የካቲት 09/2010 ዓ.ም ቀን በመላው ሃገሪቱ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ፀደቀ።
ከእረፍት ተጠርቶ አስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፅድቋል።
አዋጁ 346 የምክር ቤት አባላትን ድጋፍ ሲያገኝ 88ቱ ደግሞ ተቃውመው ድምፅ ሰጥተዋል። እንዲሁም የሰባት አባላት ድምፀ በታዕቅቦ ተመዝግቧል።
የአዋጁን መደንገግ ከተቃወሙት መካከል አብዛኛዎቹ የኦህዴድ አባላት እንደሆኑ ተነግሯል።
ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመጠበቅ መታወጁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ አመልክቷል።
ምክር ቤቱ ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች የተመረጡ ሰባት አባላት ያሉት ቦርድ ይቋቋማል ብሏል።
ቦርዱ ካሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን ምክንያት መግለፅ ይገኝበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ማናቸውም የሚወሰዱት እርምጃዎች ኢሰብዓዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል አለበት። ኢሰብዓዊ ሆነው ከተገኙ ግን ፈጻሚዎቹን ለፍርድ ያቀርባል ተብሏል።
የአሜሪካን መንግሥትን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሃገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተቸታቸው ይታወሳል።
ከዚህም በተጨማሪ ተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾች በተለያየ መልኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አዋጁን እንዳይደግፉ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
Source – BBC/AMHARIC
