ዲያእ የሚባለውን ኢስላማዊ ትምርት ቤት አመራር ዉስጥ ሻእቢያ መራሹ የኤርትራ መንግስት ያደረገውን ጣልቃ ገብነት በመቃወማቸው ሳቢያ ታስረው ሲሰቃዩ የነበሩት ሐጂ ሙሳ መሀመድ ኑር በትላንትናው እለት እስር ቤት ዉስጥ ማረፋቸው ታወቀ።
የነበረባቸውን የጤና ቀውስ ከግምት ዉስጥ በማስገባት ከእስር ቤት እንዲወጡ አማራጭ የተሰጣቸው ሐጂ ሙሳ «አብረዉኝ የታሰሩት ሰዎች ሳይፈቱ እኔ ብቻዬን አልወጣም» በማለት ለቆሙበት አላማ መስዋእት መሆናቸውን የቢቢኤን የኤርትራ ምንጮች አሳውቀዋል።
በሻቢያ የሚመራው አምባገነናዊው የኤርትራ መንግስት በአስመራ ከተማ ዉስጥ የሚገኘውን ዲያእ ኢስላማዊ ትምርት ቤት ስርዓተ–ትምርት (curriculum) በመቀየር ሴቶች ሒጃብ እንዳይለብሱ ለማድረግ ያደረገውን ጣልቃ ገብነት በቀዳሚነት በመቃወምና ድምጻቸውን በማሰማት «በክብር እሞታለሁ!» ያሉት ሐጂ ሙሳ ምኞታቸው ተሳክቶ የትዉልዱን አንገት ቀና እድርገው «በክብር ተሰዉተዋል» ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ያስረዳሉ።
የሐጂ ሙሳ መታሰርን ተከትሎ አኽርያ በመባል ከሚታወቀው የአስመራ የሙስሊሞች መንደር በርካታ ሰዎች ታፍሰው መታሰራቸው ይታወሳል። የታሰሩት ኤርትራዉያን ሁናቴና እጣ ፈንታቸው ባይታወቅም ሐጂ ሙሳ መሐመድ ኑር እስር ቤት ዉስጥ የሞቱ ብሔራዊ ጀግና ሆነው ሲታሰቡ ይኖራሉ ሲሉ ኤርትራዉያን ሙስሊሞች ያስረዳሉ።
ልክ ህወሃት መራሹ መንግስት የሙስሊሞች ተቋም የሆነውን አወሊያን ወርሶ በራሱ ካድሬዎች ለማስተዳደር በሐይማኖት ዉስጥ ጣልቃ እንደገባው ሁሉ፤ ሻእቢያ መራሹ የኤርትራ መንግስት ዲያእ የትምርት ማእከል ዉስጥ ጣልቃ ገብቶ የራሱን አስተምሮት ለመስጠትና በካድሬዎቹ አማካኝነትትምርት ቤቱን ለመውረስ ያደርገው ሙከራ ሐጂ ሙሳን በመሰሉ ቆራጥ ታጋዮች መሰናከሉን ኤርትራዉያን ሙስሊሞች ያስረዳሉ። ሻእቢያ መራሹ የኤርትራ መንግስት የገጠመውን ድንገተኛ ተቃዉሞ ለማለዘብና ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከሰተው የሙስሊሞች ተቃዉሞ ድንበር ጥሶ ወደ ኤርትራ እንዳይዛመትበት ጥረት ማድረጉ የታወቀ ሲሆን፤ አጋጣሚው በሙስሊምና በክርስቲያን ኤርትራዉያን ዘንድ መቀራረብን የፈጠረ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም።
ቢቢኤን ከአስመራ ባገኘው መረጃመሰረት ሐጂ ሙሳ መሐመድ ኑር ዛሬ ብዙ የአስመራና የአካባቢው ምእምናን በተገኘበት ተቀብረዋል። ቆራጡን የህዝብ አገልጋይ አስክሬን በመሸከም በአስመራ ከተማ ዉስጥ ህዝቡ መንቀሳቀሱ ታዉቋል። የህዝቡን ብዛትና ቁጣ የተመለከተው ሻእቢያ መራሹ የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የወታደር ስምሪትን ያደረገ ሲሆን ህዝቡንም ለመበትን ተኩስ ከፍቷል ሲሉ የቢቢኤን የኤርትራ ምንጮች ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ሲል ሻእቢያ መራሹ የኤርትራ መንግስት በዲያእ ትምርት ቤት ዉስጥ ጣልቃ ለመግባት ያደረገውን ሙከራ ተከትሎ ቢቢኢኤን ሰፋ ያለ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል። ሟቹ ሐጂ ሙሳ ሲታሰሩ 92 አመታቸው የነበረ ሲሆን፤ ከታሰሩ በሗላ በ93 አመታቸው በሻእቢያ መራሹ መንግስት እስር ቤት ዉስጥ ከተሰቃዩ በሗላ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂኡን!

