የቀድሞ የሰማያዊ አመራሮች አዲስ ፓርቲ ለመመሥረት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ
አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)

የቀድሞ የሰማያዊ አመራሮች እነ አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) አዲስ ለሚመሠርቱት የሥነ መንግሥት ማኅበር (የፖለቲካ ፓርቲ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትብብር እንዲያደርግላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ታወቀ፡፡

‹‹የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን)›› (Ethiopian National Movement – ENM) በሚል ስያሜ ያቀረቡትን የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ምርጫ ቦርድ በመቀበል አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግላቸው፣ በቦርዱ ማኅተም አረጋግጦ ምላሽ እንደሰጣቸው ከመሥራቾቹ አንዱ የሆኑት አቶ ይልቃል ጌትነት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ይልቃል እንዳስረዱት፣ የቦርዱን ይሁንታ በማግኘታቸው ፓርቲው በሚቀጥለው ወር መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. መሥራች ጉባዔ ያደርጋል፡፡ የሰነድ ዝግጅት፣ የፋይናንስ፣ የፊርማ ማሰባሰብና የጉባዔ አጣሪ ኮሚቴዎች እንደሚመረጡ፣ እነዚህን ኮሚቴዎች የሚመራ ዓብይ ኮሚቴም እንደሚሰየም አስረድተዋል፡፡

ፓርቲውን ሕጋዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን የ1,500 አባላት ፊርማ ለማሰባሰብም እየሠሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ይልቃል፣ ከአራቱም ክልሎች የሚያስፈልገውን የ900 አባላት ፊርማ ማሰባሰብ መጀመሩንና በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚያስፈልገውን የ600 አባላት ፊርማ አሰባስበው እየጨረሱ መሆኑንም አክለዋል፡፡

Source    –   መነሻ ገጽ