እንግዲህ የታደለው ተመራጭ ይሆናል፤ ከዚያ ዝቅ ያለ እድለኛ ደግሞ መራጭ ይሆናል። እንደኔ ዓይነቱ ከየትኛውም የሌለበት ደግሞ ከውጭ ሆኖ ሆያ ሆዬ ሊጨፍር ይችላል። እንግዲህ ነገሮች ሁሉ እንደዚህ ቀለል አድርጎ ማየት ነው። ወጋችንን እንዲደምቅ በሆያ ሆየ ብንጀምረው ምን ይመስላቸዋል? እንዲህ በማለት፦

አስራት አብርሃም
አስራት አብርሃም

ሆያ ሆዬ ሆ!
ሆያ ሆዬ  ሆ!
እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳል
እዚህ ማዶ ጭስ ይጨሳል
ቄሮ እና ፎሌ ይደግሳል፤
.
.
ያቺ ድንክ አልጋ አመለኛ
አለ አንድ ሰው አታስተኛ።
ያም ሆነ ይህ፣
ለማ ኬኛ
አቢይ ኬኛ!
ክፈት በለው በሩን
የአራት ኪሎውን!

የስርዓት ለውጥ በዚህ አገር እንዲመጣ ነበር ፍላጎታችን፤ ስንታገል የነበርነውን ለዚያ ነው። ለጊዜው የምንመኘውን ለውጥ ማምጣት ባንችልም እንኳ በስርዓቱ ውስጥ የሚደረግ የለውጥ አዝማሚያ መደገፍ ግን ተገቢ ነው። የማነኛውም አገር ወዳድ ሰው ትክክለኛ እርምጃም ይመስለኛል። ከዚህ እምነቴ በመነሳት ነው የዶ/ር አብይ አህመድ ለጠቅላይ ሚስትርነት መመረጥ የምደግፈው። በዚህ ላይ ኦህዴድ ቦታውን ከልብ ፈልጎታል። መፈለግ ብቻም አይደለም በቂ ዝግጅትም ያደረገበት ይመስላል። በግምባሩ ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች በብዙ መልኩ የሚሻል እጩ ለማቅረብ ብዙ ርቀትም ተጉዟል።

ህወሓት ውስጥ አዲስ አስተሳሰብ በመጥፋቱ ምክንያት ያለውን ‘status quo’ ለማስጠበቅ ደመቀ መኮንን በቦታው በማስቀመጥ ከኋላ ሆኖ መምራት ይፈልግ ይሆናል። ነገር ግን በአሁን በአገሪቱ ለተከሰተው ሁሉን አቀፍ ቀውስ በዘላቂነት ለምፍታት ደመቀ መኮንን አዋጭ ምርጫ ሊሆን አይችልም። በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርና በራሱ ፓርቲ በብአዴን ሳይቀር ተፅዕኖ መፍጠር ያልቻለ ሰው ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቢቀመጥ ከሃይለማርያም ደሳለኝ ይብስ እንደሆነ እንጂ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም።

እውነታውን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በፀጋ መቀበል ያስፈልጋል። ኦህዴድ በኢህአዴግ ውስጥ የአመራር ቦታ ይወስድ ዘንድ ጊዜው የደረሰ ይመስላል። እንዲሆን ጊዜው የፈቀደው ነገር ደግሞ ማስቆም የሚቻል አይደለም፣ ለጊዜው ማስቆም ወይም ማዘግየት ቢቻልም እንኳ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል አይሆንም።  ስለዚህ እንደ ድርጅት እመራለሁ፤ ተራዬም አሁን ነው ካለ፣ እድሉን መስጠትና የሚሆነውን ሁሉ አብሮ ማየት የተሻለ ይመስለኛል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የድርጅት ኔትዎርክና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተጠቅሞ ኦህዴድ ያቀረበውን እጩ መጣል አዋጭ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። በአንፃሩ ኦህዴድ በግንባሩ ላይ የነበረውን እምነት እንዲያጣና በተቃራኒው መንገድ እንዲጓዝ ሊያደርገው ይችላል። ይሄ ደግሞ አገሪቷ በሌላ የብጥብጥ አዙሪት ውስጥ ገብታ እንድትናጥ ምክንያት ነው የሚሆነው። ኦህዴድ ያቀረበው እጩ እንደማነኛውም ሰው የራሱ የሆነ ድክመት ሊኖረው ይችላል፣ ነገር ግን በግንባሩ ውስጥ ለዚህ ቦታ እጩ ሆነው ይቀርባሉ እየተባሉ ካሉት ጋር ሲነፃፀር በጣም የተሻለ ነው። በነገራችን ላይ ዶ/ር አብይ አህመድ በልምድም፣ በትምህርት ዝግጅትም በእድሜም፣ ኮሌኔል መንግስቱ ኃይለማርያምና አቶ መለስ ዜናዊ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ከነበራቸው ጋር ስናነፃፅረው የተሻለ ሆኖ ነው የምናገኘው። ለዚህም ነው በኦህዴድ ውሳኔ ወደፊት እንዲመጣ የተደረገው የሚመስለኝ። የፓርላማ ተመራጭ በመሆኑ ብቻ አይደለም። በዚያ ቢሆንማ ኖሮ ኢህዴድ ከአባዱላ ጀምሮ ብዙ አማራጮች ነበሩት።

ዶ/ር አብይ ወደዚሁ የታሪክ አጋጣሚ እንዲመጣ አቶ ለማ መገርሳ መንገዱን ያመቻቸለት፣ ኦህዴድ እንደ ኦህዴድ ሙሉ ድምፅ የሰጠው የተሻለ የአመራር ብቃትና አገራዊ ራዕይ ስላለው ጭምር ነው የሚመስለኝ። በደንብ ከሚያውቁት የተለያዩ ሰዎች ጠይቄ የተረዳሁም ይሄንኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ዶ/ር አብይ የኦሮሞ ህዝብና ሌላውን ኢትዮጵያዊ በተወሰነ መልኩ ከጎኑ ማሰለፍ የቻለ፣ ከመከላኪያው ጋርም በቂ ትውውቅ ያለው፣ አንደበተ ርቱእ ሰው ነው። መሪ ደግሞ ከተግባሩ ባሻገር ተናግሮ የሚያሳምን፣ ራዕዩን ወደ ሌሎች ማጋባት የሚችል ጥበበኛ ሰው መሆን አለበት።

ከሁለም በላይ ደግሞ ዶ/ር አብይ የለውጥ ኃይሉ ነው ወደፊት ያመጣው። የለውጡ እንቅስቃሴ የፈጠረው ሰው በመሆኑ ለኦልድ ጋርዶቹ የሚታዘዝበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖረውም። እንዲያውም በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የተወሰነ ማሻሽያ እንዲኖር ፈር ቀዳጅ የሆነ እርምጃ ሊወስድ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፤ በተለይ ደግሞ ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚመች ነገር ከመፍጠር አንፃር የተሻለ ሰው ሊሆን ይችላል። የኢህአዴግ ድርጅታዊ ባህል እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ እንዲኖር ባይፈቅድም እንኳ በነባሩ አሰራር ላይ የተጋፊነት ባህርይና ድፍረት ካለው ነገሮች ሁሉ ወደ በጎ ሊለውጣቸው ይችላል።

ችግሩ ግን ብአዴን የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ የሚፈልገው ከሆነና ህወሀትም ድጋፉን ለብአዴን የሚሰጥ ከሆነ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ በኦህዴድ በኩል እየመጣ ያለው የለውጥ እድል ሊያደናቅፈው ይችላል። ይህን አካሄድ ግን በአገሪቱ ያለውን ችግር የሚያባብስ እንጂ የሚፈታው አይሆንም። ህወሀት እጩ እንደማያቀርብ ታውቋል። ከራሱም ባይሆን በሌሎች እህት ድርጅቶች ውስጥ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑለት የሚፈልጋቸው ሰዎች ይኖራሉ። ከእነዚህ ውስጥ አቶ ደመቀ መኮንን አንዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ቢያንስ ብአዴን ይህ እንዲሆን መፍቀድ የለበትም። እስከ ባህርዳር ድረስ ተጉዞ የአጋርነት መንፈስ ላሳየው ኦህዴድ ልባዊ ድጋፉን በማሳየት ዘላቂ ጉድኝት ቢያተርፍ የሚሻለው።

ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ ብዙ ርቀት ተጉዞ ወደ አገራዊው የፖለቲካ መድረክ ለመሪነት የሚበቃ እጩ ይዞ መጥቷል። ለዚህ ተነሳሽነቱ ግማሽ መንገድ ሄዶ በክብር መቀበል የሚገባ ነው። ታሪካዊነቱም ነው መታየት ያለበት። የኦሮሞ ህዝብ በዚህ አገር ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ኃይል ሆኖ ሲመጣ መታደልም ነው። የተዛባውን ታሪክ የማስተካኪያ እድል የሚሰጥ፣ አዲስ ተስፋ እና የአንድነት መንፈስ የሚፈነጥቅ ነው።

ከሁሉም ነገር በላይ ግን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከየትኛውም ብሄር ወይም ድርጅት ይምጣ በእርሱ አመራር የሕግ የበላይነት የሚከበርበት፣ ዜጎች በአገራቸው በየትኛውም ቦታ ሰርተውና ተንቀሳቅሰው የሚኖሩበት፣ ንፁሃን የማይገደሉበት፣ ለዘመናት ጥረው ግረው ያፈሩትን ንብረት የማይዘረፉበትና የማይቃጠልበት፣ ዘር መሰረት ያደረገን ጥቃትና ማጥላላት ቀርቶ እውነትና እውነት ብቻ ተይዞ የፖለቲካ ውድድር የሚካሄድበት ስርዓት እንዲያሰፍን ነው። በተለይ ደግሞ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በዚህ አገር ላይ እውን እንዲሆን ዓላማ ይዞ ወደ መሪነቱ የሚመጣ ሰው ምንም ይሁን የምናከብረው መሪያችን ይሆናል።