ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ በቅርቡ 3 March 2018 “Adwa to erect memorials for war heroes” በሚል ርእስ The Reporter ለንባብ ያበቃውን ጽሁፍ ከተመለከትኩ በኋላ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የሚሰማኝን የግል ስሜትና አስተያየት ለመግለጽ ነው።
የካቲት 12/ 1937 ዓ/ም ከ30 ሺህ በላይ የአዲስ አበባን ህዝብ የጨፈጨፈ የጦር ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረበትን ግራዚያኒ ለሚባል የፋሺስት ጀነራል ለሃገሩ ለሰራው አስተዋዕጾ በሚል የጣሊያን ፖለቲከኞች ሃውል በሮም ሊያቆሙለት በነበረበት ጊዜ መጋቢት 8/ 2005 ዓ/ም ሰመያዊ ፓርቲ ከባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ጋር በመሆን የግራዚያኒን ሃውልት ግንባታ በመቃወም እዛው የወገኖቻችንን ደም ግራዚያኒ ባፈሰሰበት ለዚሁ ጭፍጨፋ ማስታወሻነት በ6 ኪሎ ሃውልት በቆመለት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው በጣሊያን ኢምባሲ ፊትለፊት ሰላማዊ ተቃውሞ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ላይ በወያኔ ወታደሮች መደብደባቸውና እስር ቤት መወርወራቸው እጅግ የሚያስከፋና የሚያበሳጭ ነው። አሁን በቅርቡ ደግሞ ወያኔ ከኢትዮጵያ ካዝና ከ260 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ አድዋን የቱሪዝም መንደር (መዳረሻ) ለማድረግ ፕሮጀክት ነድፏል። በፕሮጀክቱ በአድዋ ከሚሰሩት ሃውልቶች (memorial statues) ውስጥ በአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያን ህዝብ አስተባብረውና ጦሩን መርተው ለድል ያበቁትን የጦሩን መሃንዲስ የዳግማዊ አፄ ምኒሊክንና የእቴጌ ጣይቱ ሃውልት እንዳይቆም ወያኔ የከለከለ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ በአድዋ ጦርነት የብዙ ኢትዮጵያውያንን ደም ላፈሰሰው ለጣሊያን የጦር አዛዥ ሜጀር ጀነራል ዳቦርሚዳ ግን ሃውልት እንዲቆምለት ፈቅዷል። የወያኔ መንግስትና ደጋፊዎቹ ይህን ማድረጋቸው ለአማራ ያላቸውን ስር የሰደደ ጥላቻ የሚያሳይብቻ ሳይሆን ከፋሺስት ጋር ያላቸውን ቁርኝት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ጣሊያንን ምጽዋ እንዲሰፍር ያደረጉት እነሱ፣ ትግራይንና ኤርትራን እስከሚያዋስነው የመረብ ወንዝ ድረስ ሃገሩን ክፍት አድርገው ለጣሊያን አሳልፈው የሰጡት እነሱ። ከዛም ጣሊያን የመረብን ወንዝ በመሻገር የትግሬ መሳፍንቶችን በገንዘብና በስልጣን እያባበለ፣ እምቢ ያለውን በጦርነት እያሸነፈ መቀሌን፣ አዲግራትንና የመሳሰሉ የትግራይን አብዛኛውን ከተሞችን ባጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር ቻለ። የትግራይ ባላባቶች ጣሊያንን መቋቋም አቅቷቸው ግራ ተጋቡ፣ በየተዋጉበት አውደ ውጊያ ሁሉ በሚሸነፋበት ጊዜ አጼ ምኒልክ እኔ እስክደርስ ድረስ ጣሊያን ተጨማሪ ቦታ እንዳይዝ ባላችሁበት ቦታ እየተከላከላችሁ ቆዩ የሚል መልእክት ለራስ መንገሻና ለራስ አሉላ ላኩባቸው።
አፄ ምኒልክ ሰራዊታቸውን ይዘውና መላ የኢትዮጵያን ህዝብ አስተባብረው ሺ ኪሎ ሜትር ተጉዘው ትግራይ እንደደረሱ በተለያዩ አካባቢዎች መሽጎ የነበረውን የጣሊያን ወራሪ ጦር ከአምባላጌ፣ ከመቀሌ እና ከመሳሰሉት አካባቢዎች እየጠራረጉ አድዋ ላይ አከማቹት። በመጨረሻም ጀግናውና ብልሁ የጦሩ መሃንዲስ፣ የአፍሪካ ዳግማዊ ሃኒባል የሆኑት አፄ ምኒልክ  የካቲት 23፣ 1888 ዓ.ም በዕለተ ጊዮርጊስ ከንጋቱ ጀምሮ አንድ ላይ የከመሩትን የፋሽስት ሰራዊትን እስከ ቅጥረኛ ተባባሪ ባንዳዎቹ ጭምር ወቁት፣ አመድ ትቢያ አደረጉት።
የአድዋ ድል በነጻ አልተገኘም። ህዝቡን ለጦርነት ከመቀስቀስና ከማስታጠቅ ጀምሮ የመጨረሻዋን የጦርነት እቅድ እከመንደፍ ድረስ ብቁ የሆነ አመራር ይጠይቃል። አይደለም ያለመሪ ማሸነፍ በዓጼ ዮሃንስ 4ኛ እንዳየነው መሪ ከተመታ አውራው ወይም ንግስቷ እንደተመታች የንብ መንጋ ሰራዊቱ በየአቅጣጫው ሲበተን በታሪካችን ያየነው ጉዳይ ነው። እንግዲህ ጀግናውና ብልሁ ምኒሊክ ናቸው የኢትዮጵያን ህዝብ በፍቅር አስተባብረው፣ አስታጥቀው ለወራት ተጉዘው አድዋ ላይ ጣሊያንን አሸንፈው ከነጭ ባርነት ትግሬን ነጻ ያወጡት (ማለቴ ትግሬን ጨምሮ መላ የኢትዮጵያን)። በምኒሊክ ጀግንነት የተቃጠለው ጣሊያን በባንዳዎቹ አማካኝነት በትግርኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ውስጥ ያሰራጨው የፀረ ምኒልክ፣ የፀረ አማራ፣ የፀረ ኢትዮጵያ፣ የፀረ ኦርቶዶክስ ፕሮፓጋንዳ የትግሬ ባላባቶች ነጭ የነገራቸውን ሰምተውና አምነው ለልጆቻቸው ምክንያታዊ ያልሆነ የአማራን ጥላቻ ለትውልድ አወረሱ። ይኸው በዘመናችን ጥላቻው ጣራ ነክቶ የህወሃት መንግስትና ደጋፊዎቹ ለዚህ አሳፋሪ ውሳኔ በቁ።
በነገራችን ላይ ብዙ የትግራይ ሰዎች የገብረ ኪዳን ደስታና ብስራት አማረ የጻፉትን “የቁጭ በሉ ተረት ተረትን“ ሰምተው በአማራ ህዝብና በአማራ ንጉሶች ላይ ይህን ያህል ለበቀል መነሳታቸው የሚያሳዝን ነው። በአንድ ወቅት ገብረ ኪዳን ደስታ የአማራን ህዝብና የአማራ ንጉሶችን የሚሳደበውን መጽሐፉን ሲጽፍ ምንጩን ከየት እንዳገኘው በአሜሪካ ራዲዮ በአማርኛው ፕሮግራም ላይ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ “ሲወራ ነው የሰማሁት።” ምንጬ “የትግራይ ህዝብ ነው” ነበር ያለው። ምንም ዓይነት የጽሁፍም ሆነ ሌሎች ተጨባጭ መረጃዎች ሳይኖረውና ሳያመሳክር የፋሽስት የጣሊያንን በሬ ወለደ የውሸት ወሬና ይህንን ተከትሎ በቅብብሎሽ ወያኔና ሻዕቢያ በህዝቡ ውስጥ ሲያራግቡት የኖሩትን ፕሮፓጋንዳ እንደ ታሪክ ምንጭነት በመውሰድ ከትግራይ ህዝብ ነው ታሪኩን ያገኘሁት ማለቱ አሳፋሪና ሃላፊነት የጎደለው ስራ ነው።
ፋሽስት ጣሊያን በአድዋ፣ በማይጨው ጦርነትም ሆነ በ5ቱ ዓመት የአርበኞች ትግል ወቅት የኢትዮጵያን ህዝብ ሃይል ለማዳከም አሁን ወያኔ በጎሳና በቋንቋ እንደሚከፋፍለው ጣሊያንም እርስ በርስ በማጋጨት በከፋፍለህ ግዛ ፓሊሲ ኢትዮጵያን ለመግዛት በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ አማራ የትግሬ ጠላቱ እንደ ሆነ ያስወራ ነበር። በማይጨው ጦርነት ወቅት አስመራ ላይ በትግርኛ የተለያዩ የቅስቀሳ ጽሀፎች ጣሊያን እያተመ ወረቀት በትግራይ ሰማይ ላይ በአውሮፕላን ይበትን ነበር፣ ለጣሊያን ያደሩ ባንዳ ትግሬዎችም በህዝቡ ውስጥ እየተሽሎከለኩ ብዙ በውሸት የተሞሉ የአማራ ጥላቻ ወሬዎችን ያሰራጩ ነበር። ይህንን በትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪው ህዝብ ዘንድ ይወራ የነበረ የጠላት ወሬና ሃሜት እንደ ታሪክ ምንጭነት ይዞ በምጽሃፍ ላይ ማስፈሩ አሳፋ ብቻ ሳይሆን ሰውየው በአማራ ህዝብ ላይ ያለውን ጥላቻ በግለጽ የሚያሳይ ነው።
በመጨረሻ ማለት የምፈልገው ፋሺስት ጣሊያኖች በምኒልክ ላይ ቢያቄሙ አድዋ ላይ ሰባብሮ አሸንፏቸዋልና ምክንያት አላቸው፣ ነገር ግን ህሊናቸውን ያጡ ወያኔና እነሱን እንደግሪሳ የሚከተሏቸው ጀሌዎቻቸው ትግራይ ድረስ ዘምተው ከጣሊያን ባርነት ነጻ ያወጡዋቸው አጼ ምኒልክ ላይ ይህንን ያህል ዘመቻ መክፈታቸው እጅግ የሚያሳፍር ነው። አድዋ ለአማራው ሃገርህ አይደለችም፣ በአድዋ ላይ የፈሰሰው የአማራው ደም ደም አይደለም እስካልተባለ ድረስ፣ ወደፊትም እንደ ህዝብ አብሮ ለመኖር የሚያስቡ ከሆነ ወደቀልባቸው ተመልሰው ውሳኔያቸውን ድጋሚ ቢያስቡበት የተሻለ ይመስለኛል።
ደረጀ ተፈራ