ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ምክንያቱ በከባድ እስር ላይ የሚገኙት የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ጉዳይ ሲሆን ዋና አላማውም ከትናንት እስከ ዛሬ ያለውን የሀገራችን መሪዎችና የገዳማውያን አበውን ግንኙነት  በአጭሩ ማስቃኘት እና የዘመናችን መሪዎች ከታሪክ እንዲማሩ መጋበዝ ነው። በሀገራችን የረጅም ጊዜ ታሪክ ቤተክህነትና ቤተመንግሥት በአንድም ይሁን በሌላ መልክ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተነጣጥለው ስለማያውቁ በገዳማቱና በገዳማውያን አበው ላይ መሪዎች የነበራቸው ተጽእኖ ቀላል አልነበረም።   በአብዛኛው የቀደመው ታሪካችን የሚነግረን ነገሥታቱ ለገዳማት መስፋፋትና ለገዳማውያን አበው ጠንካራ ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው።  ገዳማቱና ገዳማውያኑ በበኩላቸው ለሀገር እድገት፣  አንድነትና መረጋጋት  ግዙፍ ሚና ነበራቸው።  ገዳማቱ የስነ ትምህርት፣ ስነ ጽሑፍ፣ ስነ ዜማ፣ ስነ ጥበብ፣ እደ ጥበብ፣ ኪነ ሕንጻ ወዘተ… መሰረቶች በመሆናቸውም  የሀገር ባለውለታ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ገዳማቱ የሀገር መሪዎችን ቀርጾ በማውጣትም ጉልህ ድርሻ ነበራቸው።  ጥቂት የማይባሉ ነገሥታት ወደ ዙፋን ከመምጣታቸው በፊት የገዳም ቆይታ የነበራቸው ናቸው።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

በሀገራችን ከአንድ ሺህ በላይ ገዳማት የሚገኙ ሲሆን ምናልባትም ይህ ቁጥር  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በገዳማት ብዛት በዓለማችን የመጀመሪያዋ መንፈሳዊት ተቋም ሳያደርጋት አይቀርም።   ከገዳማት መመስረት ጋር ቀድሞ የሚነሱት ኢትዮጵያዊ መሪ ንጉሥ ካሌብ ናቸው።   በታሪክ ዘጠኙ ቅዱሳን ተብለው የሚታወቁት በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ማብቂያና በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ በሃይማኖታቸው ምክንያት ከሮምና ቢዛንታይን ግዛት ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት መነኮሳት በአክሱምና አካባቢው ገዳማትን የመሰረቱት በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት  ነበር።  ንጉሡ መነኮሳቱ ገዳማትን እንዲመሰርቱና እንዲያስፋፉ ያደርጉት ከነበረው ድጋፍ በተጨማሪ እርሱ ራሱ ክርስቲያኖችን ለመታደግ ወደ ደቡብ አረቢያ ካደረገው የተሳካ ዘመቻ መልስ ገዳም ገብቶ  ቀሪ ህይወታቸውን  በምናኔ አሳልፈዋል።  ከንጉሥ ካሌብ ቀጥሎ ልጁ ንጉሥ ገብረ መስቀል ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ ለነበሩትና ለደብረ ዳሞው ገዳም መስራች  አቡነ አረጋዊ የላቅ ድጋፍ  ያደርጉላቸው እንደነበር ተዘግቧል። ንጉሥ ገብረ መስቀል ከቅዱስ ያሬድም ጋር  የቀረበ ወዳጅነት ነበራቸው። ንጉሥ ካሌብና ንጉሥ ገብረ መስቀል በርካታ ገዳማትና አብያተክርስቲያናትን በተለያዩ አካባቢዎች እንዲመሰረቱ አድርገዋል።

 

የዛጉየ ዘመን ነገሥታትም ለገዳማትና ገዳማውያን  አበው ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉ ነበር።  ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ እና ቅዱስ ላሊበላ ራሳቸው ወደ ንግሥና ከመምጣታቸው በፊት ረጅም ጊዜ በገዳማት ያሳለፉ መሆናቸውን ገድሎቻቸው ይናገራሉ።  በተለይ ደግሞ ንጉሥ ላሊበላ ለገዳማትና ለገዳማውያን አበው ድግፍ በማድረግ የላቀ አስትዋጽኦ እንደነበረው የሚያመለክቱ የታሪክ ሰነዶች ይገኛሉ።  ንጉሥ ላሊበላ ከአራቱ ታላላቅ የኢትዮጵያ ገዳማት  ከዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ ከጣና ቂርቆስ ገዳም፣ ከሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምና እና ሰሜን ኢትዮጵያ ይገኝ የነበረው (ዛሬ ኤርትራ ግዛት የሚገኘው) የሽማዛና ደብረ ሊባኖስ ገዳም  መመስረትና መጠናከር ጋር ስሙ ይነሳል።  የሐይቅ እስጢፋኖሱ ገዳም መስራች አባ ኢየሱስ ሞዓና የዝቋላው አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማቱን ሲመሰርቱ ጠንካራ የንጉሡ ድጋፍ እንደነበራቸው ይታመናል። ንጉሥ ላሊበላ አክሱም ጽዮንን ጨምሮ ለበርካታ ገዳማት መተዳደሪያ የሚሆን የመሬት ስሪትም አድርጓል።  በዚሁ ንጉሥ ዘመን ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም ወሳኝ የሆኑ ቦታዎችን በስጦታ ማግኘቷና በዚያው የነበሩ መነኮሳቱም ገዳማቱን ማቅናት መቻላቸው ተመዝግቧል።

 

ከ13ኛው እስከ 15ኛው መቶ ክ/ዘመን ያለው ጊዜ ደግሞ በሀገራችን ለገዳማት መስፋፋትና ለታላላቅ ገዳማውያን አበው መነሳት  ወርቃማ ጊዜ ነበር።   አቡነ ተክለሐይማኖት፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል፣ አቡነ አሮን፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን፣ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ አቡነ ሐራ፣አቡነ ኤውስጣጤውስ፣ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግና ሌሎችም በርካታ አባቶች የተነሱት በተጠቀሰው ዘመን ነበር።  ከአጼ አምደ ጽዮን ውጭ ሌሎቹ ነገሥታት ለገዳማውያን አበው የነበራቸው ክብርና ልዩ ልዩ ድጋፍ ጎልቶ የሚነገር ነው። በተለይ ደግሞ አጼ ዘርዓያዕቆብ በ15ኛው መቶ ክ/ዘመን የደብረ ምጥማቁን ጉባኤ በማዘጋጀት የቤተ ኤውስጣጤዎስና የቤተ ተክለሃማኖት አባቶችን በመሰብሰብ ልዩነቶቻቸውን በመተው እንዲቀራረቡ ያደረጉት አስተዋጽኦ በታሪክ ዘወትር የሚታወስ ነው።  በተመሳስይ የጎንደር ዘመነ መንግሥት ነገሥታት ገዳማት የትምህርት፣ የእውቀት፣ የፍልስፍና፣ የጥበብና የመሳሰሉት ተግባራት ማእከል ሆነው እንዲያብቡና ገዳማውያኑም በዚህ ረገድ እንዲበረታቱ ያደርጉት አብይ ተግባር የሚረሳ አይደለም።  እነ አጼ ፋሲለደስ፣ ታላቁ ኢያሱ፣ እቴጌ ምንትዋብ፣ አጼ በካፋ እና ሌሎቹም ገዳምትና አብያተክርስቲያንት እንዲስፋፉና እንዲጠናከሩ በማድረግ በኩል የሚደነቅ ተግባራትን ፈጽመዋል። ለምሳሌ ጥንታዊዋ የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን በግራኝ በመውደሟ ምክንያት አጼ ፋሲለደስ ሌላ ቤተክርስቲያን እንዲታነጽ አድርገዋል።  በዘመነ መሳፍንት እንኳን የየጁ ስርወ መንግሥት መሪዎች እነ ትልቁ ራስ አሊ ሳይቀር ተመሳሳይ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

በዘመናዊ የሀገራችን ታሪክ አጼ ዮሃንስ 4ተኛ ደብረ ሊባኖስን ጨምሮ  በግራኝ ወረራ የፈረሱና የተቃጠሉ ገዳማትንና አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተዋል።  በኢየሩሳሌም የምትገኘው የዘውድ ቅርጿ የደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን  በአጼ ዮሃንስ ተጀምራ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የተጠናቀቀች ናት።  አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱም በሀገራችንም በኢየሩሳሌምም ለነበሩ ገዳማውያን ልዩ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር ይታወቃል።  ለምሳሌ አጼ ምኒልክ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የዴር ሱልጣን ገዳም ሕጋዊ ባለቤትነት ለማረጋገጥ መረጃዎች እንዲሰባሰቡ ያደረጉት ጥረትና ለገዳማውያኑ ቋሚ መተዳደሪያ ይሆን ዘንድ የሚከራይ ሕንጻዎች ማሰራታቸው የሚደነቅ ነው። በተመሳሳይ እቴጌ ጣይቱም በኢየሩሳሌም የእስራኤል ሬድዮ ጣቢያ የተከራየውን ህንጻ ለገዳማቱ መርጃ ይሆን ዘንድ አሰርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ንጉሡና ንግሥቲቱ ኢትዮጵያውያን መነኮሳትን ደብዳቤ በመጻፍ ያጽናኗቸውና ያበረታቷቸው እንደነበር የሚመሰክሩ ሰነዶች ይገኛሉ።  በአንጻሩ አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ለአደዋው ዘመቻ ጥሪ የገዳማውያኑን ድጋፍ ማግኘታቸው ለድሉ መገኘት አንዱ ምክንያት መሆኑ ጥርጥር የለውም።  ንግሥት ዘውዲቱም በበኩላቸው አዲስ አበባ የምትገኘውን በዓታ ለማርያምን ጨምሮ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ ገዳማትን ማጠናከራቸውና አብያተክርስቲያናትን ማሳደሳቸውና ማሰራታቸው ይታዎቃል። አጼ ኃይለስላሴም እንደ ቀደምት ነገሥታት ሁሉ ለገዳማትና ለገዳማውያኑ የነበራቸው ድጋፍ ጠንካራ ነበር። ንጉሡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከግብጽ ቤተክርስቲያን  የሞግዚትነት አስተዳደር ተላቃ ራሷን እንድትችልና በልጆቿ እንድትመራ ትግል ከማድረጋቸው በተጨማሪ በርካታ በጎ ተግባራታን ፈጽመዋል። ገዳማት እንዲደራጁና አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ አድርገዋል።  ለአብነት ያህል በአዲስ አበባ የሚገኘው የምስካየ ኅዙናን ገዳም፣ ቅድስት ስላሴ ካቴደራል፣ የአክሱም ጽዮን ክቧ ቤተክርስቲያን ይጠቀሳሉ። ጽላተ ሙሴ የምትገኝበትን የተለየች ባለ አንድ ፎቅ ህንጻ ያሰሩት ደግሞ የአጼ ኃይለስላሴ ባለቤት እቴጌ መነን ናቸው። አጼ ኃይለስላሴ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስሊዎስና ከብጹዕ ወቅዱስ  አቡነ ቴዎፍሎስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበራቸው::

እንደሚታወቀው ዘመነ ደርግ ለኢትዮጵያ ገዳማት እና ገዳማውያን አበው የሚመች ወቅት አልነበረም። ቤተክርስቲያኗ መሪዋን ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን አጥታለች። በ1967 ዓ.ም በወጣው የመሬት ላራሹ አዋጅ ምክንያት ብዙ ገዳማትና አድባራት መተዳደሪያ የነበረውን መሬታቸውን ተነጥቀዋል።  በተመሳሳይ በ1968 በወጣው የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች አዋጅ መሰረት ቤተክርስቲያኗ ያለምንም መተዳደሪያ ራቁቷን እንድትቀር ተደርጋለች።  የገዳማቱና የገዳማውያኑ ችግር ከ1983ቱን የመንግሥት ለውጥ በኋላም ቀጥሏል።  በዚህ ዘመን ከመቸውም ጊዜ በላይ  ውድና መተኪያ የሌላቸው ቅርሶች በየገዳማቱ ለስርቆትና ለቃጠሎ ተጋልጠዋል።  በድንቅ ቅርስ ሀብት የሚታወቁ ደብረ ዳሞንና አዲስ ዓለም ማርያምን የመሳሰሉ ገዳማት ሳይቀር የውድመቱ ሰለባ ሁነዋል። በዝቋላ ገዳም የነበረውም የደን ቃጠሎ በቅርብ የሚታወስ ነው። በአንዳንድ ገዳማት መነኮሳት በታጠቁና በተደራጁ ኃይሎች ለአደጋ ተጠቂ እስከመሆን ደርሰዋል።  ለዚህ አብነት የሚሆነን በደብረ አሰቦትና ባለፉት አምታት በጣና ገዳማት የነበረውን አሳሳቢ ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል።  በተዎሰኑ ቦታዎች ደግሞ የገዳማቱ መሬቶች በአካባቢው ነዋሪዎች በመወሰዳቸው ምክንያት ገዳማውያኑ በአታቸውን ለቀው እስከመስደድ የደረሱበት ሁኔታም እንዳለ ይነገራል።  ከስኳር ልማት ጋር በተያያዘ በዋልድባ ገዳም የቀጠለውን ውዝግብም  እያየነው ነው።  ይባስ ብሎም  የዋልድባ ገዳም መነኮሳት በእስር ምክንያት እየተንገላቱ መሆናቸው ይታወቃል። የእነዚህ አበው የእስር ሁኔታ ከመነኮሳቱ፣ ከአማኞቹንና አጠቃላይ እንደ ተቋም ከቤተክርስታኗን ክብር ጋር የሚያያዝ ነውና ብዙዎቻችን ያሳሰበ ጉዳይ  ከሆነ ውሎ አድሯል።  ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ካላገኘም የእምነት ጉዳይ በመሆኑ ወደፊት ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ መገመት አይቻልም።  በዋልድባ መነኮሳት ጉዳይ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ዝምታም  ለቤክርስቲያኗ ልጆች የጤነኝነት ስሜት እንዳይሰማቸው አድርጓል። ከብፁአን አበው መካከል ከዋልድባ ገዳም የተገኙ መኖራቸው ርግጥ ነው።  ከታሪክ እንደምንረዳው የቤተክርስቲያን አባቶችን በማሰርና በማንገላታት የሚፈለገውን ሰላምና መረጋጋት ማግኘት አይቻልም። የአጼ ቴዎድሮስ ውድቀት የተባባሰው ጳጳሱን አቡነ ሰላማን ማሰራቸውን ተከትሎ ህዝባዊ ድጋፍ በማጣታቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖትንም በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት በወታደራዊ መንግሥት ደስተኛ  ስላልነበሩ  ደርግ የተረጋጋ ዘመን እንዳልነበረው ሁሉም የሚያውቀው ነው።  ሌሎችም ምሳሌዎችንም ማስታወስ ይቻላል።  በአንጻሩ ከላይ የዘረዘርናቸው ቀደምት የሀገራችን መሪዎች ከመንፈሳዊ አባቶች ጋር የነበራቸው ወዳጅነትና ከዚያም አልፎ ለገዳማውያኑ ያደርጉት የነበረው ድጋፍ ትርፍ አስገኝቶላቸዋል። ዙፋናቸው የረጋ፣ አስተዳደራቸው ቅቡል፣ ኑሯቸውም ሰላማዊ እንዲሆን አስችሏቸዋል። ስለሆነም ከታሪክ መማር ያስፈልጋል።  ከታሪክ የማይማር ትውልድ መነሻ  እንደሌለው ሁሉ መድረሻም የለውም፡፡

ማጣቀሻዎች

መንግሥቱ ጎበዜ (ዲያቆን) እና አሳመነው ካሳ (ዲያቆን)፣የቤተክርስቲያን ታሪክ (ቁ ፪)። ማኅበረ ቅዱሳን (፳፻ ዓ.ም፣አዲስ አበባ)

ኅሩይ ባየ (መ/ር )፣ ቅዱሳት መካናት:: ማኅበረ ቅዱሳን ( ፪፻፮ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ)

ዳንኤል ክብረት (ዲያቆን)፣ አራቱ ኃያላን::  (፪፻፮ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ)

ጎርጎሪዎስ (አቡነ)፣ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ:: ( ፩፱፯፬ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ)

Sergew Hable Sellassie, Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270. (1972, Addis Ababa).

Taddesse Tamrat, Church and State in Ethiopia, 1270-1527. (1972, Oxford).