የለማ አዲሱ ቡድን ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የምናየው ቁርጠኝነት ከቀን ወደ ቀን እየጠነከረ መምጣቱን አንዱ ማሳያ የነበረው የአርቡ የኦሕዴድ ተወካዮች ከሕዝብ ጋር በቁርጠኝነት መቆማቸውን ያሳዩበት አቋም ነበር፡፡ እነዚህ ተወካዮች እንደ ተወካይነታቸው ብቻም ሳይሆን ራሳቸውን ሳይቀር መስዋዕት አድርገው ለሕዝባቸው ወገንተኛ የሆኑበትን ቁርጠኛ አቋማቸውን እንዳሳዮን ስናይ ደግሞ ከተወካይነትም በላይ ትልቅ ጀግንነት እንደፈጸሙ ግልጽ ነው፡፡ የወሮበላው ቡድን በግልጽ በአደባባይ ያየንውን እውነት እንድህ በወሮበላነቱ ሲክድ ማየት አይገርምም፡፡ ይህ የተለመደና ይህ ቡድን በሰይጣን ስም ተማምሎ የገባበት አላማ ነውና፡፡ ከስብሰባው በፊት ተወካዮችን አስፈላጊ በተባለው ማስፈራራትና እንግልት እንዳይቃወሙ ለማድረግ ብዙ እንደተሞከረ ሰምተናል ከድምጹም በኋላ ያየንው ሂደት የሚያመለክተው ያንኑ የሚመሰክር ነው፡፡ የኦህድድ ተወካዮች ግን ይሄንን ሁሉ ማስፈራራትና ማስጠንቀቂያ ከምንም አልቆጠሩትም፡፡ ይልቁንም በወኔና በቁጭት ለሕዝብ ያላቸውን ቁርጠኛ ወገንተኝነት ሲገልጹ ተመለከትን፡፡ ይህ ድንቅ ነው፡፡ ከኋላ ሆነን ብዙ አምተናል፡፡ ለማና ቡድኑ ቁርጠኛ እንደነበር ግን ከጅምሩም ግልጽ ነበር፡፡ ከለማ ጎን የተሰለፈው የኦህዴድ ቡድን ከገመትንውም በላይ ጠንካራ መሆኑን ግን ግልጽ አልሆነልንም ነበር፡፡ በአለፈው አርብ ለማም ብቻውን እንዳልሆነ ተረድተናል፡፡ እንዲህ ያሉ ጀግኖች ከጎኑ አሉና፡፡
https://www.youtube.com/watch?time_continue=40&v=ert75Xls3fg
ይህ በእንዲህ አንዳለ ግን አንዳንድ ቡድኖች በእነዚህ ጀግኖች የተፈጸመውን ገድል ለተለመደ ንግዳቸው ሲጠቀሙበት አይተናል፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ የኦህዴድ ተወካዮች አዋጁን የተቃወሙት በእኛ ግፊት ነው ሲሉ ትንሽ እንኳን ሕሊና ሊኖራቸው አልፈለጉም፡፡ ይህ አሳፋሪ ብቻም ሳይሆን በሕዝብ ላይ ጦርነት ከከፈቱት ለይተን አናያቸውም፡፡ አዋጁን የተቃወሙት የለማ ቡድን የኦሕዴድ ተወካዮች ብቻ ናቸው፡፡ የለማን ቡድን እንደሙክታር ኦሕዴድና ወያኔም ማንም በፌስቡክና ለግል ጥቅም ባደሩ ግለሰቦች የሚዘወር አደለም፡፡ ይሄ ሂደት በሙክታር ጊዜ አደባባይ የወጣ ሂደት ነበር፡፡ የለማ ቡድን ፍጹም ለብዛዎች እንቆቅልሽ ሆኖባቸው ተቸግረዋል፡፡ ሆኖም ከእኛ ሀሳብ ይቀበላል በማለት በአሸባሪነት ለማስፈረጅ ብዙ እየተሞከረ ነው፡፡ ይህን እያደረጉ ያሉትን ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ደግሞ ተወካዮቹ በግልጽ ከጎኑ እንደተሰለፉ ያሳዩት የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ የጀግኖቹን ዋጋ ለራሳቸው ሊወስዱ አልፎም ጀግኖቹን ከ”አሸባሪ” ቡድን ጋር የሚሰሩ ለማስባል እያሴሩ ያሉትን በትኩረት ሊከታተላቸውና ሊነቃባቸው ይገባል፡፡ ልብ በሉ “አሸባሪ” የሚለው ሥም የሚሰጣቸው ቡድኖችም ይሁን ግለሰቦች ከወሮበላው ጋር ውስጥ ለውስጥ ለመሥራት እንዲመቻቸው እንደሆነም አስቡ፡፡ ይህን ቁማር ብዙ ጊዜ አይተናል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን በአለፈው አርብ የጸረ-ሕዝብ አዋጁን የተቃወሙት ጀግኖች ሙሉ ዋጋና ክብራቸውን ያስጠበቁ በእርግጥም የመጡበትን ማህበረሰብ ማንነትና ወኔ ያሳዩን ናቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ወደ 106 የሚሆኑ አባላት በስብሰባው ያልተገኙበት ምክነያት ሌላው ሊታሰበበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጠንካራ የለማ ቡድን አባላት እንደሚበዙም ይነገራል፡፡ ሆን ተብሎ ይቃወማሉ ተብለው የተጠረጠሩትን በስብሰባው እንደይገኙ ታግዶስ ቢሆን፡፡ በአደባባይ ሊያውም የማያሻማን የሂሳብ ቁጥር የሚያጭበረብር ወሮበላ ቡድን የትኛውንም ወንጀል ፈጽሞ አዋጁን ማጽደቅ እንደነበር በግልጽ እናያለን፡፡ የተቃወሙትና ተዓቅቦ ያደረጉት በድምሩ 95ቱም የኦፒዲዮ ተወካይ ሲሆኑ አንድም የበዓዴን ወይም የሌላ ተወካይ ከህዝብ ጎን ወግኖ አላየንም፡፡ በትክክል በስብሰባው የተገኙት 441 ናቸው 106 አልተገኙም፡፡ ለምን? ብዙ ሊቃወሙ የሚችሉ ሌሎች የኦፒዲኦ ተወካይስ ከመጀመሪያውም እንደሚቃወሙት ታስቦ በስብሰባው እንዳይሳተፉ ተደርጎ ቢሆን፡፡ ከበዓዴንስ እንዴት አንድ ሰው እንኳን ጠፋ? ከበዓዴንም ይቃወማሉ ተብሎ የተፈሩት እንዳይሳተፉ ተደርጎስ ቢሆን፡፡ ይሄ እኮ የወሮበሎች ቡድን ነው፡፡ በቃ ሁሉንም ወንጀል ከመስራት ወደኋላ የማይል፡፡ ደመቀ መኮንን ነበር ግን ዶ/ር አብይ አልነበረም ነው የተባለው፡፡ ለምን? የተቃወሙትስ ቀጥሎ በምን ሁኔታ ናቸው? አሁን ላይ እንደምናየው የኦሮሚያ ክልል ሙሉ በሙሉ በወሮበላው ቡድን ሥር ገብቷል፡፡ በአረመኔዎቹ እየደረሰ ያለውን ግፍ እንኳን የክልሉ ሚዲያም ሆነ ባለስልጣናት እያደረሱን አደለም፡፡ የአረመኔዎቹን ድርጊት እየሰማን ያለነው በቪኦኤና በሌሎች ሚዲያዎች ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ቄለም ወለጋ ያለው ሕዝብ ተጋድሎ ላይ ነው! ከወጣት እስከ አዛውንት ወገናችን እየሞተ ነው፡፡ በዛው ልክ ሕዝቡ ግን እየጠነከረና እንደማይበገር ለአረመኔዎቹ ግልጽ ሆኖላቸዋል፡፡ አሁን ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት የእነዚህ ወገኖቹን ሊቀላቀል ይገባል፡፡ ቄሮ ከሰኞ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ጠርቷል፡፡ ይህ በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊተገበር ይገባል፡፡ በተናጥል አይሁን፡፡ ቢያንስ ሁለቱ ክልሎች ማለትም ኦሮሚያና አማራ ክልልን የካለለ ወጥነት ያለው ትግል ነው የሚያስፈልገው፡፡ ከዚህ በኋላ እነ ለማም እንደ እሰካሁን እኛን ማገዝ ላይቻላቸው ይችላል፡፡ ወሮበሎቹ ከማንም በላይ እነሱን ኢላማ እንደሚያደርጉ እናስብ፡፡ እነለማ እዚህ አድርሰውታል፡፡ አሁንም የተቻላቸውን ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ እናውቃለን፡፡ ግን አሁን ሕዝብ እነሱንም ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡ ይህን የምለው ዋናዎቹን እላይ ያሉትን ብቻ ማለት ሳይሆን በዞንና ወራዳ መሪነት ሆነው ከሕዝብ ጋር የቆሙትን ማለቴ ነው፡፡ ከወዲሁ ሰለባም እየሆኑ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስም ኢላማ እየሆነ ነው፡፡ ትጥቁንም ለማስፈታት እየተሞከረ ነው፡፡ በአማራም ተመሳሳይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ግን ሁሉንም በአንዴ ስለማይችሉ በተናጥል ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ይህን ከግንዛቤ በመውሰድ በአንድነትና በፍጥነት ትግሉን ማስኬድ ያስፈልጋል፡፡ በመከላከያ ሰራዊት የአላችሁ በተለይ የኦሮሞና አማራ ተወላጆች ከዚህ ወቅት በላይ ለሕዝብ ውለታ የምትከፍሉበት እድል ወደፊት አይገጠማችሁም፡፡ ዛሬ ከሕዝባችሁ ጎን ለመቆም ወይም ከጠላት ጎራ ለመሰለፍ ግልጽ ምርጫ ነው የቀረበላችሁ፡፡ ሕዝብን ኢላማ ያደረጉ የወያኔን ጀነራሎች ዝም ልታሰኙበት የምትችሉበት ብዙ እድል አላችሁ፡፡ ይሄን ለእናንት አልመክርም፡፡ ቀጥሎም በሕዝብ ላይ ግፍ እየፈጸሙና እያስፈጸሙ ያሉ ባለስልጣናትን፡፡
እየሄድንበት ያለው ሂደት ይሄ ነው፡፡
ሰርፀ ደስታ
ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይታደግ! አሜን!
