March 9, 2018
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
በማህበራዊ መድረኮች እንደሚታየው እነ አቦይ ስብሃት ከጣራዋ ያስቀመጧቸውን ቁራዎችና ጆቢራዎች በማየት አንዳንድ ወጣቶች ቅድስት ቤተክርስትያን እውነትም ቋንጃዋን የተሰበረች እየመሰላቸው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲገልፁ ይታያል፡፡ ዳሩ ግን እንኳን እነ ስብሃት ጌቶቻቸው ምዕራባውያን የዚችን ጥንታዊት ቤተክርስትያን ቋንጃ መስበር እንዳልቻሉ ታሪክ ደጋግሞ መስክሯል፡፡
“ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት!” ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ! ቤተክርስትያኗ ሌላ የእነ ስብሃት አቡኖች፣ ጳጳሳትና መነኩሴዎች ሌላ! እነ ስብሃት ካድሬ እያመነኮሱ ከዋልድባ እስከ ሞያሌ፣ ከጅቡቲ እስከ ሰሜን አሜሪካ፤ ከደቡብ አፍሪካ እስከ አንታርክቲካ እንደ ውሻ ቢለቁባትም የተዋህዶ ቤተክርስትያንን ቋንጃ መንከስ እንጅ መስበር አይችሉም፡፡ ዋልድባን በሸንኮራ እየሸፈኑ መነኩሳቱን ቢያስሩ፣ ጣናን እያደረቁ ገዳማቱን ለአደጋ ቢያጋልጡ፣ ላሊበላን እየሰነጣጠቁ ቅርስ ለማጣፍት ቢጥሩ፣ መጻሕፍቶቿን፣ ስዕሎቿን፣ መስቀሎቿንና ቅርፆቿን እንደ ሸቀጥ እየቸበቸቡ ቢያራቁቱ እንደ ቅዱሳን ሰማእታት ማሰቃየት እንጅ ቋንጃዋን መስበር አይችሉም፡፡
“ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት” እነ ስብሃት እነ አቦይ ገረመድኅንና ማትያስን አፐትርከው “የኦርቶዶቅስ ቤተክርስትያንና የአማራን አከርካሪ ሰብረናል!” ሲሉ የፎከሩብህ የተፈፀመ እንዳይመስልህ፡፡ እንደ እነ ስብሃት ሁሉ ፈሪሳውያን ክርስቶስን ከግድ አጣብቀን ገድለን ቀብረነዋል ሲሉ ፎክረው ነበር፡፡ በአካል የተሰቃየው ክርስቶስ እንደተነሳው በአካል የተሰቃዩት የተዋህዶ ቤተክርስትያንና አማራም ይነሳሉ፡፡
የተዋህዶ ቤተክርስትያን ፖርቹጋሎች የጫኑባትን ድንጋይ ፈንቅላ ተነስታለች፡፡ የቱርኮችንና የግራኝ መሐመድን እሳት ተቋቁማ እንደ ወርቅ ፈልቃ ታይታለች፡፡ የመጀመርያውን ጣልያንን ወረራ ከነታቦቷ ዘምታ ሊያጠፏት የመጡትን በአድዋ አመድ አድርጋለች፡፡ የሁለተኛውንም የጣሊያን ወረራ እነ አቡነ ጴጥሮስን እንደ ክርስቶስ በጦር አስወግታ፣ እነ አድማሱ ጀምበሬን የጦር መሪ አድርጋ፣ እነ አባ ገብረየሱስን በወታደርነት አሰልፋ በዱር በገደሉ ክርስቶስ ለተሰቀለበት ፍትህ ተፋልማለች፡፡ ስለዚህ “ጊዜዬ ገና ነው” በሚል እንጅ ተዋህዶ ቤተክርስያን ትነሳለች፡፡ ለመነሳት ግን የልጆቿን ክንዶች ትሻለች፡፡
ወጣት ሆይ! ቤተክርስትያንህ እንድትነሳ ክንድህን ዘርጋላት፡፡ እነ አቦይ ስብሃት ቋንጃዋን ለመስበር ከጣራዋ የሰቀሉባትን ድንጋዮች፣ ቁራዎችና ጆቢራዎች እንደ መርገምት አንሳላት፡፡ ቅድመ አያቶችህ በስቅለት ማግስት ከአለት የመሰረቷት የሁለት ሺህ አስር ዓመት እድሜ ቤተክርስትያንህ በቁራዎችና በጆቢራዎች ጣራዋ እንደ ስጡ ተበትኖ ሲያልቅ ዝምብለህ አትያት፡፡ “ወጣት ተመልከት እንዳትሳሳት!”
“ወጣት ተመልከት እንዳትሳሳት*” የኔ ድምፅ አይደለም፡፡ ይህ ድምፅ ኢትዮጵያንና የተዋህዶን ቤተክርስትያን ከወራሪ ለመከላከል እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ብዕራቸውንና ጦራቸውን ያነሱት የመላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ድምፅ ነው፡፡ ይህ ድምፅ የፈፀሙት ገድልና የጻፏቸው መጻሕፍት ዛሬም ለኢትዮጵያና ለቤተክርስትኗ ጋሻ የሆነው የመላከ ብርሃን አድማሱ ድምፅ ነው፡፡
“ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት” የሃይማኖት ትምህርትና ፍልስፍና እስከ ዳርቻው፣ ግዕዝና ቅኔን እስከ ጠርዙ፣ መጽሐፈ ትርጓሜን እስከ ሆድቃው በርብረው የተረዱት የመላከ ብርሃን አድማሱ ድምፅ ነው፡፡ ይህ ድምፅ በሙያ ሥነ-ምግባርና በመንፈስ ልዕልና የታነፁት የመላከ ብርሃን አድማሱ ድምፅ ነው፡፡
“ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት” በመምህርነት ስንት ሊቃውንት ያፈሩት፣ በዳኝነት የፍትህን መንገድ ያሳዩት፣ በፋኖነት ፋሽሽትን ያርበደበዱት እግዚአብሔር ሙሉ በኩሉሔ አርጎ የፈጠራቸው የመላከ ብርሃን አድማሱ ድምፅ ነው፡፡ ይህ ድምፅ “በሥራ ያልታዬ እምነት ሙት” የሚለውን የያዕቆብን መልዕክት ተረድተው እምነታቸውን በሥራ የተረጎሙት የመላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ድምፅ ነው፡፡
“ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት” ተዋህዶ ቤተክርስትያንና አማራን ኢላማው አድርጎ የመጣውን ፋሽሽት ለመመከት ካህኖቻቸውን በሕዝብ ቀስቃሽነትና አርበኝነት አሰማርተው ሕዝብ በነቂስ ከጎበዝ አለቆች ጀርባ እንዲቆም ያደረጉት የካህኑ ፋኖ አያትህ ድምፅ ነው፡፡ ይህ ድምፅ ተፎካካሪ የጎበዝ አለቆችን አስማምተው ፋሽሽስትን እንደ ሰይጣን ያቅበዘበዙትና እንኳን ኑሮ ድንኳንም እንዳይተክል ያደረጉት የአርበኛው የመላከ ብርሃን አድማሱ ድምፅ ነው፡፡
የመላከ ብርሃን “ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት” ድምፅ የተዋህዶ ቤተክርስትያንም ድምፅ ነው፡፡ የቤተክርስትያኗ ድምፅ የሚስተጋባው እምነትን በሥራ በተረጎሙላት ልጆቿ ድምፅ እንጅ ቋንጃዋን ለመስበር በነስብሃት ከጣራዋ እንደ ብቅል በተሰቀሉት ቁራዎችና ጆቢራዎች ጩኸት አይደለም፡፡ የተዋህዶ ቤተክርስትያን ድምፅ የሚስተጋባው በነቢዩ ኢሳያስ ትንቢት ቤተ-ምኩራቧን ቤተ-ክርስትያን ካደረገችበት ጊዜ ጀምሮ በፈፀመችው ገድል ነው፡፡ የተዋህዶ ቤተክርስትያን ድምፅ የሚስተጋባው ቆዳ ፍቃና ቀለም በጥብጣ በጠረዘቻቸው መጻሕፍቶቿና ስዕሎቿ፤ ድንጋይ ፈልፍላ በሰራቻቸው ታቦቶቿ፤ ከባህር ውስጥ በመሰረተቻቸው ገዳሞቿ፤ ዳገት ወጥታ ከተራራ ጫፍ በሰራቻቸው ቤተክርስትያኖቿ ነው፡፡
“ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት!” ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ለውሸት ምስክርነት ለማዘጋጀት እነ “አባ” እውስጣጢዎስን** እንደ ግንፍል ሽሮ በፍጥነት አዘጋጅተው ባጰጰሱት አቦይ ገረመድህን አትለካም፡፡ የተዋህዶ ቤተክርስትያን ቋንጃ ለመሰባበር ከአእዋፏ በተሰቀሉት አቦይ ማትያስ የተባሉ ድንጋይና ኮረት ጳጳሳት አትመዘንም፡፡
“ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት!”ቤተክርስትያኗን ጣራዋን በወረሩት ቁራዎችና ጆቢራዎች እየመዘንክ “ለመሆኑ ቤተ-ክርስትያኗ አለች?” እያልክ እንድትጠፋ እንደሚፍለጉት ሰባኪዎች አትጠራጠር፡፡ ቤተ-ክርስትያኗ ዛሬም ከአለት እንደተተከለች አለች፡፡ የተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን የትም አትሄድም፡፡ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ክርስቶስን ምሰሶና አእዋፏ፣ መላዕክትን ወጋግራዎቿ፣ ጽኑ ካህናትን ግርግዳዎቿ፣ ምዕመናን ማገሮቿ አድርጋ ዘላለም ትኖራለች፡፡ አዎ! ቤተ-ክርስትያኗ አለች! ነገር ግን የመከላከያ ሕዋሷ ለጊዜው ተዳክሞ ከቆዳዋ የተነሱ ጀርሞች እያቆሰሏት ትገኛለች፡፡ ይህን ቁስሏንም ምሰሶዋ መለኮትና ወጋግራዎቿ መላዕክት ግርግዳና ማገሮቿን ካህናትና ምዕመናን እንደዚሁም ገንዘባቸውና ጉልበታቸውን እየለገሱ ሲጠብቋት የኖሩትን እስላሞችም በሐኪምነት አሰማርተው ያድኗታል የሚል እምነት አለኝ፡፡
“ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት! ሊያጠፏት የዛቱት ይጠፋሉ እንጅ ቅድሚያ ቤተ-ምኩራብ ከዚያም ቤተ-ክርስትያን የሆነቸው ተዋህዶ ቤትህ አትጠፋም፡፡ አከርካሪዋን ሊሰብሩ ያሴሩትን እንጅ ዓለም ሲያሳድደው በኢሳያስ ትንቢት አምና እጇን ዘርግታ የተቀብለችውን ቤተ-ክርስትያን ክርስቶስ አያጠፋም፡፡ ክርስቶስ የግድግና ማገር ዘራፊዎችን እንጅ “ከእንጨት መርጦ ለታቦት!” እያለ ምርጥ ምርጡን ለታቦት እያዋለ ግድግዳና ማገር የሆናትን አማራ ቋንጃም አይሰብርም፡፡
“ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት! አንተም ሆንክ ቤተክርስትያንህ እንዳትጠፋ ግን ክርስቶስ ያንተን እርዳታ ይጠይቃል፡፡ እንደምታውቀው ክርስቶስ “እርዱኝ እረዳለሁ” ብሏል፡፡ ክርስቶስ ያልረዳውን እንደማይረዳ ደጋግሞ አስተምሯል፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን ለመርዳት ፈቃደኛ የሆነ ልብ ያሻሃል፡፡ በዚህ ፈቃደኛ ልብህ እንደ ዳዊት አበራሮህን ወንጪፈህ ከቤተክርስትያኗ ጣራ የሚያኮሱትን ቁራዎችና ጆቢራዎች የጉዛምን ማሽላ እንደሚቀፈቅፉ ወፎች ማባረር ይጠበቅብሃል፡፡ መኮትኮቻህን እንዳገርህ ብሩክ ገበሬ ስለህ ከቤተ-መቅደሷ፣ ከታዛዋና ከጓሮዋ የበቀሉትን አረሞች እንደ ሙጃ ነቅለህ እንድትጥል የቅድመ አያቶችህ አደራ ወድቆብሃል፡፡
ይህን አደራ ባትወጣ የቅዱሱ የአባ ተክለሃይማኖት፤ የሊቃውንቱ አካለ ወልድና አራት ዓይናው ጎሹ፣ የአልቦ ዘመድ ተቀኝው የመሪጌታ ኤርምያስ፤ የመምህሮቹ የኔታ አስረስ የኔሰውና መሐሪ ትርፌ አጥንት ይጎራብጥሃል፡፡ ይህንን አደራ ሳትወጣ ብትቀር ያባቶችህ የእነ አቡነ ባስልዮስ፣ አቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ ሚካኤል፣ አቡነ ቴዎፍሎስና አቡነ ጎርጎሪዎስ አጥንት ምቾት ይነሳሃል፡፡ ይህንን አደራ ባትፈጥም የካህን አርበኞቹ የእነ አባ ገብረየሱስ፣ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬና መላከ ሰላም አለማየሁ ሻሾ፤ የፈላስፋ እናቶችህ የእነ እሙሃይ ገላነሽ አጥንት ይወጋሃል፤ ነፍሳቸውም ይወቅስሃል፡፡ ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት! ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት! ወጣት ተጠንቀቅ እንዳትሳሳት!
ዋቢ
*ኮኩሐ ሃይማኖት፤ ወጣት ተመልከት እንዳትሳሳት በመላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ
**ESAT Yesamintu Engeda: Abune Ewosṭatewos Ethiopian Orthodox Bishop February 21 2018
ESAT Yesamintu Engeda: Abune Ewosṭatewos Ethiopian Orthodox Bishop February 21 2018
የካቲት ሁለት ሺ አሥር ዓ.ም.
