
የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በአፈጻፀሙ ላይ ብዙ መሰረታዊ የሆኑትን ለምሳሌ የመሰብሰብና የመንቀሳቀስ የመሳሰሉትን የሰው ልጆችን ህገመንግሥታዊና ተፈጥሮያዊ መብት ስለሚጥስ፣ ያገሪቷ ህልውና አደጋ ውስጥ ሊገባና ይህንን አደጋ ደግሞ ለመቀልበስ የመከላከያ ሰራዊቱን ከማሰማራት ሌላ አማራጭ አለመኖሩ ካልተረጋገጠ በስተቀር አይታወጅም። በሌላ አነጋገር የአገሪቷን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል ደጅ የቆመው አስከፊ ክስተት በጸጥታ አስከባሪ ሃይሎችና በህዝቡ ብርታት ሊወገድ የማይቻል መሆኑ ካልተረጋገጠ በስተቀር፣ አገሪቷን ከውጪ ወራሪ ኃይል ለመከላከል የተመሰረተውንና፣ ሥልጠናውም ከባዕድ ጠላት ጋር ጠመንጃ እንዲማዘዝ እንጂ ባዶ እጁን አንከርፍፎ ለሰልፍ በመውጣት ህጋዊ መብቱን በጠየቀው ሲቪል ዜጋ ላይ ለውጪ ጠላት የታለመውን ጥይት ተኩሶ እንዲገድልበት የመከላከያ ሠራዊቱን ማሰማራት ማለት አይደለም ማለት ነው።
የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ/ “የውጪ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን” የፌዴራል መንግሥቱ የሚንስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው” በማለት ሶስት መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች አስቀምጧል። የሚኒስትሮች ም/ቤትም መስፈርቶቹ በሙሉ ተሟልተዋል በማለት ዓዋጁን ለፓርላማ አቅርቦ “ከተወያዩበት በኋላ” በአፈ ጉባዔው አቆጣጠር መሠረት ሁለት ሶስተኛው አባል ደግፎት ጸድቆአል። ተደርጎ ነበር ስለተባለው ውይይት ብዙ የምናውቀው ነገር ባይኖርም፣ ሾልኮ ከወጣው መረጃ የተገነዘብነው አንድ ተስፋ ሰጪ ክስተት ግን፣ የፓርላማው አባላት እንደወትሮው በአንድ ሞተር የሚዘወር ጭንቅላት ያላቸው ይመስል 547ቱም ባንድ ላይ እጅ የሚያነሱበት ልምድ ተሽሮ፣ በ27 ዓመት የኢህአዴግ አገዛዝ ሥርዓት፣ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ 90 የሚጠጉ የቁርጥ ቀን የኦሮሞ ልጆች “ተገዥነታችንና ታማኝነታችን ለህገ መንግሥቱና ለመረጠን ህዝብ ብቻ ነው” ብለው በአደባባይ ዓዋጁን ተቃውመው ድምጽ መስጠታቸው ነው። በተረፈ፣ የምርጫው ሂደት በአባላት ተደገፈም አልተደገፈም የተለመደው አሰራር “እናንተ ምረጡ፣ እኛ እንቆጥራለን” በሚል ስታሊናዊ መሪህ ስለሚመራ እንኳን 90 ሰው ይቅርና 500ም ሰው ቢቃወመው፣ ዓዋጁ ገና ለፓርላማ ሳይቀርብ ሥራ ላይ ውሎአል።
በኔ ግምት፣ ያሁኑ ዙር “የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ” በታወጀበት ወቅት በኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ፣ የውጭ ወረራ ያልተካሄደበት፣ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም በምንም መስፈርት አደጋ ላይ ያልነበረና ምንም ነገር ከተለመደው የህግ ማስከበር ሥርዓት አቅም በላይ ያልሆነ ነበረ። ለማንኛውም የነበረውን ሁኔታ በቅደም ተከተል ማስቀመጡ ለሙግቴ መንደርደርያ ይሆናል ብዬ ስለምገምት እንደሚቀጥለው ላቅርብ።
የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአስራ ሰባት ቀናት በዝግ ያካሄደውን ስብሰባውን እንዳጠናቀቀ በአደባባይ ወጥቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሰጠው መግለጫ መሰረት፣ ድርጅቱ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ስላልነበረውና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ባለመቻሉ ህዝቡን ማስቆጣቱን አምኖ ይቅርታ ጠይቆ ነበር። ጥፋትን አምኖ ይቅርታም ከመጠየቅ አልፎ ለተበደለው ህዝብ ካሳ እንዲሆን ከማሰብ፣ መልካም አስተዳደር እጦትን አስመልክተው ለመብታቸው መከበር በመታገላቸው ብቻ ያላግባብ ታስረው የነበሩትን የፖሊቲካ እስረኞች በሙሉ እፈታለሁ ብሎ ቃል ገባ። ለብዙ ዓመታት “ዲሞክራቲክ ድርጅት ነኝ፣ በመሆኔም ደግሞ ባገሪቷ ላይ ዲሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ስላሰፈንኩ፣ መንገድ ላይ ወጥተው ለመረበሽ የሞከሩት አንዳንድ ጸረ ሰላም ቡድኖች በቀሰቀሱት ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ እንጂ የፖሊቲካ እስረኞች በኢትዮጵያ ምድር ላይ የሉም” ብሎ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላውን የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ለማሳመን ይሞክር ስለነበረ፣ የኢህአዴግ እስረኞችን ለመፍታት መወሰኑ ያልተጠበቀ መለኮታዊ ምርቃት የሆነውን ያህል ህዝቡን አስደሰተ። ቃል በተገባውም መሰረት፣ አንዳንድ የፖሊቲካ መሪዎች ተፈትተው ከዘመዶቻቸው ጋር ተቀላቀሉ። በምድሪቷም ከብዙ ዓመታት በኋላ አንዳች አይነት የደስታ ድባብ ሰፈነ። የተፈቱት
