የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሰኞ የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ አዲስ አበባ እንደገቡ የታወቀ ሲሆን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ደግሞ ረቡዕ የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ላብሮቭ ደግሞ ሐሙስ የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ እንደሚገቡ ታውቋል፡፡

የእነዚህ ሦስት አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትኩረትን የበመሳብ የተለያየ ትርጉም ሲሰጠው ተስተውሏል፡፡ የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በአንድ በኩል ትልቅ ተስፋ እንዳለው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከወትሮው የተለየ ትርጉም እንደሌለው ሲነገር እየተደመጠ ነው፡፡ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከመንግሥት ጋር ለመመካከርና ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ ነው ሲሉ የሚከራከሩ ወገኖችም አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእነዚህ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት፣ አገሪቱ ከዚህ ቀደም ታደርገው ከነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተለየ ትርጉም ሊሰጠው እንደማይችልና በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ቀውስ ኢትዮጵያውያንን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ ነው ብለው ሲከራከሩ ተደምጧል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ብሔር ተኮር ግጭቶች ተቀስቅሰው በበርካታ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ችግር ደርሷል፡፡  እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት ከላይ ታች ቢባልም፣ እስካሁን መፍትሔ አልተገኘም፡፡ በዚህም ሳቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከመንግሥትና ከኢሕአዴግ ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

አገሪቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ማስተዳደር ባለመቻሉም፣ መንግሥት ለስድስት ወራት የሚቆይና በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ክርክርና ውይይት ከተደረገበት በኋላ በ395 ድጋፍ፣ በ88 ተቃውሞና በሰባት ድምፀ ተዓቅቦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ከታወጀ በኋላ፣ በአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተው ነበር፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀ በአራተኛው ቀን በኦሮሚያ ክልል በአብዛኛው አካባቢዎች የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልልና ከኦሮሚያ ክልል ወደ አዲስ አበባ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡ አገሪቱ በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት የሦስቱ  አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከማክሰኞ የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ አዲስ አበባ እየገቡ ነው፡፡ የእነዚህ ሦስት አገሮች ኢትዮጵያ መጥተው ምን እንደሚሠሩና የመምጣታቸው ፋይዳ ምን እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በተለይ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ትኩረት የሚስብና የሚያነጋግር ሆኗል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ የእነዚህ ሦስት አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ፋይዳ እንደሌለው፣ መጥተውም ምን እንደሚሠሩ ግልጽ የሆነ አይደለም ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም ከዚህ በፊት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ባራክ  ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት አገሪቱ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንደነበረች፣ በወቅቱ  ችግሩ እንዲፈታ ምክረ ሐሳብ አቅርበው አልሄዱም ይላሉ፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በምን ጉዳዮች እንደተወያዩና ምን ዓይነት ምክረ ሐሳብ እንዳቀረቡ ግልጽ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡ የአሁኑ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም የተለየ ትርጉም ሊሰጠው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

የሦስቱ አገሮች ከፍተኛ አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የየራሳቸውን ፍላጎት ከማሳካት አኳያ እንጂ፣ በአፍሪካ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ ችግሮች ባሉባቸው አገሮች የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰትና ሌሎች ችግሮችን ከመፍታት ጋር የተያያዘ ይሆናል ብለው እንደማያስቡ አስረድተዋል፡፡

የውጭ  ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ የሦስቱ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ካለው የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ ‹‹በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ መወሰን የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡  ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከሩሲያና ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ትልልቅ ሹማምንት መምጣታቸው ልዩ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ሦቱም አገሮች በየአካባቢያቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደሆኑ አስታውሰው፣ ‹‹አሁን ያሉብን ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆነው ከኢትዮጵያ ጋር ላላቸው ግንኙነት የሚሰጡትን ትኩረት ነው የሚያሳየው፤›› ብለዋል፡፡ የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተመሳሳይ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የመገጣጠም ጉዳይ እንጂ፣ አንዱ ከሌላው ጋር የሚያያዝ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፕሮግራሙ ከወራት በፊት የተያዘ እንጂ አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹የእነዚህ ኃላፊዎች በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ  ጋር የተያያዘ ነው ብለው የሚያስቡ ካሉ የተሳሳቱ ናቸው፤›› ያሉት አቶ መለስ፣ ‹‹በአገር ቤት የምናደርገውን ጉዳይ በተመለከተ ሞግዚት አያስፈልገንም፤›› ብለዋል፡፡

የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ በአቶ መለስ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የራሷ ችግሮች አሉባት፡፡ አሁን ከባድ በሆነ ችግር ውስጥ ነው ያለችው፤›› ብለው፣ የእነዚህ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሚያመለክተው የኢትዮጵያን አስፈላጊነት ነው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ የሚያገባቸው ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ያስታወሱት አቶ ልዑልሰገድ፣ የየአገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በዋናነት የሚያያዘው፣ አገሮች በተናጠል የራሳቸውን ፍላጎት ከማሳካት የመነጨ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

አቶ ጥሩነህ ደግሞ ሚኒስትሮቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሠሩ የሚችሉት ከዚህ በፊቱ የተለየ ሊሆን እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ምናልባት አሁን ወደ መጨረሻው አካባቢ የኢትዮጵያ ችግር ተሰምቷቸው የተወሰነ ምክር ወይም ድጋፍ ሊያደርጉ ከመጡ ጥሩ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ በሚመጡበት ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሊነጋገሩባቸው የሚችሉ ጉዳዮች ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም ብለዋል፡፡

አቶ ልዑልሰገድ በበኩላቸው የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ በሚቆዩበት ወቅት ሊያከናውኗቸው የሚችሉ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል በምሥራቅ አፍሪካ የሰላምና ደኅንነት፣ በሽብርተኝነትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሊመክሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አቶ መለስ ደግሞ የሦስቱ አገሮች የኢትዮጵያ ጉብኝት በተናጠል መታየት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ግንኙነት ለረዥም ዓመታት የቆየ እንደሆነ አስታውሰው፣ ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች በጋራ እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም ይህንን ለማጠናከር ታስቦ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ በሚቆዩበት ወቅት ምን ይሠራሉ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መለስ፣ ሁለቱ አገሮች ተባብረው የሚሠሩባቸውን ጉዳዮች በመገምገም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደረስ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በመካከለኛው ምሥራቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡ ከዓረብ አገሮች በተለይም ከሳዑዲ ዓረቢያና ከመሰሎቿ ተወዳዳሪ የሆነ ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት የዓረብ አገር ነች፡፡ አሸባሪ ኃይሎችን ትረዳለች በማለት ኳታርን ካገለሉና ማዕቀብ ከጣሉ የዓረብ አገሮች መካከል አንዷ የተባበሩት ዓረብ  ኤምሬትስ ነች፡፡