ማርቆስ ረታ

የኢሀዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ተቀምጧል አሉ፤ እንደገና። ሊቀመንበር ለመምረጥ ነው አሉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ጸድቋል፤ እንደገና። ኢህአዴግ ውስጡ ችግር አለ፤ ከአባል ግንኙነቶችና አደረጃጀት ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም። ከሕዝብ ጋር ያለው ችግር ይታወቃል። ሕዝብ ይጮኻል ኢህአዴግ ምንም ሊያደርግለት አልቻለም። ምክንያትም ፖሊሲ ሳይለውጡ ወይም ሳያሻሽሉ ያገርና የሕዝብ ችግር መፍታት አይቻልም። ኢሀዴግ ለውጥ አመጣለሁ እያለ ከመፎከር በቀር ትርጉም ያለው ሥራ ለመስራት አልቻለም። ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ፖሊሲ አመንጭቶ የመተግበር ስልጣኑ በአበዳሪዎች እጅ ገብቷል። ይህን አልነገረንም፤ የተመዘገበው እድገት በኢሀዴግ ትክክለኛ ፖሊሲዎች የተገኙ ናቸው ሲል ልክ ፖሊሲዎቹን ራሱ ያመነጨ፥ እንደፈለገም ሊቀይራቸው የሚችል መስሎ ሲታይ ኖሯል። ሆኖም ፖሊሲዎቹን ልቀይር ቢል እውነተኛ ባለቤቶቹ አይፈቅዱለትም። ስለዚህ መቼም ቢሆን የህዝቡን ችግር ሊፈታ አይችልም። እውነት እንነጋገር ከተባለ ኢሀዴግ በአበዳሪዎቹ መዳፍ ሥር ገብቶ የሚገኝ፥ አለቆቹ በግድ የጫኑበት፥ የአገርና የሕዝብ መከራ ምንጭ የሆነውን ፓሊሲ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ የራሱ አስመስሎ ለማቅረብ ሲሞክር የኖረ አሳዛኝ ድርጅት ነው። ሆኖም ኢሀዴግ ራሱን በአበዳሪዎች ቁጥጥር ሥር በማስገባቱ አገራችንንም ለባዕዳን የቅኝ ግዛት ኃይሎች አሳልፎ ሰጥቷል። ስለሆነም እሱ ከአለቆቹ ነጻ ለማውጣት እኛም ራሳችንንና አገራችንን ከመሪር አገዛዙ ለማውጣት የሚቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን።

የመጀመሪያው ሥራ የኢሀዴግን ቤት ማጽዳት ነው። ለዚህም የድርሻችንን እነሆ።

መግቢያ

መሪዎቹ ባለፈው ታህሳስ ወር ከግምገማው በኋላ በሰጡት መግለጫ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ከሰማይ በታች ሳይነሳ የቀረ አግባብነት ያለው ጉዳይ የለም ማለታቸው ይታወሳል። ሆኖም የፖሊሲ ለውጥ፥ ማሻሻያ ሲባል አልሰማንም። የአገራችን የፖሊሲ አስተዳደር ስልጣኑን የተቆጣጠሩት የገንዘብ ተቋሞች ጉዳይም ሳይረሳ አልቀረም መሠል። በርግጥ አዳዲስ ሀሳቦችን አለመቀበል አመራሩ ራሱን በድክመት ከገመገመባቸው ነጥቦች አንዱ ሆኖ ቀርቦ ነበር።

በርግጥ የመንግሥት ስልጣን ይዣለሁ የሚል አመራር ችግሮችን ለመፍታት ተነስቶ ሲያበቃ ፖሊሲዎቹን ይዘነጋል ለማለት ቢከብድም ኢህአዴግ የተጀመረውን ማስቀጠል አለብኝ በማለቱ ዋናውን የለውጥ መሣሪያውሳይጠቀም በምን መንገድ ለውጥ እንደሚያመጣ አልታወቀም። ሆኖም የኢህአዴግ ፖሊሲዎች እንከን የለባቸውም፥ ችግሩ የአመራር ድክመት ነው የሚለው ድምዳሜ የግምገማውን ትኩረት በአመራሩ ዙርያ ብቻ ወስኖ በማስቀረት የፖሊሲዎቹ እውነተኛ ይዘትና የሚያስከትሏቸው ውጤቶች ሳይፈተሽ እንዲቀር አድርጎታል። በሌላ በኩል አንድ መሪ ችግሮችን ለይቶ መፍትሔ የሚሰጥ መሆን እንደሚገባውና ኢህአዴግ ውስጥ ያለው አመራር ይህን ማድረግ ባለመቻሉ የአመራር ውድቀት ማጋጠሙን የተገነዘበና ለውጥ ማምጣት አለብን የሚል ኃይል ተፈጥሯል። ከግምገማው በኋላ የኢህአዴግ አመራር ከደረሰባቸው ድምዳሜዎች አንዱም አገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በፈጠረው ተስፋና የፖለቲካ ችግሮች በደቀኑት ስጋት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች የሚል ነበር። ከዚህ ድምዳሜ በስተጀርባ የድርጅቱ የቆየ እምነቱ አለ፤ ኢህአዴግ የአፈጻጸም እንጂ የፓሊሲ ችግር የለበትም የሚል። በዚህ ጽሑፍ እንዲያውም የኢህአዴግ ዋነኛ ችግር ፖሊሲዎቹ መሆናቸውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተያዘውን መንገድ በምሳሌነት በማንሳት አስረዳለሁ። በመቀጠል የኢህአዴግ አመራር አለብኝ የሚለው ዋነኛ ችግር የአመራር ድክመት ቢሆንም ከዚያ ይልቅ ለእውነተኛው ችግር የሚቀርቡ፥ ነገር ግን በግምገማው ሳይነሱ አልያም በማብራሪያው ሳይጠቀሱ የቀሩ የኢህአዴግ ድርጅታዊ መዋቅርና የአባል ድርጅቶችን ግንኙነት የሚመለከቱ ነጥቦችን አነሳለሁ። በመጨረሻም ኢህአዴግ የእውነት ለኅበረተሰባዊ ለውጥ የተሰጠ ከሆነ ከአለቆቹ የገንዘብ ተቋሞች ተቀብሎ በአገራችን ላይ የጫናቸውን ፀረ ድኻ ፖሊሲዎች ፈትሾ ለማስተካከል መድፈር እንዳለበትና የምር እታደሳለሁ ካለም ራሱንም ውስጡ በበቀለው የአገራዊነትና ሕዝባዊነት መንፈስ ለመቃኘት መድፈር እንደሚገባው እጠቁማለሁ።

 

1.1 የኢህአዴግ የእርሻና የምግብ ዋስትና ፖሊሲ

ኢህአዴግ የአፈጻጸም እንጂ የፖሊሲ ችግር የለብኝም ሲል ራሱን የትክክለኛ ፖሊሲዎች ባለቤት አድርጎ ያቀርባል። ምን ያህል እውነት ነው? የእርሻውን ዘርፍ ባጠቃላይና በተለይም የምግብ ዋስትናን የሚመለከቱ ፖሊሲዎቹን በምሳሌነት በማንሳት እንመዝነው።

ኢህአዴግ “ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ሚስጥር ነው” ማለቱን ገና አሁን መጀመሩ ቢሆንም እስቲ ኢትዮጵያን ብቻ የሚመለከት አንድ ያደባባይ ሚስጥር እናንሳ። ኢህአዴግ አለኝ በሚለው ፖሊሲም ሆነ በሚያቀርበው የኢኮኖሚ እድገት ዜና፥ በማንም ምስክርነት ሊቀየር ያልቻለ ሁሉም የሚያውቀው አንድ እውነታ ቢኖር ያገራችን ሕዝብ የሚበቃውን አምርቶና በልቶ ተመስገን ብሎ እንዲያድር አለመደረጉ ነው።

ከሌላው አገር ሁሉ ተለይታ “እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የተባለላት አገራችን፥ ከሌላው ሕዝብ ተለይተው እግዚአብሔር “ምግባቸውን ሰጣኻቸው” የተባለላቸው ልጆቿ የሚበሉትን ለመለመን ካመት ዓመት ባለስልጣኖቿ እጆቻቸውን ለፈረንጆች ምፅዋት ዘረጉ ሲባል ሰሚ ተመልካቹን ‘አምላካቸው ወዴት አለ?’ ለማሰኘት ያለመ የጠላት ሥራ ይመስላል። በዚያ ላይ ከሷ ሌላ ማንም አገር ያለማቋረጥ እጆቿን ለምግብ ርዳታ ዘረጋች ሲባል አለመሰማቱ ‘እውነትም ጠላት አለቆቿን ቢያሞኛቸው’ ነው ያሰኛል። ባይሆን ታዲያ በቂ መሬት እንዳለን ይታወቅ የለም? እነሆ ሳውዲ አረቢያ ዜጎቿን ለመቀለብ የኢህአዴግ መንግሥት “የመጣል ያክል” በተባለለት የሞተ ዋጋ ከሚቸበችበው መሬት ተከራይታለች። ውሃም ቢሆን ከዝናቡ በተጨማሪ ብንፈልግ ጠልፈን የምናመርትበትን እግዚአብሔር ሰጥቶናል። እነሆ ግብጽ እንኳ ከኛ ፈልቆም ዘንቦም ከሚጎርፍላት ውኃ ለራሷ በልታ ለሌላም ትሸጣለች። [ራሺያ የአውሮፓ ምርት አገሯ እንዳይገባ ማዕቀብ በጣለች ጊዜ ለፍራፍሬ አቅራቢነት ግብጽን መምረጧ ይታወቃል።] አሁንማ ጭራሽ ፍራፍሬዋን፥ (አፕል ተብርቱኳን) ወደኛው መላክ ጀምራለች። እንግዲህ እኛ መሬቱም ሆነ ውኃው ሳይቸግረን ለራሳችን የሚበቃ ያክል እንኳን ማምረት ያልቻልንበት ምክንያት ምንድነው? ባንድ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሦስቴ እንዲበላ አደርጋለሁ ሲል የተናገረ የኢህአዴግ መንግስት ሌሎች አገሮች እዚህ ድረስ መጥተው የሚያደርጉትን ማድረግ፥ ማለትም ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚበቃ የምግብ እህል አገር ውስጥ ማምረት እንዴት ያቅተዋል? በዚያ ፋንታ የትም የተመረተ እህል በምጽዋት ብር እየሸመተ ማስገባቱን ለምን መረጠ?

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ቢያንስ ሁለት አማራጭ መንገዶችን ሊከተሉ ይችላሉ። አንዱ የዓለም ገበያን እንደ መፍትሔ የሚያቀርበው፥ ለዓለም ገበያ እያመረቱ ከዚያውም እየሸመቱ መብላትን የሚመክረው [የኒዮ ሊበራል] መንገድ ሲሆን፥ ሁለተኛው ላገር ውስጥ ፍጆታ በራስ አገር ውስጥ በማምረት የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ መንገድ ነው። የመጀመሪያው አማራጭ የገበያ ኃይሎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይችላሉ ከሚል እምነት የሚንደረደር ሲሆን፤ የምግብ ዋስትናንም በዓለም ገበያ አማካይነት በዓለም ደረጃ ለማረጋገጥ የሚያልም ነው። ስለሆነም ገበሬው ለገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲያመርትና ያን ሽጦ በሚያገኘው ገንዘብ ደግሞ ለራሱ የሚሆነውን ምርት እንዲገዛ የሚመክር ነው። ሁለተኛው የምግብ ሉዓላዊነት አማራጭ በበኩሉ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት እያንዳንዱ አገር ባለው የተፈጥሮ ሀብት ለራሱ የሚመገበውን ለማምረት ሲችል ብቻ የሚሳካ መሆኑን፥ እያንዳንዱ ማኅበረሰብም ሆነ ቤተሰብ ለራሱ የሚፈልገውን የምግብ ዓይነት በሚፈልገው መጠን እንዲያመርት ሲደረግ የምግብ ዋስትናው እንደሚረጋገጥ ያስረዳል። ይህ አማራጭ እንደ አገር ነጋዴ መሆን ሳያስፈልግ ሰርቶ፥ አርሶና አርብቶ፥ በልቶ ማደር ሊባል ይችላል። በአንጻሩ ገበሬው ለገበያ በተለይም ለዓለም ገበያ እንዲያመርት ሲደረግ ባንድ በኩል ለምርቱ ደህና ገዢና ደህና ዋጋ የማግኘት ዕድሉ፥ እንዲሁም ለራሱ የሚያስፈልገውን ምርት የሚገዛበት ዋጋ ተለዋዋጩን የዓለም ሁኔታ ተከትሎ መዋዠቁ እንደማይቀር ይታወቃል። እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ፖለቲካዊ፥ ኢኮኖሚያዊና የተፈጥሮ ሁኔታዎች በዓለም ገበያ ላይ፥ ብሎም በገበሬው ገቢና እንጀራ [የምግብ ዋስትና] ላይ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል። ስለሆነም ኑሮው መቼም ከስጋት ሊላቀቅ አይችልም። ገበሬው ለራሱ የሚመገበውን አምርቶ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ በልቶ ማደር እንደሚችል ግልጽ ነው።

ዛሬ በኢህአዴግ ፊታውራሪነት በአገራችን የሚተገበረው የገበያው መንገድ የምግብ ዋስትናችንን ጉዳይ ከዓለም ገበያ ጋር የሚያቆራኘው አማራጭ ነው። አተገባበሩም የገበሬውን ፍላጎት የሚከተል አይደለም።  ይልቁንም የምግብ ዋስትና ጉዳይ ከዓለም ገበያ ጋር ማቆራኘቱ አምራቹን ገበሬ ከከተሜው እኩል የምግብ እህል ሸማች ሆኖ እንዲሰለፍ ስለሚያደርግ በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትና ሊረጋገጥ አለመቻሉ ነው።

የግብርናውን ዘርፍ በትራንስፎርሜሽን እቅዱ እንደሚመራ የሚታወቅ ሲሆን የዕቅዱን ትግበራ የሚቃኘው እኤአ ሚያዝያ 2012 የቀድሞው ጠ/ሚ/ር የፈረሙትና በስፋት የማይታወቀው “ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና የቡድን 8 አዲስ ዕቅድ” [G8 New Alliance for Food Security and Nutrition in Africa] የተሰኘው ስምምነት ነው። በባራክ ኦባማ ሰብሳቢነት የአፍሪካ አገራት መሪዎችና የድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች በተገኙበት በተካሄደ ስብሰባ የተቀረጸው ስምምነት ቡድን 8 አገራት ርዳታ ሊያቀርቡ፥ ምዕራባውያን ኩባንያዎች ኢንቨስት ሊያደርጉ፥ የአፍሪካ አገራቱ [ያኔ ጋና እና ኢትዮጵያ] በበኩላቸው ለግሉ ዘርፍ የሚመቹ የፖሊሲ ማሻሻያ ሊያደርጉ ቃል የገቡበት ነበር። ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ 15 ዝርዝር እርምጃዎችን ያቀፉ አራት ግዴታዎችን ይጭናል፦ 1) የግሉ ዘርፍ በየዕጽዋት ዘር ማባዛትና ስርጭት ላይ እንዲሳተፍ ማሰቻል [አዲስ የዕጽዋት ዘር ሕግ ማውጣትን ይጨምራል] 2) የግሉ ዘርፍ ገበያ ውስጥ ለመግባት የሚከለክሉ እንቅፋቶችን መቀነስ [የማዳበሪያና ጸረ ተባይ ኬሚካሎች የሚመለከቱ የፖሊሲ ማስተካከያዎች ማድረግን ይጨምራል] 3) በእርሻው ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የመሬት ይዞታ መብቶችን ማጠናከር፤ 4) የግብርና ብድር አቅርቦት መጨመር።

በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ የየዕጽዋት ዘር ገበያውን ለግሉ ዘርፍና ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የተመቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን መውሰድ ነበረባት። በመሆኑም የኢትዮጵያ የየዕጽዋት ዘር አቅርቦትና ገበሬው የሚያመርተውን የሚወስኑ፥ ለገበሬው የሚቀርቡ ግብአቶችንና አቅራቢዎቹን፥ ገበያውንም ሁሉ የሚመለከቱ ህጎችና ደንቦች ወጥተዋል። የውጭ ኩባንያዎች የሚያቀርቡት ‘የዕጽዋት ዘር’ እንደ ተራ ሸቀጥ በየሱቁ እንዲቸረቸር የሚያስችሉ “ቀጥታ የዘር ሽያጭ” የተባለ አሠራር ሁሉ ተዘርግቶላቸዋል። [የስምምነቱ ዓላማ በኢትዮጵያ በአስር ዓመታት ውስጥ 2.9 አነስተኛ አርሶ አደሮችን ከድኽነት ማውጣት ሲሆን ኢትዮጵያ የምታደርጋቸው የፖሊሲ ለውጦች ግን የጊዜ ገደብ ያልተበጀላቸውና የሁሉንም ገበሬ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ህይወት የሚነኩ መሆናቸው በአዲሱ የዕጽዋት ዘር ሕግ ለመረዳት ይቻላል። ለምሳሌ ስምምነቱ መሰረት በፍጥነት የወጣው አዲሱ የዕጽዋት ዘር ሕግ ጤፍን ጨምሮ የአገራችንን የዕጽዋት ዘር በሙሉ በድንጋጌዎቹ ስር የሚያስገባ ሲሆን የቀድሞው ግን የተመዘገቡ የዕጽዋት ዘርን ብቻ የሚመለከት ነበር።] ስምምነቱ ትኩረቱን ሁሉ በዓለም ገበያ ላይ ካደረገው ዕቅድ ትግበራ ጋር ተቀናጅቶ የሚፈጸም ሲሆን ሕጎቻችንንም ከአፍሪካ አህጉራዊ ውሎች ጋር እንዲስማሙ የሚያደርግ ነው። በዚያ መሠረት ገበሬው የማይፈልገውን እንዲያመርት ከመገደዱም በላይ እንደለመደው ያገሩን ነባር የዕጽዋት ዘር ለማምረት እንዳይችል የሚያደርጉ የፖሊሲ ለውጦች ተደርገዋል። በዚያው ስምምነት መሠረት የየዕጽዋት ዘርና የማዳበሪያ ገበያው ለትላልቅ ዓለም አቀፍ ምዕራባዊያን ድርጅቶች ክፍት ከመደረጉም በተጨማሪ ገበሬው የዕጽዋት ዘርን ያክል ነገር እንደ ኦሞና ሳሙና ከየሱቁ እንዲገዛ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል። ምርጥ ዘራችሁ ይቅርብኝ አልፈልግም፥ ነባሩን ያገሬን ዘር ዘርቼ እበላለሁ የሚለውንም ነባሮቹና “የገበሬው” የሚባሉት “ምርጥ” ዘር በመደበኛው የዕጽዋት ዘር ገበያ አማካይነት ለገበሬው ስለማይደርሱት ወደደም ጠላ ገበሬው የማይፈልገውን የዕጽዋት ዘር እየገዛ እንዲዘራ መሬቱንም ያልፈጠረበትን የማዳበሪያ ሱስ እንዲያስለምድ ተደርጓል። ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያስፈልጋል በማለት የሚከራከሩ ወገኖች የሕዝብ ቁጥር መጨመርና ነባሩን አዝርዕትና ያለማዳበሪያ ቢዘራ ሊገኝ የሚችለውን የምርት መጠን አናሳነትን ማዳበርያና ምርጥ ዘር ሲተባበሩ ከሚሰጡት ከፍትኛ መጠን ጋር በማነጻጸር ያነሳሉ። ሆኖም ለገበሬው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ቀርቦለት የሚያመርተው ለራሱ የሚፈልገው ሳይሆን ለዓለም ገበያ የሚሸጥ በመሆኑ ያሳሰባቸው የሕዝብ ቁጥር ጉዳያቸው እንዳልሆነ በድርጊት ያረጋግጡታል።

የግብርና ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ በኢህአዴግ ፓሊሲና በገበሬው ፍላጎት መካከል ያለውን ሰፊ ክፍተት የሚያስረዳ በዝናብ አጠር አከባቢ የተስተዋለውን ሁኔታ የሚመለከት አስተያየት ሰጥተው ነበር። [ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ምሽት] የኢቴቪ ጋዜጠኛው አርሶ አደሩ የሚቀርብለትን የዕጽዋት ዘርና ማዳበርያ የመግዛት ፍላጎቱ ቀንሷል መባሉን ጠቅሶ ምክንያቱን ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ. . . በዝናብ አጠር አካባቢ ያለው ገበሬ የሚቀርብለትን የዕጽዋት ዘር ገዝቶ እንዳይከስር ስለሚፈራ፥ በጁ ያለችውን ምርታማነቷ አነስተኛ ቢሆንም ችግር መቋቋም የምትችለውን ዘር ለመዝራት እንደሚመርጥ፥ ማዳበሪያም እንደዚሁ እንደሚያስፈራው ገልጸው፥ ችግሩን ለመፍታት [ችግር የተባለው ምርጫው መሆኑ ነው] ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ እዚያ ያለው ባለሙያ ደግሞ አሳምኖ መሄድ አለመቻሉን ከጠቀሱ በኋላ፤ ዝናብ አጠር ለሆኑ አካባቢዎች የሚሆን ዘር ማቅረብ ባለመቻሉ ዝናብ አጠር ግብርና ለብቻው መሆን እንዳለበት፤ ካልሆነ ግን ኮሜርሻላይዝ ማድረግ እንደሚያስቸግር ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ፖሊሲውና ገበሬው አልተገናኙም። በግንዛቤ ማስጨበጫ ለማገናኘት መሞከርም ገበሬውን ደንቆሮ ከማለት አይተናነስም።  የመሬቱንና ያካባቢውን ባሕሪ ከማንም በላይ ጠንቅቆ የሚያውቀው ዝናብ አጠር አካባቢ ያለው ገበሬ በተለይ ለአካባቢው የሚሆን ዘር ከምርምር ተቋሞች ጋር በመተባበር ለማዘጋጀት እድል ቢያገኝ አይጠላም። ሆኖም ከውጭ የሚመጣውም ሆነ ካንዱ የምርምር ተቋም ገብቶ የወጣና በውድ ዋጋ የሚሸጠው ዘር እንደማይሆነው ነጋሪ አይፈልግም። ደግሞስ የገዛ መንግሥቱ የሚሆነውን በማቅረብ ፋንታ የማይሆነውን አሳምኖ እንዲቀበል ለማድረግ ከሞከረ ገበሬው ለራሱ ማሰብ እንዳለበት አያጣውም። ታዲያ ላካባቢው የሚስማማ ዘር በማቅረብ ፋንታ ገበሬው የማይሆነውን ዘር ተቀብሎ እንዲወስድ ለማድረግ ባለሙያው ምን ብሎ ሊያሳምነው ይችላል? ባለሙያው ተሳክቶለት ገበሬውን ለማሳመን ቢችልም የተቀየሰው መንገድ የገበሬውን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ይልቅ ገበሬውን የየዕጽዋት ዘር እና ማዳበሪያ ሻጭ ድርጅቶች ደንበኛ ብሎም ጥገኛ እንዲሆን ያስገድዳል።

እንግዲህ የኢህአዴግ መንግሥት እንደሚለው በርግጥ የፖሊሲ ችግር ከሌለበት የአገራችንን ዋነኛ የምግብ እጥረት ችግር በዘላቂነት በመፍታት ፋንታ ገበሬው የማይበላውን እንዲያመርት፥ የማይሆነውን እንዲዘራ እያስገደደ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ለዓለም ገበያና ለምጽዋት ቋሚ ጥገኝነት የሚዳርግ ፖሊሲ የተከተለበት ምክንያት ምንድነው?

ይህን እየፈቀዱ ፖሊሲያችን ምርጥ ነው ማለት፥ ይህን እያደረጉ ኒዮ ሊበራሊዝምን እጠላለሁ ማለት ጨዋታ ነው። ምክንያቱም ኒዮ ሊበራሊዝም ማለት በዜጎች ኑሮ ውስጥ የመንግሥት ሚና ውሱን መሆን አለበት፥ ነጻ ገበያ ይስፋፋ፥ ድንበሮች ለዓለም ገበያ ክፍት ይሁኑ የሚል አስተሳሰብ ነው። ኢህአዴግ እገነባዋለሁ የሚለው የገበያ ሥርዓትና ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ ገበያ የማስተሳሰር ዓላማው መንግስትን የሃብታም ንብረት ጠባቂ የሚያደርግ ነው። ሆኖም ኢህአዴግ ካፒታሊዝምን እየገነባም ቢሆን ልማታዊ ነኝ ይላልና፥ ልማታዊ መንግሥት ማለት ደግሞ ከተራ መንግሥታዊ ዘበኝነት የተሻለ ሥራ መሥራትን የሚጠይቅ ከሆነ ኢህአዴግ ይህን ከማድረግ ማን ከለከለው? የኒዮሊበራል ኃይሎችን “ምክር” እና ትዕዛዝ ካልሰማና ካልተከተለ በቀር ማንም ከልካይ የለውም። የኒዮሊበራል መርህ አራማጅ አገሮች/ድርጅቶችን ጫና የማይቋቋም፥ ይልቁንም አጥፊ ትዕዛዛቸውን የሚቀበል መንግሥት ደግሞ ቢያንስ የግብርናውን ዘርፍ በሚመለከት መሪነቱን ተነጥቆ የዘበኝነት ሚናውን ፈቅዶ ተቀብሏል ማለት ነው።

እዚህ ላይ አንዲት ነጥብ በቅንፍ አስቀምጬ እንዳልፍ ይፈቀድልኝ። [ዛሬ ኋላ ቀር ሲል ተሳድቦ ላሰልጥን የሚል ደፋር፥ ድኻ ሲል አዋድቆ ላበልጽግ የሚል ጥጋበኛ በዝቷል። ለብልጽግናውም ሆነ ለስልጣኔው የሚቀርብልን መፍትሄ ዘራችን እንዳይበዛ መሆኑ  ደግሞ ይገርማል። ሳር ቅጠሉ አትዋለዱ ባይ ነው። የቤተሰብ ምጣኔ ለኢኮኖሚ ዕድገት ይጠቅማል፤ አለመውለድ ዘመናዊነት ነው። ኢህአዴግም በበኩሉ ስልጣንን ለዝርፊያ ብንጠቀምበትም የኢኮኖሚ እድገት አምጥተናል፥ የተጀመረውን እድገት ለማስቀጠል የሚያስችል ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ ይዘናል፤ ይኸውም አገራችን ለውጭ ኢንቨስተር የተመቸችና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ማድረግ ነው ብሎናል። ታዲያ በፈጣን እድገት አስጎምዢውም ሆነ በአዘማኙ ሁሉ አለብን ለሚሉት ችግር ማስረጃ ተብሎ የሚጠቀስብን በአገራችን ስም ለምጽዋት የተዘረጋው የባለስልጣኖቻችን እጅ መሆኑን ልብ ማለት ነው. . . ስለሆነም ከአሁን በኋላ ስማችን ከምግብ ዕጦት ጋር ተነሳ ብለን ልንቆጭ አይገባም። በፍጹም! ይልቁንም ስማችን ከዕጦት ተያይዞ መነሳቱን ብንሰማ መንግሥት የመረጠውን የተሳሳተና፥ ፈረንጅ—ሰራሽ የእርሻ ፖሊሲ ማስታወስና የተሻለ ማድረግ እንደምንችልም መገንዘብ ይስፈልጋል።

ዋናው ነጥብ ግን የኢህአዴግ ፖሊሲዎች እንከን የለባቸውም፥ ችግሩ የአፈጻጸም ነው የሚለው የተለመደው ክርክር ስህተት መሆንኑ ለማየት መቻላችን ነው።

 

1.2 የፖሊሲዎቻችን እውነተኛ ባለቤቶች እነማን ናቸው?

ከዐድዋ ድል በኋላ በቁጭትና ስስት ኮርኳሪነት ኢትዮጵያን ለመውረር ከመነሳትዋ በፊት ኢጣሊያ በአገራችን ላይ የከፈተችው የወሬ ጦርነት ነበር። ዋናው ክስ የባርያ ንግድን ማስረጃ በማድረግ የታቀርበው ኢትዮጵያን አልሰለጠነችም የሚለው ነበር።  ክሱ በወቅቱ አውሮፓውያን በአፍሪካና እስያ ሕዝቦች ላይ አለን ይሉት በነበረው የበላይነትና የማሰልጠን መብት ላይ የተመሠረተ ነበር።  አውሮፓውያን ሁሉ የሚያምኑበትና የሚመሩበት አስተሳሰብ አውሮፓዊ ካልሆነው ዓለም ጋር ያለውን የባህል ተለያይነት የበላይ/በታች መለኪያ አድርጎ የራሳቸውን የሰለጠነ/የበላይ፥ የሌላውን የበታች የሚል ነበር። በመቀጠል ሁሉም ባህል የአውሮፓውን እንዲመስል ሊሻሻል ይገባል፤ ህጎቹ፥ አሰራሮቹ ሁሉ ሊቀየር ይገባል። ይህን የማድረግ ኃላፊነቱንም ለራሳቸው ሰጥተው በጉልበት ቅኝ የሚገዙትን ሕዝብ ከኋላ ቀርነት በማላቀቅ ውለታ እንደዋሉለት ያደርጉ ነበር። የጣልያንም ክስ ይኸው ዓላማና ግቡ ያው ነበር። ሊበሏት ያሰቧትን ቆቅ እንዲሉ አልሰለጠነችም ማለቷ ‘ላሰልጥን’ ለማለት፥ ለማሰልጠን ደግሞ ቅኝ መያዝ ይገባኛል ለማለት ነበር። ሞከረች፤ አልሆነም። ይመስገነው!

ለመሆኑ ቅኝ መግዛቱ ቢሳካላት ምን ልታደርግ ኖሯል? የታሰበ የተሠራውን ያጠና አልቤርቶ ሳባቺ [Ethiopian Under Mussolini ከሚለው መጽሐፉ] ይንገረን፦

የሙሶሊኒ ዓላማ የምስራቅ አፍሪቃ ግዛቱ በምግብ ራሱን እንዲችልና በሚተርፈውም ለአባት አገሩ [ኢጣሊያ]

ቀለብ በማቅረብ በየዓመት ለምግብ እህል ግዢ የሚመደበውን 2.5 ቢሊዮን ሊሬ ወጪ እንዲቀንስ ነበር።

በተጨማሪ ታዋቂዎቹን የኢትዮጵያን ምርቶች [ቡና፥ ቆዳ፥ የጥርኝ ዝባድ፥ ሰም፥ እህል] ለውጭ አገሮች በመሸጥ

የሚገኘው ገቢም ለኢጣሊያ ኢኮኖሚ በጣም ተፈላጊ የውጭ ምንዛሪ ያስገኝለታል። [95] ያጭር ጊዜ

ዕቅዱ ግን በግዛቱ ለሚገኙት የጣልያን ስደተኞች ማረፊያ በመስጠት ያገር ቤቱን የሥራ አጥነት ችግር

መፍታት ነበር። በፖለቲካና በባህል ረገድም ኢትዮጵያ የኢጣሊያና የፋሽስት ስልጣኔን ወደ አፍሪካና እስያ

ለማሰራጨት ማዕከል ተደርጋ ትታይ ነበር። በተጨማሪ ምንም እንኳ ለኢጣሊያ ጥቅም ሲባል

የታቀደ ቢሆንም ከሰብአዊ፥ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መርሆች አንጻር የእርሻን ምርታማነት በመጨመር

ኢኮኖሚውን ከጅ ወዳፍ ወጥቶ ሞልቶ እንዲተርፈው በማድረግ የኢትዮጵያዊያንን ሕይወት ማሻሻል

አስፈላጊ ነበር። የኢትዮጵያ እህል ለጣልያኖች እንዲሸጥ በማድረግ የባላገሩን አማካይ ገቢ እንዲጨምር

ያደርጋል። [ገጽ 95]

በዚያ መሠረት ግብርና ላይ ለመሠማራት ፈቃደኛ የሆኑ የኢጣልያን ዜጎች መምጣት ጀመሩ። ሲመጡ ብድር ይመቻችላቸዋል፤ መሬት (በሊዝ) ይሰጣቸዋል፤ ቤት መስሪያ ይሰጣቸዋል፤ የርሻ ማሽን ይቀርብላቸዋል። ለጉልበት ሥራው ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ አሉላቸው። ሁሉ ምሉ፤ ሁሉ ዝግጁ። በአንጻሩ ያገሬው ሰው ከርስቱና ከቀዬው ይነቀላል። እንደነገሩ ካሳ ይከፈለዋል። ከዚያም ደመወዝ እየተከፈለው ለባለሃብቱ ከበርቴ በጉልበቱ እያገለገለ እየተገዛ ይኖራል። ፖሊሲው ኢትዮጵያዊውን በገዛ አገሩ የበይ ተመልካችና ሁለተኛ ዜጋ ተደረገ።

 

በፋሽስት ዕቅድ መሠረት ጣልያናዊው መጀመሪያ ጭሰኛ ቀጥሎም ባለመሬት ሲሆን በአንጻሩ

ኢትዮጵያዊው ከባለመሬት ወደ ቀን ሰራተኝነት ተሸጋገረ። ከመንግሥት የእርሻ ድርጅቶች

ጋር በተነደፈው የቅኝ ግዛት መርሐ ግብር መሠረት የኢጣሊያዊው ገበሬ ፍላጎት ከመሬቱና

ከሚሰበሰበው ሰብል በትንሽ ወጪ ከፍ ያለ ትርፍ ለማግኘት ነበር። በዚህ የኢኮኖሚ

ሂደት ወጪ ለመቆጠብ ለኢትዮጵያውያኑ የሚከፈለው ደመወዝ መቀነስ ነበረበት። ስለሆነም መሬቱን

አላግባብ በተቀማው፥ በተጭበረበረውና ከሚገባው በታች በሚከፈልው ኢትዮጵያዊ ገበሬና በቅኝ ገዥው

መካከል የነበረው ግንኙነት በውጥረት የተሞላ ነበር። [238]

ለዚህ ነበር ኢጣሊያ ያን ሁሉ ወታደር አስታጥቃ፥ መድፎቿን በ’ቄስ’ አስመርቃ፥ ባህር አቋርጣ መጥታ ያን ሁሉ ደም ያፈሰሰችው — አገሪቱን የሚበዘብዙ ፖሊሲዎችን ያለ ተቃዋሚ ለመተግበር፤ የኢትዮጵያን መሬትና የአየር ንብረት፥ የሰው ኃይልና የየዕጽዋት ዘር ሀብት ለኢጣልያ ሕዝብ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል። ኢጣሊያ ፖሊሲዋን ለመተግበር ተጣጣረች፤ አልተሳካላትም። እግዚአብሔር ይመስገን!

ሆኖም ዛሬሳ በአገራችን ፖሊሲ ላይ የፈረንጅ ተጽዕኖ ምን ይመስላል? ያለን ፖሊሲ የአገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በዓለም ገበያ ላይ እንዲያተኩሩ ያደረገና የማታማታ አገራችንን ለጥገኝነት የሚዳርግ፥ ሕጎቻችንንም ለኢንቨስተሮች ምቾት ሲባል እንዲሻሻሉ ያደረገና ገበሬውን ለየዕጽዋት ዘር ጥገኝነት፥ ቀዬውንም ለማዳበርያና መድኃኒት ብክለት የሚዳርግ ነው። በመሆኑም የአገር ሀብት ለአገር ጥቅም እንዲውል ከማድረግ ይልቅ የራስን አዘርፎ የባዳ እጅ የሚያስጠብቅ ነው። ትላንት ወራሪው ፈረንጅ የአያሌ ኢትዮጵያውያንን ደም አፍስሶ ያልሆነለትን ነገር ዛሬ የልጅ ልጁ ኢንቨስተር ተሰኝቶ በዲፕሎማቶቻችን ግብዣ ይደረግለታል፤ ያገር ፖሊሲም ለሱ ሲባል ይከለስለታል። እንዴት ሊሆን ቻለ?

አንድ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ደግሞ ሌላ ጸሐፊ ያብራራልን፦ [Antony Anghie “Imperialism, Sovereignty and the Making of International Law”]

ጸሐፊው በጥናቱ የደረሰበት ዋና ድምዳሜ ዓለም አቀፍ ሕግ የ3ኛው ዓለም አገሮችን ሉዓላዊነት በመደፍጠጥ የጥንቱን የቅኝ ግዛት ዓላማ ለማራመድ የሚጠቅም ተቋም ሲሆን የዓላማውም አስፈጻሚዎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ናቸው፥ የሚል ነው። ዓለም አቀፍ ሕግ የዱሮውን የቅኝ ግዛት ዓላማ ዛሬ በዓለም አቀፍ ገንዘብ ተቋሞች [ዓገተ] በተለይም በአይኤምኤፍና ዓለም ባንክ አማካይነት እንዲቀጥል ለማድረግ የሚጫወተውን ሚና ያስረዳል፤ የተኬደባቸውን መንገዶች ያስጎበኛል። ዱሮ በቅኝ ግዛት ዘመን ምዕራባዊያን ባህላቸው ከአፍሪካና እስያው ዓለም ባህል በመለየቱ ብቻ ስልጡን [የበላይ] የሌላውን ያልሰለጠነ [የበታች] አሉት። ቀጥለው የማሰልጠን ኃላፊነት አለብን ሲሉ ያልሰለጠነ ባሉት ሕዝብ ላይ ራሳቸውን ባለመብት አድርገው በመሾሙ ቅኝ መግዛት ነበር። የቅኝ ግዛት ጊዜ አበቃ ከተባለ በኋላ ደግሞ ምዕራባውያኑ አሁንም ራሳቸውን ‘ያደጉ’ አገሮች ብለው ሌላውን ህዝብ ‘ያላደገ’ [ወይም ታዳጊ] ብለዉት ሲያበቁ ደግሞ የዕድገት መንገዱን የማሳየትና በኢንቨስትመንትም የማገዝ ኃላፊነቱን ይዘናል አሉ። ራሳቸውን የልማት መንገድ ፋና ወጊና መንገድ መሪ፥ የልማትን ትርጉምና መለኪያዎችም አመንጪ ሆነው ቀርበዋል። ውለው አድረውም የሞግዚትነት አገልግሎታቸውን በያገሩ አዳርሰዉታል።

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶቹ ልማት ለማምጣት ያዘጋጁትን ፖሊሲ ከነብድሩ በማቅረብ የኛን ጨምሮ አያሌ ‘ያላደገ’ አገር ካጋጠሙት ጊዜያዊ ችግርች ጋር በእነሱ ጫና የሚሉትን ተቀብሏል። አንዴ ወጥመዳቸው ውስጥ በመግባቱም ሉዓላዊ አገር ነኝ ሲል በገንዘብ ድርጅቶቹ ቁጥጥር ሥር ወድቆ ይገኛል። ስለሆነም ይላል ጸሐፊው ስልጡንና ያልሰለጠነ በሚለው ምደባ ላይ የተመሠረተው የዱሮው የማሰልጠል ተልዕኮ [civilizing mission] ለቅኝ ግዛት መነሻ ኾኖ እንዳገለገለ ሁሉ ያሁኑ “ያደጉ” እና “ያላደጉ” የሚለው ምደባ የወለደው ዕድገት የማምጣት ጥረትም በገንዘብ ድርጅቶቹ የልማት አጋርነት አማካይነት የእጃዙር ቅኝ ግዛት ዓላማ በማራመድ ላይ ይገኛል። ዱሮም ቢሆን ቅኝ ገዢዎቹ ከቅኝ ግዛቶቻቸው የሚፈልጉት ጥሬ ዕቃቸውን፥ ሸቀጥ የሚያራግፉበት ገበያቸውንና ርካሽ የሰው ኃይላቸውን ነበር። ዱሮ ገዥዎቹ ሰፋፊ እርሻ ሲያለሙ ወይም ማዕድን ሲያወጡ ያገሩን ሰው ይዘው በጉልበት ያሠሩት ነበር፤ ቢበዛ ሆዱን ቢችሉት ነው። ዛሬ ደግሞ ኢንቨስተሩ ፋብሪካ ሲከፍት፥ ማዕድን ሲያወጣ፥ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ምርት ሲያመርት ለአገሪቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራላቸዋል ይባላል። ያውም ዘንዱሮ ለሰራተኛው የሚከፈለው ደመወዝ በልቶ ለማደርም አይበቃ።

 

የሚገርመው ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በተለይ ኢኮኖሚን በሚመለከት የራሱን ፕሮግራም ተከትሎ የሠራበት ጊዜ አለመኖሩ ሊሆን ይችላል። ላስረዳ። የኢህአዴግ የትግል ጊዜ ዓላማ በፖለቲካው ረገድ ‘የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝብ ጠላቶች የሆኑትን አሜሪካ-መራሹ የምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም፥ ሶቭየት-መራሹ የምስራቅ ኢምፔሪያሊዝምና ያገር ውስጡ የመንግስት ካፒታሊዝም ማስወገድ፤ የጭቁን ሕዝቦችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነጻ የሕዝብ መንግሥት ለማቋቋም መታገል፤ በኢኮኖሚውም የጥገኛ ካፒታሊዝምና የኢምፔሪያሊዝም የግል ንብረት ባለቤትነት መብት መደምሰስ፥ የአገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድ ከኢምፔሪያሊዝም ጥገኝነት ነጻ ማውጣት’ የሚሉትን ያካተተ ነበር።

ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም ገና ስልጣን ከመያዙ “የኢምፔሪያሊዝም ተቋሞች” በሚላቸው አይ ኤም ኤፍና ዓለም ባንክ ተጽዕኖ ዓላማዎቹን ትቶ በሌላ ለውጧል። “ዲሞክራሲና ሉዓላዊነት በኢትዮጵያ” በተባለው መጽሐፋቸው የቀድሞው ባለስልጣን አቶ ገብሩ አስራት እንደሚሉት ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣ የርዕዮተ ዓለም ቀውስ ውስጥ ገብቶ ነበር። ምክንያቱም ኢህአዴግ ከበረኻ ይዞት የመጣው ለጭቁን የሚያደላው ሃሳብ ምዕራባውያኑ ግድ ከሚሉት እርምጃ ጋር ለማስታረቅ የማይቻል በመሆኑ ነበር። ኢህአዴግ ‘መንግሥት ገዢ የኢኮኖሚ ተቋሞችን መቆጣጠር አለበት’ ይላል፤ በአንጻሩ አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ “መንግስት ወሳኝ የኢኮኖሚ ተቋሞችን መቆጣጠር የለበትም፤ እንዲያውም መንግሥት ከምርትና ከንግድ ተቋሞች እጁን በማውጣት መድረኩን ለግል ባለሀብቱ ክፍት ማድረግ አለበት” ባዮች ናቸው።

ኢህአዴግ ‘ኢምፔሪያሊዝም በኢኮኖሚ እንቅስቃሴያችን ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተጽዕኖ’ ለመቋቋም መዘጋጀት አለብን ባይ ነበር። “ይሁን እንጂ ተቋማቱ ኢህአዴግ በኢኮኖሚው ዘርፍ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ አስገዳጅ መመሪያ ሲሰጡ ያለምንም ማንገራገር ተቀብሏል።” የመንግሥት የንግድ ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎችን ወደ ግል እንዲያዛውር፥ ለመንግሥት ብቻ ተከልለው የነበሩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለግል ባለሃብቶች ክፍት እንዲያደርግ፥ የቀድሞው መንግሥት ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ያወጣቸውን ህጎች እንዲያሻሽል የታዘዘውን ፈጽሟል። “በውጭ ተጽዕኖ የተቀበልናቸው የማሻሻያ መርሆች እንከተለዋለን ከምንለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር ይጻረሩ ነበር።”

በወቅቱ መሪዎቹን የጨነቃቸው በጫና የተቀበሏቸው የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች ታገልንለት ከሚሉት ዓላማና እንገነባዋለን ከሚሉት ሥርዓት ጋር ተጻራሪ መሆናቸው፥ አልያም ማሻሻያዎቹ በአገርና ሕዝብ ላይ በተለይም በጭቁኑ ሕዝብ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት አልነበረም። ከዚህ ሁሉ ይልቅ ያሳሰባቸው በወቅቱ ስልጠና ይሰጧቸው ለነበሩት ካድሬዎቻቸው ምን ማለት እንዳለባቸው አለማወቃቸው ነበር። ምክንያቱም የዓለም የገንዘብ ተቋሞች ትዕዛዝ እስከተቀበሉበት ጊዜ ድረስ ኢምፔሪያሊዝም ጠላት መሆኑንና የኢህአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳይተገበር እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ነበር ለካድሬዎቻቸው ሲያስተምሩ የኖሩት። [ገጽ 150] መጨረሻውሳ? “ድርጅታዊ ፕሮግራማችንን ሳናዛንፍ ማሻሻያዎቹን ለመተግበር እንደምንችል ማስረዳት ነበረብን” ይላሉ አቶ ገብሩ። [ገጽ 157] እንደማይሆን ልቡናቸው ያውቀው ነበር፤ ሊሆንም አልቻለም።

 

እነሆ ከግምገማው በኋላ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማርያም በሰጡት ማብራሪያ ኢህአዴግ የሚገነባው ካፒታሊስት ሥርዓት ራሱ የግል ሀብት የሚመነጭበት፥ ካፒታል ተከማችቶ ግለሰቦች የሚበለጽጉበትና ስግብግብ ፍላጎት ለማራመድ የሚመች ኢፍትሐዊ [ፍትሐዊ ተብሎ ሊወሰድ የማይችል ይሉታል] ሥርዓት ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ ግለሰብ ሕዝብን ለማገልገል ቁርጠኝነቱ ከሌለው በቀር ውጫዊ ሁኔታው ለብልሽት ሊያጋልጥ የሚችል ሥርዓት ውስጥ የሚሰራ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ነባራዊ ሁኔታውን መካድ እንደማይቻል ጠቅሰው፤ መፍትሄው በስልጣን ላይ ያለን አመለካከት በማስተካከል ድርጅቱ ስልጣን የሚፈለገው ለውጥ ለማምጣት እንጂ የራስን ቡድን ለመጥቀም ሊሆን እንደማይገባ የተገነዘቡና ‘ለመስዋዕትነት የቆረጡ ታጋዮች ብቻ የሚሰበሰቡበት ሊሆን ይገባል’ ብለዋል። የሚገርም ሐሳብ ነው። ቀድሞ ነገር ኢፍትሐዊ ሥርዓት መገንባትን ምን አመጣው? ኢህአዴግ አመራሩን/አባሉን ለኢፍትሐዊ ሥርዓት ግንባታ በሚደረገው ትግል መስዋዕትነት እንዲከፍል መጠየቅና አዎንታዊ ምላሽ መጠበቅ ምን ይባላል? ሰው ፍትህ ለቸገረው ይታገላል፤ ለተጨቆነ ይታገላል፤ አድልዎን ለማጥፋት ይታገላል፤ እኩልነትን ለማረጋገጥና ችጋርን ለማጥፋት ይታገላል። እንዴት ሰው ፍትሐዊ ያልሆነ ሥርዓት ለመገንባት እታገላለሁ ይላል?

ደግሞ በዚያው አፉ ኢህአዴግ ራሱን አብዮታዊና “ኀብረተሰባዊ ለውጥ ለማምጣት የተሰጠ ድርጅት” ብሎ ሲጠራ ሁለት ጸበኛ ጌቶችን ላገልግል ማለቱ ነው ወይስ ተቃርኖውን ለማየት አልቻለም? ተቃርኖውን የሚያሻግር መላ አግኝቷል ወይስ ኢፍትሐዊ ሥርዓት በመገንባት የማታ ማታ ‘ፍትሐዊ’ ሥርዓትን ለማስፈን የሚያስችል ዐቅም አገኛለሁ በሚል ቅዠት ቅልቅል ስሌት ራሱንና አባሎችን እያሞኘ ይሆን? አሁንም ራሱን “ታጋይ” ድርጅት የሚልበት ምክንያቱ ለጭቁኖች ነጻነት የመታገሉን ዓላማ አልከዳሁም ለማለት ይሆን? ራሱን የሚሸነግልበት ዘዴ ምንም ይሁን ምን የገንዘብ ድርጅቶቹን ትዕዛዝ በመቀበሉ ምክንያት ዛሬ አገሩን ለብዝበዛና ጥገኝነትና የዚያ ሁሉ ምንጭ ለሆነው የጃዙር ቅኝ ግዛት ኃይሎች ተጽዕኖ አሳልፎ ሰጥቷታል። እስካሁን ኢትዮጵያ ለኢንቨስተር የተመቸች አገር ለማድረግ በተደረገው ‘ትግል’ ኢንቨስተሩ ያገሪቱን ሀብት እንደፈለገ እንዲጠቀምበት፥ ልጆቿንም በመሰለው ክፍያ እንዲቀጥር፥ ባሻው ጊዜ እንዲያባርር አስችሎታል። አሁን ከየአገሩ ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስተር ነኝ ባይ ሁላ የሚጎርፍበት ምክንያት በመንግሥት ቁጥጥር መላላትና በልጆቿ ጉልበት ርካሽነት እየተሳበ መሆኑ ይታወቃል። ኢህአዴግ ለኅበረተሰባዊ ለውጥ መሥራት የሚለው፥ ለህዝብ መሰጠት የሚለው ይህ መሆኑ ነው። ቢያንስ ታጋይ ነን እያሉ ራስን ማሞኘቱ ቢቀር፥ ጓድ ጓድ መባባሉ ቢቀር ምናለ።

 

እዚህ ላይ ለምን የታጋይነት ዓላማውን ለወጠ አይደለም። ከበረኻ ይዞት የመጣውን የልዩነት ፖለቲካ ሳይለውጥ አንድነትን በዘነጋ መልኩ በመተግበሩ እንዳልተጠቀምን ይታወቃል። ሆኖም ኢፍትሐዊ ሥርዓት ለመገንባት እየታገልኩ ነው ማለቱ ሳያንስ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው በጨካኙ የገበያ ሥርዓት የሚጎዱትን ወገኖቹን ለመጠበቅ እጁን እንደማስገባት ጭራሽ ደህናውን ገበያ በመበጥበጥ ኑሮ እንዲወደድ ያደረጉ እርምጃዎችን የሚወስድ መሆኑ ነው።  ከዚህ አንጻር የኢህአዴግ ነጻ ገበያ ከደርጉ የእዝ ኢኮኖሚ ይሻላል ባዩ ብዙ ቢሆንም የድኻውን ኙሮ በሚመለከት አንዳንዴ ሊብስም እንደሚችል ማስረዳት አይከብድም። ደርግ የእዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት መከተሉ እውነት ነው፤ ማለትም በአገር ውስጥ የሚመረተውንና የተመረተውም የሚከፋፈልበትን ሥርዓት፥ እንዲሁም ከአገሪቱ ሀብት ለውጭ ገበያ የሚቀርበውንና በተገኘው ገቢም የሚገዛውን የውጭ ሸቀጥ ይወስን ነበር፤ ባጠቃላይ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የሰው ኃይል ስልጠናውን ይወስን ነበር፤ ተገቢ በሚለው ሥራ ላይ ያሰማራ ነበር። ሆኖም ደርግ ኩሩ መንግሥት ነበር፤ እንደ ቤቱ ኗሪ እንጂ እንደ ጎረቤቱ ልኑር ባይ፥ የሰው ትሪ ተመልካች አልነበረም። ደርግን ኢኮኖሚያዊ ጥፋት አንስቶ ልውቀስ የሚል ሁሉ ሳያነሳ የማያልፈው በገበሬው ምርት ላይ ማዘዙ፥ ራሱ በወሰነው ዋጋ በግድ መግዛቱ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ የማይነሳው ደግሞ ደርግ ለገበሬው ለያካባቢው አየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የዕጽዋት አዝርዕት ሲያቀርብ መኖሩ ነው። እህሉን በግድ የመሸመቱ ዓላማም ባገር የተመረተውን በየኅብረት ሱቁ በማከፋፈል ለሁሉም እንዲዳረስ ለማድረግ እንደነበር አይዘነጋም።

ዛሬ ደግሞ ኢህአዴግ ከገበሬው ፍላጎት ውጭ የሚመረተውን የምርት ዓይነት ወስኖ ምዕራባውያን ከበርቴ ኩባንያዎች መንግስት በሚያመቻቸው ብድር የሚያቀርቡለትን ምርጥ የተባለ ዘር ከነማዳበርያውና አገር ከሚበክል ኬሚካል ጋር እንዲወስድ ማስገደዱ ትእዛዝ አይደለም? እንዲያውም የኢህአዴግ ትዕዛዝ የአገሩን አቅም ባገናዘበ መልኩ ድሃውና ሀብታሙ እንደያቅሙ በልቶ እንዲያድር ከማድረግ ይልቅ ጭራሽ የከተሜውን ኑሮ ቀንበር ያከበደ መሆኑን፤ ከላይ ስለ ምግብ ዋስትና ከተነገረው በተጨማሪ ጥቂት ምሳሌዎችን በመጥቀስ ማስረዳት ይቻላል። ሉካንዳዎች አንዱን ኪሎ ሥጋ በብር 52 [አምሳ ሁለት] እንዲሸጡ በማስገደድ ያገር ከብት ድንበር ጥሶ እንዲወጣና ሕገ ወጥ ገበያ እንዲስፋፋ ያደረገ፤ ደግሞ የዋጋ ተመኑ ቀርቶ ሥጋ ቤቶች በመሰላቸው ዋጋ መሸጥ ሲጀምሩ ነጻ ገበያ እንዳልተባለ ከአንድ በሬ ብር ሁለት ሺህ ለማስከፈል ወስኖ የሥጋ ዋጋ እንዲጨምር በማድረግ ድኻው ፈጣሪ ከሰጠው ያገሩ ከብት ለጾም መያዣና መግደፊያ ቅንጥብጣቢ እንዲያርበት ያደረገው ማነው? ይህ ትዕዛዝ ተፈጻሚ ሆኖ የለም ዛሬ?

 

1.3 ስልጣን ላይ ሲወጣ ግቡ ስልጣን ሆነ

ጭቁኖችን ከባለፀጋ በዝባዦች ነጻ ለማውጣት የታገለውና ወደፊት ካፒታሊዝምን በጉልበት አስወግዳለሁ የሚል ሶሻሊስታዊ አቋም የነበረው ኢህአዴግ ድኻነትን ለማጥፋት ፀረ ድኻውን የከበርቴ ስርዓት ለመገንባት ሲስማማ ያኔ እንደ ድርጅት ስልጣንን ግብ ማድረግ ጀመረ ለማለት ይቻላል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ ሥር የወደቀ ሲሆን ያኔ የተጣባው ታዛዥነት መቼም አልለቀቀውም። በ1993 ዓ.ም አመራሩ ለሁለት ተከፍሎ አፈንጋጭ የተባለው ቡድን ከድርጅቱ ከወጣ በኋላ ዛሬ የቀድሞው አመራር አንስቶ የማይጥግበው “ተሃድሶ” ያመጣው አዲስ ነገር ቢኖር የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ የግዱን የተቀበለውን የነጻ ገበያ መርህ የራሱ አድርጎ ማቅረቡና ይህን ለማካተትም የፓርቲውን ፕሮግራም እንዳዲስ መጻፉ ነው። ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ በዱሮው ፕሮግራሙ መሠረት የአገርን ኢኮኖሚ ከምዕራባውያን ጥገኝነት በማላቀቅ ፋንታ ጥገኝነቱን አማራጭ የሌለው አስመስሎ ማቅረብ ጀመረ። “በዚህ የግሎባይዜሽን ዘመን ያለን አማራጭ ወይ ዋኝቶ መውጣት፥ አልያም ሰጥሞ መቅረት ነው” በማለት ደምድሞ ሲያበቃ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ያላትን ድርሻ ማሳደግ በሚል መርህ አገሪቱን ሙሉ በሙሉ የዓለም ገበያ ጥገኛ ለማድረግ ፈቀደ። የምግብ ዋስትናውም ሳይቀር የዓለም ገበያ ጥገኛ ሆኖ እንዲቀር የተደረገበት ምክንያት ይኸው ነበር።

ይህ ሁሉ ሲሆን የኢህአዴግ አመራር በዐበይት የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሳያደርግ ከበላይ የወረደለትን ተቀብሎ ሲያስፈጽም መኖሩን ከሕወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች አንደበት ሰምተናል። ፖሊሲዎቹ በትዕዛዝ ካልሆነ በማሳመን ሊተገበሩ የሚችሉ ባለመሆናቸው በቂ ውይይት ሳያስፈልግ በቀጭን ትዕዛዝ ማስፈጸሙ አማራጭ አልነበረውም። በዚህም በተለይ ፈረንጆቹ ደስተኞች ነበሩ። በተለይ ከላይ ከተጠቀሰው የቡድን 8 ስምምነት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ የተጀመረው አካሄድ እንዳይቀለበስ ፈንጆቹ እጅግ ሰግተው ነበር። ፈረንጆቹ በገበሬው ስም የሚያራምዱት የገበሬውን ጥቅም የሚጎዳውን የፖሊሲ አቅጣጫ እውነተኛ መልክ ተገንዝቦ ተቃውሞ የሚያነሳ ሰው ከኢህአዴጎች መካከል አይጠፋ ይሆናል ብለው ነበር መሰል፤ አልተገኘም። ለባዕዳን የሚበጅ ፖሊሲ ለአገሬው ህዝብ የመከራ ምንጭ፥ ህዝቡን የሚጠቅም የመንግስት አቋም ደግሞ ያልዘሩትን ማጨድ ለለመዱት ባዕዳን ኪሳራ መሆኑን ማወቅ የመንግሥትነት ሥራ ሀሁ ሊባል ይችላል። ሆኖም ኢሀዴጎች በትዕዛዝ ሲያስፈጽሟቸው የነበሩትን ፖሊሲዎች በመፈተሽ ፋንታ እንዳሉ ተቀብለው።

የፈረንጆቹ አድናቆትና ድጋፍ ከኢኮኖሚ ዕድገት ተረኩ ጋር ቢያስጎመዣቸው፥ ድርጅቱን የስኬት ምንጭ የሆኑ ፖሊሲዎች ባላቤት አሰኝተው ሁሉንም ነገር በነበረበት እንዲቀጥል አደረጉት። ሁሉንም ሲወርሱ የበጎውም ሆነ የክፉው ሁሉ ጅምር ጨራሽ ባላደራ ሆነው ቀረቡ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢህአዴጎች ራሳቸውን ከፖሊሲ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ እጃቸውን ሳያወጡ የቀሩ አይመስለኝም። እንዲያውም ምንም ነገር ማሰብ ሳያስፈልግ አቶ መለስ ቀምረው የተዉትን መተግበር ብቻ ይበቃል እስከማለት ተደርሶ እንደነበር ሰምተናል። ስልጣን ሲወርሱ፤ ስልጣኑ ግብ ሆነ።

ሆኖም ከኢሀዴግ ጋር አብረው ከመጡት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች በተጨማሪ በአገራችን የፖሊሲ ውሳኔ በሚሰጥበት ጠረጴዛ ዙርያ ከበው የሚቀመጡት ሌሎች ናቸው። ዛሬ በግብርናው ዘርፍ የሚደረግ የግል ኢንቨስትመንት አስተባባሪው፥ አስተዳዳሪውና መሪው “የግሉ ዘርፍ ልማት ግብረ ኃይል” የተሰኘ አካል ነው — የግብርና ሚኒስቴር ባቋቋመው የኢትዮጵያ የገጠር ኢኮኖሚ ልማትና የምግብ ዋስትና ኮሚቴ ሥር የተዋቀረ። ግብረ ኃይሉ የአሜሪካና የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅቶች፥ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም፥ የአውሮፓ ሕብረት ልዑክን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና መያዶችንም በአባልነት ያቀፈ ሲሆን በአንድ ምዕራባውያን የልማት አጋር ድርጅትና የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይ ቢባልም በውጭ ድርጅቶች በሚደጎመው አግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኢጀንሲ (ኤቲኤ) [ወይም የግብርና ሚኒስቴር] በጋራ ሰብሳቢነት የሚመራ ነው።

ዋናው ነጥብ የአገራችንን አጠቃላይ የኢኮኖሚና የእርሻውን ዘርፍ የሚመሩት ፖሊሲዎች አመንጪና አድራጊ ፈጣሪዎቹ፥ ተመዘገበ የሚባለው የዕድገት መጠን ተንባዮቹና ተንታኞቹ፥ ምስክሮቹም የጥንት የጥዋቶቹ ምዕራባውያን የገንዘብ ተቋሞችና በምዕራባውያኑ የልማት አጋሮች የሚመራው ግብረ ኃይል መሆኑ ነው። ዛሬ በአገራችን የሚተገበሩትን ፖሊሲዎች መቆጣጠር ቀርቶ አብጠርጥሮ የሚያውቅ መሥሪያ ቤት መኖሩም እንጃ። [ከላይ በተጠቀሰው “ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና የቡድን 8 አዲስ ዕቅድ” ላይ የመመረቂያ ጽሑፌን ሳዘጋጅ ቃለ መጠይቅ ካደረግኩላቸው መካከል በግብርና ሚ/ር የዕጽዋት ዘር መምሪያ/ዳይሬክቶሬት ኃላፊው ስምምነቱን እንደማያውቁት የገለጹልኝ ሲሆን፥ የሚገርመው በስምምነቱ መሠረት የተሻሻለው የዕጽዋት ዘር ሕግ የተረቀቀው መምሪያው ውስጥ ባሉ የህግ ባለሙያዎች ነበር።] ኢትዮጵያን ለየዕጽዋት ዘር ሀብት ዝርፊያ ከማጋለጥ በቀር ከቶ ከማይመለከቷት አፍሪካዊና ምስራቅ አፍሪካዊ ማኅበሮች እንድትገባ ለማድረግ በሚካሄዱ ድርዱሮችና ስምምነቶች የሚሳተፉት ጥቂት ባለሙያዎችም ጥልቅ እውቀቱና ኅሊናው ባይቸግራቸውም እንኳ ስልጣኑ ከሌላቸው ጥሩ እንስራ ቢሉም አይችሉም።

ከዚህ አንጻር ኢህአዴግ ስልጣንን ግብ ቢያደርግም ስልጣኑ ፖሊሲዎችን አመንጭቶ መተግበርን የማይጨምር እስከሆነ ድረስ እንደሚሉት ማኅበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሳይሆን ያገር ሀብት የሚዘርፉበት፥ ተቀናቃኞችን የሚመቱበት፥ መብቴን ያለውንም የሚያፍኑበት ጠመንጃ ሆኖ ይገኛል።

ባለፈው ታህሳስ በተካሄደው የኢህአዴግ ግምገማ ዋዜማና ማግሥት በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ችግር የተገነዘቡ አዳዲስ መሪዎችን መመልከታችን አይካድም። በተለይ አቶ ለማ መገርሳ የኢህአዴግ አመራር ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ በመስጠት ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ለአመጽ ግብረ መልስ የሚሰጥ ሆኗል ማለታቸው የኢህአዴግ ስልጣን ጠበንጃ ከማንገብ ያላለፈ መሆኑን በትክክል ያስረዳል። ምክንያቱም ችግሮችን ለይቶ መፍትሔ በመስጠት ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችል ፖሊሲ ቀርጾ ለመተግበር ሲቻል፥ የፖሊሲ አስተዳደር ስልጣን ሲኖር ብቻ ነው። ሆኖም ፖሊሲ አስተዳደር ውስጥ ከሌለበትና ስልጣን ማለት ጠመንጃ ከሆነ ችግርን በጠበንጃ ለመፍታት ቢነሳ፥ በትክክል ለአመጽ ግብረ መልስ መስጠት ቢሆንም ያለውን የሰጠ እንዲሉ ኢህአዴግ ከዚያ የተለየ የሚወስደው የፖሊሲ እርምጃ አልነበረውም፤ የለውምም። ዶ/ር ደብረጽዮንም በበኩላቸው ለውጥ እያመጣን አይደለም፤ ይህን ሁሉ የሕዝብ ችግር እየተመለከትን ደህና ነን ማለት አንችልም፥ ማለታቸው እውነት ቢሆንም ፖሊሲ ማመንጨትና መተግበር ካልተቻል በስተቀር ለውጥ ማጣትም ሆነ የሕዝብ ችግር መፍታት የሚቻል አይደለም። በተጨማሪ አመራሩ በዐበይት የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በቂ ውይይት ሳያደርግ ወደ ትግበራ ሲገባ መቆየቱን፥ ህዝቡንም በማሳመን ሳይሆን በትዕዛዝ ውሳኔዎችን እንዲተገብር ሲያስገድድ መኖሩን ጠቅሰው በምሳሌነት ገበሬው ሳያምንበት ማዳበሪያና የዕጽዋት ዘር እንዲጠቀም መገደዱን አውስተዋል። ታዲያ አመራሩ በቂ ውይይት ሳያደርግ ሲተገብራቸው የኖሩት ፖሊሲዎች ባለቤትና አመንጪ ነበራቸው፥ አላቸውም፤ አበዳሪና አጋር የተሰኙት ተቋሞች ናቸው።

ሆኖም የሚያዝጎመዥ እድገት ያመጡ እየተባሉ ዛሬም ድረስ በኢህአዴጎች ሲሞካሹ የምንሰማው እነዚያው ፖሊሲዎች ናቸው። ከዚህ አንጻር የአመራር ውድቀት ተፈጥሯል የሚሉት እነ አቶ ለማ እና ለውጥ ማምጣት አለብን የሚሉት ዶ/ር ደብረጽዮንም ቢሆኑ ፖሊሲዎቻችንን በሚመለከት ምን ያህል እውቀት/ግንዛቤ እንዳላቸው ገና አልታወቀም። በርግጥ እንደ መሪዎች በየዘርፉ የተካኑ አማካሪዎቻቸውን እስከተጠቀሙ ድረስየግድ ራሳቸው ሁል-አውቃ መሆን አይጠበቅባቸውም።

ይሁንና አዲሱ ጠ/ሚ/ር የሚያጋጥመው መሠረታዊ ፈተና የፖሊሲ አስተዳደርን ስልጣን አጋር ከተሰኙትና ጥቂት እርዳታና ጥቂት ብድር ሰጥተው በአገሪቱ ሁለንተናዊ ዐቅም ፈጠራና ስምሪት ላይ ከሚወስኑት ባዕዳን ድርጅቶች ተቀብሎ የእውነት ለመምራት የሚያስችል ስልጣን መያዝ መቻል መሆኑ አይቀርም። [ከሥር ይመልከቱ]

ታዲያ ለአገር የሚተርፈውን የፖሊሲ ችግር ለመፍታት ቅድሚያ እንደ አመራር የርስ በርስ ግንኙነታቸውን፥ እንደ ግንባር ሕብረቱ የቆመበትን መርህ፥ እንደ መንግስት ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጋር ካለው ግንኙነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የሚከተሉትን ድርጅት ነክ ችግሮች መልክ ሊያስይዙ ይገባል።

 

  1. የኢሀአዴግ መሠረታዊ ድርጅት ነክ ችግሮች

ኢህአዴግ ራሱ በሚያደርስብን በደል መሰቃየታችን ሳያንስ ጭራሽ እሱ ደረሰብኝ የሚለው ቀውስ በሚጎትተው ጦስም ስንጨነቅ ኖረናል። በእውነቱ ቢያንስ በውስጡ የሚፈጠር የድርጅት ጉዳይ ሊያሳስበን አይገባም ነበር። ሆኖም ‘የራሱ ጉዳይ፥ እኛን ምን አገባን’ ብለን እንዳንተወው ችግሩ በአገር ላይ የመጣ ነው ተብሎ፥ ያገር ሰላም በሚያደፈርሱ ግጭቶች ታጅቦ ይቀርብልናል። ኢህአዴግ በረዥም የስልጣን ዘመኑ ባራመደው ልዩነት ተኮር አጀንዳ የተፈጠረው እውነታ እንዲሁ የሚተዉት አይደለም — የድርጅቱን ብተና ያገር አስመስሎ በማቅረብና በግጭት በማጀብ የሚያስጨንቀን የህዝቡን ያገር ፍቅር አውቆ አይደለም? በሌላ በኩል ለረዥም ጊዜ የተዘነጋውን በማስታወስ አንድነትና ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ መሪዎች ከኢህአዴግ መካከል ዛሬ ብቅ ማለታቸውን ተመልክተናል። ዛሬ ስለ ኢህአዴግ ስናስብ ይኸው አዲሱ የአንድነት፥ የፍቅርና የኢትዮጵያዊነት ኃይል ሊዘነጋ አይችልም። በአዲሱ ኃይል ምክንያት የኢህአዴግ ማንነት ተዥጎርጉሯል፤ በቀድሞው ጠሚር ይወከል የነበረው ወጥ አቋሙ/ማንነቱ አሁን ቢያንስ ብቸኛ አማራጭ መሆኑ ቀርቷል። ስለሆነም ድርጅቱ ወደፊት ችግሮቹን ለመፍታት የሚጓዝበት መንገድና የሚያራምደው ዓላማ ምንም ቢሆን ከቀድሞ የተለየ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ ለማለት ይቻላል። ጥናንጥ ምልክቶችም ታይተዋል።

ኢህአዴግ የፌዴራል መንግሥት ስልጣን ለመያዝ የሚያስችል ህብረብሄራዊ አደረጃጀት በመሆኑ አባል ድርጅቶቹንና በነሱም አማካይነት የክልል መንግስታትን በአንድ የእዝ ሰንሰለት ሥር በማስገባት በተለይ ለመሪው በአገሪቱና በፓርቲዎቹ ላይ ፍጹም ስልጣን ያስጨበጠ አስተማማኝ መንገድ ሆኖ ቆይቷል። ግንባሩ በዚህ ቁመናው እንዳለ ነበር አቶ ኃ/ማሪያም መሪነቱን የተረከቡት። ከዚያ በኋላ ጥቃቅንም ቢሆኑ አንዳንድ ለውጦች ታይተዋል። ለምሳሌ በአቶ መለስ ጊዜ ኢህአዴግ ከሹመኞቹ የሚፈልገው ከችሎታ ይልቅ ታማኝነትን ነበር፤ በአቶ ኃ/ማርያም ጊዜ ግን ችሎታ ያለው ባለሙያ አባልም ባይሆን ሊሾም እንደሚችል በ2008 ዓ.ም ታይቷል። በተጨማሪ ኢህአዴግ ‘ብሔራዊ መግባባትን’ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚመኙ ተቃዋሚዎች የሚያቀርቡት ሃሳብ ነው ብሎ ሲያጣጥለው እናስታውሳለን፤ አሁን ግን ቢያንስ አስፈላጊነቱን ሳይገነዘብ አልቀረም። ፤ እንዲያውም ለዚሁ መግባባት ሲባል የፓለቲካ እስረኞች “የሉም” ብሎ በመሸምጠጥ ፋንታ “አሉ፤ እንፈታማለን” በማለት እነሆ ፕ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ከመቶ በላይ፥ በክልሎችም በሺ የሚቆጠሩ ታሳሪዎች ነጻ ወጥተዋል። አባል ድርጅቶቹ በመግለጫዎቻቸው ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የአብረን እንስራ ጥሪ እስተላልፏል። ይህም ሁሉ ሆኖ አሁንም እውነተኛ ብሄራዊ መግባባት አልተፈጠረም። እንግዲህ ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ጤናማና በመርሕ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊኖረው እንዲኖረው ቅድሚያ የራሱን ድርጅታዊ ጤንነት መጠበቅ ሲችል ነው። በዐበይት አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚፈተሩ የሐሳብ/አቋም ልዩነቶች የአባል ድርጅቶችን ግንኙነትና በተለይም አንድነቱን የሚፈትኑበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እሙን ነው። በዚያን ጊዜ ልዩነቶችን ይዞ አንድ ላይ ለመጓዝም ሆነ ሌሎች የግንኙነት አማራጮችን ለመወሰን የቆመባቸው መርሆች በሁሉም አባላት ዘንድ የተከበሩና ልዩነት ባለበትም ቢሆን አስፈላጊውን ሥራ ከመስራት የማይከለክሉ ሊሆኑ ይገባል።

ከዚህ አንጻር ኢህአዴግ በአባል ድርጅቶቹ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመራበት ከፌዴራል ሥርዓቱ የተስማማና ደጋግሞ በሚያነሳው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ እንደልብ ለመንቀሳቀስ የሚፈቅድለት የግንኙነት መርሕና አሠራር ማበጀት ያስፈልገዋል።

 

 

2.1 የኢህአዴግ አሐዳዊ መዋቅርና ፌደራላዊ የብዝኃነት ሥርዓት

ኢህአዴግ አራት ብሄራዊ ድርጅቶችን ያቀፈ እንደመሆኑ ህብረብሄራዊ ድርጅት ሊባል ቢችልም አባል ድርጅቶችን በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ በአንድ የእዝ ሰንሰለት ማስገባቱና በድርጅቱ መዋቅር የበታቹ ለበላዩ ታዛዥ እንዲሆን ግድ ማለቱ የህብረብሄራዊነት መገለጫ የሆነውን ብዝኃነትን እንዳያስተናግድ አስቸጋሪ ያደርግበታል። ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሐሳብ ብዝኃነት ፋንታ አንድ ሐሳብ፥ ለያንዳንዱ ችግርም የየራሱ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ ሁሉንም በአንድ የመፍትሔ ሐሳብ ማስተናገድ፥ ባልተማከለ አስተዳደር ፋንታ ስልጣን በአንድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን በአንድ ግለሰብ/ቡድን እንዲከማችና ውሳኔዎችም ከዚያ ብቻ እንዲመነጩ የሚያደርግ መርህ በመሆኑ ሲተች ኖሯል። ሆኖም የሐሳብ ብዝኃነትን እንዲያስተናግድ ለተለያዩ ችግሮች ልዩ ልዩ የመፍትሄ አማራጮችን ለማበጀት በሚችልበት መልኩ ለማሻሻል ይቻል ይሆናል። አሁንም ቢሆን ‘እህ’ት ድርጅቶቹ የግንባሩን የፖሊሲ መርሆች ለያካባቢያቸው እንዲስማማ አድርገው ሊተገብሩ እንደሚችሉ በድርጅቱ ፕሮግራም ተደንግጓል። ሆኖም ያልተማከለውን የፌዴራል-ክልል-ዞን መዋቅር በተማከለ ሥልጣን ለመምራት የሚደረግ ትረት ብዝኃነትና ተለያይነት ከሚጠይቁት ስልጣንን በውክልና የመስጠት ሁኔታ ጋር ተጣጥመው መሄዳቸው ያጠራጥራል፤ ከታሰበበት ግን የሚይቻል አይደለም። ለጊዜው ግን ተጣርሶቹን መመልከት ግድ ነው።

የአባል ድርጅቶች አንድነት በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ እስከተመራ ድረስ ዛሬ ባለው ሁኔታ እያንዳንዱ እህት ድርጅት ክልላዊ መንግሥትን እንደሚመራ ድርጅት በክልሉ ባለሙሉ ስልጣን ሲሆን እንደ አባል ድርጅት ደግሞ የኢህአዴግ የበታች መሆኑ ነው። ባንድ በኩል የፌዴራል ሥርዓቱ ለክልል መንግሥታት ከፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት ውጭ የሆነ ስልጣን ሲያጎናጽፍ፥ በሌላ በኩል የኢህአዴግ አሐዳዊ አደረጃጀት ሕገ መንግስቱ በግልጽ የሰጠውን ስልጣን አባል ድርጅቶቹን በሚመራው የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሕ አማካይነት ከጀርባ ገብቶ ከፈቃዴ እንዳትወጡ ቢል የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የክልል መንግሥት በሚመሩበት ጊዜ ከነ ሥልጣናቸው ለድርጅቱ የበላይ ተገዢ መሆን ሊኖርባቸው ነው። ዛሬ ከብሄራዊ ፓርቲ መሪነት ጋር የክልል ርዕሰ መስተዳድርነትን የደረቡት ፕሬዚደንቶች ባንድ በኩል ክልላዊ መብትና ስልጣናቸውን ለማስከበር፥ በሌላ በኩል አባል ለሆኑበት ፓርቲ የበላይ አካል ተገዢነታቸውን ለማረጋገጥ ሲጣጣሩ በተጣርሶሽ መወጠራቸው አይቀርም። ከዚህ አንጻር ባንድ በኩል የበታች አካል ለበላይ አካል እንዲገዛ በሚያስገድደው ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ላይ በቆመው አሐዳዊና የተማከለ አደረጃጀቱ በሌላ በኩል የፌዴራል ሥርዓቱን በሚቃኘው የብዝኃነት መርህና ያልተማከለ አስተዳደር መካከል ያለው ቅራኔ ኢህአዴግን መቼም የማይፋታው ዐቢይ ፈተና ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። ምን ማድረግ ይቻላል?

አንዱ አማራጭ ስልጣን እንዳይማከል ተደርጎ የተዋቀረው የፌዴራል ሥርዓት በመጻረር በድርጅቱ መዋቅር አማካይነት የድርጅት ብሎም የመንግሥት ስልጣን እንዲማከል የሚያደርገውን ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ማሻሻል አልያም መቀየር ነው። ሌላው አማራጭ ፓርቲውን ከመንግሥት መነጠል ሲሆን ይህም ማለት ለምሳሌ የአባል ድርጅት መሪዎች የክልልና የፌዴራል ባልስልጣናት ሆነው ሲሾሙ ለፓርቲው የሚኖራቸው ተጠሪነት በፓርቲ ጉዳዮች ብቻ የተወሰነና በተለይም የመንግሥትን ሥራ የማያካትት እንዲሆን አድርጎ ማሻሻል ነው። ይኸውም ከሥር እንደምንመለከተው አንድነቱን በማይጎዳበት መልኩ ማከናወን የሚቻል ቢሆንም የአባል ድርጅቶችን አንድነት ፋይዳም ራሱ ቢፈተሽ ምናልባት ለአንድነቱ የተሰጠው ቦታና ድርጅት የሚበትን ተግባር ሊፈጸም ይችላል የሚል ጥርጣሬ የሚፈጥረውን ጭንቀት በአግባቡ ለመረዳት ማገዙ አይቀርም።

 

2.2 አባል ድርጅች ከኢሀዴጋዊ ‘አንድነት ሌላ አማራጭ የላቸውም?

የአባል ድርጅቶችን “አንድነት” በቦታው መኖሩን ለማረጋገጥ ሲል ነበር ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ታህሳስ የመንግሥት ሥራ ሁሉ ትቶ ስብሰባ የተቀመጠው። በአንድነቱ ላይ የተነሳው ጥርጣሬ በኢህአዴግ ህልውና ላይ የተደቀነ አደጋ ተደርጎ በመቆጠሩ የአባል ድርጅቶቹ የጭንቀት ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር የመንግሥትን ባለስልጣናት፥ ከዚያም አልፎ ሕዝብን ሲያሸብር ተመልክተናል። ምናልባት ለአንድነቱ የተሰጠው ቦታ እጅግ ሳይጋነን አልቀረም። [ድርጅቱ ትጥቅ ያልፈታ መሆኑ የሚፈጥረው ጫና ዝቅ ብለን እንመለከተዋለን።] ‘አንድነቱ’ አባል በድርጅቶቹ ፍላጎትና ፈቃድ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ ፍላጎትና ፍቃድም ሊለወጥ የሚችል እንደመሆኑ መጠን አንድነቱ ሁሌም ባለበት ከመቀጠል ውጪ አማራጭ የሌለው ተደርጎ ሊታሰብ አይገባም። ምክንያቱም አንድነቱ ዓላማ ያለው እስከሆነ ድረስ ለምሳሌ ዓላማው ግቡን ከመታ አልያም ግቡን የማይመታ መስሎ የታየ እንደሆነ አንድነቱ ላይቀጥል ይቻላልና ነው። ይልቁንም የግንባሩ አንድነት አባል ድርጅቶቹን እንዲያገለግልና በተናጠል የማያገኙትን ጥቅም/አገልግሎት የሚያገኙበት መድረክ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮችን ለመዘርጋት ጥረት ቢደረግ ፍሬያማ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ አባል ድርጅቶቹ ለጋራ ግንባሩ ያለባቸው ግዴታ በተናጠል ሙሉ ሕጋዊ ሰውነት የሚያጎናጽፋቸውን ድርጅታዊ መብትና ስልጣን በብቃት ከመጠቀም የማይከለክል፥ [የክልላዊ መንግሥት ሥልጣን በሚይዙበት ጊዜም] የህዝብን ችግር ለመፍታት፥ ወይም በምርጫ ጊዜ ለመራጩ የገቡትን ቃል ለመፈጸም የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን ለመተግበር የሚያስችላቸውን ሕገ መንግሥታዊ ስልጣን በአግባቡ ከመጠቀም የማይገድብ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ የግንባሩን አወቃቀር ማስተካከል ይቻላል። ኢህአዴግ የብሄራዊ ድርጅቶች ጥምረት እንደመሆኑ የድርጅቱን ዓላማ በፌዴራል መንግሥት በኩል በአገር ደረጃ ለመተግበር የሚያስችል ሥልጣን የሚገኝበት አንድ መንገድ እንደመሆኑ መጠን መንገዱ ለሁሉም እህት ድርጅቶቹ ክፍት መሆኑን ማረጋገጥ ለአንድነቱ መጎልበት ትልቅ አስተዋጽዖ ሊኖረው ይችላል። ስለሆነም አባል ድርጅቶቹ የጋራ ግንባሩን ሊቀ መንበርነት እንዲሁም [ምርጫ ባሸነፉ ጊዜ] ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን በዙር ለመቀባበል ሊስማሙ ይችላሉ። ይህም ከአባል ድርጅቶች መካከል ማንም የበለጠ ወይም ያነሰ ተጠቃሚ እንዳይሆን ከማድረጉም ባሻገር እያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት በፌዴራል መንግሥት ከመሳተፉም በተጨማሪ የየክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ [የፓርቲም ሆኑ የመንግሥት] ሥራዎችን ለማከናወን ያስችለዋል።

በአንጻሩ አባል ድርጅቶቹ ዛሬ እንታገልለታለን የሚሉትን ፍትሐዊ ያልሆነ ሥርዓት መገንባትን የመሰለ አውቆ አጥፊነት ወይም የገበሬውን ብሎም ያገራችንን የምግብ ዋስትና በዋዣቂነቱ ከሚታወቀው የዓለም ገበያ ጋር ማቆራኘትን የመሰለ የፖሊሲ ዕዳ ለመሸከም መገደድ የለባቸውም። በሌላ በኩል የያንዳንዱ አባል ድርጅት እህትነት የሚነሳው በኢህአዴግ ሥር በሚሆኑበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን የየክልሎቻቸውን መንግሥታት በሚመሩበት ጊዜም ጭምር መሆኑን በመገንዘብ ሁለትም ሦስትም ክልሎች ለጋራ ክልላዊ መደጋገፍና ብሎም ለጋራው አገራዊ ሰላም፥ ልማት፥ ፍቅርና አንድነት የሚበጁ ሥራዎችን ለማከናወን ያስችላቸዋል። ዝምድና መፍጠሩና ማዳበሩ መብታቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ኢህአዴግ አባላት እህት የተሰኙት ድርጅቶች እንደክልል መሪዎች እህት/ወንድም ቢሆኑ የሚጠበቅ [ሊጠበቅም የሚገባ] በመሆኑ ነው።

ሆኖም ፓርቲዎቹ በኢህአዴግ አባልነታቸው የሚያደርጓቸው የርስ በርስ ግንኙነቶችን የሚመለከቱ መርሆችና ደንቦችን በማውጣት የተከለከሉና የተፈቀዱ፥ ያልተከለከሉና ለያንዳንዱ ድርጅት ምርጫ የተተዉ ጉዳዮችን በግልጽና በዝርዝር በማስቀመጥ፥ የሁሉን ይሁንታ ካገኙ በኋላም በጋራ መመሪያነት ተቀብሎ ማጽደቅ ቢቻል የአባል ድርጅቶቹ ግንኙነት ተቋማዊ መሠረት እንዲኖረው ያደርጋል። ለምሳሌ የኢህአዴግ መሪዎች ከግምገማው በኋላ በሰጡት መግለጫ የአመራር ችግር ተብለው ከተነሱት አንዱ መርሕ አልባ ግንኙነት ነው። ሆኖም “መርሕ አልባ ግንኙነት” ማለት ለምሳሌ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች መሪዎችና ሕዝቦች መካከል የተደረገው ዓይነት አለመሆኑን አቶ ደመቀ አስረድተዉናል። እሳቸው እስኪናገሩ ድረስ ግን መርሕ አልባ ሲባል ያንን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ነበር የሚመስለው። ስለሆነም የአመራር አባላትን ግንኙነት መርሕ አልባ በማለት በቀላሉ የመፈረጅ አደጋን ለመከላከል ግልጽ የሆነ ትርጉምና የግንኙነት መርሆችን መዘርዘር አስፈላጊ መሆኑ አይቀርም። ሌላው የተነሳው ችግር ‘የኔ ወገን ለሚሉት ማድላት’ ነው ተብሏል። ሆኖም ‘የኔ ወገን ለሚሉት ማድላት’ በምን ይገለጻል? በህግና ደንብ፥ መመሪያ ወይም አሠራር ወይስ ሕገ ወጥ በሆነ ተግባር? በሕግ/ደንብ የሚገለጽ አድልዎ ለማረም አያስቸግርም፤ በዚያው ልክ የአመራር አባላትን ድርጊቶችና ግንኙነቶችን የሚመለከቱ መርሆችን በማስቀመጥ ተገቢና “መርህ አልባ” የሚሰኙትን ለመለየት፥ መልካሙን እያበረታቱ ጎጂውን ለማረም የሚያስችልና ሁሉንም የሚያግባባ መንገድ ለመቀየስ ይቻላል። በአመራሩ መካከል የሚኖረው ግንኙነትም የጋራ ግዴታውን ያልዘነጋና ሁሉም የተስማማባቸው መርሆችና ደንቦችን የተከተለ እስከሆነ ድረስ አባል ፓርቲዎች የሚያከናውኑት ሥራ ዞሮ ዞሮ ከጋራ ድርጅታቸው ዓላማና ጥቅም ውጭ የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው። ይሁንና ከእህት ድርጅቶቹ አንዱ የፈጸመው ተግባር ከድርጅቱ ዓላማ ውጭ ነው/አይደለም የሚል ክርክር ቢነሳም በግልጽ የተቀመጡ መርሆችና ደንቦች መኖራቸው ለመካሰስና ለመዋቀስም ሆነ ለመማማር፥ ባጠቃላይ ለሚተላለፍ ውሳኔ ሁሉ ሕጋዊ መሠረት ተበጀለት ማለት ነው።

ከዚህም ባሻገር ከላይ እንደተጠቀሰው ወደፊት በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ ተዘርግቶ ጠንካራ ፓርቲዎች ተፈጥረው በክልልና በፌዴራል ምክር ቤቶች ፉክክሩ ጦፎ፥ ማንም ድርጅት ለብቻው መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል የወንበር ቁጥር የማያገኝበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል፥ በዚያን ጊዜም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመደራደርና በመዋሐድም ጭምር መሥራት አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው።

 

2.3 በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ የአባል ድርጅቶች ግንኙነት

በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እውን በሆነበት ሁኔታና እንዲሁም በግንባታው ሂደት አራቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች በግንባሩ ጥላ ሥር ሆነው በአንድነት ለአንድ ዓላማ ቢሰለፉ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ከተፎካካሪዎች ጋር በሚያደርጓቸው ውድዱሮች ርስ በርስ በመደጋገፍ አሸንፎ የመውጣት ዕድላቸውን ሊያሰፉ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። በተፎካካሪዎች ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት የአንድነቱ አስፈላጊነት ባያከራክርም አንድነቱ ብቻውን አባል ድርጅቶች በየክልላቸው እንዲመረጡ ዋስትና አይሆናቸውም፤ አባል ድርጅቶቹ አንድ የጋራ ዓላማ በማራመዳቸው ምክንያትም በድልም ሆነ በሽንፈት ዕጣ ፈንታቸው የግድ አንድ አይሆንም። ለምሳሌ አንዱ የኢህአዴግ አባል ድርጅት በሚወዳደርበት ክልል በተፎካካሪ ፓርቲ ተበልጦ ቢሸነፍና በፌዴራል ም/ቤትም ጥቂት ወንበሮችን ብቻ ቢያገኝ፤ በአንጻሩ የተቀሩቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የየክልሎቻቸውንና የፌዴራል ም/ቤቶችን ወንበሮች ቢያሸንፉ፤ ግንባሩ ኢህአዴግ በሦስቱ አማካይነት የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን ይይዛል፤ ሦስቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ደግሞ የየክልሎቻቸውን መንግሥታት ሥልጣን ይይዛሉ። የክልሉን መንግሥት ምክር ቤት ወንበሮች ለማሸነፍ ያልቻለው አራተኛው አባል ድርጅት በበኩሉ የግል ዕጣ ፈንታው ለቀጣዩ ምርጫ መዘጋጀት መሆኑ አይቀርም።

እንዲሁም አራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያሸነፏቸው የፌዴራል ም/ቤት ወንበሮች ቁጥር መንግሥት ለመመስረት ከሚያስፈልገው በታች ሆኖ ቢገኝ፥ ኢህአዴግ መንግሥት ለመመስረት ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መደራደርና አብሮ ለመስራት መስማማት ይኖርበታል። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያገኙት የክልል ም/ቤት ወንበር ቁጥርም እንዲሁ መንግሥት ለመመስረት በቂ ካልሆነ ተቀዋሚ ፓርቲዎችን ወክለው ም/ቤት ከገቡት አባላት ጋር በተናጠል መደራደር አማራጭ አይኖረውም። ከዚህ አንጻርም ሲታይ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች በአላማ እና/ወይም በአደረጃጀት አንድ ቢሰኙም ዕጣ ፈንታቸው የግድ አንድ ይሆናል ማለት አይደለም።

 

በተጨማሪ በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እውን በሚሆንበት ጊዜ እህት ድርጅቶቹ በክልል ደረጃ ሲወዳደሩም ሆነ በጋራ የፌዴራል መንግሥት ለማቋቋም ሲተባበሩ የእያንዳንዱ ድርሻ የተለያየ መሆኑ አይቀርም። እንዲያውም ሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች እንደመሆናቸው መጠን አንዱ ለሌላው ወሳኝ አስተዋጽኦ ሊያደርግ መቻሉ ያጠራጥራል። ከስልጣን አንጻርም የአባል ድርጅቶቹ መለያየት በራሱ በተናጠልም ሆነ በጋራ የሚያስከትልባቸው ጉዳት ለማየት ያስቸግራል። ለምሳሌ አራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ተለያይተው ለፌዴራል ም/ቤት ወንበሮች በጋራ ሳይሆን በተናጠል ተወዳደሩ እንበል። ከምርጫው በኋላ እያንዳንዱ ያሸነፈውን ወንበር ይዞ ሁሉም በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መገናኘታቸው አይቀርም። [በክልል እንደሆነ አሁንም አይገናኙም።] ታዲያ በፌዴራል ምክር ቤት ተገናኝተው መንግሥት ለመመሥረት የግድ መደራደርና መስማማት ይኖርባቸዋል — ማለትም የዛሬዎቹ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ቢለያዩም እንኳ ተለያይተው አይለያዩም፤ የሚገናኙበት የጋራቸው የሆነው የፌዴራል ም/ቤት አለና። እንዲያውም ከዚህ አኳያ ሲታይ አራቱም እህት ድርጅቶች ርስ በርስ የሚፈላለጉበትና ሁሉም አንድነቱን የሚንከባከቡበት ምክንያት ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል።

በዚህ መሠረት ‘አንድነት የህልውና ጉዳይ ነው’ እያሉ ተሳቆ ማሳቀቅ ሳያስፈልግ በነጻነትና ያለ ምንም ፍርሃት የሚያዳብሩት መቀራረብና አንድነትም ቀጣይና ምናልባትም ዘለቄታዊ የመሆን ዕድሉ ሰፊ እንደሚሆን ለማየት አይቸግርም።

 

  1. የኢህአዴግ አደረጃጀት በመንግሥት ሥራና በሕዝብ ላይ የሚያደርሳቸው ችግሮች

የኢህአዴግ ድርጅታዊ የውስጥ ችግሮች ለብልሹ አስተዳደር መንሰራፋትና ለመልካም አስተዳደር መጥፋት ምክንያት መሆናቸውን ከአመራሩ ኑዛዜ ተገንዝበናል። በዚህ ክፍል በድርጅቱና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት የሕግ የበላይነት እንዳይከበር ለማድረግ ያለውን አስተዋጽኦ እንመለከታለን።

ኢህአዴግ ሐሳብ ብቻ የታጠቀ ጠመንጃ አልባ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ አያውቅም። በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲነትንማ የት አይቷት። በረኸኛ ሆኖም መንግሥት ተሰኝቶም ሲፋጅ በጠበንጃ ሲቀዘቅዝ በቃል ሲያዝ የኖረ ድርጅት ነው። ሁሌም አዋቂ ነው፤ ሰዉ — ሕዝቡም ሆነ ተቃዋሚ ድርጅቶች — ኢህአዴግ ያቀረበላቸውን ሐሳብ ለመቀበል ቢያንገራግሩ ችግሩ ከነሱ ነው። ሕዝቡ ችግሩ ከራሱ መሆኑን ውሎ አዱሮ እስኪገነዘብ ድረስ በስብሰባ ይጠምዱታል፤ ተቃዋሚ ፓርቲውን በድርድር፤ እምቢ ካሉ ሁለቱንም አሳራቸውን የሚያበሉበት ኃይል አያጡም።

የታህሳሱን ግምገማ ተከትሎ ማብራሪያ ከሰጡት መሪዎች መካከል ሕገ መንግሥቱን የነቀፈ አንድም አልነበረም። ሁሉም ችግሩ ሕገ መንግሥቱ ሳይሆን የሕገ መንግሥቱ አለመተግበር ነው ብለዋል። ግን ያልተተገበረበትን ምክንያት አልነገሩንም። ኢህአዴግ እንዲያ የሚመካበትን ሕገ መንግሥት እንዳያከብር ማን ከለከለው? አንደኛው ምክንያት ኢህአዴግ አሁንም ትጥቁን ያልፈታ ታጋይ ድርጅት እንጂ መንግሥት ለመሆን አለመቻሉ ሲሆን፥ ሁለተኛው ምክንያት የፓርቲው አመራር ከአገሪቱ ሕጎች ሁሉ በላይና ከፍተኛው የስልጣን አካል ሊሆን መቻሉ ነው። አራት አባል ድርጅቶችንና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላትን የያዘው ኢህአዴግ አደረጃጀቱን በሚመራበት ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ አማካይነት የበላዩ የበታቹን እየታዘዘ በተዋረድ አባላቱ በደረሱበት ሁሉ ውሳኔዎቹ እንዲተገበሩ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያለው ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። ገዢ ፓርቲ እንደመሆኑም አቋሞቹን ሕግ በማድረግ በመላ አገሪቱ እንዲተገበር ለማድረግ ይችላል። ችግሩ ፓርቲውንና መንግሥቱንም የሚመራው ያው የኢህአዴግ አመራር ሲሆን እንደ ፓርቲ የፓርቲ ሥራ፥ እንደ መንግሥት ደግሞ የመንግሥት ሥራ ሲሠራ በሁለቱም መካከል ያለውን ሕጋዊ ድንበር ለማክበር አልቻለም። በመንግስትና በፓርቲ መካከል ሊኖር የሚገባው ድንበር ባለመጠበቁ በመንግሥት ብቻ ሊታዘዝ የሚገባው ጦር በፓርቲው ይታዘዛል። በሌላ አባባል የፖርቲ/መንግሥት ድንበር ባለመጠበቁ ኢህአዴግ አሁንም ትጥቁን አልፈታም። አሁንም ታጣቂ፥ አሁንም ታጋይ ነው። ብቸኛው ባለትጥቅ ፓርቲ በመሆኑም በአመራሩ መካከል የሚፈጠረው ችግር በፓርቲው ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር አድርጎታል። በኢህአዴግ አመራር መካከል ችግር ሲፈጠር የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር የተነገበ ጠመንጃ የውስጠ-ድርጅት የቡድን ወይም የግለሰብ አመራር ጥቅም፥ ስልጣን ወይም ሙግት ለመደገፍ አልያም ለማጨናገፍ በማስፈራሪያነትና በማሸበሪያነት ጥቅም ላይ ይውላል። ጠመንጃ ባይኖረው ኖሮ ያ ሁሉ አይሆንም። የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራር አባላት ተጣሉ ሲባል ስንሰማ ኖረናል። ሆኖም ምርጫ ቦርድ ላንዱ ማኅተም ለሌላው የድርጅት ስም ሲሰጥ ሲነሳ፥ ሁሉም የተሰጠውን ተቀብሎ የተቀማውን ባይዋጥለትም ይሁን ብሎ ይኖራል። ጸቡ አገር ሳያሸብር የቀረው ነገሩ ጦር የማያማዝዝ ሆኖ አይደለም። ኢህአዴግ ግን በፖለቲካ ሕይወቱ ሁሉ ጠመንጃ ተለይቶች አያውቅም። ስለሆነም በአመራሩ መካከል የሚፈጠር የግንኙነት መሻከር የድርጅቱን ህልውና ከመፈተን አልፎ የአገርን ሰላም ያደፈርሳል፤ ሕይወት ያጠፋል፥ ንብረት ያወድማል።

በሌላ በኩል ያው አመራር ድርጅትና መንግሥትን እንደሚመራ ሁሉ ለድርጅትና ለመንግሥት ሥራም የሚያሰማራቸው እነዚያኑ አባላቱን ነው። መሆኑም በተለይ የአባላቱን ሥራ ሲገመግም፥ ጥፋቶቻቸውንም ሲመዝንና የእርምት እርምጃ ሲወስድ የመንግሥት ሰራተኝነታቸውን ትቶ አባልነታቸውን ብቻ መመልከቱ አልቀረም። በመንግሥት ሥራ ኃላፊነትን የሚሰሩትንም ጥፋት ጨምሮ ድክመቶቻቸውን ቁርጠኝነታቸውን እንዲያረጋግቱ፥ የተዛባ አመለካከታቸውን በቀናው በማስተካከል ለመፍታት ይሞክራል። በዚህ ምክንያት ራሳቸው እንደሚሉት የድርጅት አባልነት ባለስልጣንነት ወደ መንግሥት ሥልጣን መወጣጫ መሆኑን የተረዱ ሰዎች ድርጅቱ ውስጥ ገብተዋል። በአገሪቱ ሕግ ወንጀል ተብለው ቅጣት የተቀመጠባቸው ድርጊቶች በአባላት ሲፈጸሙ ከመቅጣት ማስተማርን ባስቀደመ ሆደ ሰፊነት ይታለፋሉ። ይህን ማድረግ በመቻሉ ድርጅቱ እንደ ድርጅት ከሕግ በላይ ሆኗል። የፓርቲው ባለስልጣናት ይህን ማድረግ እንደሚችሉ የተገነዘበ አባል የመንግሥት ሕጎችን ከማክበር ይልቅ ለድርጅቱ ኃላፊዎች ትዕዛዝ ቅድሚያ መስጠቱ አይቀርም። ቅድሚያ አልሰጥም ካለም ምንም ሕግ ከፓርቲው እርምጃ እንደማያስጥለው ያውቃል።

የፓርቲው አባላት የመንግሥትን ስልጣን ይዘው በሚሠሩት ሥራ ተጠያቂነታቸው ለፓርቲ ብቻ በሆነበት ሁኔታ ፓርቲው በወንጀል መጠየቅ የሚገባቸውን አባላቱን በፓርቲ ደረጃ በተግሳጽ እንዲታለፉ ማድረጉ ስለማይቀር ፓርቲው የዘራፊዎች ምሽግ እንደሆነ ይቀጥላል። ባለስልጣኖች ለሰሩት ሥራ በአባልነታቸው በፓርቲ መድረክ እንዲገመገሙና ወንጀሉ የዲሲፕሊን ጉድለት ተሰኝቶ እንዲቀርብ በማድረግ፥ በግምገማ ሽፋን [አባላት] ከተጠያቂነት ውጭ እንዲሆኑ ከማድረጉም ባሻገር የመንግሥት ተቋሞችን ገለልተኝነት በማጥፋት የፍ/ቤቶችንና ሌሎች ተቋሞችን ሥራ በድርጅት ግምገማ ልተካ ባይ ይሆናል።

የፓርቲው ስልጣን የበታች ለበላይ መታዘዝ አለበት በሚለው የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ አማካይነት ያልተማከለውን የመንግሥት መዋቅር ተሻግሮና ምንም ሕግ ሳያደናቅፈው ከኢህአዴግ አመራር መንጭቶ በፌዴራልና በክልል ለሚገኙት አባሎቹ በተዋረድ የሚፈስ ሆኖ ይገኛል። ሆኖም በህጎችና የአስተዳደር ክልሎች ሳይገደብ በዘረጋው መዋቅር ገሸሽ ባላቸው ህጎችና አስተዳደራዊ ወሰኖች ልክ አባላቱ በየደረጃው የሚጥሷቸውን ሕጎች እንዲያከብሩ የማድረግ አቅሙን አጥፍቶታል።

የፓርቲው መዋቅርና የመንግሥት መዋቅር በመቀላቀሉ የመንግሥት ሠራተኛ በሕግ ብቻ እንዲመራ ተደርጎ፥ ማንም ቢያጠፋም ቢያለማም በሥራው ተመዝኖ የሚገባውን ያግኝ እንዳይባል አንድ አባል የሚፈጽመው ሕገ ወጥ ሥራ በራሱ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን በፓርቲው ትዕዛዝ የተሰጠበትም ሊሆን ይቻላል። በመሆኑም ከፓርቲ በሚወርድ መመሪያ መሠረት [ለምሳሌ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን የሚያጠቁ] ሕገ ወጥ ድርጊቶች የፓርቲው አባል በሆነ የመንግሥት ባለስልጣን የተፈጸሙ ቢሆንም የሥራው ባለቤት ያው ፓርቲው ነው። ፓርቲው ከህግ በላይ እስከ ሆነ ድረስ አባላቱም በፓርቲው መመሪያ ሲወርድላቸው የሚጥሱትን ሕግ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ቢጥሱት ጠያቂ እንደማይኖራቸው ያውቁታል። ጠያቂ ቢኖርም ያው የፓርቲ ባለስልጣን ነው። ፓርቲው ከሁሉም ሕጎች በላይ በመሆኑም የአባላት ተጠያቂነት ለፓርቲው ብቻ ይሆናል።

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሕገ መንግሥታዊ ተቋሞች ብቻ ሊጠበቅ ሲገባው ጭራሽ የሥርዓቱ ህልውና ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አንድነት መቀጠል አለመቀጠል ጋር በማያያዙ፥ የግንባሩንም ህልውና በአመራሩ መግባባት/አለመግባባት የሚወሰን አድርጎ በመተው፥ አውቆም ይሁን ሳያውቅ የኢህአዴግ አመራር ለድርጅቱ የሚሰጠው ቦታ ከሕገ መንግሥቱ በላይ ሲሆን አመራሩ ለራሱ የሚሰጠው ቦታ ደግሞ ከድርጅቱ ኢህአዴግ በላይ መሆኑ አልቀረም። ስለሆነም ኢህአዴግ ከሕግ በታች መሆን እስካልቻለ ድረስ አመራሩ/አባላቱም ሕግ እየጣሱ መቀጠላቸው አይቀርም።

 

3.1 የመበስበስ ግርሻን ለመከላከል ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት

የኢህአዴግ አመራር ዛሬ እንደ ድክመት የሚያነሳው መቧደንና መርህ አልባ ግንኙነት አብሮት የኖረ የቤት ጣጣው ሲሆን፥ በዚያው ልክ ግለሰብና ቡድን ተሻጋሪ ለሆነው ተቋማዊ አስተሳሰብ እንግዳ ነው። ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ደጋግሞ ሲያነሳ እንሰማለን። ሆኖም ሥርዓቱ ሕግ አክብሮ ከመሥራት ጋር፥ የተቋሞችን ገለልተኝነት ከማረጋገጥ ጋር፥ ከዜጎች መብት ጋር ያለው ግንኙነት አይታየውም። በግንባር ደረጃም ያለው ችግር ተቋማዊ አሠራር ካለማበጀት/ካለመከተል፥ ተቋማዊ አስተሳሰብ ካለመልመድ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ከአመራሩ ማብራሪያ ብቻ ለመገንዘብ ይቻላል። ድርጅቱ በየጊዜው የአመራር ቀውስ ውስጥ ሲገባ፥ ሲገማገምና ተከፋፍሎ፥ ተለያይቶ ታድሼ መጣሁ ሲል የኖረበት አንዱ ምክንያት ተቋማዊ ዓላማዎቹና መርሆቹ ተለዋዋጭ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የድርጅቱን ደንብና አሠራር ገሸሽ ከማለትና ከተቋማዊ አስተሳሰብ ያለማዳበር ጋር መያያዙ አይቀርም።

ከግምገማው በኋላ የኢህአዴግ የቀድሞ አመራር አባላት ድርጅቱን በዚህ ሁኔታ ጥለን አንሄድም በማለት አስቀድመው ያቀረቡትን የስንብት ጥያቄ በማንሳት ወደ ፓርቲው መመለሳቸውን ሰምተናል። ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙት መብቶች ተጥሰው፥ የተዘረጋው ሥርዓት ፈርሶ እነሱ የታገሉለትና በርካቶች የተሰዉለት ድል ተቀልብሶ መና እንዳይቀር በማለት ነው ተብሏል። ታዲያ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ቀጣይነት ሊረጋገጥ የሚችለው ዛሬ በተለይ ኢህአዴግን ጨምሮ በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ታውቆ የታመነበትና በሁሉም የሚከበር የፓለቲካ ፉክክር ሥርዓት ለመሆን ሲችል ብቻ ነው። ለዚህም ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጥበቃ/ጥገኝነት ነጻ ወጥቶ ተቋማዊ ሕልውና ሊጎናጸፍ ይገባል። ነባር ታጋዮቹ ያቀረቡትን የመልቀቂያ ጥያቄ አንስተው ወደ ሥራ ለመመለስ ግድ ያላቸውም ለመብቶቹም ሆነ ለሥርዓቱ ቀጣይነት የሚያስፈልገውን ተቋማዊ ሥራ ሳይሰሩ በመቆየታቸው ነው። አሁንም ወደ ድርጅቱ ተመልሰው የሚሰሩት ሥራ ምንም ይሁን ምን ተቋማዊነትን ካልተላበሰ እንደጓዶቻቸው ሁሉ እነሱም ሲያልፉ አብሯቸው ማለፉ አይቀርም።

ቀደምቱም ሆኑ የትናንቱ ታጋዮችና ሰማዕታት የፈጸሙት ገድል፥ ሞተው የጠበቁት አገርም ሆነ ታግለው ያመጡት ድል ሁሉ ለሁሉም ያገር ልጅ እኩል የሚደርሰውን ያክል፤ እንደውለታቸው ሁሉ ዝምድናቸውም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ነው። ሕይወት ከፍለው የጠበቁለትን መልካሙን ሁሉ እንደተጠበቀ እንዲዘልቅ የሚተጋውና ዘመኑ የሚጠይቀውን ኃላፊነት ለመወጣት በሚደረግ ጥረት ሁሉ የነሱን ጽናት የሚመጥን ወኔ ታጥቆ የሚሰራው ሁሉ የአደራቸው ጠባቂና አክባሪያቸውም ነው። ጋዜጠኛው፥ ጦማሪው፥ ተፎካካሪ ፓርቲው ሁሉም የዚያው ጥረት ተዋናዮች ናቸው። የሥጋ ዘመዶቻቸውን ጨምሮ ለታጋይ/ሰማዕታቱ የተለየና የበለጠ ቀረቤታ አለኝ የሚል ሁሉ ወገንተኝነቱ የሚለካበት ለፍትሕ፥ እኩልነትና ነጻነት፥ ለፍቅርና ለአንድነት የሚደረግ ጥረት ሊሆን ይገባል። ከዚህ አንጻር ኢህአዴግ ራሱ በኢኮኖሚው ረገድ ኢፍትሐዊ የሚለውን ሥርዓት በመገንባት ላይ መሆኑና ፍትሕንም ለመበየን አለመቻሉ፥ ጭራሽ ራሱ ባመነው ስልጣንን ለዝርፍያ መጠቀሙ ብቻ አደራ በሊታነቱን የሚያረጋግጥ ሲሆን እረፍት ይቅርብን ብለው ወደ ሥራ የተመለሱት ነባር ታጋዮችም የሚደክሙት አሁን ያለው ሁኔታ እንዲቀጥል ለማድረግ ከሆነ ትርፉ ድካም ነው። አንጋፋዎቹ ታጋዮች ዛሬ ኢህአዴግን ጨምሮ ማንም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት ሊደክምለት የሚገባው ዓላማ ከአንዳች ኢትዮጵያዊ አመለካከት አልያም ከተጨባጭ የአገራችን ልዩ አቋሞችና ችግሮች የሚንደረደርና የወደፊቱን አገራዊ መዳረሻ የሚያመላክት ሆኖ ሕዝብንና አገርን ከነጣቂዎች ጠብቆ አገራዊ አቅምን የሚገነባና አገራዊ እሴቶችን የሚያጎለብት ሊሆን እንደሚገባ አያጡትም።

 

  1. የእርምት እርምጃ ከየት ይጀመር?

የፖሊሲ ችግሮችን ለመፍታት ቅድሚያ በአመራሩ መካከል በየጊዜው የሚቀሰቀሰውን መጠራጠር በድርጅት ሕልውናና በአገር ሰላም ላይ አደጋ እንዲደቅን ሊፈቀድለት አይገባም። መቼም ኢህአዴግ ትጥቁን እስካልፈታ ድረስ ይህን ለማረጋገጥ አይቻልም። ሆኖም ከላይ ለማስረዳት እንደተሞከረው የአባል ድርጅቶቹ አንድነት የሞት ሽረት ጉዳይ አለመሆኑን ከመገንዘብ ቢጀመር፥ የኢትዮጵያ አንድነትም የአራቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አንድነት— ያውም በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ የቆመ አንድነት —  በቦታው ሲኖር ብቻ የሚረጋገጥ አለመሆኑን መረዳት ቢቻል ይጠቅማል። የዝርፊያውን መፍትሄው ለማለት ያክል እነሱም ይሉታል። አዎን የሕግ የበላይነትን በማረጋግገጥ ነው የሚፈታው። ሆኖም የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅር በተቀላቀሉበት ሁኔታ የሕግ የበላይነት ማለት ምን ማለት ይሆናል? የኢህአዴግ አባል የሆነ የመንግሥት ሠራተኛ/ባለስልጣን በሕግና በህግ ብቻ ይስራ ማለት ነው? ፓርቲው የሚሠጠውን መመሪያ ከተቀመጠለት ህጋዊ አሠራር ጋር የሚጋጭ ቢሆን አልቀበልም ይበል ነው? ፓርቲው ቀድሞ ነገር የመንግሥትን ሕግ የሚጥስ መመሪያ/ትዕዛዝ ለአባላቱ ማውረድ የለበትም ነው? አውርዶሳ ቢገኝ ምን ይደረጋል? ፓርቲው ራሱን ከሕግ በታች ለማድረግ ቆረጠ ሊባል የሚችለው የመንግሥት ሰራተኛ/ባለስልጣን የሆኑት አባሎቹ በሕግና በሕግ ብቻ እንዲሰሩ፥ ሕግ ጥሰው ቢገኙ ግን እያንዳንዱ በስራው ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ ሲፈቅድ ነው።

አሁን ያለው እውነታ ግን ባንድ በኩል የፓርቲ አባልነት ለመንግሥት ስልጣን መወጣጫ መሰላል ሲሆን ፓርቲውም የመንግሥትን ስልጣን ተጠቅሞ የራሱን ሕገ ወጥ ፍላጎቶች ለማራመድ ሲል ያንኑ ባለስልጣን መረማመጃ የሚያደርግበት ነው። ስለዚህ በስልጣን አላግባብ ተጠቃሚው ግለሰብ ባለስልጣኑ ብቻ ሳይሆን ድርጅቱም ጭምር በመሆኑ ማን ማንን ሊቀጣ ይችላል? ስለዚህ እያንዳንዱ ጥፋተኛ በሥራው ልክ በተናጠል እንዲጠየቅ ካልተደረገ በቀር የፓርቲው መሪዎች ቢፈልጉም ችግሩ አይጸዳም። ከዚህ አንጻር በተለይ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ችግር ኢህአዴግ ራሱን በራሱ በማረም ሊፈታው አይችልም። በርግጥ ጠንከር ባሉ ድንቦች አማካይነት የአባላቱን ሥነ ምግባር ደረጃ ከፍ ለማድረግ ሊጣጣር ይችላል። በመንግሥት ሥራ ውስጥ የሚሳተፉ አባላቱን በሚመለከት ግን እያንዳንዱ ሰራተኛ ለሚፈጽመው ጥፋት በግሉ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ፥ ይህንንም ለማረጋገጥ ገለልተኛ የመንግሥት መ/ቤት ማቋቋም ወይም ካሉት መካከል መርጦ ገለልተኝነታቸውን በሚያጠናክር መልኩ እንዳዲስ በማደራጀት ሥራውን መስጠት ነው።

 

4.1 የአበዳሪ ቅኝ ገዢዎችን “ልማት” ከማስቀጠል ተነስና አገሬን በል!

ኢህአዴግ ድኽነትን ለማጥፋት የመረጠው መንገድ ፀረ ድኻ ሥርዓት መገንባት መሆኑ አስገራሚ ሊሆን ይችላል። ፓሊሲው ኢህአዴግ መርጦት ሳይሆን የግዱን የተቀበለው መሆኑ ደግሞ በጣም ያሳዝናል። ከላይ እንደተጠቀሰው የፖሊሲው እውነተኛ ባለቤቶች ፈረንጆች ሲሆኑ ኢህአዴግ እንደ አንድ ሰው ተስማምቶ የቀረበለትን በሚያጸድቀው ፓርላማው፥ እንደ አንድ ሰው በተዋረድ በሚሰራው መዋቅሩ የፈለጉትን ሲፈጽምላቸው ኖሯል። በተለይ በ2012 እኤአ የኢትዮጵያን የዕጽዋት ዘር ሐብት እንዳሻቸው ለመመዝበርና ገበሬውንም ለየዕጽዋት ዘርና ማዳበረያ ደንበኛ ለማድረግ ያስቻሉ ሕጎችን አስረቅቀው አጸድቀዋል። አንድ የገበሬ ወገን ነኝ የሚል ድርጅት የመንግሥት ሥልጣን በያዘበት አገር ይህ ሊደረግ አይገባም ነበር። ሆኗል። አሁን ለውጥ ማምጣት አለብን፤ በማዘዝ ሳይሆን በማሳመን መምራት አለብን የሚለው አዲሱ አመራርና በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን ትልቅ ጥፋት ለማስወገድ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀው ሊረዳ ይገባል።

ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያለበት የወቅቱ ዐቢይ ፈተና ከሁሉ በፊት የአገርን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን አመንጭቶ ለመተግበር የሚችለው የሉዓላዊ አገር መንግሥትነት መለያ ባህሪ የሆነውን የአገር ፖሊሲ አስተዳደር ስልጣን ከአበዳሪ/አጋር ድርጅቶች ትዕዛዞችና ጫናዎች ነጻ አውጥቶ እጅ ማስገባት ነው። የአገርን ዕድገት አቅጣጫ የሚወስኑ ቁልፍ ዕቅዶች በባዕዳን ቁጥጥር፥ ትዕዛዝና ጫና ሥር እስከሆኑ ድረስ ለሕዝብ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ገንዘብ ልመድብ ቢሉ ቅድሚያ ለብድር ክፍያ በሚል ይከለከላል፤ መንግሥት ሊሠራው የሚገባ ሥራ ሁሉ ‘እዚህ ውስጥማ መንግሥት መግባት የለበትም’ ይባላል፤ ለምሳሌ በትምሕርት ዘርፍ መዋቅር ላስፋ ቢሉ ‘መንግሥትማ ሥራው ደመወዝ መክፈል ብቻ ነው መሆን ያለበት ይባላል፤ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት አኳያ [አሁን ለታ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከውጭ በሚገባ ብረትና አሉሚንየም ላይ 25% ታሪፍ እንደጣሉት] ወደ አገር የሚገባ ሸቀጥ ላይ ገደብ እንዳይጣል የነጻ ገበያ ሥርዓቱን ማወክ በሚል ያገር የኢኮኖሚ በር ክፍቱን ያድራል፤ [ሌላው ቤቱ ይቅቁጠረው] በዚህ መልኩ መንግሥት በገዛ አገሩ የመሪነትን ስም ብቻ ከጠመንጃ ጋር ተሸክሞ ችግራቸውን እያወቀ በመፍትሔ እጦት በሚጮኹት ዜጎቹ ላይ ለመተኮስ ከተገደደ ቢያንስ መሪ አለመሆኑን አይክድም።

በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ ያለበት ሁኔታ ከዚህ ምን ያህል እንደሚለይ እሱ ባያጣውም የሕዝብን ችግር እፈታለሁ ብሎ ፎክሮ ሲያበቃ መሬት ላይ ጠብ የሚል ነገር የማይታይበት ምክንያቱ ካለበት የስልጣን ውሱንነት ጋር መያያዙ አይቀርም። ከዚህ አንጻር የችግሩን ምንጭና መፍትሄውን ሌላ ሌላ ቦታ ከማፈላለግ፥ ችግሩን በደፈናውም የአመራር ችግር ነው ብሎ ለማለፍ ከመሞከር፤ የችግሩንም መፍትሔ አንዴ በስልጣን ላይ ያለን አመለካከት ማስተካከል ሌላ ጊዜ ለውጥ ለማምጣት የቆረጡ ታጋዮችን ማሰባሰብ’ ከማለት ይልቅ ኢህአዴግ ራሱ ችግር ብሎ የለየውን ነገር ለመፍታት ያፈለቀውን ሐሳብ፥ ያመነጨውን መፍትሄ ሕግ አድርጎ ለማውጣትና ገንዘብ መድቦ ለመተግበር ያለው ዐቅም ምን ያህል እንደሆነ መመርመር ነው። የማይችል ከሆነና ችግሩን ችግር አይደለም፥ ወይም መፍትሄውን መፍትሄ አይደለም የሚል ከልካይ ካለበት ባለስልጣኑ ከልካዩ ነው። ከላካይ ከሌለበት ግን መፍትሔ አይቸግርም።

ሆኖም ከልካይ እንዳለበት፥ ከልካዮቹም የገንዘብ ተቃማቱ መሆናቸው ይታወቃል። ቢሆንም ካላቸው የገንዘብ ዓቅም፥ በተለይም በነሱ አመራር በተንቦረቀቀው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችን ላይ ካላቸው ቁልፍ ሚና አንጻር የፖሊሲ አስተዳደር ስልጣኑን ከባዕዳኑ መልሶ መውሰድ ቀላል ሊሆን እንደማይችል የታወቀ በመሆኑ በማስተዋል፥ በጥንቃቄ የሚተገብረውን መላ መምታት ነው። በዚያ ላይ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችን እነሱ በቀየሱልን ፖሊሲ አለቅጥ ቢሰፋም ወይ አበዳሪ ወይ አበዳሪ [ተበዳሪ አላልኩም] እያሉ አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን በዕቅድና በትጋት እያፈላለጉ ለጊዜው ከነሱ የሚገኘው ብድር የሚደፍነው ቀዳዳ አያጣም [የድኻ ቀብራራ!]። ታዲያ በዚህ ሂደት ሁሉ ከነዚህ ድርጅቶች ጫና መላቀቅን እንደግብ ይዞ የሚሠራ አመራር ያስፈልጋል። እስከዚያውም ድረስ በተቻለ መጠን ተቋማቱ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን የአጭርም ሆነ የረዥም ጊዜ ጥቅም ያስገኛሉ ከሚል የዋህ ድምዳሜ መጠንቀቅ ያሻል። እነሱ ኢትዮጵያን ሸቀጣቸውን ለሚያራግፉበት ሰፊ ገበያዋ፥ ለርካሽ ጥሬ ዕቃዋና ‘የሰው ኃይሏ’ ለሚፈልጓት/ላገኟትም አገሮችና ኩባንያዎች ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚያመቻቹ መንገድ ጠራጊዎች ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ ሥራቸው አይደለም። ስለ ኢትዮጵያና ልጆቿ ማሰብ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አመራር ነው። የፖሊሲ አስተዳደሩን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን ለመተግበር የሚያስችል አቅም መፍጠር የራሱ ግዴታና ኃላፊነት ነው። እስካሁን ድረስ የቅርብ ጊዜውን የብር የምንዛሪ ዋጋ መቀነስን ጨምሮ በዐበይት የአገር ጉዳዮች ላይ ያለ መረጃ ሲወራ ከሚሰሙት ተነስተው እየወሰኑ፥ ሥራውን በገንዘብ ተቋማቱና አጋር በተባሉ ድርጅቶች እጅ የመተዉን [ወይም እንደተተወ እንዲቀጥል የመፍቀዱን] ጥፋት በማስተዋል ወደፊት በሚደረገው ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግና የቁጥጥር ተቋሞችንም መዘርጋት ለመስራት ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። የተቋማቱን እምነቶች የተፈጥሮ ሕግ እስመስሎ ማቅረብ የሚችል ዐቅም ያላቸው እሳት የላሱ ባለሙያዎች እንዳሏቸው ከቶ መዘንጋት አይገባም። ይሁንና አማራጭ የለንም የሚል የቀቢጸ ተስፋ ስሜትና አተያይ የመፍትሔ ምንጮችን በማድረቅ ተወዳዳሪ የሌለው መርዝ በመሆኑ አመራሩ ለጊዜው የሚለውን ባጣበትና በጨነቀው ሰዓትም ጭምር ሊታገለው ይገባል።

አገር ውስጥ የማይገኙና እዚህ ሊመረቱ የማይችሉ አንዳንድ አስፈላጊ ዕቃዎችን መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ምርቶችን መሸጥ ማስፈለጉ ባይካድም እንደ አገር ነጋዴ ለመሆን እንገደዳለን ማለት አይደለም። እንዲያውም ነጋዴ አገር እንድንሆን ግድ የሚል ምንም ምክንያት አለመኖሩን ከቶ መዘንጋት አይገባም። ይህ ማለት ዜጎች በዓለም ገበያ ውስጥ አይሳተፉም፥ ለምሳሌ ኢንተርኔት የሚፈጥረውን ፈርጃ ብዙ ዕድል ተጠቅመው እንደሰዉ ሊነግዱ አይችሉም ማለት አይደለም። ይችላሉ። እንዲያውም የፖለቲካ ግብ ሳያስቅሰምጡ ማደራጀትና ማገዝ ሊያስፈልግ ይችላል። ሆኖም እንደ አገር በሌለ ምንዛሪ ከዓለም አገራት ሁሉ ሸቀጥ የምናስመጣበት ምክንያት የለም፤ ቢኖርም እነሱን መጥቀም ብቻ ነው። ክፋት ላይኖረው ይቻላል። ሆኖም ፍላጎታችን አይደለም። አበዳሪ የተሰኙ ድርጅቶች በሰው ስጥ እንደሚጋብዘው ዶሮ ሆነውብን፤ ጓሯችንም የሞኝ ጓሮ በመሆኑ ነው።

ከዚህ አንጻር የኢህአዴግ አመራር ባጠቃላይ፥ በተለይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር “የተጀመረውን የሕዳሴ ጉዞ ማስቀጠል” ወዘተ ማለቱን ትቶ በቆራነት እስካሁን ሲተገበሩ ከነበሩት “የኢህአዴግ” ከተሰኙ ምዕራባውያን ፖሊሲዎች ራሱን ማራቅና በኢትዮጵያዊ ወገንተኝነቱ ልክ ለኢትዮጵያውያን የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችን፥ በረዥም ጊዜም ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የሚታደጉ አማራጮችን ለመቀየስ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኘውን የኢትዮጵያውያን ኃይል ማስተባበር ያስፈልጋል፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አመራር የሚቀርቡለትን ሀሳቦች ሁሉ “ለሕዝቤ ምን ይፈይድለታል? ምንስ ጉዳት ያመጣበታል? ምንስ አማራጮች አሉት? የሚሉትን ጥያቄዎች በተለያዩና ተቃራኒ አመለካከት ባላቸው አማካሪዎች ጭምር እየታገዘ ለመምረጥና ለመተግበር አብዝቶ ማሰብና መጠንቀቅ ግድ ይለዋል።

የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል ይገባል የሚለው ወገንም ለአገር የሚያስበውን ቀና ነገር የፖሊሲ አስተዳደሩን ስልጣን የያዙት የገንዘብ ተቋሞች ለአገሩ ከሚያስቡትና አስበውም ከሚፈጽሙት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ከሚያራምደው የልማት ማስቀጥል ዓላማ ለያይቶ መመለከት ያስፈልገዋል። ደግሞም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ለመተንተን ሲነሳ ኢህአዴግ ያልነገረንና የህዝቡን ችግር ለመፍታት እንዳይችል ያደረገው መሠረታዊ ምክንያት የአገራችንን ፖሊሲዎች ይዘትና አፈጻጸም የመወሰን ስልጣኑ በአበዳሪ የገንዘብ ተቋሞች ቁጥጥር ሥር የሚገኝ የመሆኑን እውነት ማስተዋል ማየት እንደሚያስፈልገው አያጣውም።

የፖሊሲ አስተዳደር ስልጣኑን ከባዕዳን አለቆቹ ተረክቦ እጅ ሳያስገባ ኢህአዴግ መቼም ቢሆን ምንም ዓይነት የህዝብ ጥያቄ ሊመልስ አይችልም፤ ጊዜ በገፋ ቁጥር ደግሞ ብድሩና ጥገኝነቱ ይጨምራል። በዚያው ልክ የገንዘብ ተቋማቱ ጫናና ትዕዛዝ ያይላል። ዛሬ የማያዙባቸው ዘርፎች ካሉ [ምናልባት የባንክና የቴሌኮም] አድብተው ጊዜ እየተጠባበቁ መሆናቸውን እርግኛ መሆን ይቻላል። ኢህአዴግሳ? ምን እያሰላ ነው? ዕድገቱን ለማስቀጠል? አለቆቹ በሳቅ እንዳይሞቱበት ይጠንቀቅ! ባዕዳኑ የሚቀይሱት መንገድም የህዝባችንን ችግር የሚፈታ ሳይሆን የየህዝባቸውንና የየወገናቸውን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ የሚቀመር በመሆኑ ያልፈጠረበትን፥ ደንታ የማይሰጠውን የኢትዮጵያውያንን ችግር እንዲፈታ፥ ፍላጎታቸውንም እንዲያሟላ አይጠበቅበትም። የሚያሳዝነው ገዢዎቻችን አስጨንቀው የጫኑብን ጠማማ ፖሊሲዎች ውጤታማ ሳይሆኑ ሲቀሩ ችግሩ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው እያሉ መሪዎቹ ላይ መደፍደፋቸው ሳያንስ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር የሚበጁ ማሻሻያ ካላቀረብን ማለት የታወቁበት ሙያ መሆኑ ነው። በዚያ ላይ የኢህአዴጎች ኑዛዜ ሲጨመር የሚያቀርቡላችሁን የማሻሻያ ዓይነት እያሰቡ አቤት የሚስቁት ሳቅ! ስለሆነም የአበዳሪ ቅኝ ገዢዎችን “ልማት” ከማስቀጠል ተነስና አገሬን በል! ደግሞስ የዐድዋ ድል ሰሞን መሆኑ ቀረ! ባትዋጋ እንኳን. . . እንዲሉ።

 

4.2 ኢሀዴኤግ የመለወጥ ዕድል አግኝቷል፤ የመለወጥ ግዴታም አለበት

ከግዴታው ብንጀምር አሁን ያለንበት አጠቃላይ ሁኔታዎች ኢሀዴግ በመረጣቸው ውሳኔዎች አማካይነት የተፈተሩ ናቸው። ውሳኔዎቹ በማድረግም ባለማድረግም የሚገለጹ ነበሩ። የባዕዳንን የፖሊሲ ጫና መቋቋም ነበረበት፤ አጥፊ ውሳኔዎችን በግድ መተግበር አልነበረበትም። አህሁን ያበላሸውን ለማስተካከል መጣጣር አለበት፤ ኢህአዴግ አገራችንን ከቅኝ ገዢዎች መዳፍ ውስጥ እንዳስገባት ራሱ ፈልቅቆ ለማውጣት መታገል ይኖርበታል። የተፈጠረለት እድል አዲሱ አመራር ያመጣው አዲስ አገራዊ መንፈስ ነው። ይህን ተገንዝቦ፥ በመካከሉ ነፋስ እንዳይገባ አድርጎ አንድ ላይ ቆርጦ ከተነሳ ብዙ ላይቸግረው ይችላል። ለዚህም በጥንቃቄ የታቀደ የእምቢታና የድርድር አቅጣጫ መቀየስ መቻል አለበት። ኢህአዴግ በሚያደርገው ጥረት ሁሉ አዲሱ አመራር ይዞት በመጣው የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት መንፈስ ቢከተል ራሱን ከተዘፈቀበት የርዕዮተ ዓለም ቀውስ እንዲያወጣና እስከ ዛሬ አልያዝልህ ብሎት የኖረውን አገራዊ ዓላማ እንዲጨብጥ ያስችለዋል።

በሁሉ አስቀድሞ እናስቀጥለዋለን የሚለውን ውርስ/ውጥን ምንነት፥ የተባለውን ‘የሕዳሴ ጉዞ’ የሚመሩት ፖሊሲዎች ምንነትና የፖሊሲዎቹን እውነተኛ ባለቤት በሚገባ ተገንዝቦ፥ አንጋች ከማሰማራትና የሕዝብ ገንዘብ ከመዝረፍ የተሻለ ሥራ ሊያሰራ የሚችል ዕቅድ ነድፎ በመተግበር የሚገለጽ፥ የማስተዳደር ሥራ የሚያሰራ ስልጣን በማን እጅ ተይዞ እንደሚገኝ ተረድቶ መልሶ እጅ ማስገባት መቻል አለበት። ኢህአዴግ ሕዝብን የሚጠቅም ፖሊሲ ለመቅረጽ የሚያስችል ስልጣን በእጁ መኖሩን ሳያረጋግጥ፥ ይልቁንም ሌሎች የጫኑበትን ተቀብሎ እያስፈጸመ መቼም ሕዝባዊ ሊሆን አይችልም። በፈረንጆች አድናቆትና በዜና አውታሮቻቸው ልፈፋ ላይ የተንጠላጠለ ሆያ ሆዬውንና የተያዘው መንገድ እውነተኛ ጥቅምና ጉዳቱን መለየት የመሪ ሥራ ለማከናወን ቁልፍ ነው። እውቀት ያስፈልጋል። ሆኖም ሁል-አውቃ መኮን የለበትም። ጥርት ያለ ዓላማ ተይዞ፥ የአገር ጥቅም የሚገኝ የሚታጣበት መንገዱን ለይቶ፥ ወዳጅ ጠላቱንም ጠንቅቆ አውቆ፥ አስፈላጊውንም ሙያ ሁሉ ጠንቅቆ ታጥቆ የተነሳ በማንም ማስፈራሪያም ሆነ ሽንገላ ከመንገዱ አይወጣም። ከባዕዳን ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ሁሉ መብቱንና ጥቅሙን ስለሚያውቅ፥ ማንም — ኃያልም ይሁን ደካማ — አገህን ላስተዳድርልህ ለማለት እንዲደፍር አይፈቅድም። ሲደራደርም ሰጥቶ የሚቀበለውን ስለሚያውቅ የሚያዋጣው ስምምነት ካልሆነ በቀር ማንም ምንን ቢል በጅ አይልም። ደግሞም እውቀትና ሙያውን የታጠቀ በመሆኑ በቀላሉ አይረታም።

ይህንን የኛው አክሊሉ ሀብተወልድ በጊዜው አድርጎታል፤ ኤርትራን ከኢትዮጵያ የመቀላቀል ዓላማውን ይዞ ዓለምን ዞሮ ድጋፍ በማሰባሰብ ያሰበውን ፈጽሟል። ዛሬ ደግሞ ለዚህ ምሳሌ ልትሆን የምትችል አገር ኢራን ናት። የኒኩሊየር ኃይል የማመንጨት ዓላማዋን ይዛ የጀመረችው ጥረት ወደ ጦር መሣሪያ እንዳትለውጠው ስጋት የተሰማቸው ኃያላን አገሮች ከኢራን ጋር ንግግር ጀመሩ። የኒኩሉየር ፕሮግራሙ የእውነት ለሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚውል መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ለመቅረጽ አሜሪካ፥ እንግሊዝ፥፥ ፈረንሳይ፥ ሩሲያ፥ ቻይናና ጀርመን አንድ ላይ ሆነው ድርድር ገጠሟት። እስራኤል በበኩልዋ ድርድሩ እንዲከሽፍ ለማድረግ ትጣጣር ነበር። ሆኖም የኢራን ዲፕሎማቶች ድርድሩን በተደራዳሪ ወገኖችና ለድርድር በቀረበው ጉዳይ ብቻ እንዲወሰንና ወሰኑን ሳያልፍ እንዲዘልቅ በማድረግ ከውስጥና ከውጭ በሚሰነዘር ጫና ሳይረበሹ ትኩረታቸውንም ከተነሱበት ያገራቸው ዓላማ ለአፍታም ሳይነቅሉ ዳር እንዲደርስ ለማድረግ ችለዋል። ዕውቀቱ፥ ዝግጅቱ ነበራቸው። የሚፈልጉትን ያውቁ ነበር። የሚሆናቸውን ባዕዳን እንዲወስኑላቸው አልፈቀዱም። ይልቁንም በዚህ ዓለም ለመኖር የማንንም ፈቃድ መጠየቅ ወይም የማንንም ይሁንታ ማግኘት እንደማያሻቸው ነጋሪ የሚፈልጉ አልነበሩም። አይደሉምም። ከምዕራባውያን ሸር ለማምለጥ የሚፈልግ ሁሉ በኒኩሊየር ድርድሩና በዚያ ዙርያ የኢራንን አካሄድ ልብ ሊለው ይገባል። የኢራን ስኬት ጥቅሙን ለማስከበር ለሚፈልግ አገር ሁሉ ልምድ ከወኔ የሚያሰንቅ ሲሆን የስኬቱን ታላቅነት ማስታወስም በቂ ጥንቃቄና ዝግጅት ለማድረግ ወሳኝ ነው። [እኛ ዘንድ ያገር ሚስጥር የሚባል ነገር መኖሩ ተረሳ ይሆን? የባቄላ ወፍጮ ሁላ! የኛማ ፓርላማ ፈረንጆች ርዳታ/ብድር የተባለ የመግቢያ ዋጋ ከፍለው ገብተው ይመለከቱታል። ምንኛ ይስቁ!]

ስለሆነም ቅድሚያ የራሳችሁ የሆነ አገርና አገራዊ/ሕዝባዊ ፖሊሲ/ዕቅድ እንደሌላችሁ ማመን፥ ከዚያም መቅረጽ ይቻላችሁ እንደሆነ፥ እንቅረጽ ስትሉ አለቆቻችሁ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠንቅቆ በማወቅ መከላከያ ማበጀት ያስፈልጋል። ኢህአዴግ አንዳች  ዐቢይ አገራዊ ዓላማ ቢኖረው ኖሮ ከሥራ ፈትነት ብቻ ሊመጣ በሚችል መጠራጠር/አለመተማመን ተበጣብጦ አይበጠብጠንም ነበር። በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ሊከናወን የሚችልና የሚገባው አያሌ ሥራ ባለበት ባሁኑ ወቅት ግንኙነታችን ሻከረ ብሎ ተሸብሮ ማሸበር ሳያንስ ሥራ ሁሉ ተትቶ ስብሰባ ከተገባ በኋላ ደግሞ ሕዝብን ዘርፈናል፤ ሆኖም ላለመዝረፍ ተስማምተናል፤ ሕዝብ ከሕዝብ አጋጭተናል፤ ላለማጋጨት ተስማምተናል፤ ጭራሽ ድርጅታችን ስህተቱን ማመኑ ትልቁ ጸጋው ነው. . . ቀልድ ነው ሥራ ነው?

እንደ መንግስት መብትን አውቆ ለመጠየቅና ለመደራደር አቅም መገንባት ያስፈልጋል። በመቀጠል የአገራችንን የፖሊሲ አስተዳደር ሥራውን የተቆታጠሩት፥ ‘አማካሪ’ ድርጅቶች ድኻ የሚሏትን ሀብታም አገር ለመዝረፍ የተሰማሩ ጩልሌዎች መሆናቸውን ሳይረሱ ማንነታቸውን ለራሳቸው ማስታወሱ ለጉራቸው መድኃኒት ሲሆን፤ በአገራችን ጉዳይ ዋናዎቹ ባለ ጉዳዮቹ ባለ አገሮቹና ባለመብቶቹ እኛው መሆናችንን እና በገዛ አገራችን ላይ የሚያራምዱት ፖሊሲ እንኳን ስህተት ሆኖ ትክክልም ቢሆን የመቀበል ግዴታ የሌለብን መሆኑን ለአፍታም አለመዘንጋት ነው። በዚህ ጊዜ እነሱም በበኩላቸው የብሔር ልዩነትን እያነሱ አንድነት የላችሁም ለማለት መከጀላቸው፥ ከመካከላችንም አንዱን አይዞህ እያሉ ሌላውን እያጣጣሉ ሊያጋጩን መቃጣታቸው አይቀር ይሆናል። ለዚህ መፍትሄው ከነሱ ጋር ክርክር መግጠም ሳይሆን የእውነት አንድ ሆኖ መገኘት ቢሆንም አፍ ለማስያዝ የሚሰነዘር ደህና ነገር ቢገኝም አይከፋም። ከዚህ ጎን ለጎን ግን የነሱን የድጋፍ ቃል ሰምቶ የገዛ ወገኑ ላይ የሚነሳ እንዳይኖር በጥንቃቄ መጠበቅ ግድ ነው።

በሌላ በኩል አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአገር ወዳድነታቸውና ለሕዝብ ባላቸው ተቆርቋሪነት ምክንያት የገንዘብ ተቋሞቹ በፍቅር ዓይን ሊመለከቷቸው እንደማይችሉና ይልቁንም ድጋፋቸውንም ሊነፍጓቸው እንደሚችሉ ከቶ ሊዘነጋ አይገባም። በመሆኑም ከነሱ ጋር በሚደረግ ግንኙነት ሁሉ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ፥ ከነሱ በኩል መረጃ መጣ ሲባልም በተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ መመዘን ያስፈልጋል። በተጨማሪ ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ፖሊሲዎች ላይ ሙሉ መብት ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ አሃዳዊ አደረጃጀት በተዘረጋው አገር አቀፍ መዋቅር አማካይነት የፈለጉትን ትዕዛዝ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመፈጸም የሚያስችላቸው በመሆኑ አሁን ያለውን አሐዳዊ አደረጃጀት ከነዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነቱ እንዳለ እንዲቆይ ሊፈልጉ እንደሚችሉ አለመዘንጋት ነው። ሆኖም ክልላዊ ስልጣን ተጠቅሞ በክልል የሚተገበሩትን ሥራዎች በተመረጡ ባለሙያዎች ድጋፍ በቂ ግንዛቤ እየወሰዱ በትንሽ በትንሹ ለማስተካከል መሥራትና በሂደቱም የፖሊሲዎቹን ይዘት በተግባር መዝኖ ለመለወጥ መሥራት ግድ ነው። በሌላ በኩል የገንዘብ ድርጅቶቹ ዐቅም ከውጭ ምንዛሪና ከብድር ፍላጎታችን ጋር የተያያዘ መሆኑን በማስታወስ የነሱን ጊዜያዊ አድራጊ ፈጣሪነት ለመመከት የሚያስችል አማራጭ የገንዘብ ምንጭ ለማዘጋጀት መጣጣርና ይህንንም በጥብቅ ምስጢር ይዞ ማራመድ ግድ ነው።

 

ማሳረጊያ፦ የአንድ ተራ ዜጋ ቁጭትቀመስ ምክሮች

የገዢው ፓርቲ የበላዮች የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችንን በፍጥነት የሚጨምሩ እርምጃዎችን እንድንወስድ ሲመክሩና ሲያስገድዱን ቆይተዋል። አገር ውስጥ የሚፈለጉ ዕቃዎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎቻችንን እንድንሸጥ ፥ ገበያችንን ክፍት እንድናደርግና ሸቀጣቸውን በገፍ እንድንገዛ ግድ ሲሉን ኖረዋል። ያኔም ሆነ አሁን ብድር ስንጠይቅ የሚያዙንን እንድንቀበል ማስጨነቃቸው አልቀረም። ወደፊትም ልብ ገዝተን፥ የአገር ወዳድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን ዐቅም አሰባስበን መላ ካልመታን በቀር አይለቁንም። ከውጭ የማናስመጣው የዕቃ ዓይነትና ከማናስመጣበት አገር የለም። አንዳንዱ ዕቃ እዚህ የሚገኝ ብቻ ሳይሆን በተለይ የውጩን ዕቃ ለመተካት ተብሎ በብድር ጭምር በተገነቡት አዳዲስ ፋብሪካዎች የሚመረት ሆኖ ሳለ ያው ዕቃ ከውጭ እንዲገባ ይደረጋል። ለምሳሌ በአገራችን አራት ክልሎች የተገነቡት የማዳበሪያ ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ማዳበርያ እያለ ከውጭ በዶላር ገዝተን እያስመጣን ነው፤ ያገር ውስጡን እንከን አናጣበትም።

በዓመት 16 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ዕቃ ተበድረን የምንገዛ ደህና የፈረንጅ ሸቀጥ ማራገፊያ  መሆናችን ታውቋል፤ ሃብታችንን የማናውቅ መሆናችንም ሁሉም አውቆታል፤ የገዛ ዜጎቻችንን ጉልበት አሳልፈን ለበዝባዥ እንደምንሰጥ ታውቋል። ጭራሽ የዓለም አቀፉ የሰራተኛ ድርጅት ኃላፊዎች እዚህ ድረስ መጥተው ኢንቨስተሩ ዜጎቻችንን ሲቀጥር የሚከፍለው ደመወዝ ለኑሮ የሚበቃ መሆኑን ማረጋገጥ አለባችሁ እስኪሉን ድረስ የዜጎቻችንን ጉዳይ ረስተነዋል። ግዴለም። ልዩ የፖሊሲ ትኩረትና የሚፈልጉት ከውጭ የምናስመጣቸው ዕቃዎች የሚፈጥሩብን ተጨማሪ ፍላጎት የሚመለከት ነው። ተገንብተው ለማያልቁት ግድቦች የሚፈለገውን ትተን በተለይ እንዳሸን ለፈሉት ተሽከርካሪዎች የሚያስፈልገን ላምባና መለዋወጫ ዕቃ ነው። እስከ 1996/7 ዓ.ም 230-280 ሺህ የነበረው አጠቃላይ የኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች ቁጥር ዛሬ 850 ሺህ ደርሷል። በአስራ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ520 ሺ መኪኖች በላይ አስገብተናል። ሀብት መሆኑ እውነት ቢሆንም ይሄ ሁሉ እንግዲህ ነዳጅ ሳይጠጣ፥ ጎማ ሳይጫማ፥ የተጎዳ አካሉ ሳይለወጥለት አይነቃነቅም። አሁንም እየገዛን ነው፤ ያው በብድር። እንግዲህ በምስራቁ ያገራችን ክፍል አለ የሚባለው ነዳጅ የእውነት ካለ ለዛሬ ካልሆነ ለመቼ ሊሆን ነው? ደህና ወዳጅና ሸሪክ ፈልጎ ለማውጣት መጣጣር ግድ ነው። ከዚያ ጎን ለጎን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች እንዲገቡ ማበረታታት፥ መኪና እንገጣጥም የሚሉት ያገር ውስጥ ድርጅቶችም እዚያ ላይ እንዲሰማሩ መጠቆምና ማገዝ፥ እዚህ መጥተው መገጣጠም የሚፈልጉ ትላልቅ ኩባንያዎች የሚፈልጉትን አጥንቶ ማሟላት፥ በመስኩ የሚሰማሩ ልጆችን አሰልጥኖ ማዘጋጀት፥ ለዚህም ልዩ የቴክኖሎጂ ትምሕርት ቤቶችን መክፈት [ጌቶች ከፈቀዱ፤ ደግሞ ለመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ፈረንጁን ጥሩት አሉ!] ከዚያም ጎን ለጎን በላምባ የሚሰሩ መኪኖች ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር መቻሉ የታወቀ ስለሆነ የኛ ሰዎች እዚያ ላይ እንዲሰማሩ ማበረታታት ያስፈልጋል።

አሁን ይህን ሁሉ ያተትኩበትን ምክንያት ላስቀምጥ። በዚሁ በውጭ ምንዛሪ ችግራችን ምክንያት መንግሥት በቅርቡ ብሔራዊ የትንባሆ ሞኖፖል ድርጅት ውስጥ የነበረውን ድርሻ ሙሉ በሙሉ ለጃፓኖች ለመሸጥ መገደዱን ሰምተናል። ሌላም እኛ ሳንሰማው የሸጠውና የፈቀደው ሳይኖር አይቀርም። አበዳሪዎቻችን ግን አሁንም ሌላ አምጡ ማለታቸው፥ ያገርና የሕዝብ ንብረት ስጡን ማለታቸው አይቀርም። ጨካኞች ናቸው፤ ግሪክን ደሴቶቿን ለመሸጥ እስክትገደድ አድርሰዋታል። ያገር ጥቅም የሚጎዱ ጥያቄዎቻቸውን አንቀበልም ማለትና የሚመጣውንም ጫና ለመቋቋም የሚቻለው መንግሥት ሕዝቡን ከጎኑ ለማሰለፍ ሲችል ብቻ ነው። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ እነዚያው ምዕራባውያን አገሮችና ድርጅቶች በፍርደ ገምድልነት የጣሉብንን የጦር መሣርያ ማዕቀብና በወቅቱ ያጋጠመንን የእህል እጥረት ተቋቁመን ለማለፍ የቻልነው ከእግዚአብሔር ጋር በኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነት ስሜት በተፈጠረው ኢትዮጵያዊ አቅም ነበር። ስለሆነም አንድነትንና የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ለማጠናከር፥ እውነተኛ አገራዊ መግባባት ለመፍጠርም የምር መስራት ያስፈልጋል።

ዛሬ በኢህአዴግ አመራር ውስጥ የተነሳው የኢትዮጵያዊነትና የፍቅር አጀንዳ ቢተገበር ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር ከውጭም ከውስጥም በማስተባበር አንድ ላይ እንዲቆሙ ሊያደርግ መቻሉ እሙን ነው። እንግዲህ ኢትዮጵያን በማለታችን ምዕራባውያኑ የገዢዎቻችን አለቆች ያስለመዱንን ብድር ቢከለክሉን፥ የቀራችሁ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከአንድ ወር ተኩል በላይ አያቆይም ቢሉን፥ በድንቁርና የጀመርነው የስንዴ ሸመታ ለመገብየትም ምጽዋቱን ቢከለክሉን፤ ባጠቃላይ ከኤርትራ ጋር ጦርነት በገጠምን ጊዜ እንዳደረጉት አንቀው ሊያሽመደምዱን ቢፈልጉ ሕዝብና መንግሥት አንድ ከሆነ ሁሉንም ለመሸከም የሚያስችል አቅሙና መላው አይጠፋም። ያኔ መንግሥትን ለመርዳት በአንድነት መንፈስ የተረባረቡት ውጭ ኗሪ ኢትዮጵያዊያንን ዐቅም ኢህአዴግ ያውቀዋል፤ ከጎኑ ቢቆሙ አይጠላም፤ ታዲያ ስለ አንድነት፥ ስለኢትዮጵያ የሚያሰሙትን ጩኸት መስማትና በጎ ምላሽ ለመስጠትም የእውነት መትጋት ግድ ይላል።

 

ከዚህ ጎን ለጎን ቃል በተገባው መሠረት ጥፋትን በሥራ ለመካስ መጣጣር ግድ ነው። ከግምገማው በኋላ በተሰጠው መግለጫ ለተሠራው ጥፋት ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀው አመራሩ ህዝቡን በሥራ ለመካስ እንደሚሰራ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም። የእውነት ሕዝብን ለመካስ ፍላጎቱና ማስተዋሉ፥ ወኔውም ካላቸው ፀረ ድኻውን ፖሊሲ ለማሻሻል መታገል ነው። በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥቂት እርምጃዎችን ባስቸኳይ መውሰድ አይከፋም። አንደኛ ሞልቶ በተረፈ መሬትና ውሃ ለአገር የሚበቃ እህል አገር ውስጥ ተመርቶ የሚቀርብበት መንገድ በመቀየስ ህዝቡ በልቶ ተመስገን እንዲል አድርጉ፤

የከተሜውን የቤትና የትራንስፖርት ችግር ባስቸኳይ መፍታት፤ ሰው መቸም ቢሆን ባለው አቅም መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይታወቃል። በተለይ በአዲስ አበባ ያለውን የቤት ችግር ብታውቁትም በተቻለ ፍጥነት ለመገንባት ከመድከም ሰበብ ፍለጋ መባከናችሁ ሳያንስ የኪራዩን ሁኔታ ተመልክታችሁ እንደ መሪ መፍትሔ እንደማበጀት ትታችሁታል። ‘ይጠላናል’ የምትሉትን ከተሜ በዚህ ሲያማርር ይበለው እያላችሁ ችግሩን በደላላ ላይ ታላክካላችሁ። [ውይ ሞት ይርሳኝ፤ ከልካዮቹን የገንዘብ ተቋሞች እርስት!] በገበያዋ ነጻነት ዓለም ያወቃት ዱባይ እንኳ በኪራይ ላይ በዓመት ከ15% በላይ መጨመር አይቻልም ስትል ደንግጋለች፤ እናንተ ግን አከራይ የተመነውን ዋጋ አንሷል ትላላቹ [ሕዝባዊነት!]

የታክሲው ችግር ባይገባችሁም አላጣችሁትም። ከዚያ መከረኛ ምርጫ 97 በኋላ የጠመዳቹኋቸውን ባለታክሲዎች ለመቆጣጠርና ለመበቀል የጀመራችሁት የታፔላ ምደባ በየወሩ የታፔላ መቀየሪያ የሚሰበሰበው ብር ጣማችሁ መሰል ቀጥላችሁበታል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ተሳፋሪ የሚጠብቅ ታክሲና ታክሲ የሚጠብቅ ሰው በአንድ ጎዳና ላይ ማዶ ለማዶ ቆሞ ሲተያይላችሁ ይውላል። ይኸውም መፍትሔው የግድ የመኪኖች ቁጥር መጨመር ብቻ አለመሆኑን ለመጠቆም ነው። [በርግጥ ስንጠብቅ ውለን ታክሲ ስናገኛ ሎተሪ የደረሰን ያህል እየፈገግን የሄድንበት ጊዜ መኖሩ አይካድም።]

 

አዎን! ፍቅር ያስፈልገናል!

ኢትዮጵያውያን በፈጣሪያቸው ኃይልና ቸርነት የበጥባጭ ገዢዎችን ግፍ ለመሸከም ያስቻላቸው ርስ በርሳችሁ ተዋደዱ የሚለውን የፈጣሪያቸው ትዕዛዝ አክብረው በመኖራቸው ነው። ፍቅራቸውና እምነታቸውም የውስጥና የውጭ ጠላትን ድል የሚነሱበት ትጥቃቸው ሆኖ ኖሯል። ኢህአዴግ ቤት የተነሳው ‘ፍቅር ያስፈልገናል’ የሚለው ሐሳብ በህዝቡና በፖለቲከኞች መካከል ጠንካራ ድልድይ ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑ የሐሳቡን ፋይዳ በጥንቃቄ ማጤን ያስፈልጋል። የኢህአዴግ አመራሮች ‘ፍቅር ያስፈልገናል’ የሚሉትን ጓዶቻቸውን በመከተል ኢትዮጵያዊነትን ልባቸው ውስጥ ፈልገው ለማግኘት መትጋት ይገባቸዋል፤ ሲያገኟትም ጓዶቻቸው እንዳቀፏት አገራቸውን በልባቸው ይቀፏት፤ አገር በልብ ነውና የሚታቀፍ! ኢትጵያዊነት፥ አንድነትና ፍቅር ሰላምን ያሰፍናል፤ ፈጣሪንም ያስደስታል። አዎን! ፍቅር ያስፈልገናል።