አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲሉ፤ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስንል
የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም እንዲሉ፤ በአዋጅ ጋጋታ አመጽ አንግቦ የተነሳን ሀዝብ ማስፈራራትም ሆነ መገሰጽ እንደማይቻል አፋኙ አገዛዝ በቅጡ የተረዳ አይመስልም። እነሆ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ አስቸኳይ አዋጅ ለፈፈ። ያሁኑን አዋጅ ከበፊቶቹ የሚለየው ነገር ቢኖር በገዢው ቡድን በራሱ ውስጥ ያለው ቅራኔ በህዝብ ፊት ወጥቶ በይፋ መታየቱ ነው። ፓርላማ ተብየው የህወሐት መገልገያ ተቋም ውስጥ ቅራኔው በድራማ መልክ ተከስቷል፤ በአንድ በኩል በአባዱላ ገመዳ የሚመራው ጸረ ህዝብና የለየለት አፋኝ ክንፍ በመንጋ ሆዳሞች ታጅቦ የህዝቡን የነጻነት ድምጽ ለማፈን ከእንቅልፉ እንደባነነ አውሬ ሲራወጥ ታይቷል፤ በሌላ በኩል የህዝብን እሮሮ ያደመጡ፤ እንባውንም ለማበስ የቆረጡ፤ ደፋርና አርቆ አሳቢ የሆኑ የአገር ልጆች፤ አይ ከእንግዲህ አፈናው ይቁም፤ የአፈናው አገዛዝ አካል የሆነው አዋጅም አያስፈልግም ብለው ተከራከሩ። ይሁን እንጂ ማጭበርበርን እንደሙያ፤ ውሸትን እንደጥበብ የተካንው የሕወሃት ጉጅሌ “አዋጁ በድምጽ ብልጫ’’ አልፏል ብሎ አንድ ሌላ የውርደት ታሪክ በህዝብ ፊት አስመዘገበ። ይህ የአሁኑ ሂደት ህወሀት/ኢህአዴግ ከመላ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከራሱ ድርጅት መሪወችም ድጋፍ የሌለው፤ ጭንቅ ላይ የሚገኝ ሀገርን የማስተዳደር ብቃቱ ተሟጦ ያለቀ አገዛዝ እንደሆነ በግልጥ የሚያሳይ ነው።
ፓርላማ ተብዬው ውስጥ የታየውን ትያትር ሁላችነም በከፊል የተመለከትነውና ለታሪክም የተመዘገበ ነው። ሁለት እጅ ከማውጣት ጀምሮ የተሰጠውን ቁጥር በሰአታት ውስጥ ቀይሮ የተለመደ የኮሮጆ ግልበጣን የመሰለ ማጭበርበር እንደተካሄደም ታዝበናል። ይህ በከፊል እንድናየው የተደረገውን ትያትር እያደር ሙሉ ገጽታውን ስናይ ደግሞ የተካሄደውን አሳፋሪ ስራ በግልጵ እናውቀዋለን።
አፋኙ የገዢ ቡድን ይህን አዋጅ ለመደንገግ የተንቀሳቀሰበት አካሄድ ሆን ተብሎ የታቀደ መፈንቅለ መንግስት ነው የሚሉ በርካታ ወገኖች አሉ። ሌሎች ደግሞ አገሪቱ ሁልጊዜም በወታደራዊ አገዛዝ ስር ነው የቆየችው፤ ይሁን እንጂ ይህንን የተለየ የሚያደርገው፤ ገዢው ቡድን ማስመሰሉን ትቶ፤ ክራባቱን አውልቆ፤ መለዮውን ደፍቶ በተጠንቀቅ መቆሙ ብቻ ነው ይላሉ። ወጣም ወረደ፤ በምንም ስም ይጠራ፤ ህዝባችን ይህን የዘረፋና የአፈና ስርዓት አምርሮ ከመታገል ሌላ አማራጭ እንደሌለው ግልጽ ነው።
ሕወሀት እና ቀንደኛ ፖለቲከኞቹ ሰሞኑን በየቦታው እየዞሩ እጅግ አፍራሽ ስራ ሲሰሩ እንደከረሙት ሁሉ 27 አመት ሙሉ ጨምድደው የቆዩትን ስልጣን አሁንም ለማስቀጠል “በመቃብራችን ላይ ተረማምዳችሁ ብቻ ነው ለውጥ ልታመጡ የምትችሉት” በማለት ሲነግሩን ከርመዋል። በዚህ አንጻር የህወሀት ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑትን የአቶ አባይ ጸሀየን ንግግር ማስታወስ በቂ ነው።
የህወሀት መራሹ ስርአት ባለስልጣኖች ያደረጉት ሌላው የተለመደ አሳፋሪ ድርጊት ደግሞ በመሀላቸው የህዝብ ጥያቄን አንስተው የሀገርን ችግር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማለትም በተጨማሪ እመቃ ና አፈና ሳይሆን፤ በመግባባት፤ በእርቅና የህዝብን መብት በማረጋገጥ እንፍታ የሚሉትን ወገኖች ግማሹን በማስፈራራት፣ ግማሹን በመገሰጽ ወዘተ.. በፓርላማ ውስጥ ምንም ተቃውሞ እንዳያሳዩ በማስገደድ በድርጅታዊ አሰራር ጠርንፈው ውሳኔ ለማሳለፍ ሞክረዋል። ያም ሆኖ ግን ይህን ማሰፈራሪያ፣ ማጭበርበርና ባዶ ቀቢጸ ተስፋ፤ በእነሱ አቆጣጠር ቢያንስ 95 ግለሰቦች እምቢ ብለው ለህዝብ መብት መቆማቸውን በይፋ ያስመዘገቡ መሆኑ ራሱ ታሪካዊ እርምጃ ነው።
ይህ ፓርላማው አጸደቀው የተባለው ውሳኔ ህወሀትና ቀንደኛ ደጋፊወቻቸውን ያልተጨበጠ ተስፋ ይሰጣቸው እንደሆነ እንጂ ከዚያ የዘለለ ጠቀሜታ ግን ለህወሀትም ለኢህአዴግም የሚያስገኝ አይደለም። አስቸካይ ጊዜ አዋጁ የሚያሰከትለው ተጨማሪ የመብት ረገጣን፣ እስራትን፣ ግድያን ፣ አፈናን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ተቃውሞው መብታችን ተረገጠ፤ አፈና በዛብን፣ ብሎ ነው። ስለዚህ መብቱ እንዲከበርለት ለጠየቀ ህዝብ ተጨማሪ የመብት ረገጣ፣ ፍትህ ለጠየቀ ህዝብ ፍትህን ይበልጥ መግፈፍ ወዘተ..እንደተከበበ አውሬ ሞቴም ሕይወቴም ይኸው ነው
ብሎ ከመከላከል ወደ አጥቂነት እንዲሸጋገር ይገፋዋል እንጂ ቁጭ ብሎ ሞቱን እንዲጠብቅ አይጋብዘውም። መብቴ ይከበር፤ የራሴን መንግስት ልምረጥ ለሚል ህዝብ አምባገነንንትን አጠናክሮ መቀጠል፤ የተጀመረውን የህዝብ አመጽ ይበልጥ ያባብሰዋል እንጂ አያበርደውም።
በመሆኑም እጅግ የጠነከረና በስፋት የሚካሄድ የተቃውሞ ሰልፍ፣ ስራ ማቆም አድማ፣ የትምህርት መቋረጥ፣ የንግድ መቋረጥ ፣ ያለመረጋጋት መስፈን፤ በውጭው ደግሞ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግፊት ስራ በስፋት ተግባር ላይ እንደሚውል ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ያስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መጽደቅ ተከትሎ በጊንጪ፤ በአምቦ፣ በደምቢ ዶሎ ወዘተ የታየው ተቃውሞ አንድ ማሳያ ነው። ተመሳሳይ ተቃውሞ በመላ ሀገሪቱ እንደሚስፋፋ በፍጹም አንጠራጠርም።
ሕዝባችን ዛሬ ፍርሃት የለውም፤ የግፍ ቀንበሩንም አልሸከምም ብሏል። ይህን የህዝብ ተቃውሞ ለማስቆም መብቱን ከማክበር ውጭ ሌላ መንገድ የለም። የህወሀት መራሹ ኢህአዴግ እቅድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን አስሮና ገድሎ ለመግዛት ከሆነም በፍጹም አንደማይቻልና እንደማያዋጣ አሁንም መገንዘብ ይኖርበታል።
ስርአቱ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት መፍትሄው አንድና አንድ ብቻ ነው፤ ይህም ራስን የማታለያና ሀገርና ህዝብን አጥፊ የሆነውን አካሄድ አቁሞ፤ ሁሉንም ባለድርሻወች ያሳተፊ፤ ብሄራዊ የመግባባትና የሽግግር ጉባኤ አሁኑኑ ጠርቶ ወደ ሰላማዊ ሽግግር የሚገባበትን መንገድ በጋራ መፈለግ ነው።
የሕወሀት/ኢህአዴግ ፖሊሲወች የችግሮቻችን ሁሉ መሰረት ቢሆኑም፤ አገዛዙ የመፍትሄው አካል መሆን ከፈለገ የመጨረሻ ዕድሉ አሁን ነውና ጊዜው ሳይረፍድ የህዝብን ጥያቄ በአስቸኳይ ይመልስ እንላለን። ምላሽ ሳይሰጥ ቢቀር ግን በግብጽ፣ በሊቢያ፣ በኢራቅና እንዲሁም በአገራችን በደርግ ጊዜ እንደሆነው ሁሉ፤ የመፍትሄ አካል የመሆኛ እድል በር ክፍት ሆኖ የሚጠብቀው እስከተወሰነ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ልናስገነዝብ እንወዳለን።
የህዝባችን ትግል ያሸንፋል !!
