስንማ ወያኔዎች ተክነውበታል፤ በመተማ፣ በአድዋ፣ በማይጨው፣ በጨለንቆ፣ ወዘተ ጦርነቶች በጋራ ተሰልፎ የጋራ አገር ያቆየውን ሕዝብ የታሪክን ደካማ ጎኖች /ጠባሳዎችን/ አጋኖና አዛብቶ በማቅረብ ሕዝቦችን በዘርና ብሔረስብ አከፋፍለው በማካለል፤ በሃይማኖትና ቋንቋ በማናቆር  እርስበርሱ የማያቃርጥ ግጭት ውስጥ እንዲገባ እና በአንፃሩ ለጋራ የአገር ጉዳይ እንዳያስብ አድርገውታል፤ የነፃነትንና የፍትሕን መርህ አዛብተው በበረቶች እንደሚለያዩ ከብቶች ሊነዱት ሞክረዋል፤ አሞሌ እየላሱ እረኛቸውን እንደሚከተሉ ሙክቶች የራሳቸውን ሕዝብ በጭቆና ለማስገዛት ወኪል የሆኑላቸው መሪዎችንም ተጠቅመውባቸዋል፤  ለዘመናት አብሮ የኖሩትን ሕዝቦች ታሪክ በመቶ ዓመት ውስጥ ገድበው የጋራ አገር እንዳልነበራቸው አድርገው ታሪካቸውን አዛብተዋል፤ በጥንታዊነቱ የአፍሪቃ ክፍለአህጉር በስሙ የተሰየመውን አፋር ከፋፍለው አሳንሰውታል፤ ጥፋት ቢፈጽምም ኢትዮጵያዊውን አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ(ግራኝን) የሶማሌ ዜጋ አድርገው እሱ የረገጣቸውን አካባቢዎች ለባዕድ አገር ለማካለል ቃጥተዋል፤ የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰው ለሱዳን ሰጥተዋል፤ ሕዝቡን አስረበዋል፤ አምክነዋል፤ አፈናቅለዋል፤ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ፈጅተዋል፤ አፋጅተዋል፤ የአገር ንብረት ዘርፈዋል…ወዘተ። በመሠሪ ሴራቸው እስካሁን በሥልጣን ራሳቸውን ለማቆየት ተሳክቶላቸዋል። ይህ ሁሉ ባለመተባበር የመጣ ነው። ሞኝ እስካለ ድረስ ሌባ የሚሠርቀው አያጣምና፤ በወቅቱ ስህተትን ማረም አዋቂነትና ጥንካሬ ሲሆን ከስህተት የማይማር ከመጃጃል ስለማያልፍ እንኳን መገንባት ማፍረስም አይሆንለትም። በእርግጥ ለሕዝብ የቆመ ከሆነ መገንባት እንደሚችል ያሳየ ድርጅት ለማፍረስ የሚተባበረው አያጣም።

ሕዝቡ የአንድን መራሽ አምባገነን በሌላ መራሽ አምባገነን መቀየር አይፈልግም፤ የተወሰኑ ወገኖችን ድብቅ አጀንዳ ይዞ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ሳይሆን የመላውን ኢትዮጵያውያን ድምፅ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚሰማለት አንድ የአገራዊ ድርጅቶች ኅብረት /አካልበሚፈልግበት ባሁኑ ጊዜ ድርጅቶች ልዩነት እንኳ ቢኖራቸው በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ላይ ግን የማያወላውል አቋም ይዘው በጋራ መሥራታቸው የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፤ ይህን ካልሠሩ አንድም የየራሳቸው የግልና የቡድን ሕልም የመፈጸም አላማ እስካላቸው ድረስ፤ ሁለተኛም በተናጥል በሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች ከሰፊው ሕዝብ ከመራቃቸውም በላይ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ  የወያኔን የመከፋፈል ዓላማ አስፈጻሚዎች ከመሆን በስተቀር ሕዝባዊ ግብ አይኖራቸውም፡፡ ይዋል ይደር እንጂ የሕዝብ እምቢተኛነት በመሣሪያ ኃይል የሚተማመኑ ፀረሕዝብ ሥርዓቶችን እንደሚያሸንፍ በታሪክ ተደጋግሞ የታየ ቢሆንም ለአገር የሚበጀውን እርምጃ በወቅቱ አለመውሰድ የሕዝቡን ትግል ጊዜ ያራዝመዋል እንጂ አይጠቅምም፡፡ ስለሆነም ለአገር ደህንነት የሚቆረቆሩ ድርጅቶች የከፋ እልቂትና መስዋዕትነት ከመከሠቱ በፊት ሕዝባዊነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ የሕዝቡን የልብ ትርታ ተከትለው ለፍላጎቱ ተገዥ በመሆን በጋራ ጥምረት ሊያገለግሉት በወቅቱ ካልተሰለፉ በሕዝብ ስም እንዳሉ ስለማይቆጠር ሳይመሽ ሚናቸውን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል፡፡

ተፈራ ድንበሩ