ዶ/ር አቢይ አሕመድ እና አቶ ደመቀ መኮነን

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቅ ጥያቄያቸውን በይፋ ካቀረቡ ዛሬ ሁለተኛ ሳምንታቸው ነው።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢ እየተከሰቱ ካሉት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ጎን በበርካቶች ዘንድ በቀጣይ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበርና የሃገሪቱ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆናል? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ እንደሆነ ነው።

በዚህ ዙሪያ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በአመራሩ ውስጥ ያደረገው ሽግሽግ በበርካቶች ዘንድ ዶ/ር አብይን ለቀጣዩ ቦታ የማመቻቸት እርምጃ እንደሆነ ተገምቷል።

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄም (ብአዴን) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን አቶ ደመቀ መኮንን በድርጅቱ ሊቀ-መንበርነት እንዲቀጥሉ ወስኗል። ይህም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ሊወዳደሩ ይችላሉ የሚል ግምት እንዲኖር አድርጓል።

አቶ ኃይለማሪያም የመጡበት የኢህአዴግ አባል ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ቀሪውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመን የመጨረስ ድርሻ አለው በሚል እጩ ሊያቀርብ ይችላል እየተባለ ነው።

ድርጅቱ ባደረገው የአመራር ለውጥ በክልሉና በፌደራል መንግሥት ውስጥ የቆዩትን አቶ ሽፈራው ሽጉጤን በሊቀ-መንበርነት መምረጡን አሳውቋል። አቶ ሽፈራውም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታው ከሚቀርቡት ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ እየተባለ ነው።

ከሁሉ ቀድሞ የአመራር ለውጥ በማድረግ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን ሊቀ-መንበሩ ያደረገው ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) በብዙዎች ዘንድ ለጠቅላይ ሚኒስትርነቱ መንበር ፍላጎት እንደሌለው እየተነገረ ነው።

ነገር ግን እስካሁን ኢህአዴግ ማን ሊቀመንበሩና የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ አልሰጠም። አባል ብሔራዊ ድርጅቶችም እንዲሁ ሊቃነ-መናብርቶቻቸውን ከመሰየም ውጪ በይፋ የገለፁት ነገር የለም።

የህወሓት/ኢህአዴግ የቀድሞ አባልና በትግራይና በድርጅቱ ውስጥ በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት እንደሚሉት ሊቀ-መንበር የመምረጡ ነገር የሚወሰነው በአራቱ ድርጅት ውሳኔ መሰረት ይሆናል።

አቶ ገብሩ እስካሁን ያለውን ዝንባሌ በመመልከት በዋናነት ሁለት እጩዎችን ”ከብአዴን አቶ ደመቀ መኮንንና ከኦህዴድ ዶ/ር አብይ አህመድ የቅርብ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ” ብለው ያስባሉ።

ለዚህም ”አቶ ደመቀ በሰላ ተተችተው ደክመዋል እስካልተባሉ ድረስ ምክትል በመሆናቸው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ሊይዙ ይችላሉ” በማለት ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።

የኢህአዴግ አርማ Image copyright EPRDF official

በሌላ በኩል ደግሞ ”በሃገሪቱ ውስጥ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ከኢህአዴግ አመራር ወጣ በማለት የኢትዮጵያንም ሆነ የሕዝቡን ጥያቄ እንመልሳለን ብሎ ከተነሳው ከኦህዴድ አመራር መካከል የሆኑት ዶ/ር አብይ ሌላኛው ተወዳዳሪ ይሆናሉ” ብለው ያስባሉ አቶ ገብሩ።

በኢህአዴግ አሰራር የፓርቲውን ሊቀ-መንበር የሚሰየመው ምክር ቤቱ ነው። ምክር ቤቱ ከእያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት በእኩል 90 ድምፅ የተወከሉበት 180 አባላት ያለው ነው።

ስለዚህም ሊቀ-መንበር ለመሆን አንድ እጩ ከሁለት አባል ድርጅቶች አባላት በላይ ድምፅ ማግኘት ይኖርበታል። እንደ አቶ ገብሩ ግምት ዶ/ር አብይና አቶ ደመቀ እጩ ሆነው ከቀረቡ ”በምርጫው ሂደት ተወዳዳሪዎቹ ከድርጅታቸው በተጨማሪ የህወሓትንና የደኢህዴን አባላት ድምፅን ማግኘት የግድ ይኖርባቸዋል።”

በእዚህ የምርጫ ሂደት የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ወሳኝ ነው። የምክር ቤቱ አባላት ካሉበት ብሔራዊ ድርጅት እጩዎች ውጪ በእራሳቸው ውሳኔ የፈለጉትን እጩ የመምረጥ ዕድል ቢኖራቸውም ይህ ሊሆን ይችላል በሚለው ላይ አቶ ገብሩ ጥርጣሬ አላቸው።

”በግልፅ ድምፅ የሚሰጥ ከሆነ አባላት በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር ስለሚያዙ ተመሳሳይ ምርጫ ሊያደርጉ ይችላሉ” ብለዋል አቶ ገብሩ።

ጨምረውም ”ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደሚሆነው የድምፅ አሰጣጡ ምስጢራዊ ስለሚሆን የምክር ቤቱ አባላት ከራሳቸው ፓርቲ እጩና ከድርጅታቸው ፈላጎት ውጪ የመምረጥ እድል እንዳላቸው አመልክተዋል።

አቶ ገብሩ ለቀጣይ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበርነትና ለሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አቶ ደመቀ መኮንንና ዶ/ር አብይ አህመድ እጩ ሆነው እንደሚቀርቡ ያላቸውን ግምት ሲያስቀምጡ በሌሎቹ በኩል ያለውን ሁኔታም ገልፀዋል።

የቀድሞ ድርጅታቸው ህወሓትን በተመለከተ ዶ/ር ደብረፅዮን የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው መሄዳቸው በውድድሩ ውስጥ እንዳይገቡ አድርጓቸው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ደኢህዴንን በተመለከተም ድርጅቱ በአቶ ኃይለማሪያም በኩል እድሉን ማግኘቱንና ”እስከማውቀው ተገምግመው ብቃት የላቸውም ተብለው በመውረዳቸው እንዲሁም እራሳቸውም አልፈልግም ብለው በመልቀቃቸው ይህ ዕድል ለእነሱ ተመልሶ የሚሰጥ አይመስለኝም” ብለዋል።

ምንጭ  –  ቢቢሲ/ አማርኛ